ሪፖርተር
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በትላንትናው ውሎው ኢትዮጵያ ‹‹ሶቨሪን ቦንድ›› ለዓለም አቀፍ ገበያ መሸጥ አለበት በሚለው ጉዳይ ላይ በዝግ ተወያይቶ መወሰኑን የሪፖርተር ምንጮች ገለጹ፡፡
ምክር ቤቱ ባካሄደው በዚህ መደበኛ ጉባዔ ላይ አምስት አዋጆች በግልጽ በአጀንዳነት መያዛቸውን የገለጹት ምንጮቻችን፣ የኢትዮጵያና የብራዚል የአቪዬሽን ስምምነትና ሌሎች ተመሳሳይ የሁለትዮሽ ስምምነቶች በይፋ በአጀንዳነት እንደሚታወቁ ገልጸዋል፡፡
በይፋ በአጀንዳነት ያልተያዘውና ለፓርላማ አባላትም ጊዜው እስኪደርስ ያልተነገረው የሶቨሪን ቦንድ ሽያጭ መሆኑን ምንጮቻችን ገልጸዋል፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ለሚነሱ ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠትም በኢኮኖሚ ጉዳዮች ከአገሪቱ ቁልፍ ሰዎች መካከል አንዱ የሆኑት የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስትር አቶ ሱፊያን አህመድ መገኘታቸውን ምንጮቻችን ገልጸዋል፡፡
በቀረበው አጀንዳ ላይ ፓርላማው ለረዥም ሰዓት ከፍተኛ ክርክር ማድረጉን ተናግረዋል፡፡ ፓርላማው የተወያየበትን ጉዳይ በዝርዝር እንዲነግሩን የምክር ቤቱ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊን ብንጠይቅም፣ ‹‹በዝግ የተካሄደ ጉዳይ ላይ መረጃ መስጠት አይቻልም፤›› ብለዋል፡፡
ውይይት የተደረገበት አጀንዳ ሶቨሪን ቦንድ ለዓለም ገበያ ማቅረብ የተመለከተ ቢሆንም፣ መረጃው ወደ ውጭ እንዳይወጣ የምክር ቤቱ አባላት እንደተነገራቸውና በጉባዔው ላይ የቀረበው ሰነድም ከፓርላማ እንዳይወጣ የፓርላማው የጽሕፈት ቤት ሠራተኞች ሳይቀሩ ማስጠንቀቂያ እንደተሰጣቸው ከምንጮቻችን ለመረዳት ተችሏል፡፡ ጉዳዩን በዝርዝር ለማወቅ ለሚኒስትር ሱፊያን አህመድና የሥራ ባልደረቦቻቸው እንዲሁም አንዳንድ የፓርላማ አባላትን በስልክ የጠየቅን ቢሆንም አልተሳካም፡፡
በተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት የኢኮኖሚ ጉዳይ አማካሪና የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህር የሆኑት ዶ/ር ቆስጠንጢኖስ በርሄ የሶቨሪን ቦንድ ጉዳይ ለፓርላማ ሊቀርብ የሚችልበት ምክንያትን ከዓለም አቀፍ ልምዳቸው እንዲያስረዱን በጠየቅነው መሠረት፣ ኢትዮጵያ ሶቨሪን ቦንድ ለዓለም አቀፍ ገበያ ማቅረብ አለባት ወይስ የለባትም የሚለውን ተወያይቶ ፓርላማው የማፅደቅ ኃላፊነት ያለበት በመሆኑና ይህንን ኃላፊነትም የትኛው ተቋም ይምራው የሚለውን ለመሰየም ሊሆን እንደሚችል ግምታቸውን ሰጥተዋል፡፡ ጉዳዩ ይህ ከሆነ ኃላፊነቱን በኢትዮጵያ ሁኔታ ሊወሰድ የሚችለው የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
ለህዳሴው ግድብ ግንባታ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ቦንድ ሲሸጥ የሚሰጠው የዋስትና ሰርተፍኬት መሆኑን ያስታወሱት ዶ/ር ቆስጠንጢኖስ፣ ለዓለም አቀፍ ገበያውም የሚሰጠው ሰርተፍኬት ተመሳሳይ ሆኖ አገሪቱ በቦንድ ሸያጩ በውጭ ምንዛሪ የምታገኘውን ብድር የምትከፍለው ዕዳዋ መሆኑን ፓርላማው በሚያፀድቀው አዋጅ ዋስትና መስጠት እንዳለበትም አስረድተዋል፡፡
ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም ዕዳዋን መክፈል አቅቷት ከፍተኛ የብድር ዕዳ ያለባቸው አገሮች ኢኒሼቲቭ (ሂፒኮ) አማካኝነት ከተሰረዘላት በኋላ ስታገኝ የነበረው ብድር ከኮሜርሽያል (ንግድ) ባንኮች ሳይሆን በአገሮች መካከል በሚደረግ መግባባት የረዥም ጊዜ ቀላል ብድር እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
ነገር ግን በቅርቡ በኢትዮጵያ መንግሥት የተቀጠሩ ሦስት ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች የኢትዮጵያ የውጭ ብድር የመሸከም ጫና ከገመገሙ በኋላ በሰጡት ምዘና ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ የቦንድ ገበያ ላይ መሳተፍ እንደምትችል መረጋገጡን ዶ/ር ቆስጠንጢኖስ ገልጸዋል፡፡
የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስትሩም ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ የቦንድ ገበያ ውስጥ እንደምትገባና ለዚህም ይረዳ ዘንድ ሦስት ዓለም አቀፍ ኤጀንት (ወካይ) ባንኮችን መመረጣቸውን ባለፈው ጥቅምት ወር መጀመሪያ ላይ መግለጻቸው ይታወሳል፡፡
የሪፖርተር ዝግጅት ክፍል ፓርላማ ስለቀረበው አጀንዳ ማክሰኞ ማምሻውን መረጃ ከማግኘቱ ሰዓታት በፊት በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ መግለጫ የሰጡት የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ሚኒስትር አቶ ሬድዋን ሁሴን፣ መንግሥት ከሶቨሪን ቦንድ ሽያጭ ምን ያህል የውጭ ምንዛሪ ብድር ማግኘት እንደሚፈልግ የተጠየቁ ቢሆንም ከመመለስ ተቆጥበዋል፡፡
‹‹ከዓለም አቀፍ የቦንድ ሽያጭ (ሶቨሪን ቦንድ) ምን ያህል ገንዘብ ነው የምንፈልገው የሚለውን የሚመለከተው የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴርን ነው፤›› ብለዋል፡፡
ይሁን እንጂ በጣም ጥንቃቄ በተሞላበት መንገድ በአገር ውስጥ ብር ሊሠሩ የማይችሉና የግድ የውጭ ምንዛሪን የሚጠይቁ የልማት ፕሮጀክቶችን ለመሥራት የሚያስችል ብድር ብቻ በሶቨሪን ቦንድ ሽያጭ ለማግኘት እንደተፈለገ ሚኒስትር ሬድዋን ገልጸዋል፡፡
‹‹እነዚህን ፕሮጀክቶች በመሥራታችንም ኢኮኖሚው ይበልጥ ራሱን መገንባትና የተበደረውንም መክፈል የሚያስችሉ መሆናቸውን ታሳቢ ያደረገ ብድር ለማግኘት እንሠራለን፡፡ ይህም ሲሆን ደግሞ የአገሪቱን የመበደር አቅም ያገናዘበ ኢኮኖሚው በቀላሉ መክፈል የሚችለው መሆን እንዳለበት መንግሥት አምኖ እየሠራ ነው፤›› ብለዋል፡፡
‹‹ከሚፈለገው በታች ብድሩ ቢመጣ መንግሥት የሚፈልገውን ሥራ ለመከወን አያስችለውም፤›› ያሉት አቶ ሬድዋን፣ ‹‹በውጭ ምንዛሪ እጥረት ማነቆ የሚሆንበት ፕሮጀክት የትኛው ነው የሚለው ተለይቶ ለዚያ የሚሆን ገንዘብ ለማምጣት ነው የሶቨሪን ቦንድ ሽያጭ ውስጥ የሚገባው፤›› ብለዋል፡፡