ህጻን ልጇን በሻሽ አንቃ በመግደል የጣለችው ተከሳሽ ላይ የእስራት ቅጣት የተወሰነባት መሆኑን የኢትዮጵያ ፖሊስ አስታወቀ፡፡
በአርሲ ዞን የሒጦሳ ወረዳ ፖሊስ እንደገለፀው በተከሳሽ መስታወት ደረጄ ላይ የእስራት ቅጣት ሊወስንባት የቻለው ከወለደችው የሶስት ወር እድሜ ያለውን ልጇን ሐምሌ 14 ቀን 2ዐዐ6 ዓ.ም ከቀኑ 11 ሰዓት በሚሆንበት ጊዜ ጎንዴ ፊንጨማ ልዩ ስሙ ሾሪማ ተብሎ ከሚታወቅበት አካባቢ በመውሰድና ከበቆሎ ማሳ ውስጥ በመግባት በያዘችው ሻሽ አንቃ በመግደሏ ነው፡፡ እንደ ሒጦሳ ወረዳ ፖሊስ ገለጻ የተገደለውን ህጻን የተመለከቱ የአካባቢው ነዋሪዎች ለፖሊስ በሰጡት ጥቆማ መሰረት አስከሬኑ ተነስቶ በዳግማዊ ሚኒሊክ ሆስፒታል በተደረገለት የአስከሬን ምርመራ መሠረት ህጻኑ ታንቆ መገደሉ ተረጋግጧል ተብሏል፡፡
ተከሳሿ በቁጥጥር ስር ውላ በሰጠችው የእምነት ቃልም በቡና ቤት አስተናጋጅነት እየሰራች ሳለ ከተዋወቀችው አሽከርካሪ ጋር ፍቅር በመመስረቷና ከወለደችለት በኋላ ሊረዳት ፍቃደኛ ባለመሆኑ ድርጊቱን ልትፈጽም መነሳሳቷን ፖሊስ አስታውቋል፡፡
ጉዳዩን ሲከታተል የቆየው የአርሲ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ተከሳሽ መስታወት ደረጄን በአስራ ስድስት ዓመት ጽኑ እስራት እንድትቀጣ ወስኖባታል፡፡