ከአንዷለም አስፋው
በምስራቅ ሸዋ ሎሚ ወረዳ (ሞጆ) ታህሳስ 19 ቀን 1979 ዓ/ም ተወልዳ በናዝሬት ቅዱስ ዮሴፍ ት/ቤት ከጀማሪ እስከ 12ተኛ ክፍል የተከታተለች ሲሆን በናዝሬት የጥበቡን ኢንዱስትሪ ለማሳደግ ተፍ ተፍ ከሚሉት ወጣት ገጣሚያን መካከል አንዱዋ ነበረች፡፡ ይሄን እንቅስቃሴዋን ያዩት ኮሜዲያን እንግዳዘር ነጋ እና ገጣሚ ፊርማዬ ዓለሙ ወደ አዲስ አበባ መጥታ ስራዎችዋን እንድትገፋበት ከፍተኛውን ሚና ተጫውተዋል፡፡
ልፋታቸውም ባዶ ሜዳ ላይ አልቀረም በጋዜጠኝነት አጫጭር ስልጠናዎችን በመውሰድ በኤፍ.ኤም 96.3 እና በኢቲቪ 2 (ኢቢሲ 2) ላይ ከ10 ዓመት በላይ በማገልገል ላይ ትገኝ ነበር፡፡
በዚህም አላበቃችም በ1999 ዓ.ም የመጀመሪያ ግጥም መድብል የሆነውን ‹‹የጠፈር አበባ›› የተሰኘውን መፅሐፍ ስታሳትም በ2003 ዓ/ም በሴት ገጣሚያን ማህበር ውስጥ የተለያዩ ግጥሞችን ለንባብ አብቅታለች ከነዚህ ውስጥ ‹‹የእኛ›› የተባለው የግጥም መድብል በአንባቢያን ዘንድ ተወዳጅነትን አትርፎላታል፡፡
ጋዜጠኛ ፣ ገጣሚ እና አርቲስት ትዕግስት ምትኩ ወደ ትወናውም እንድትመጣ እንደ አብዛኞቹ አርቲስቶች ሁሉ የክቡር ደ/ር ተስፋዬ አበበ (ፋዘር) እጅ አርፎበታል፡፡ በዚህም ለቁጥር የሚከብዱ የሬዲዮ ድራማዎች ላይ የተሳተፈች ሲሆን በቴሌቭዥን አጫጭር ድራማዎችን በመስራት ላይ ትገኝ ነበረ፡፡
በፊልሙ ዘርፍ ከአምስት ያላነሱ ፊልሞችን የሰራች ሲሆን ከዚህ ውስጥ በህዝብ ዘንድ ተወዳጅነትን ያተረፈችበት ‹‹እሾአማ አጥር›› ይጠቀሳል፡፡
በእነዚህ ፊልሞች ልምድ እና ተሞክሮ የወሰደችው ትዕግሰት በ2006 ዓ/ም ለስክሪን የበቃው ‹‹ኤመን›› የተሰኘው የሙሉ ጊዜ ፊልም ላይ በድርሰት እና በአዘጋጅነት እንዲሁም ፕሮዲዩስ አድርጋለች፡፡
በጋዜጠኝነቱ ከኤፍ.ኤም 96.3 እና ከኢቲቪ 2 (ኢቢሲ 2) በተጫማሪ በቃል ኪዳን ፣ በሮዳስ እና በሮያል መፅሔቶች ላይ የተለያዩ ፅሁፎችን ለንባብ ታቀርብ ነበር፡፡
ጋዜጠኛ ፣ ገጣሚ እና አርቲስት ትዕግስት ምትኩ በቅርቡም አዲስ ነጠላ ዜማ ሰርታ ለማሳተም በእንቅስቃሴ ላይ ትገኝ ነበር፡፡
የ28 ዓመትዋ ወጣት ጋዜጠኛ ፣ ገጣሚ እና አርቲስት ትዕግስት ምትኩ በቅዱስ ጴጥሮስ ሆስፒታል ህክምናዋን በመከታተል ላይም ነበረች፡፡
ጋዜጠኛ ፣ ገጣሚ እና አርቲስት ትዕግስት ምትኩ የቀብር ስነ-ስርዓት ሐርብ 12/03/07 ከቀኑ 6፡00 ሰዓት በቀራኒዮ ቅዱስ ገብርሔል ቤተ ክርስቲያን ይፈፀማል፡፡
……..እሱ የወደደውን አደረገ የወደደውንም ወሰደ….. ቲጂዬ ነብስሽን በገነት ያኑረው አዘኔ ከባድ ነው፡፡