በበጎ አድራጎት ሥራዎች ላይ ለበርካታ ዓመታት ተሰማርተው የቆዩ ማኅበራት ፍቃድ ማደሰ ባለመቻላቸው ሕልውናቸው አደጋ ውስጥ መግባቱ ተገለጸ፡፡
የሲቪል ማኅበራትና በጎ አድራጎት ድርጅቶች ኤጀንሲ ማኅበራቱ አዋጁ በሚፈቀድው መሠረት አደራጃጀታቸውን ካላስተካከሉ ፈቃድ እንደማይታደስላቸው አስታውቋል፡፡
በዚህ ሒደት ከመቶ በላይ የሚሆኑ ሲቪል ማኅበራት በድጋሚ መዋቅራዊ ማስተካከያ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡ መዋቅራዊ ማስተካከያ ቢያደርጉም የመዘጋት ዕጣ ፈንታ የተጋረጠባቸው ግን አሉ፡፡ በርካታ በጎ አድራጎት ድርጅቶች መጀመርያ ፈቃድ የወሰዱት ከፍትሕ ሚኒስቴር እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ለበጎ አድራጎትና ለሲቪል ማኅበራት ፈቃድ የመስጠቱንና የመቆጣጠሩን ኃላፊነት ማኅበራት ኤጀንሲው ከተረከበ በኋላ በርካታ ለውጦች ተደርገዋል፡፡
በዚህ መሠረት የኢትዮጵያ የሥነ ምግባር መኮንኖች ማኅበር፣ ነጋዴ ሴቶች ማኅበር፣ በሌሎች አገሮች የተማሩ ምሑራን ያቋቋማቸው ማኅበራት ለምሳሌ ሩሲያና ጀርመን ተምረው አገራቸው የተመለሱ ምሑራን ያቋቋሟቸው ማኅበራት በሙሉ አደጋው ከተጋረጠባቸው መካከል ይገኙበታል፡፡
የሥነ ምግባር መኮንኖች ማኅበር የተቋቋመው ከተለያዩ መንግሥታዊ ተቋማት በተውጣጡ የሥነ ምግባር መኰንኖች ነው፡፡ ይህ ማኅበር የተቋቋመ ሙስናን ለመዋጋት የተጀመረውን ጥረት ለማገዝና ከሙሰኞች የሚሰነዘረውን ጥቃት በጋራ ለመከላከል መሆኑን የማኅበሩ ፕሬዚዳንት አቶ ጌቱ አለማየሁ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
አቶ ጌቱ ጨምረው እንደገለጹት፣ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች ኤጀንሲ ለማኅበራቸው በጻፈው ደብዳቤ፣ የእርሳቸው ድርጅት ቀደም ሲል ፈቃድ የተሰጠው በስህተት መሆኑንና የሥነ ምግባር መኮንን የሚባል ሙያ እንደሌለ በማስታወቅ፣ ማኅበሩ እንዲፈርስ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡ ማኅበሩ ባለፈው ረቡዕ በጠራው ጠቅላላ ጉባዔ ለአባላቱ ይህንን ያስታወቀ ሲሆን፣ አባላቱ አቤቱታቸውን ለመንግሥት እንደሚያቀርቡ ገልጸዋል፡፡ አቶ ጌቱ ግን የማኅበሩ ህልውና ያበቃ መሆኑንን ተናግረው፣ ያለውን ሀብት ለኤጀንሲው ለማስረከብ መዘጋጅቱን ጠቁመዋል፡፡
በውጭ አገር የተማሩ ምሑራንም የአደራጃጀት ለውጥ እንዲያደርጉ ተገልጾላቸዋል፡፡ የሲቪል ማኅበራትና የበጎ አድራጎት ድርጅቶች ኤጀንሲ ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ኃላፊ አቶ አሰፋ ተስፋዬ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በማኅበራቱ ያሉ አባላቶች የተለያዩ ትምህርቶች የተማሩ ሰዎች ናቸው፡፡ ይህንን የሙያ ማኅበር ብሎ ለማስተናገድ የማይመች በመሆኑ፣ ምሁራኑ በሠለጠኑበት ሙያ ተለያይተው ሊደራጁ እንደሚችሉ ተናግረዋል፡፡ ‹‹ይህ ካልሆነ ግን ማኅበራቱ ያቀረቡት የፈቃድ እድሳት ጥያቄ አይስተናገድም፤›› ሲሉ አቶ አሰፋ አስርድተዋል፡፡ በሌላ በኩልም ነጋዴ ሴቶች ያቋቋሙት ማኅበር ከንግድ ውጪ የበጎ አድራጎት ባህሪ የሌለው ነው በሚል ምክንያቶች በኤጀንሲው ሊስተናገድ አልቻለም፡፡
አቶ አሰፋ እንደገለጹት፣ ቀደም ሲል የተሰጠው ፈቃድ ድብልቅልቅ ያለ በመሆኑ መጥራት ይኖርበታል፡፡ በአሁኑ ወቅት በኤጀንሲው ፈቃድ በማደሰ በኩል ያለውን ችግርና የተደበላለቀ አሠራር በመለየት ጥርት ያለ መንገድ መፍጠር እንደሚያስፈልግ ባለጉዳዮቹ አሳስበዋል፡፡
Source:: Ethiopian Reporter