ከሱራፌል ወንድሙ
ተሼ … አንተን የዓመቱ ታላቅ ሰው ብለን ስንሰይም ስናከብርህ፤ ክበሩ የእኛ ነው። ፍኖተ ጥበብ የጥበብ ሰውነትህን ከፍ ከፍ ሲያደርግ፣ ላንተ ደርሶ አዲስ ከፍታ ለመስጠት ሳይሆን መጪውም ትውልድ ስምህን ሲዘክር እንዲኖር ጥቁምታ ለመስጠት ነው። የግማሽ ምዕት የሙዚቃ ስራህን አስበን፣ ለዘመናት የትዝታዎቻችን አካል መሆንህን በአንክሮ ተመለክተን፣ እንደሁላችን በስደት እየኖርክ የስደት ቀናቶቻችንን በሙዚቃ ስራዎችህ ማዋዛትህን አድንቀን፣ ዓይናማዎች ነን የምንለው እኛ የሚችሉ አካል ጉዳተኞችን እንዳይችሉ በምናንጉዋጥጥበት፣ በምናደናቅፍበት ዓለም ውጣ ውረዶችን አልፈህ ለዓይነ ስውራን ወገኖቻችን ብቻ ሳይሆን ለሁሉም የፅናት ተምሳሌት መሆንህን ተረድተን፣ ለወጣት የኪነ ጥበብ ሰዎች መነቃቂያ መሆንህን መስክረን ነው ዛሬ በዚህች በመጥን ትንሽ በሃሳቡዋ ግን ትልቅ በሆነችው የማህብረሰባችን መድረክ ልናነግስህ የወደድነው። በብዙ የሙዚቃ መሳሪያዎች ተጫዋችነት፣ በሙዚቃ ደራሲነት፣ አቀናባሪነት እና ድምፃዊነት ገና ከ1950ዎቹ መጨረሻ ጀምረህ እስከአሁን ድረስ በጥበብህ ህይወታችንን በማድመቅህ እንዲህ በደማቁ እናደንቅሃለን።
…//…
ተሾመ አሰግድ በ1942 ዓ.ም ነው በድሮዋ ወለጋ ጠቅላይ ግዛት የተወለደው። አሁን 63ኛ ዓመቱን ይዙዋል። ገና የአምስት ወር ልጅ እያለ የአይኑን ብርሃን ያጣው ተሾመ እናት ሆነው ያሳደጉት በዝምድና ቁዋጠሮ አክስት በወል ግን እናቱ የሆኑት ወይዘሮ አማካለች ይመር ናቸው። ስድስት ወንድ እና ስምንት ሴት በተወለደበት ቤተሰብ ውስጥ ተሾመ ለአቶ አሰግድ ይመር አራተኛው ልጅ ነው። ቨምንም እንኩዋን በአክስቱ ወ/ሮ አማከልች ጥረት፣ የመንደሩን ልጆች የኔም ናቸው ብሎ በሚያሳድገው ጎረቤት ክብካቤ ቢያድግም ተሾመ ራስን መቻል ይሉትን ጥበብ፣ በገዛ እግር መቆም ይሉትን ብልሃት ገና ብላቴና ሳለ ነው የሚያውቀው። በደምቢዶሎ ቡና በረንዳ ከትላልቆቹ ነጋዴዎች ጆንያ ሾልኮ የሚፈስ ቡና እየለቀመ በመሸጥ ትምህርት ቤት ሲሄድ የሚያጌጥበትን ሸራ ጫማ መግዛት ችሎ ነበር። ተሰጥኦ የሚሉት መክሊት ገና በጠዋቱ እድል ፈንታውን ያሰመረለት ተሾመ በመንደሩ ሰርግ ቤቶች አይታጣም ነበር።
“የኔን የህይወት መስመር እግዚአብሔር በመልካም ሲያበጅልኝ ነው የኖረው” ብሎ የሚያምነው ተሾመ አሰግድ፤ ሚስተር ራሰል ከሚባሉ ኦሮሚኛን አቀላጥፈው ከሚናገሩ ካናዳዊ የወንጌል መምህር ጋር የተገናኘባትን ጀምበር የዛሬ ማንነቴ መሰረት የተጣለባት ነች ይላል። እኚህ ሰው ተሾመን ገና በስድስት ዓመቱ መንገድ አግኝተውት ይህ ህፃን ትምህርት ማግኘት አለበት ብለው ጂፕ መኪናቸው ውስጥ አስገብተው ይዘውት ተፈተለኩ። አዲስ ነገርን የመከተል የልጅነት ጉጉት የሁዋሊት ወደቤተሰቦቹ ጎትቶ ያላስቀረው ተሾመም ሚስተር ራሰልን በፈቃደኝነት ተከተላቸው።
በሃገሩ ወግ ባህል ወደ ሰውነቱ ይዘልቅ የጀመረው የጥበብ እርሾ ከፈርንጁ ዘመናዊ የሙዚቃ ዕውቀት ጋር ተዋህዶ የወደፊት የሙያ እንጀራው ይጋገር ዘንድ ተሾመ ገና በልጅነቱ ከታች በእግር እየተረገጠ ከሚሰራው የድሮ ፒያኖ ጋር ተዋወቀ። ይህ የሆነው የሚስተር ራሰል ባለቤት ቤቱዋ ይህንን የሙዚቃ መሳሪያ ትጫወት ስለነበር ነው። ፒያኖውን ስትጫወት እስሩዋ ሆኖ በአርምሞ ያዳምጣት የነበረው ይህ ልጅ እሱዋ ዘወር ስትል ተደብቆ የልጅ ጣቶቹን ፒያኖው
ቁልፎች ላይ ያሩዋሩጣቸው ጀመር። ገና በአስራ ሶስት ዓመቱ ጥሩ ሙዚቃ መጫወት የመቻሉ ሚስጥር ቁዋጠሮ እንዲህ ባሉ የትላንት ወዲያ ታሪኮቹ ውስጥ ነው የሚገኙት።
ቁምጣ፣ ጥበቆና ሸሚዝ ተገዝቶለት በትምህርት ቤት ገበታ ሊቀመጥ የቻለው ተሾመ ማየት ለሚችሉት ብዙ ቦታዎችን ለአይነ ስውራን ደግሞ ጥቂት ቦታዎችን አሰናድቶ ያስተምር በነበረው የአሜሪካን ሚሽን ትምህርት ቤት ውስጥ ነበር። እናም እስከ አስር ዓመት እድሜው ድረስ እዚያው ተማረ።
አንድ ቀን በአጋጣሚ ቀዳማዊ ሃይለስላሴ ተሾመ የሚማርበትን ትምህርት ቤት ለመጎብኘት ደምቢዶሎ ይሄዳሉ። ህፃናቱን እየዞሩ እያናገሩ ነበርና ለታዳጊው ተሾመም ጥያቄዎችን አቀረቡለት። በኦሮምኛ ነበር ያናገሩት። “ኦሮምኛ ትችላለህ?” የሚለውን ጥያቄ አስቀድመው “እኛ ማን ነን?” ብለው ጠየቁት። እሱም ምን ልጅ ቢሆን ወቅቱ የሚፈልገውን ቁዋንቁዋ ያውቅ ነበርና “የኢትዮጵያ ብርሃን ግርማዊ ጃንሆይ” አላቸው። “ምን እንድናደረግልህ ትፈልጋለህ?” ጠየቁት። በወቅቱ ከፍተኛ የመሰለውን ነገር እንዲፈፅሙለት ነገራቸው። ንጉስ ነበሩና አልክብዳቸውም። ሸራ ጫማው ተገዛለት።
የሚማርበት ትምህርት ቤት ተማሪዎቹን ይዞ ይጉዋዝበት የገንዘብ አቅም ስላለነበረው ጥያቄውን ለቀዳማዊ ሃይለስላሴ አቅርቦ ከስምንት ተማሪዎች ገሚሶቹ ወደ ባኮ ሲሄዱ ገሚሶቹ ደግሞ ወደ ሰበታ ተሸኙ። ተሾመ ለሶስት ዓመታት ባኮ ቢመቀመጥም ለጆሮ ህክምና ስዊድን ደርሶ ከመጣ በሁዋላ ወደ ሰበታ ተዛወረ።
በወቅቱ አጠራር “መርሃ ዕውራን” ተብሎ በሚታወቀው ትምህርት ቤት ዛሬ በካናዳ ከሚኖረው አብዱቄ ከፈኔ እና ከሌሎች ባልንጀሮቹ ጋር ሙዚቃን በቅጡ መለማመድ ጀመረ። የትምህርት ቤቱ ዳይሬክተርን ጨምሮ እነ ፕሮፍሰር አሸናፊ ከበደ፣ ተስፋዬ ለማ፣ ዓለማየሁ ፋንታ እና መላኩ ገላውን የመሰሉ ሰዎች ተሾመን በማበረታቱ እና የሙያ ፈር በማስያዙ ረገድ በኩል ጉልህ ሚና ተጫውተዋል።
እናም ገና በወጣትነቱ ፍሬውን ማየት ማሳየት ጀመረ። ከስድስት የሰበታ አይነ ስውራን ትምህርት ቤት ጉዋደኞቹ ጋር ሆኖ “ሬንቦው” የተባለ ቡድን አቁዋቁመው ለረዥም ጊዜ ሰርተዋል። “ይህች አጋጣሚ” የተሰኘው የጥላሁን ገሰሰ ዜማ አስቀድሞ ተሾመ አሰግድ ገና በለግላጋነቱ ሊጫወተው የነበረ ዜማ ነው። በአሁኑ ሰዓት ዊስኮነሰን የሚኖረው የህግ ባለሙያ ዶክተር በቀለ ሃይለየሱስ የደረሰው ይህ ስራ በመጀመሪያ ሊቀነቀን የነበረው በተሾመ አሰግድ ቢሆንም የፊሊፕስ ኩባንያ ባለቤት በተፅዕኖ ዜማው ለጥላሁን ገሰሰ እንዲሰጥ ቢያደርጉም ጥላሁን የተሾመን ያማረ አጨዋወት አይቶ የገበያው መሪ ባለሃብት የወሰኑትን መቀልበሱ ባይቻለው እንባውን አፍስሶ ከሙዚቃ ሽያጩ ያገኘውን ሙሉ ገቢ በወቅቱ እሱን ላጀቡት ለእነ ተሾመ አሰግድ – ለሬንቦ ባንድ ስጥቱዋል።
ተሾመ “ውጋጋን” በተባለው የኢትዮጵያ ዓይነ ስውራን ማህበር የሙዚቃ ቡድን ውስጥም አገልግሉዋል። ተሾመ ከውጭ የትምህርት ቆይታው በሁዋላ ሙያዊ አበርክቶውን ከለገሰባቸው ተቁዋማት መካከል የዓይነ ስውራን ማህበር አንዱ ሲሆን አመራር በመስጠትም ሙያዊና ወገናዊ ሃላፊነቱን ተወጥቱዋል።
ተሾመ እንደአብዛኛው የወቅቱ ወጣት በእድገት በህበረት ዘመቻ ተሰልፎ ነበር። ያንን የወቅቱን ግዴታ ከተወጣም በሁዋላ ነበር ጀርመን አገር ሄዶ የፒያኖ ቅኝት እና ፒያኖ አሰራር ትምህርቱን የተከታተለው። አሁን ኬምኔትስ ተብላ በምትጠራው፤ በቀዝቃዛው ጦርነት የበርሊን ግንብ ዘመን ካርልማረክሽታት ትባል በነበረችው ከተማ በብሎንደን ሴነትሩም ወይም የዓይነ ስውራን ትምህርት ማዕከል ነበር እንደ አውሮፓ አቆጣጠር በ1980 ዓ.ም ወደ ከፍትኛ ትምህርት ምዕራፍ የተቀላቀለው። የጀርመንኛ ቁቃንቁዋን ያጠናበትን ስድስት ወር ጨምሮ በአጠቃላይ ለሁለት ዓመት ከመንፈቅ ነበር ተሾመ ትምህርቱን በጀርመን ሃገር ተከታትሎ በዲፕሎም የተመረቀው።
ተሾመ ትምህርቱን በብቃት ጨርሶ ሃገሩን ለማገልገል ወደ ኢትዮጵያ በመንፈሰ ሙሉነት ተመልሶ በቅድሚያ ወደ ያሬድ ሙዚቃ ትምህርት ቤት ነበር ያቀናው። ተቁዋሙ ግን በልምድ ከሌላ መምህር የተማሩትንና በዘልማድ የሚሰሩትን ዓይናማ ሰው በፒያኖ ቃኚነት ቀጥሮ እያሰራ በጀርመን ሃገር ትምህርት ቤት ገብቶ ሙያውን በብቃት ቀስሞ የመጣውን ተሾመ አሰግድን አልፈልግህም አለው። ለነገሩ ይህ የሙዚቃ ትምህርት ቤት እንደ ፐሮፌሰር አሸናፊ ከበደ አይነት በእኩልነት የሚያምኑ ሰዎች የነበሩበት መሆኑ ባይታበልም አይነ ስውራን ሙዚቃን መማርም ሆነ ማስተማር አይችሉም በሚል እና እነሱን ተቀብለን ለማስተናገድ በበቂ አልተዘጋጀንም በሚል አስባብ እስከዘንድሮ አይነ ስውራንን ከሙዚቃ ትምህርት ገበታ ነጥሎ ኖሩዋል።
ተሾመ ግን በዚያ መገፋት ተስፋ ሳይቆርጥ የባህል ሚኒሰቴርን እና ቴአትር ቤቶችን በር ደጋግሞ አንኩዋኩዋ። የእነዚህ ተቁዋማት በሮች በዋናነት ለዓይናማዎቹ ብቻ የተከፈቱ ነበሩና ማንኩዋኩዋቱ ተሰምቶ በሮቹ አልተክፈቱለትም። ተሾመ ግን “አንኩዋኩቻለሁ፤ በሮቹ ግን አለትከፈቱም” ብሎ መቆዘምን፣ ቀያጅ የሆነው የማህረሰቡ አስተሳሰብ የሚፅፍለትን ዕጣ መቀበልን ምርጫው አላደረገም። የማይከፈቱ በሮችን ከማነኩዋኩዋት ይልቅ ሌሎች በሮችን ወደ መሰራት ሄደ። በተለያዩ ባንዶች ውስጥ ማገልገሉን፣ ከእውቅ ሙዚቀኞች ጋር ተባብሮ መስራቱን ቀጠለ። በሁዋላም ጎረቤት ሃገር ጅቡቲን መኖሪያው አደረገ። ለነገሩ ወደዚያም ሄዶ መስራት ዋዛ አልነበረም። ከሃገር እንዳይወጣ በሮችን ሊቆልፉበት የታገሉም ነበሩ። ማመልከቻው በአንድ ባለስልጣን ጠረጴዛ ላይ ልታርፍ በመቻሉዋ ነበር የጅቡቲ ጉዞውም በመጨረሻ የተሳካው።
በጅቡቲ የአምስት ዓመት ቆይታው “የኩባያ ወተት” የተሰኘ ስራው ገንኖ ቢወጣም ተሾመ የተለያየ ሃገር ዜጎችን ለማዝናናት በተለያዩ ቁዋንቁዋዎች ያዜም ነበር። እንግሊዝኛ፣ ፈረንሳይኛ፣ አፋርኛ፣ ሶማልኛ እና ሌሎችም።
ተሾመ በሙዚቃ ቅንብር በኩል ከኦርኬስትራ ኢትዮጵያ ጋር ስራዎችን አበርክቱዋል። ከነዚህም ውስጥ ለጥላሁን ገሰሰ ያቀናበራቸው “አልማዝን አይቼ”፣ “ያለቀሰ ሲስቅ” እና “ውቢት ህይወቴ ነሽ” የሚሉት ተጠቃሾች ናቸው። በተጨማሪም በኦርኬስትራ ኢትዮጵያ ቆይታው የፀሐይ እንዳለን ዜማም አቀናብሩዋል። ይህም ሆኖ ግን ተሾመ ቅንብርን በሙሉ መንፈስ ስራዬ ብሎ የያዘው በኢትዮጵያ ሙዚቃ ውስጥ የራሱን የድምፅ አሻራ ካተመው ከኢትዮ ስታር ባንድ ጋር ሲሰራ እንድሆነ ይናገራል።
ተወዳጁ አርቲስት ቴዎድሮስ ታደሰ ከህዝብ ጋር በሰፊው ያስተዋወቀው ስራው የሉባንጃዬ ካሴቱ እንደሆነ ይታወቃል። ከዚያ ካሴት ውስጥ በዜማም ሆነ በግጥም እንዲሁም በቅንብር የሚገደፍ አንድም ስራ የለም ብንል ማጋነን አይሆንም። እንደ ሉባንጃዬ እና ቀን ሳይመሽ ሳይጨልም በጊዜን የመሳሰሉት ምርጥ ስራዎች የተካተቱበትን ይህንን ሙሉ ስራ ያቀናበረው ተሾመ አሰግድ ነው።
በሁዋላም የሂሩት በቀለን ልጅ የመስፍን ኤልያስን እና ጥላሁንን ይተካል በሚል ማሞካሻ ይሞገስ የነበረውን ነገር ግን በልጅነቱ በሞት የተቀጨውን የደሳለኝ ቢሻውን ካሴቶችም አቀናብሩዋል። ኪቦርድ ወይም ሲንተሳይዘር የሚባለውን መሳሪያ በመጫወትም ድምፃውያንን አጅቡዋል።
የሙዚቃ መሳሪያዎች ጨዋታ ከተነሳ የተሾመ ችሎታ ሊወሳ ግድ ነው። ተሾመ ክራር፣ መሰንቆ፣ ዋሽንት፣ አኮርዲዮን፣ ፒያኖ- ኪቦርድ የመሳሰሉትን መሳሪያዎች ይጫወታል።
አርቲስት ተሾመ አሰግድ በግልና በጋራ በአጠቃላይ ስድስት አልበሞችን ለህዝብ አበርክቱዋል።
1. “ትዝታ”፡ ከሬንቦው ባንድ ጋር በመሪ ድምፃዊነት ፊሊፕስ ባስቀረፀው ሸክላ 2. “በላሽው”፡ የካሴት ስራ ከሬንቦው ባንድ ጋር
3. “የኩባያ ወተት”፡ ከሮሃ ባንድ ጋር
4. “ደርባባዬ”፡ ከሮሃ ባንድ ጋር
5. በቡድን ከኬኔዴ መንገሻ እና ራሄል ዮሐንስ ጋር
6. በቡድን ከነበዛወርቅ አስፋው፣ ኤሊያስ ተባባልና ማርታ አሻጋሪ ጋር
ተሾመ በተናጥል ተወዳጅ ከሆኑለት እና ዛሬ ድረስ ወጣቶችን እያነቃቁ ከሚገኙት ዜማዎች መካከል “የኔ አካል የኔው ነሽ”፣ “አገሬ ነገር የዛው ሙዳይ”፣ “እንዲያው ዘራፌዋ”፣ “ያዘልቃል ያልሽው ፈጣን መኪና” እና ሌሎችም ተጠቃሾች ናቸው።
ተሾመ አሰግድ በግሪክ፣ ጣልያን፣ ጀርመን፣ ሆላንድ፣ ስዊድን፣ ጅቡቲ፣ ካናዳ እና እንግሊዝ ሃገራት የሚኖሩ አድናቂዎቹን በሙዚቃ ስራዎቹ የደረሰ ሲሆን፤ በሰሜን አሜሪካ ኢትዮጵያውያን በሚኖሩባቸው ከተሞች ሁሉ ማለት በሚባል ደረጃ ተፈጥሮ በለገሰችውና በዘመናት ልምድና ችሎታው ሲያገለግለን ኖሩዋል።
እናመሰግንሃለን! እናከብርሃለን!