Quantcast
Channel: Ethiopian News | ዘ-ሐበሻ | Latest News Provider | News For All
Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

ኢትዮጵያ ፋናዬን ትመስላለች –ሀገርና ልጆቿ እንዲህ በመከራ ሰጠሙ። (ሥርጉተ ሥላሴ)

$
0
0

ከሥርጉተ ሥላሴ 06.12.2014 /ሲዊዘርላንድ – ዙሪክ/

እሜቴ ነፃነት እንደምን ከርመሻል?!

ከአምናው ሸክማሸክምሽ ዘንድሮ ብሶሻል ።

ዕንባነን አቅንተሽ ዘመን ሸኝተሻል ….

እትብትን ገብረሽ መከራ ወሮሻል። …

ያልፋልም ሳይመጣ እንዲህ ጠቋቁረሻል፤

የፋሽስቱ ኑሮ እንዲህ አሳሮሻል

ያገተው ተፈጥሮሽ – ራሄልን ሆኗል።

Teme & momየሀገሬ ልጆች እንዴት ናችሁልኝ? የዛሬን „የወያኔን የዱላ ቀን“ ሰበር ዜና ከዘሃበሻ እዬተከታተልኩ – እያነበብኩ የጻፍኩት ነው። ይህ ፎቶ ሀገራችን ከነውስጧ ይናገራልስለማያልቀው አሳሯ ይመስክራል። እያደር ስለሚጎላው የበቀል ዱላ ያብራራል። ኢትዮጵያ ለእኔ ፋናዬን ትመስላለች። አዛውንቷ እናት ሀገራችን ኢትዮጵያ እንዲህ በግራጫ ዘመኗ ክልትምትም ትላለች። ልጇ እንደ ናፈቃት፣ እንደሳሳት፣ ወጥቶ ሳይመለስ ይቀርባታል። በሰው እጅ ወድቆ በመከራ ስንቅነት ይቀጠቀጣል። ለንዳድ ወይ ለባሩድ ገጸ በረከት ይሰጣል። አዎን እናት ኢትዮጵያ ፋናዬን ትመስላለች ….

ዕድሜ ጠገቧ እመቤት ሀገራችን ኢትዮጵያ ዛሬ አልጋ አያስፈልጋትም – መሬት እንጂ። …. መቀነት አላስፈለጋትም ገመድ እንጂ፣ እህል አለስፈለጋትም – ፆም እንጂ፤ ደስታን አታቅድም ልጇቿ አሳራቸው ጠንቷልና፤ ሠርግ አያምራትም ልጃቿ ተስፋቸውን ተቀምተው ወጣትነታቸው ካቴና እንዲሆን  በአረመኔዎችና በጨካኞች ተገምድሎባቸዋልና *። ግን አቅሟ ያለው ከብሌኗ ስለሆነ ታነባለች – ሌትና ቀን። አዎን ልዕልተ ኢትዮጵያ እንዲህ ፋናዬን ትመስላለች ..

ልጇ ስጋቱ መንፈሱን ሲወጥረው ተንፍሶ ሃሳቡን ቢገልጽ  – ዱላ ነው፤ ወስፋቱ ሲንጫጫ፤ መጋኛው ሲተራመስ እራበኝ ብሎ ቢናገር – እርግጫ ነው፤ ጉሮሮው ድርቆ ሊያረጥብ ጠብታ ለምኖ ጠማኝ ለማለትም – ቅጥቀጣ ነው፤ ሌማቱ ድሆኖ* በባዶነቱ ሲያቅትቱ ኑሮን አልቻልኩም ቢል – መከትከት ነው፤ የተጣፈችው፣ ዘመን በልቷት አፍረተ ሥጋውን ለመከወን አቅም ያነሳትን ጥብቆ እያያት ከበላዩ ስታልቅ ታርዝኩኝ ቢልም –  ወንጀል ነው፤ የዘመን አራጣ ከፋይ ሆኗልና።

ሀገሬ፣ እናቴ ኢትዮጵያ ብሎ ደፍሮ ለመናገርም አሸባሪ“ ተብሎ ከርቸሌ ወይንም የባሩድ እራት ይሆናል፤ የማንነቴ መግለጫ ባርነትን ያለሳህኝ ባለውለታዬ ዓርማዬ ሰንደቄ እራቡንም ጥማቱንም በአንተው ልቻለው ብሎ ፈተናውን ለመተጋስ ሰንደቁን ቢለብስም የከፋ ጦር ይታዘዝበታል – ማረጃ ይሰናዳለታል።  ብሄርተኛ አክራሪ“ ነህ ተብሎ የፊጥኝ ታስሮ መፈጠሩን እስኪረግም ድረስ በዱላ ይቀጠቀጣል፤  ስለሆነም ዬልጇቻ ፍዳ እዬጠና መሄድ ያሳሰባት እናት ታወርደዋለች ዕንባዋን። …. እዬረጨችም በመማጸን … አዎ ኢትዮጵያ እንዲህ ናት ውስጧ ፋናዬን ትመስላለች።

መጣህልኝ ልጄ? ምን ይሻልህ? ደከመህ ወይ? አመመህን? የት አመሸህ? ቀረ … እንደ ራበ … ጠጋ ብሎ ጠረንን – ለጠረን እዬጣጣሙ በፍቅር እናታዊ ዓይን ልጅን መዳበስ – መዳሰስ – ማሻሸት- የፆም ውሃ ሆነ፤ ልጅና እናት የሆድ የሆድን ጧት ማታ ማውጋጋት ቀረ፤ የወጣነውም ብንሆን ቢታመሙ አንደርስ፤ ቢሞቱ አንቀብር እንደ ወጣን ቀረን፤  ሀገር ቤት ያለውም እንደ ወጣ ቀረ ጅቦቹ ኑሮውን ነጠቁት አራዊቶች ባዕቱን ቀሙት። ለፍዳው ዞን ተበጀለት። አዎ ኢትዮጵያ ዛሬ ያረረባት ፋናዬን ትመስላለች ….

እሷ የሚያስፈልጋት የፋካ የልጇ ጠረን ብቻ ነበር። ወጥታ ገብታ፣ አግኝታው፣ ቅርብ ብላ ጠረኑን መጠጣት። ድራ ኩላ ከጎረቤቱ፣ ከቤተዘመዱ ጋር ሐሤታን ተጋራታ ዓይኗን በዓይኗ ማዬት፤ የልጅ ልጅ መሳም፤ አዲስ የጋብቻ ዝምድና ፈጥራ ዝክሩን ማህበሩን ሞቅ ደመቅ አድርጋ በፈግጋታ ፍሬዋን መዬት ነበር፤ ለፍታ – ደክማ – ጠቁራ – ከስላ ያሳደገችው ለዚህ እንጂ ለበቀል ቁርስ ምሳና እራት አልነበረም። ግን ሆነ … እንዲህ ተስፋዋን አተነነው ዞገኛው ወያኔ።

ፍላጎቷን እንደ ህልሟ ማዬት እናት ሀገር ኢትዮጵያ አልቻለችም። ልጇ ለተለያዩ የቋሳ መፈተኛ እዬዋለ ነው። …. እያለ ሰውነቱ ዝሎ የራሴ የሚለው አካሉ ሸሽቶት ሞትን ናፈቀ። ይህን ታያለች አናት። የፈዘዘውን የልጇን አካል ታስተውላላች – እናት። ዬልጇ ክብሩ አካል ለአራዊት ፈንጠዝያ፤ ለባህር ሲሳይ፤ ይሄው ነው ኑሮዋ ኑሮ ከተባለ። …. ስለሆነም እንቅልፍ እልባዋ ቀንም ሌትም  በአሳር – ትፈተላለች። በጥቃት – ትባዘታለች። በሰቀቀን – ትወጋላች። ነገር ግን ሩቅ ታሰባለች። ቢሆንም እያች ግን የለችም። ሁለመናዋን መንፈሷን ሳይቀር ተነጥቃለች።  … አዎን እናት ሀገር ኢትዮጵያ ፋናዬን ትመስላለች ..

የፋናዬ ዕንባ ጅረት ነው፤ የአባይ ፏፏቴ ነው። …  ይነጉዳል ዘመንን እዬወቀሰ። ይሄዳል … ዘመንን እዬነቀሰ፤ ፈጣሪን ግን ተማጽኖ – መጪውን ዘመኑን በርኮ ከበለኃሰቦች እንዲታደግ እያሳሰበ … ጠብታዋ ጉዞውን አሁንም ቀጥሏል – እዬተከዘ። አያልቅበት ይፈሳል … መከራው የሚያልቅበትን ቀን ያልማል፤ ፍዳው የሚቋጭበትን ሁኔታ ያሰላል …. ዋናው በዕንባ ወንዝነት …. ይሠግራል ….

ተፋሰሱ አልፎ ደረቷን እራስ ሲያደርገው፤ ተፋሰሱ ቀጥሎ ዕንብረቷን ሲጎበኘው። ያን ጊዜ እትብቱና መከራው ተገናኝተው ያወጋሉ፤ ማለፊያውን ቀን ያልማሉ። እንደ ገና በህቅታ ቃና እና ሲቃ የፈላ አዲስ ፋፋቴ ይተካል። እኔ እቀድም እኔ እቀድም በአዲስ ጉልበት ይሯሯጣሉ። ገደቡን ጥሶ ይለቀቃል …. አዎን ኢትዮጵያ ፋናዬን ትመስላላች ….

ዱላው ቀጥላሏ፤ ዛሬም የዱላ ቀን ነው። ነገም እንዲሁ … ግን ሲከር ይበጣሳል ሲሞላም ይፈሳል። እግዚአብሄር ይስጥልኝ – ኑሩልኝ  የእኔዎቹ። የራሄልን ዕንባ የታደገ ዕንባ የፋናዬንም ይታደግ! አሜን! አዛውንቷ ፋናዬ ልዕልት ኢትዮጵያ ናትና ….

መፍቻ * መገምደል …  ኢ – ፍታህዊነት፤ ኢ – ህጋዊነት የወረረው ጋድም ዳኝነት።

* ድሆኖ ከጭቃ የተሠራ የእንጀራ መያዣ፤ ነገር ግን ጉዝጓዝ ጥሬ ሽንብራ ወይንም የቁንዶ በርበሬ ዛላ ቅጠል ወይንም  ባህርዛፍ ቅጠል ወይንም እንሰት /ኮባ/ ቅጠል ከሥር ያስፈልገዋል። በዘመነ ደረቁ ለምለም ስለመኖሩ ግን አላውቅም።                

ኢትዮጵያዊነት ፈተናን አሸንፎ የተፈጠረ ሚስጢር!

እግዚአብሄር ይስጥልኝ።


Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>