(ነገረ ኢትዮጵያ) ትናንት ህዳር 3/2007 ዓ.ም ከቀኑ 5 ሰዓት ጀምሮ በቦሌ ክፍለ ከተማ የማሪያም ቤተ ክርስቲያን እንዳይፈርስ በመቃወማቸው የታፈኑት ዜጎች የት እንደደረሱ አልታወቀም ሲሉ በወቅቱ ጉዳዩን ሲከታተሉ የነበሩ የአካባቢው ነዋሪዎችና የእምነቱ ተከታዮች ለነገረ ኢትዮጵያ ገለጹ፡፡
በወቅቱ 600 ያህል ዜጎች ተገኝተው ቤተ ክርስቲያኗ እንዳትፈርስ ሲቃወሙ እንደተመለከቱ የገለጹት የነገረ ኢትዮጵያ ምንጮች የቤተ ክርስቲያኗን መፍረስ የተቃወሙትን ጨምሮ ሌሎች በአካባቢው የተገኙ ዜጎችም በፖሊስ መታፈሳቸውን ገልጸዋል፡፡ ነዋሪዎቹ ‹‹ህዝቡ በሰንደቅ አላማ አምላክ አታፍርሱብን እያለ ቢለምንም እነሱ ግን ጥይት ወደላይ በመተኩስ ህዝቡን ከማሸበራቸውም በላይ ያገኙትን እየደበደቡ በ9 የድንጋይ መጫኛ መኪና አስገድደው በመጫን ወዳልታወቀ ቦታ ውስደዋቸዋል፡፡ አድማ በታኝ ፖሊስ ቄስ፣ አዛውንት፣ ህጻንና ሴት ሳይል ያገኘውም አፍሶ ወስዷል፡፡ የኮብል ስቶን ጠራቢዎች ሳይቀሩ በአካባቢው በመገኘታቸው ታፍሰው ታስረዋል፡፡ አሁን የት እንዳሉ አይታወቅም፡፡›› ሲሉ ገልጸዋል፡፡
ቤተ ክርስቲያኗ ከተሰራች ከሁለት አመት በላይ እንደሆነ የገለጹት አንድ የአካባቢው ነዋሪ ‹‹ቤተ ክርስቲያኗ ከተሰራችበት ጊዜ ጀምሮ እንድትፈርስ ጥያቄ እንደቀረበ ተገልጾልን አያውውም፡፡ አሁን ነው ደርሰው ያፈረሱት፡፡ የቤተ ክርስቲያኗን አገልጋዮች ጨምሮ በጣም ብዙ ሰው በዱላ ተደብድቧል፡፡ ይህ ሁሉ የሆነው የእምነቱን ተከታዮች በመናቅ ነው፡፡›› ሲሉ ቅሬታቸውን ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጸዋል፡፡
የአካባቢው ነዋሪዎችና አማኞች ከቀኑ 5 ሰዓት ጀምሮ እስከ 9 ሰዓት ቤተ ክርስትያኗ እንዳትፈርስ እንደተቃወሙ፣ አድማ በታኝ ፖሊስ በአካባቢው ያገኘውን ሰው ካፈሰ በኋላ ቤተ ክርስቲያኗን በማፍረስ ቆርቆሮውን በመኪና ጭኖ እንደሄደ የአይን እማኞች ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጸዋል፡፡