የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ የወረዳ 19 ምክትል ሰብሳቢ ወጣት ባህሩ ራህመቶ ግንቦት 20/2005 ማለዳ ከመኖሪያ ቤቱ በደህንነት አባላት ከተወሰደ በኋላ የሚገኝበት ፖሊስ ጣብያ ሳይታወቅ ለቀናት መቆየቱንና በማረፊያ ቤቱ እንዲቆይ ያደረገው ፖሊስም እስከ ግንቦት 27/2005 ፍርድ ቤት ሳያቀርበው መቆየቱን መዘገባችን አይዘነጋም፡፡
ሜክሲኮ ዋቢ ሸበሌ ሆቴል ፊት ለፊት በሚገኘው የአዲስ አበባ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በ27/2005 እንዲቀርብ የተደረገው ባህሩ ሰማያዊ ፓርቲ ግንቦት 17/2005 ሊያደርገው የነበረን ሰላማዊ ሰልፍ ስትቀሰቅስ ነበር የሚል ክስ እንደቀረበበት ለመረዳት ተችሏል፡፡የፍርድ ሂደቱን የባህሩ ወዳጆች፣ጋዜጠኞችና ታዛቢዎች በሚገኙበት ግልጽ ችሎት እንዲከናወን አለመደረጉም ብዙዎችን አስገርሟል፡፡ባህሩ ፍርድ ቤት በቀረበበት ዕለት የባለ ራዕይ ወጣቶች ማህበር ተቀዳሚ ፕሬዘዳንትና የህዝብ ግኑኝነት ሃላፊ የሆነው ወጣት ብርሃኑ ተክለያሬድ ለህዝብ ዝግ በሆነ ችሎት ጉዳዩን እንዲከታተል ተደርጓል፡፡
ፖሊስ የእነ ብርሃኑን ክስ ለመምራት የሚያስችለው ስልጣን እንደሌለው በመጥቀስ ሁለት ቀጠሮ የጠየቀበትን ጉዳይ ፍርድ ቤቱ እንዲዘጋለት ቢጠይቅም
ዳኛው የአዲስ አበባ ፖሊስ ክሱን ለፌደራል ፖሊስ እንዲያዞር በማዘዝ ክሱ ለፌደራል ፖሊስ ካልዞረ ግን በ29/5/2005 መዝገቡን በመዝጋት ተጠርጣሪዎቹን በነጻ እንደሚያሰናብቱ አስረድተዋል፡፡የእነ ብርሃኑ ጠበቃ የሆኑት አቶ ተማም አባቡልጉ‹‹ፍርድ ቤቱ ከፖሊስ የቀረበለትን ጥያቄ በመቀበል ያለ በቂ መረጃ እየተንገላቱ የሚገኙትን ደምበኞቻቸውን በነጻ ማሰናበት ሲገባው ተለዋጭ ቀጠሮ መስጠቱ እንዳስገረማቸው ገልጸዋል፡፡
የባህሩና የብርሃኑ ቤተሰቦችና የቅርብ ሰዎች ነገ በሚካሄደው የፍርድ ችሎት ሁለቱ ወጣቶች በነጻ ሊሰናበቱ እንደሚችሉ ተስፋ ማድረጋቸውን ለፍኖተ ነጻነት ተናግረዋል፡፡
source:- http://www.fnotenetsanet.com/?p=4543