ዛሬም እዚያው ነሽ ወይ!
የዱሮ ግጥሞች መሰረታቸው የማይነቃነቅ፤ ትርጉማቸው ረቂቅ በመሆናቸው እወዳቸዋለሁ፡፡ለምሣሌ
እዚያው ነሽ ወይ ዛሬም እዚያው ነሽ ወይ
አስሮ የሚቀጣ ዘመድም የለሽ ወይ
ዛሬም እዚያው ነሽ ወይ?
ይህ የተባለላት መግባባት ተስኗቸው ከተለያዩ በኋላ እንቅፋት በመታ፤ አስደንጋጭ ነገር በተሰማ ቁጥር፤ ያንን የተፈታውን ባል ስም በመጥራት ለምትፎክር የተገጠመ ነው ሲሉ ሰምቻለሁ፡፡እንዲያው በግርድፉ እንተርጉመውም ቢባል የቀረን ነገር ለሚያስታውሱና ባለፈው ላይ ለሚንጠላጠሉ፤ አለያም ተበልቶ ያለቀን እቁብ የሚመኙትን በተመለከተ የተገጠመ ነው ማለት ይቻላል፡፡
እኔ ደሞ ከግንቦት 25 በፊትና ከዚያም ተሻግሮ ገዢው ፓርቲና ባለስልጣናቱ ሲያዜሙት የነበረውን ያረጀ ያፈጀ፤ ለዛው የተሟጠጠውን፤ አድማጭ ጆሮ የነሳውን፤ የገረጣ ዘዴ አሁንም እንደገና እንካችሁ ማለታቸው ስላስገረመኝ ለነሱ የተገጠመ ነው አልኩ፡
ባለፈው 1997 ላይ የተካሄደው ሰላማዊ ሰልፍ ገዢው ፓርቲ ላይ ጭንቀት፤ ምጥ፤ መደነባበር በመፍጠሩ ሳቢያ በሰላማዊ መንገድ የምርጫ ካርዳችን ተሰረቀ በማለት የወጡትን ንጹሃን ዜጎች መሳሪያቸውን ወድረው ለመግደል ብቻ በወጡ ሰብአዊነታቸውን በጥቅምና በጊዜያዊ ድጎማ በለወጡ የጥፋት አርበኞች ተጨፈጨፉ፡፡
ከዚያ በማስከተል ደግሞ ግፍ በቃን፤ ባርነት ሰለቸን፤ መገፋት አስከፋን፤ ስደት መረረን፤ አንተም ገዢ ፓርቲ ሆይ! የሰለጠነ ፖለቲካ ማወቂያ ሕሊናህ ስለሻገተ፤ የማሰቢያ ሃይልህ በጥቅማ ጥቅም ስለተሸነገለና ስለተሰናከለብህ፤ የምትበድለው ሕዝብ ምሬት ያንገሸገሸው መሆኑን ባለማወቅህ በከንቱ ውዳሴ እየተሞኘህ ያለህ ነውና በቃሕ! በቃህ! ስትባል ማዳመጥ የሚሉት ባህል ስለሌለህ በቃህን እንደጋግመዋለን ያሉትን በሙሉ በእውር ድንብርብር ያወጣኸውን የሽብር አዋጅህን ጠቅሰህ ንጹሃን ለሃገርና ለወገን ተቆርቋሪዎችን አስረህ፤ ያም አልበቃ ብሎህ ያላዋቂ ሳሚ እንዲሉ በተደበቀ ካሜራና ቴፕ ቀርጸህ እንድናይ ያቀረብከው ‹‹አኬልዳማ››ህ ክስረትህን እንጂ ሌላ ያሳየው አንዳችም ጉዳይ የለም፡፡
ያም አልበቃህ ሙስሊም ኢትዮጵያውያንንና ክርስቲያን ኢትዮጵያውያንን ማምለኪያ ቦታቸውን ‹‹ለልማት›› በሚል ልታፈርስ በመነሳትህና፤ሙስሊም ኢትዮጵያውያንም በሃይማኖታቸው ጣልቃ ገብተህ የማይፈቅዱትንና ያልመረጡትን አስተምህሮ ከድንበር ማዶ አምጥተህ የነበረውን አፍርሳችሁ በዚህ መንገድ ሂዱ በማለትህ ‹‹ምን ጥልቅ አርጎህ›› በማለታቸው ተቃውሟቸውን እንደድፍረት በማየት ትንኮሳህን አባብሰህ የማይጠፋ እሳት ለኩሰህ አስካሁንም ድረስ በመደከር ላይ ነህ፡፡
ያንንም ሁኔታ በተመለከተ በፈረደበት የቴሌቪዥን ጣቢያ ላይ ሌላ ካለፈው ተመሳሳይ ዳማ ጨዋታህን አኬል ብለህ ስታቀርብ እንደነበር ይታወሳል፡፡
ለዚህ ነው ‹‹ዛሬም እዚያው ነህ ወይ››ን ያነሳሀት፡፡
ገና ግጥሙን አስታውሼ ሳልጨርስ ግንቦት 25 ደረሰና ‹‹ማንም አይወጣላቸውምና ፍቀድ!›› በሚል ትዕዛዝ ተፈቀደው ሰልፍ ተካሄደ፡፡ መንግስታዊ ግብር በላ ጋዜጠኞች ከቢሯቸው ሳይነቃነቁ ነው ‹‹በሰማያዊ ፓርቲ የተጠራው ሰላማዊ ሰልፍ ተሳታፊ ባለመገኘቱ ጠሪዎቹ ይህን ዘገባ እስካጠናቀርንበት ጊዜ ድረስ ከመነሻ ጣቢያቸው……….›› ብለው አረፍተ ነገሩን ሳይጨርሱ በአሰርት ሺህ የሚቆጠረው ሰልፈኛ ‹‹ኢትዮጵያ ሃገሬ!›› በማለት ድምጹን ከፍ አድርጎ በመዘመር ሲተም በጋዜጠኛው ቢሮ ብቻ ሳይሆን በኮሙኒኬሽን ቢሮ መስኮቶች ደርምሶ በመግባት የገዢውን ሎሌዎች ጋኔል እንደሰፈረበት ሕመምተኛ ከየወንበራቸው እየፈነቀለ ያስበረገጋቸው፡፡
በዚህን ጊዜ ነው ሽመልስ ከማል ጋዜጣዊ መግለጫ ለመስጠትና ባላየው ግን በሃይለኛ ‹‹ኢትዮጵያ ሀገሬ›› ዜማ ባስደነበረው ድምጽ በመናደድ ሰበብ አስባብ መደርደር የጀመረው፡፡ ሰልፉ ሳይጠናቀቅ ገና በሂደት ላይ ሳለ ነው የሽመልስ ከማልና የሬድዋን መግለጫ ለቴሌቪዢናቸውም ለሬዲዮናቸውም የተሰጠው፡፡
እዚህ ላይ የላይኛውን ግጥም ደጋግሜ አልኩት ሳቅ እያፈነኝ፤ ትዝብት እያደረብኝና ምኖቹ ናቸው የሚመሩን እያልኩ በማዘን፡፡
የሚገርመው ጉዳይ ሽመልስ ከማል በሰልፉ ላይ ሙስሊሞች ተሳትፈዋል፤ ብሎ ሲጸልዩ ማሳየት ምን ለማለት ነው? ክርስቲያኖች በጠሩት ሰልፍ ላይ ሙስሊሞች ተሳተፉ ለማለት ነው ወይስ ሙስሊሞችና ክርስቲያኖች በአንድ ላይ ለአንድ ሃገር ክብር ለአንድ ሕዝብ እኩልነት ለዴሞክራሲ፤ ለፍትሕ፤ ለነጻነት አብረው መቆም አይችሉም ተብሎ የታወጀ አለ እንዴ? ሙስሊሙና ክርስቲያኑ እኮ ለዘመናት አብረው የኖሩ፤ በችግራቸው ሲረዳዱ፤ በደስታቸው ሲጠራሩ፤ የኖሩ ናቸው፡፡ አንዱ የሌላውን ሃይማኖት አክብሮ በመተሳሰብና በመከባበር ዘመናት አሳልፈዋል፡፡ ይሄንን ደግሞ ሽመለስ ከራሱ ስም አወጣጥ ጀምሮ ሊገነዘበው የሚገባ ጉዳይ ነበር አልሆንልህ አለው እንጂ፡፡ እርግማን ይሰራል ከተባለም የአቶ ከማል እርግማን ሰርቶላቸዋል፡፡ የሰው ፍቅር ይንሳህ ብለውት ነበርና ይሄው እሳቸው ባይኖሩም እኛ እያየንላቸው ነው፡፡
ግራም ነፈሰ ቀኝ ወጣቱ ሰማያዊ ፓርቲ ጥሪው ተሰምቶለት፤ ፕሮግራሙ ሰምሮለት፤ ምኞቱ ተሳክቶለት፤ ሰልፉ ደምቆለት፤ ሠላማዊ መሆኑ ተረጋግጦለት ጠጠር ኮሽ ሳይል፤ ዝናብም ጠብ ሳይል ፖሊስም ስርአት ሳይጥስና ‹‹የገዢውን ስም በክፉ›› ያነሳ ብሎ ሳይደነፋ በሰላማዊ መንድ ተጠናቆ ሁሉም እየዘመረ ተሰባስቦ እየዘመረ ተሰነባበተ፡፡
ታዲያ ከምኑ ላይ ነው የነሽመልስና ረድ ዋን አካኪ ዘራፍ የተፎከረበት፡፡ ምን ተደረገ ነው የሚሉን? ባንዲራውን እናውጣ አታወጡም ክርክርና ትግል የጀመሩትም ተልከው የመጡ ሽብር ፈጣሪዎች ስለነበሩ የቴሌቪዠዥን ካሜራም ጀምሩ ስላላቸው የፈጠሩት ለመሆኑ ማስረጃ የማያስፈልገው የተለመደ አካሄድ ስለሆነ ማንም አልተቀበለውም፡፡
የኢትዮጵያ ቴሌቪዥንም ቢሆን በሽታ ስላለበት ተቃዋሚዎች ፕሮግራም ላይ የሚገኘው ‹‹ካንዲድ ካሜራ›› ፕሮግራም ለማንሳት ስለሆነ ያንኑ አድረጓልና አለቆች ሽላማት ቢጤ ቢጥሉለት መልካም ነው፡፡ለመሆኑ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ጥሩና እውነት ሆነን ነገር እንዳያነሳ ተብሎ በቻይና የተገጣጠመ ይሂን እንዴ፡፡ ልብ ብላችሁ እንደሆነ ስንት ጸአዳ ልብስ የለበሰ ሰው ባለበት እንደምንም ብሎ ያለቀና የተቀዳደደ ልብስ ማንሳትን ይመርጣል፡፡ስንት እውነት በሚነገርበት ቦታ ተጠምዶ እንደምንም ቅጥፈት ፈልጎ ይቀርጻል፡፡ አያሰዝንም?
በዕለቱ የተፈራው የተደፈረበት፤ የተዘጋው የተከፈተበት፤ የታሰበው የተፈጸመበት፤ ሠላም ተብሎ ሠላም የነገሰበት፤ እኩይ ድርጊት ፈላጊዎች ያሰቡት የከሸፈበት፤ ያልጠበቁት የወጣት አርበኛ የተመመበት፤ ዕለት ነበር፡፡ ወጣቱ አሁንም ለውጥ ፈላጊነቱንና ለለውጥ መነሳሳቱን በተግባር አሳይቷል፡፡ ከእንግዲህ በሚታቀደው ሠላማዊ እንቅስቃሴ ሚያዝያ 30/1997ን መድገም ሳይሆን ያ ዕለት የያዘውን ክብረወሰን መስበር ነው መሆን የሚጠበቅብንና ወጣቱ ጎን በመቆም የወጣቱን ሰማያዊ ፓርቲን ጥሪ ለመተግበር ዝግጁ እንሁን፡፡ በየጓዳችን ቁጭ ብለን ማውራት ጠቀሜታ ስለሌለው ሁላችንም ለነጻነት፤ ለዴሞክራሲ፤ ለሰብአዊ መብት መከበር፤ ለፍትሕ የበላይነት፤ አብረን እንቁም፡፡
አንዳንድ አልኩ ባዮች እራሳቸው ከፍርሃት ለመላቀቅና የተካሄደው የሰማያዊ ፓርቲ ሠላማዊ ሰልፍ ሕዝባዊ አጀንዳ መሆኑንና ዘር ሃይሞኖት ፆታ ሳይለይ ኢትዮጵያዊ የሆነና መገዛት ያንገፈገፈው፤ ኑሮን መግፋት የተሳነው፤ መብቱ የተደፈረበት፤ ፍትህ የተነፈገ፤ የዴሞክራሲ መብት የተነፈገ ወንድ ሴት ትልቅ ትንሽ ሳይል ሁሉም እንዲወጣ ማለታቸውን ቸል በማለት በብዛት የወጡት ሴቶች ናቸው፤ የሙስሊሙ ቁጥር በዛ፤ የሰማያዊ ፓርቲ አባሎች ምነው አነሱ በማለት ከቤቱ ቁጭ ብሎ ቡናውን ሲያንቃርር የዋለ ሁሉ ለትችት ቀደም ቀደም ይላል፡፡ለመሆኑ ይህን መሰሉ ሕዝባዊ ጥሪ ማንንም ከማንም አይለይም ሲባል ለምን ተብሎ ነው በሃይማኖት በፆታ እየመዘኑ በዛ አነሰ ማለት ያስፈለገው፡፡ ይቺ ተልእኮ ያላት አካሄድ ስለሆነች አድማጫ አታገኝም እዚያው መንደር ተቦክታ ሳትጋገር ኮምጥጣ ትደፋለች፡፡
ግንቦት 25 የማይረሳ ሆኖ ባለፈ ማግስት ደግሞ የገዢው ፓርቲ ቅርሻቶች እነ ሰራዊት ፍቅሬ ሌላ ሴራ አውጠንጥነው ቀርበዋል፡፡ አርቲስቶችና ጋዜጠኞች ወደጂጂጋ ወርደው የሶማሌን ክልል ጎበኙ ለልማት ቃል ገቡ፤ ምኑ ቅጡ፡፡ በሰሞኑ ሙስና ለእስር ከተዳረጉት መሃል በጥላቻ የተወነጀሉ እንደመኖራቸው ያህል በምርም የተጠረጠሩበትን ፈጽመው የተከሰሱ መኖራቸው ግልጽ ነው ባይባልና ሊደመደም ባይቻልም በሂደት የምናየው ሆኖ ሠራዊት ፍቅሬ መዘለሉ ግን ብዙውን ያስገረመ ጉዳይ ነው፡፡
ሠራዊት ምልጃና ጉዳይ ማስፈጸምን እንደቋሚ ስራው፤ ግን በከለላ የሚያካሂደው የሙስና ሽምቅ አቀባባይ ድልድይ ለመሆኑ አቃቤ ሕግ ቢሮ ያሉ በርካታዎቹ የሚያውቁት ነው፡፡ ሠራዊት እኮ ግንባር ቀደም የአርቲስቶች ተጠሪ እንዲሆን በሹመት መልክ የተሰጠው ቦታ እንጂ ባለሙያዎቹማ ምን አውቀው፡፡ ብቻ ዝም ብለው በፍርሃት ሲጠራቸው እየተንጋጉ ይሄዳሉ፤ ምነው ሲሏቸው ከጀርባው ያሉት ሴት ሃይላቸው ከፍተኛ በመሆኑ ይላሉ፤ ማን ባለቤቱ ሲባሉም እንዲያውም ዋናዋ የነበሩት ሴት እንጂ፤ ይላሉ፡፡ ስም አይጠሩም በደፈናው ነው የሚናገሩትም የሚፈሩትም፡፡ ለነገሩ ይህን ማከናወን ከነበረበትም መከናወን ያለበት በየሙያ ማሕበሩ ሲሆን ሠራዊት ጥልቆ በመን ደንብና ሕግ ዘው እንዳለ ሲታሰብ ከገዢው ፓርቲና ከባለስልጣናቱ ለወንጀል ማካካሻ እንዲሆን የተሰማራበት ቦታ ነው ማለት ይቻላል፡፡
ሰይፉ ፋንታሁን፤ ሙሉዓለም ታደሰ፤ተስፋዬ አበበ፤ አበበ ባልቻ፤ጌትነት እንየው፤……….ሌሎችም አንድ ሕበረት ፈጥረው በመታደም ገዢውን ፓርቲ ለማገልገል ተማምለው የቆሙ ስለሆኑ በተጠሩ ቁጥር እጥፍ ዘርጋ በማለት ሕዝብን ክደው፤ ሃገርን ዘንግተው፤ ራሳቸውን በማስቀደም ለሆዳቸው አድረዋል፡፡ ሲነጋስ ምን ይሉን ይሆን?
ጊዜ ምስክር ሆኖ ለማየት ያብቃን፡፡
ሌላው እንዳይታወቅበት አድብቶ ዋነኛ አቀንቃኝ በመሆን ከአዜብ መስፍን ጉያ በመወሸቅ ማንኛው ነጋዴ ምን አደረገ፤ ምን አተረፈ፤ ምን አዘዘ ከውጭ ምን አስመጣ፤ እነማን ምን እያደቡ ነው የሚለውን በሽምቅ እያሰባሰበ ዕለት ተዕለት ሪፖርት በማቅረብ ቀደም ብሎ ተቀራርቦ ጥቅሙን በማስጠበቅና ባለሙያውን ሁሉ በተለይም በቪዲዮ ፕሮዳክሽን በኩል ሲኒማ ቤቶችን ማዘዝና ፕሮግራም በማሰረዝ የራሱ ብቻ እንዲታይ፤ የራሱን ፊልሞች ሲያዘጋጅም አስፈላጊውን ሁሉ ያለ ችግር እንዲመቻችለት ቀጭን የትዕዛዝ ሰነድ በጉያው ያነገበው፤ በኤግዚቢሽን አዳራሽ ያለውን የሴቫስቶፖልን የፊልም ማሳያ እንደንብረቱ እንዲያዝበትና በጣም አነስተኛ ክፍያ ብቻ ከፍሎ እንዲረከበው የተመቻቸለት ቴዎድሮስ ተሸመ የተባለው ፍቅር ሲፈርድ፤ ቬጋስ ወይስ አባይ፤ እና ሌሎችንም የቪዲዮ ፊልሞች በአዘጋጅነትና በፕሮዲዩሰርነት ያቀረበው ነው፡፡
ቴዎድሮስ ከወ/ሮ አዜብ ጋር ባለው የጠበቀ ቁርኝት ወ/ሮ አዜብ የኤይድስ መቆጣጠርያ ቢሮ የቦርድ ሰብሳቢ ሆነው በሚሰየሙበትና በርከት ያለ የውጭ ምንዛሪ እርዳታ ለተጠቂዎች እንዲውልና ለመከላከል ተብሎ ለሚነደፍ ፕሮግራም ማካሄጃ እንዲሆን የታቀደውን ገንዘብ ቴዎድሮስ እንደልቡ እንዲገለገልበት መንገዱ የተመቻቸለት ለሆዱ ያደረና በስውርም ራዊት ፍቅሬ ጋር ግንባር ፈጥሮ ለወያኔ አገልግለ፤ት አበርካችና ሰብቀኛ ነው፡፡
ብዙ በጥበብ ስም ጥበበኛውን በሽርፍራፊ ክፍያ እየገዙ የራሳቸውን ገቢ የሚያዳብሩ ስለ ጥበብም ሆነ ስለ ጥበበኛው አንዳችም ደንታ የሌላቸው ከሚጨበጠው በርካታ ቁጥር ገንዘብ ተርፎ የሚንጠባጠበውን በመላስ እራሳቸውን ለባርነት ያስገዙ ሞልተዋል ወደፊት ማን ምን እንዴት በሚል ዘርዘር ተደርጎ እስኪቀርብ ለመነሻ ያህል ይህን ካልኩ ዘንዳ፤
ከስንብቴ በፊት ግን አንድ መሰረት ያለው ጥያቄ ላንሳና መልስ የሚሰጥ ካለ ልጠብቅ፡፡
ለመሆኑ ሠማያዊ ፓርቲ ጥሪ ያደረገላቸውና በዚህ ሕዝባዊና ሃገራዊ በሆነው ሠላማዊ የትግል ሰልፍ ላይ አብረን እንቁም ያላቸው የየተቃዋሚ ድርጅቶች አባላትና አመራሮች በዕለቱ የት ገቡ?
ተቃዋሚ ድርጅቶቹ አባላት ሌላው ቢቀር በአደባባዩ ተገኝተው የድጋፍ ንግግር ለማድረግ አለመብቃታቸው ምናልባት ገዢው ፓርቲ ፈቅዶ አደጋ የጣለ እንደሁ ብለው ይሆን በየቤታቸው የመሸጉት?
ከሰልፍ በኋላ አንዳንዶቹ መግለጫ ሰጥተዋል ሲባል ሰማሁ ዕለቱ ካለፈና ክንዋኔው ተስፋ ያሳየ፤ ጥንካሬን ያረጋገጠ፤ ሲሆን የዚያ አካል ለመሆን ነው መግለጫው?
እስቲ ይህ የገባው ካለ ቢያስረዳኝ!