Quantcast
Channel: Ethiopian News | ዘ-ሐበሻ | Latest News Provider | News For All
Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

ዘመን ሞቷል –ኃይሉ አትበሉ (ወለላዬ ከስዊድን)

$
0
0

hai2

ማስታወሻው ጠፍቶ ምስሉ

ተገርስሶ ወድቆ አካሉ

ተሰርዞ ቃለ ውሉ

ዘመን ሞቷል ኃይሉ አትበሉ።

 

ታሪክ የለም አምልጦናል

ዘመን ቆመን ሞቶብናል

ሁሉም አልቆ ተጠቃሏል

ጋሼ ኃይሉ ይዞት ሄዷል

 

ለዘመን ነው እንባ ማፍሰስ

ለታሪክ ነው ከል መልበስ

ለጊዜ ነው ፊት መከስከስ

ለጋሽ ኃይሉ ይብቃን ማልቀስ

 

የዘመንን በሞት ማምለጥ

የጊዜውን መገላበጥ

ገና በፊት ጋሼ ኃይሉ

ተናግሮታል በአፉ ሙሉ

መጣ ብለን ሚሊኒየም

በክብሩ ላይ ልንታደም

ወዲያ ወዲህ ስንሯሯጥ

ምድር ስንቀድ ሰማይ ስንፈልጥ

ከረምንና አገር ወጥቶ

ተበልቶና ተጠጥቶ

ጋሼ ኃይሉ ብቻ ቀርቶ

ምነው ጠፋህ? በዚህ በዓል

አንተ ብቻ ብሎ ሲባል

ያልኖርኩትን አላከብርም

ይሄ በዓል የኔ አይደለም

መች ኖሬ ነው የማከብረው

የኔ ዘመን ሞቷል ተወው

ብሎ ነበር መልስ የሰጠው

 

ጋሼ ኃይሉ እንዲህ ልቆ

ከዘመኑ ተራርቆ

ከጊዜው ጋር ተናንቆ

አንድ ራሱን ብቻ ችሎ

አንድ ራሱን ብቻ ጥሎ

ቢገላገል ቢሄድ ከፍቶት

አረፈ እንጂ ሞተ አትበሉት

 

ታሪክ የለም አምልጦናል

ዘመን ቆመን ሞቶብናል

ጋሼ ኃይሉ ይሄን አውቋል

ቀደም ብሎ መኖር ትቷል

 

ማስታወሻው ጠፍቶ ምስሉ

ተገርሶ ወድቆ አካሉ

ተሰርዞ ቃለ ውሉ

ዘመን ሞቷል ኃይሉ አትበሉ።

 

ትልቁ ሰው ጋሼ ኃይሉማ

ገና ድሮ ይዞ ዓላማ

ተልኮውን እስኪጨርስ

አጠገቡ ሞት እንዳይደርስ

ብዙ ሮጧል ብዙ ሰርቷል

አሸንፎት ሞትን ኖሯል

አሁን ግና ሰርቶ ደክሞት

ቤቱ ድረስ ሲመጣ ሞት

ተቀብሎ በሩን ከፍቶ

ሳይከፋ ተደስቶ

ስለሄደ ተሰናብቶ

ይበቃናል እንባ ማፍሰስ

በረፍቱ ላይ አንላቀስ

ወዲያ ወዲህ አናዋክበው

በኡኡታ አናጅበው

በዋይታ አንቀስቅሰው

በጥሞና በእርጋታ

እንሸኘው በዝምታ

 

ጋሼ ኃይሉን የምታውቁት

ወዳጆቹ ምታከብሩት

የበፊቱን አታስታውሱት

እባካችሁ እንባ ተዉት

ታሪክ ቆመን የሞተብን

እውነት ፊቱን ያዞረብን

ዘመን ጥሎን ያመለጠን

እሱ ሳይሆን እኛ እኮ ነን

ጋሼ ኃይሉ ሞቱን አውቋል

ቀደም ብሎ ተሰናብቷል

እየኖረም መኖር ትቷል

 hai3

ማስታወሻው ጠፍቶ ምስሉ

ተገርስሶ ወድቆ አካሉ

ተሰርዞ ቃለ ውሉ

ዘመን ሞቷል ኃይሉ አትበሉ።

***

ወለላዬ ከስዊድን (welelaye2@yahoo.com)


Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>