Quantcast
Channel: Ethiopian News | ዘ-ሐበሻ | Latest News Provider | News For All
Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

ኢትዮጵያ የአንድ ቢሊዮን ዶላር ‹‹ሶቨሪን ቦንድ›› ለዓለም ገበያ አቀረበች

$
0
0

euros_390_1102የኢትዮጵያ መንግሥት በቅርቡ የ‹‹ሶቨሪን ቦንድ›› ሽያጭ ለዓለም ገበያ ለማቅረብ በወሰነው መሠረት የአንድ ቢሊዮን ዶላር ቦንድ ሽያጭ ረቡዕ ኅዳር 17 ቀን 2007 ዓ.ም. በእንግሊዝ ለንደን ከተማ ለኢንቨስተሮች ይፋ ማድረጉን የሪፖርተር ምንጮች ገለጹ፡፡

ኢትዮጵያ በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ ያቀረበችው ‹‹ሶቨሪን ቦንድ›› ሽያጭ በአሥር ዓመት ተከፍሎ የሚያልቅ መሆኑን የጠቆሙት ምንጮቻችን የወለድ ምጣኔው ከስድስት እስከ ሰባት በመቶ እንደሆነም ጠቁመዋል፡፡

በገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስትሩ የሚመራው ልዑካን ቡድን ውስጥ የአገሪቱ ብሔራዊ ባንክ ገዥ አቶ ተክለ ወልድ አጥናፉ፣ በገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር ውስጥ የዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት ትብብር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተሩ አቶ ፍስሃ አበራ፣ የሕግ አገልግሎት ዳይሬክተሩ አቶ ዋሲሁን አባተና የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲና ማኔጅመንት ዳይሬክተሩ አቶ መዝገቡ አምሃ እንደተካተቱም ተገልጿል፡፡

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ኅዳር 3 ቀን 2007 ዓ.ም. በዝግ ባካሄደው መደበኛ ጉባዔው በሥራ አስፈጻሚው የቀረበለትን የ‹‹ሶቨሪን ቦንድ›› ሽያጭ ተወያይቶ በማፅደቅ፣ ቦንዱን የመሸጥ ኃላፊነት ለገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር ተሰጥቷል፡፡

በዚህም መሠረት ነው የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስትሩ የሚመሩት ልዑካን ቡድን ቦንዱን ለመሸጥ ወደ ለንደን ያመራው፡፡ ከለንደን ቆይታው በኋላም በተወሰኑ ሌሎች የአውሮፓ አገሮች ቦንዱን ለሽያጭ የሚያቀርብ ሲሆን፣ በሚቀጥለው ሳምንት ደግሞ ወደ አሜሪካ በመጓዝ የቦንድ ሽያጩን ያከናውናል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ አህመድ ሸዴ ባለፈው ዓርብ ከዓለም ባንክና ከአፍሪካ ልማት ባንክ ጋር የብድር ስምምነት በተፈራረሙበት ወቅት ሪፖርተር በ‹‹ሶቨሪን ቦንድ›› ሽያጩ ዙሪያ ሊያነጋግራቸው ቢሞክርም፣ የቀረበውን መጠን ከመግለጽ ተቆጥበዋል፡፡ ይሁን እንጂ ‹‹እጅግ በጣም ጥሩ የሚባል የወለድ ምጣኔ አግኝተናል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ቦንዱን ያቀረብንበት ወቅት ጥሩ ስለሆነ ነው፤›› ብለዋል፡፡

‹‹ሶቨሪን ቦንድ›› በሌላ መጠሪያው ደግሞ ‹‹ዩሮ ቦንድ›› ማለት የኢትዮጵያ መንግሥት የህዳሴውን ግድብ ለመገንባት ለኢትዮጵያውያን በአገር ውስጥ እንዳቀረበው ዓይነት የመንግሥት ሰነድ ሆኖ ይኼኛው የሚለየው ለዓለም አቀፍ ገበያ ወይም ለኢንቨስተሮች በዶላር ወይም የውጭ ምንዛሪ የሚቀርብ መሆኑ ነው፡፡

የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር የ‹‹ሶቨሪን ቦንድ›› ሽያጩን ለማከናወን በአመቻችነት የአሜሪካውን ጄፒ ሞርጋንና የጀርመኑን ዶች ባንክን የመረጠ ሲሆን፣ ባንኮቹም በአሁኑ ወቅት ቦንዱን መግዛት የሚችሉ ኢንቨስተሮችን በመምረጥ ከኢትዮጵያ ልዑክ ጋር እያገናኙ መሆኑን ምንጮች ጠቁመዋል፡፡

አጠቃላይ የልዑኩ ቆይታ በሚቀጥለው ሳምንት ይጠናቀቃል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን፣ በማጠናቀቂያው ዕለትም ከቀረበው ቦንድ ምን ያህል መሸጡ ይፋ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

በቦንድ ሽያጩ የሚገኘው ገንዘብ የውጭ ምንዛሪን የሚጠይቁ ፕሮጀክቶችን ብቻ ለመገንባት እንደሚውል የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ሚኒስትሩ አቶ ሬድዋን ሁሴን ባለፈው ኅዳር 3 ቀን 2007 ዓ.ም. ወቅታዊ ጉዳዮችን በተመለከተ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ላይ ገልጸዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት የውጭ ምንዛሪን የግድ ከሚጠይቁት ግዙፍ ፕሮጀክቶች መካከል የታላቁ ህዳሴ ግድብና በዕቅድ ተይዘው ያልተጀመሩ አገር አቀፍ የባቡር ትራንስፖርት ፕሮጀክቶች ይጠቀሳሉ፡፡

Source:: Ethiopian Reporter


Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>