አቶ አስራት አብርሃም በእስር ላይ የሚገኘው የአቶ ሃብታሙ አያሌው የስራ ኃላፊነት ተክቶ የአንድነት ፓርቲ ተጠባባቂ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ሆኖ በመስራት ላይ ይገኛል፡፡ ስለ ፓርቲው ወቅታዊ ሁኔታና የወደፊት አቅጣጫ በተመለከተ ከአቶ አስራት ጋር ተወያይተናል፡፡ ፍቱን፡-በዚህ ወቅት መንግሥት በያዘው አቋም እና ተቃዋሚዎች ባላቸው ደካማ አደረጃጀት እና ምላሽ ምክንያት ፓርቲዎቹ እንኳን የህዝቡን መብት ከጥቃት ሊከላከሉ ለራሣቸው መሆን አቅቷቸዋል፣ የፓርቲዎች መኖር ጉዳት እንጂ ጥቅሙ አልገባንም የሚሉ ድምጾች በዝተዋል?
አስራት፡-ባለው ነባራዊ ሁኔታ ነው የሚወስነው ፣ በእርግጥ እዚህ አገር ችግር አለ:: ተቃዋሚዎች በውጪያዊ ተጽዕኖና በውስጣዊ ችግር እንደተፈለገው ተጠናክረው ሊወጡ አልቻሉም:: እየተከፋፈሉ፣ እየፈረሱ፣ እየተገነቡ ነው ያሉት:: በዚህ ምክንያት የአቅመቢስ ሆነዋል:: ይህ ሂደት መቀየር አለበት ብለን ነው የምናስበው:: ከዚህ ጋር ተያይዞ በአንድነት ውስጥ ፖለቲካውን በተሻለ አቅምና ራዕይ መምራት ያስፈልጋል፣ አዲስ አመራር መምጣት አለበት የሚል አቋም አምጥተዋል:: ያንን የለውጥ ፍላጐት ተከትሎ ፕሬዝዳንቱ ስልጣናቸውን ለቀው ለውጡ መጥቷል:: በዚህም ምክንያት ፓርቲውን ለሚያጠናክር አንዳንድ ሥራዎች እየሠራን ነው:: ፓርቲው የህዝብ ፓርቲ የሚሆንበትን መንገድ እየፈለግን ነው:
:በእርግጥም ፓርቲዎች ካልተጠናከሩ በስተቀር ብቅ የሚሉትን የፖለቲካ አመራሮች ለእስር እየዳረጉ፣ ፓርቲ እየተጐዳ፣ የህዝብ ሞራል እየተዳከመ የሚሄድበት ሁኔታ ሊቀጥል ይችላል::