ትምህርትህ ሚኒስተር የዜጎችን ህገ መግስታዊ መብት በመጣስ አዲስ ባወጣው የአምልኮ፣ አለባበስ እና አመጋገብ ስርአት ደንብ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከህዳር 30 ጀምሮ ተግባራዊ እንዲደረግ የዩኒቨርሲቲው አስተዳደር ትዕዛዝ ማስተላለፉን ምንጮች ዘግበዋል፡፡
በአዲሱ የትምህርት ሚኒስተር ደንብ መሰረት ማንም ሙስሊም ሃይማኖቱ የሚደነግግበትን ግዴታዎች መፈፀም የሚከለክል ሲሆን በተለይም ሙስሊም ሴት እህቶቻችን ሂጃባቸውን እንዲያወልቁ አልያ ደግሞ ትምህርታቸውን እንዲያቋርጡ የሚያስገድድ ነው፡፡
ሴኩላሪዝም ሲባል መንግስት እና ሃይማኖት የተለያዩ መሆናቸውን የሚገልፅ መርህ ቢሆንም ሴኩላር ሊሆን የሚችለው መንግስታዊ ስርአቱ እንጂ ሰዎቹ አለመሆናቸው ግልፅ ነው፡፡ ሆኖም ሙስሊሙን ማህበረሰብ ከሃይማኖቱ ለማራቅ ከተነደፈው ዋነኛ ስትራቴጂ አንዱ በትምህርት ቤቶች እና በዩኒቨርሲቲዎች እንዲሁም በመንግስት መስሪያ ቤቶች ውስጥ ሙስሊሞች በሃይማኖታቸው ግዴታ የተደረገባቸውን ድንጋጌዎች እንዳይተገብሩ የሚያዝ መመሪያ ማውጣት አንዱ ነው ፡፡
ይህ ህገ ደንብ በረቂቅነት በወጣበት ጊዜ በወቅቱ በሙፍቲህ ሃጂ ኡመር ኢድሪስ በሊቀመንበርነት ይመራ የነበረው የኢትዬጲያ ኡለማዎች ምክር ቤት ህገ ደንቡ ከኢስላማዊ ድንጋጌዎች ጋር የሚጋጭ በመሆኑ ማስተካከያ እንዲደረግበት መጠየቃቸው የሚታወስ ቢሆንም በመንግስታዊ ተሷሚ መጅሊሶች እንዲጸድቅ መደረጉ ይታወቃል፡፡
ይህንንም ህገ ደንብ የተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ተግባራዊ እያደረጉት ሲሆን አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲም ከ ህዳር 30 ጀምሮ በሁሉም ካምፓስ የሚገኙ አስተዳደሮች እና የጥበቃ ሰራተኞች ህገ ደንቡ ተግባራዊ መሆኑን በጥብቅ እንዲከታተሉ ጥብቅ ማሳሰቢያ ከዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ፅ/ቤት ትዕዛዝ መውጣቱን ምንጮች አስታውቀዋል፡፡
በመላው ሃገሪቱ ሙስሊም ሴት እህቶቻችን ሂጃባችሁን አውልቁ በሚል ከትምህርት ገበታቸው እየተፈናቀሉ እንደሚገኙ መዘገባችን የሚታወስ ነው፡፡