Quantcast
Channel: Ethiopian News | ዘ-ሐበሻ | Latest News Provider | News For All
Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

የጂቡቲ መንግሥት ኢትዮጵያ ላይ ትኩረት ያደረጉ የ9.8 ቢሊዮን ዶላር ፕሮጀክቶቹን ይፋ አደረገ

$
0
0

d8b51c865d4592b0c67a08a55db302e0_L

የጂቡቲ መንግሥት እ.ኤ.አ. ከ2015 ጀምሮ በሚቀጥሉት ሦስት ዓመታት ተግባራዊ የሚሆኑና የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ መሠረት ያደረጉ የ9.8 ቢሊዮን ዶላር ኢንቨስትመንቶቹን ይፋ አደረገ፡፡

ፕሮጀክቶቹ በአብዛኛው ወደብና ወደብ ነክ አገልግሎቶችን ያካተቱ ናቸው፡፡ ፕሮጀክቶቹን ይፋ ያደረጉት የጂቡቲ ፖርትና ፍሪ ዞን ባለሥልጣን ሊቀመንበር አቡበከር ኦመር ሃዲ ናቸው፡፡

ሊቀመንበሩ ከኢትዮጵያ ወደ ጂቡቲ የተጓዘውን የጋዜጠኞች ቡድን ባገኙበት ወቅት እንደተናገሩት፣ የጂቡቲ መንግሥት በከፍተኛ ሁኔታ እያደገ ከመጣውና በዚያው ዕድገት እየቀጠለ ካለው የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ተጠቃሚ ነው፡፡ ይህንኑ የጂቡቲ ጥቅም ለማሳደግ ከኢትዮጵያ ፍላጐት ቀድሞ መንቀሳቀስ እንደሚያስፈልግ የጠቆሙት ኃላፊው፣ አብዛኛዎቹ ፕሮጀክቶች በዚሁ አግባብ መታቀዳቸውንም ገልጸዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት ዶራሌ ተርሚናል ወደ 60 በመቶ የሚሆኑትን በኮንቴይነር ብቻ ታሽገው የሚመጡ የኢትዮጵያ ዕቃዎችን ያስተናግዳል፡፡ ይህንን ተርሚናል ከኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ዕድገት እንዲሁም ከሌሎች የአካባቢው ተጠቃሚዎች ፍላጐት ጋር ለማጣጠም በሚቀጥለው የአውሮፓውያን አዲስ ዓመት ጀምሮ ተግባራዊ የሚደረግ ማስፋፊያ ለመጀመር የጂቡቲ መንግሥት አቅዷል፡፡

የመጀመሪያው ዙር የዶራሌ ተርሚናል በአሁኑ ወቅት አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኝ ሲሆን፣ በዓመት 1.6 ሚሊዮን ባለ 20 ጫማ ኮንቴይነሮችን የማስተናገድ አቅም አለው፡፡ የዚህ ተርሚናል ሁለት ሦስተኛ ባለአክሲዮን የጂቡቲ መንግሥት ሲሆን፣ የተቀረው ድርሻ በ65 አገሮች ወደቦችን በማስተዳደር የሚታወቀው የዲፒ ወርልድ ነው፡፡

የማስፋፊያ ፕሮጀክቱንም ሆነ አሁን በሥራ ላይ የሚገኘውን ዶራሌ ወደብ ከፕሮጀክት ጥንሰሳው ጀምሮ ዲፒ ወርልድ ተሳታፊ ሆኗል፡፡

የማስፋፊያ ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅ አሁን ያለውን አቅም በ30 በመቶ በማሳደግ አጠቃላይ የተርሚናሉን አቅም በዓመት ሦስት ሚሊዮን ባለ 20 ጫማ ኮንቴይነሮችን እንዲያስተናግድ ያደርገዋል፡፡

ሌላኛው ፕሮጀክት የታጁራ ወደብ ሲሆን፣ ግንባታውም በቻይና ኩባንያ እየተከናወነ እንደሚገኝ ለመረዳት ተችሏል፡፡ የታጁራ ወደብ በጂቡቲ ሰሜናዊ ክፍል ግንባታው የተጀመረ መሆኑንና ዓላማውም የኢትዮጵያ መንግሥት ለማልማት የፈለገውን የፖታሽ ማዕድን በብቸኝነት ለማጓጓዝ መሆኑን የጂቡቲ ፖርትና ፍሪ ዞን ባለሥልጣን ሊቀመንበር ገልጸዋል፡፡

የታጁራ ወደብ በአጠቃላይ 160 ሚሊዮን ዶላር የሚያወጣ ሲሆን፣ በዓመት አራት ሚሊዮን ቶን ፖታሽ የማጓጓዝ አቅም እንዳለውና የፖታሽ ሀብቱን የሚያጓጉዙ ግዙፍ መርከቦችንም ማስተናገድ እንደሚችል ተገልጿል፡፡

የዚህን ወደብ ግንባታ የሚያከናውነው የቻይናው ኩባንያ ባኦ ዬ ሁቤ ሲሆን፣ በተቆጣጣሪነት ደግሞ የጣሊያኑ ቴክኒካል ኤስፒኤ ተቀጥሯል፡፡ የተቆጣጣሪ ኩባንያው የጂቡቲ መሐንዲስ ቶማስ ሪኮቦኒ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ወደቡ ለኢትዮጵያ የፖታሽ ሀብት የትራንስፖርት አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል እንደመሆኑ መጠን የፖታሽ ማዕድኑን ወደ መርከብ የሚጭኑ ኮንቬዬር ቤልቶች ይኖሩታል፡፡ ከወደቡ ጋር የተገናኘ የባቡር ሐዲድ ወደ ኢትዮጵያ እንደሚዘረጋም ገልጸዋል፡፡ ይህ የታጁራ ፕሮጀክት ከመቀሌ – አዋሽ – ወልዲያ – አሳይታ – ታጁራ የባቡር ፕሮጀክት ጋር የሚገናኝ ነው፡፡

ከወደብ ግንባታዎቹ ጋር የሚገናኙ የባቡር ፕሮጀክቶችን በሦስት ዓመት ውስጥ ለማጠናቀቅ ዕቅድ ተይዟል፡፡ እነዚህም ከጂቡቲ ከተማ ጋላሊህ ወደምትባለው የጂቡቲ የኢትዮጵያ ድንበር ድረስ የሚዘረጋው የ98 ኪሎ ሜትር እና ከታጁራ ወደብ ወደ ኢትዮጵያ ድንበር ጋላፊ የሚዘረጋው 124 ኪሎ ሜትር ናቸው፡፡ እንደ ቅደም ተከተላቸውም 550 ሚሊዮን ዶላርና 600 ሚሊዮን ዶላር በጀት ተመድቦላቸዋል፡፡

ሌሎቹ በዕቅድ የተካተቱ ወደቦች እንደዚሁ የኢትዮጵያ የወጪና የገቢ ንግድ ዕቃዎችን ፍላጐት መሠረት አድርገው እንደሚገነቡ አቡበከር ኦመር ሃዲ አስረድተዋል፡፡

የድፍድፍ ነዳጅ ተርሚናል በ200 ሚሊዮን ዶላር ለመገንባትና የፈሳሽ ዘይቶች ማጠራቀሚያ ተርሚናል ለመገንባት በሦስት ዓመት ዕቅድ ውስጥ ተካቷል፡፡

የነዳጅ ማጠራቀሚያ ተርሚናሉ ሦስት ቢሊዮን ዶላር በጀት ተመድቦለታል፡፡ በአሁኑ ወቅት የነዳጅ ማጠራቀሚያ ዲፖውን 54 በመቶ የምትጠቀመው ኢትዮጵያ ስትሆን፣ የተቀረውን ደግሞ የጂቡቲ መንግሥትና በጂቡቲ የሚገኙ የአሜሪካ፣ የፈረንሳይና ሌሎች ወታደራዊ ካምፖች ይጠቀሙበታል፡፡

በአሁኑ ወቅት አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኘውን የአገሪቱ የመጀመሪያ የሆነው የጂቡቲ ወደብን ወደ ንግድ ማዕከልነት የመቀየር ዕቅድ በአገሪቱ መንግሥት ተይዟል፡፡ ይህንን ወደብ የሚተካ ጂቡቲ መልቲ ፐርፐዝ ፖርት በ525 ሚሊዮን ዶላር ለመገንባት የቦታ ዝግጅት መጠናቀቁ ታውቋል፡፡

ከኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ወደ ውጭ የሚላኩ የቀንድና እንደ ግመል ያሉ የጋማ ከብቶችን በብቸኝነት ለማጓጓዝ የሚያገለግል ወደብም በ5.5 ሚሊዮን ዶላር ለመገንባት ታቅዷል፡፡

ራስ ሲያን የሚል መጠሪያ የሚኖረው አየር መንገድ እንዲሁም ቢሲድሌ ዓለም አቀፍ የመንገደኞችና የዕቃ ማጓጓዣ አየር መንገድ ለመመሥረት በዕቅድ ደረጃ 730 ሚሊዮን ዶላር ተይዞላቸዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም የጂቡቲ መርከብ ድርጅትን ለማቋቋም እየተንቀሳቀሱ መሆኑንና ከጂቡቲ ውጪ የኢትዮጵያንና የአካባቢውን ትራንስፖርት ፍላጐት መሠረት ያደረጉ ወደቦችን በሶማሊያና በደቡብ ሱዳን ለማቋቋም እየሠሩ መሆናቸውን አቡበከር ኦመር ሃዲ ገልጸዋል፡፡ ወደቦቹን ለማቋቋም ቻይና መርቻንትስ ከተባለ የቻይና ኩባንያ ጋር በሽርክና እየሠሩ መሆኑንና ለታቀዱት ፕሮጀክቶች 58 በመቶ የሚሆነው ገንዘብ መገኘቱንም ገልጸዋል፡፡

በዮሐንስ አንበርብር (ጂቡቲ) Source:: Ethiopian Reporter

Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Trending Articles