ጭራቁ ህዳር 2005!
እ.ኤ.አ በ2005 ኢትጵያውያን/ት ለመናገር የሚዘገንን እጅግ በጣም የሚያስፈራ ድርጊትን አስተናግደዋል፡፡ በዚያኑ ዓመት በግንቦት ወር የተካሄደውን ፓርላሜንታዊ ምርጫ ተከትሎ የህዝብ ድምጽ በአደባባይ በጠራራ ጸሐይ በመዘረፉ ምክንያት ታቃውሟቸውን በሰላማዊ መንገድ ለመግለጽ ወደ አደባባይ የወጡ በመቶዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን/ት አሁን በህይወት በሌለው የገዥው አካል ቁንጮ ፈላጭ ቆራጭ መሪ በነበረው በመለስ ዜናዊ ልዩ ትዕዛዝ እና ቁጥጥር በግፍ በጥይት ተደብድበው እንዲያልቁ ተደርገዋል ወይም ደግሞ በፖሊስ እና በደህንነት ኃይሎች በጥይት ተደብድበው በከፍተኛ ደረጃ ቁስለኛ ሆነዋል፡፡ በመለስ ዜናዊ ልዩ ትዕዛዝ በተቋቋመ አጣሪ ኮሚሽን የምርመራ ውጤት መሰረት ተቃውሟቸውን ለመግለጽ በሰላማዊ መንገድ በአውራ መንገዶች ተሰልፈው የነበሩትን 193 ምንም ዓይነት የጦር መሳሪያ ያልታጠቁ ወንዶች፣ ሴቶች እና ልጆች እንዲሁም በከፍተኛ ደረጃ ጥብቅ ክትትል እየተደረገባቸው በእስር ቤት ይገኙ የነበሩ የህግ እስረኞችን ጨምሮ ሆን ተብሎ ታስቦበት እና ተመክሮበት በወሮበላ ፖሊሶች እና የደህንነት ኃይሎች ጭንቅላቸውን እና ደረታቸውን በጥይት እየተደበደቡ እንዲገደሉ ተደርገዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ 763 ወገኖቻችን ከባድ ቁስለኛ ሆነዋል**፡፡
እ.ኤ.አ ከ2007 ጀምሮ ሁልጊዜ በየዓመቱ ህዳር በመለስ ልዩ ትዕዛዝ እና ቁጥጥር የዕልቂቱ ሰለባ የሆኑትን በመቶዎች የሚቀጠሩ ንጹሀን ዜጎች ሰማዕት ለመዘከር እና ለማስታወስ የዝክረ ሰማዕት ጸሁፍ እያዘጋጀሁ ለአንባቢዎቼ ጀባ እላለሁ፡፡ እነዚህ ጀግኖች ሰማዕታት ለዴሞክራሲ እና ለነጻነት ሲሉ መተኪያ የሌላትን ውድ ህይወታቸውን ገብረው አልፈዋል፡፡ እነዚህን ጀግኖች የነጻነት ሰማዕቶቻችንን መርሳት ነጻነትን እና ሰብአዊ መብትን መካድ እና መርሳት ማለት ነው፡፡ እ.ኤ.አ በ2007 “የሰኔ እና የህዳር 2005 የኢትዮጵያን ሰማዕታት ለዘላለም እናስታውስ!“ በሚል ርዕስ ባዘጋጀሁት የመጀመሪያ የሰማዕታቱ መታሰቢያ ጽሁፍ በአንድ ወቅት ከእልቂት በታምር የተረፈውን የኤሊ ዊሰልን አባባል በመዋስ በኢትዮጵያ “ለሞቱት እና በህይወት ላሉት ምስክር የመሆን የሞራል ግዴታ አለብን” በማለት አንባቢዎቼን አሳስቤ ነበር፡፡
የመለስ የእልቂት ሰለባ የሆኑትን ወገኖቻችንን ማስታወስ አለብን ምክንያቱም ኤሊ ዊሰል እንዲህ ብሎ ነበርና፣ “ያለፈውን የእኛ የጋራ ትውስታ የሆነውን ታሪክ እና ድርጊት ቀጣዩ ትውልድ እንዳያውቀው የመከልከል እንዲረሳ የማድረግ መብት የለንም፡፡ ያለፈውን እልቂት እና ሰቆቃ አለማስታወስ ወይም ደግሞ መርሳት አደገኛ ብቻ አይደለም፣ ሆኖም ግን በህዝብ ላይ የሚደረግ ዘለፋም ነው፡፡ የሞቱትን እና ሰማዕት የሆኑትን መርሳት እነዚህን የክብር ሰማዕቶች እንደገና ለሁለተኛ ጊዜ መግደል ማለት ነው፡፡“
ህዳር አረመኔ ወር ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ የማድረግ አቅሙ ቢኖረኝ እና የምችል ቢሆን ኖሮ በቀጥታ ህዳርን በመዝለል ከጥቅምት ወደ ታህሳስ ተወርውሬ እጓዝ ነበር፡፡ ስልጣን እና ኃይል ቢኖረኝ ኖሮ ህዳርን ወንጀለኛ ዘራፊ አድርጌ ለህግ አቀርበው ነበር፡፡ ህዳር የሚባል ወር ባይኖር ኖሮ የማስታውሰው ምንም ዓይነት ነገር አይኖርም ነበር፡፡ ማርክ ዋይን ይህንን ጉዳይ በማስመልከት እንዲህ ብለው ነበር፣ “እውነቱን እስከተናገርህ ድረስ ምንም ዓይነት የምታስታውሰው ነገር አይኖርም፡፡“ በእውነቱ ማርክ ዋይን ይህንን ሲሉ ተሳስተዋል፡፡ እውነታውን በተናገርህ ጊዜ ሁሉንም ነገር ታስታውሳለህ በተለይም ውሸቶችን፣ ጩኸቶችን፣ ወንጀሎችን፣ እልቂቶችን እና ፍጅቶችን፡፡
አሁን በህይወት የሌለው መለስ ዜናዊ እና የእርሱ የወንጀል ፈጻሚ እና ተባባሪ የሆነው የወሮበላ ድርጅት ህዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ (ህወሀት) በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ የሰሩትን ግፍ እና ሰቆቃ ማስታወስ እና እውነታውን ፍርጥርጥ አድርጌ ለወገኖቼ እና ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ማሳወቅ ለእኔ በጣም አስፈላጊ ጉዳዬ ነው፡፡ መለስ ዜናዊ እ.ኤ.አ በሰኔ እና በህዳር 2005 በመቶዎች የሚቆጠሩ ምንም ዓይነት የጦር መሳሪያ ሳይታጠቁ ተቃውሟቸውን በሰላማዊ መንገድ ለመግለጽ ወደ አደባባይ የወጡ ንጹሀን ዜጎችን በእርሱ የማን አህሎኝ የድፍረት እና የእብሪት ትዕዛዝ በጥይት እየተደበደቡ እንዲያልቁ ሲያደርግ ያለምንም ስህተት እና ግልጽ በሆነ መልኩ ለኢትዮጵያ ህዝብ ሊያስተላልፍ የፈለገው መልዕክት ነበረው፡፡ ይኸውም እርሱን እና ህወሀት የሚበለውን የጉግ ማንጉግ ደርጅት ለዘላለም በስልጣን ኮርቻ ላይ አጣብቆ ለማኖር ሲል በአውሬያዊ እና በአረመኒያዊ ምግባሩ ለሰላማዊ ተቃውሞ የሚነሳውን ንጹሀን ዜጋ ሁሉ ያለምንም ርህራሄ በገፍ መግደል፣ መምታት እና ማቃጠል እንደሚችል በተግባር ለማሳየት ነው፡፡ መለስ ዜናዊ የሬይችፉህረር ሄንሪክ ሂምለር (የጀርማን አረመኔ ናዚው ) ጎበዝ ተማሪ ነበር፡፡ የሄንሪክ ሂምለር አስተምህሮ በጎበዙ እና በባለራዕይው መሪ በመለስ ዜናዊ ጭንቅላት አድሮ እንዳለ ምንም ጠብ ሳትለው ኮርጆ እንዲህ የሚለውን የዕኩዮች ስነምግባር በስራ ላይ አውሎታል፣ “በጣም ተመራጭ የሆነው የፖለቲካ መሳሪያ ሽብርን መንዛት እና ማስፋፋት ነው፡፡ ጨካኝነት ክብርን ያዝዛል፡፡ ሰዎች ሊጠሉን ይችላሉ፡፡ ሆኖም ግን ስለእነርሱ ፍቅር ማግኘት አንጠይቅም፣ የምንጠይቀው ነገር ቢኖር ፍርሀት እንዲፈሩ ማድረግ ብቻ ነው፡፡“
መለስ እና የእርሱ ህወሀት ወሮበላ ቡድን ገና ከጫካ ከነበሩበት ጊዜ ጅምሮ ሁልጊዜ ሽብርን በመሳሪያነት ይጠቀሙ ነበር፡፡ እናም በአሁኑ ጊዜም የጸረ ሽብር ህግ እየተባለ የሚጠራ ቀያጅ ህግ በማውጣት እራሱ ሽብርተኝነትን በመተግበር ላይ ይገኛል፡፡ መለስ በንጹሀን ዜጎች ላይ ሊነገር የማይችል ጭካኔ እና ክልከላን በማድረግ ሰብአዊ መብትን ሲደፈጥጥ እና ክብርን ሲያዋርድ ቆይቷል፡፡ ምንም ዓይነት ክብር አልነበረውም፡፡ በአብዛኛው የኢትዮጵያ ህዝብ ክፍል ውስጥ ውርደት እና ንቀትን የሚቸረው ሰው ነበር፡፡ መለስ እና የእርሱ ወሮበላ ግብረ አበሮች ሁልጊዜ እንዲፈሩ ይፈልጋሉ፡፡ እነርሱ ግን በህዝቡ ዘንድ ተፈሪነት የላቸውም፣ ይልቁንም በኢትዮጵያ ህዝብ ይጠሉ እና ይናቃሉ፡፡ ይኸ ነው እንግዲህ እውነታው!
መለስ እ.ኤ.አ በ2005 ያልታጠቁ ሰላማዊ አመጸኞችን በጥይት ተደብድበው እንዲያልቁ በሚያደርግበት ጊዜ ከአዲስ አበባ በ9 ሺ ማይል ርቀት ላይ የሚገኝ እና ላለፉት ሶስት አስርት ዓመታት በኢትዮጵያ ምድር ላይ ያልነበረ የእርሱ የማይበገር እና ሰላማዊ ተቃዋሚ እንዲሁም እረፍትየለሽ ትችትን የሚያቀርብበት ከኢትዮጵያ ተገንጥሎ ያለ የአካዳሚ እና የህግ ባለሙያ ያለ አልመሰለውም ነበር፡፡ የመለስ እልቂቶች በህይወቴ አንድ ጥቁር ጠባሳ ጥለው ያለፉ እና የማልረሳቸው ሰቆቃዎች ሆነው ይኖራሉ፡፡ እኔ ኢትዮጵያን በለጅነቴ ጥዬ ስወጣ ወደ ኢትዮጵያ የመመለስ ሃሳብ ፈፅሞ አልነበረኝም። መለስ አነዚያን ንፁሃንን ሲያስጨፈጭፍ ምንያህል ኢትዮጵያ ከኔ ልብ አንዳልወጣች ተገነዘብኩ።
አንደሚባለው አስቸጋሪ ሁኔታ በሚፈጠርበት ጊዜ እኛ እራሳችን ድርጊቱን እነወስነዋለን ወይም ደግሞ ድርጊቱ እራሱ እኛን ይወስናል፡፡ በእኔ ላይ ሁለቱም ነበሩ፡፡
በመጀመሪያ ደረጃ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ለመሆን አልመረጥኩም ነበር፡፡ ሆኖም ግን መለስ ዜናዊ የእብሪት ትዕዛዝ በመስጠት ያልታጠቁ ንጹሀን ወገኖቻችንን በጥይት ባስፈጀበት ወቅት እራሱ መረጠኝ፡፡ መለስ ላስፈጃቸው ንጸሀን ዜጎች ምስክርነት ለመሆን አልመረጥኩም ነበር፡፡ ሆኖም ግን የመለስ የእልቂት ሰለባ የሆኑት ንጹሀን ዜጎች እራሳቸው ምስክር እንድሆናቸው መረጡኝ፡፡ ለዚህም ነው በእያንዳንዷ የሰኞ ዕለት አንዷንም ሳምንት ሳላስተጓጉል ለስምንት ዓመታት በሰማዕታቱ ጎን ቆሜ ምስክርነቴን ለዓለም የህሊና ፍርድ ቤት ማስረጃ ሳቀርብ የኖርኩት።
እ.ኤ.አ ከ2005 በፊት አሁን በህይወት የሌለው መለስ ዜናዊ ለእኔ ፍሬከርስኪ ዋጋቢስ ጨካኝ የአፍሪካ ሸፍጠኛ አምባገነን ነበር፡፡ የ2005ን የሞት እልቂት ካዘዘ በኋላ ግን በእኔ አዕምሮ ውስጥ የጭራቃዊነት፣ የአውሬነት ዋና ባለስልጣን ካቦ ሆነ፡፡ ጭራቃዊነትን መዋጋት አለብኝ ምክንያቱም ጭራቃዊነት አይሞትምና፡፡ ከሁሉም በላይ ጭራቃዊነትን መዋጋት አለብኝ ምክንያቱም በመጨረሻ ምንም ይሁን ምን መልካም ነገር በጭራቃዊነት ላይ ድል መቀዳጀቱ የማይቀር መሆኑ አጠራጣሪ አይደለምና፡፡
ለዚህም ነው ሁልጊዜ ህዳርን ማስታወስ ያለብኝ፡፡ የህዳርን፣ የታህሳስን፣ የመስከረምን፣ የጥቅምትን፣ ጭራቃዊነት ማስታወስ አለብኝ…
ጭራቁ መለስ ዜናዊ እና የእኩይ ምግባሩ ተባባሪ የሆነው ህወሀት የሚባለው የማፊያ ቡድን በኢትዮጵያ ላይ የሰሩትን ግፍ እና ሰቆቃ ማስታወስ አለብኝ፡፡ ኢትዮጵያን ለመገንጠል እና ለመገነጣጠል ያደረጉትን እኩይ ምግባር እና ጭራቃዊ ሁነት ሁልጊዜ ማስታወስ አለብኝ፡፡ በስልጣን ላይ እንደ መዥገር ተጣብቀው ለመኖር ሲሉ ብቻ የኢትዮጵያን ህዝብ እንዴት አድርገው መከፋፈል እንደቀጠሉ ማስታወስ አለብኝ፡ የኢትዮጵያ ህዝብ በረኃብ አለንጋ እየተገረፈ እና በድህነት አዘቅት ውስጥ እየማቀቀ ባለበት ሁኔታ እነዚህ ግፈኞች የሀገሪቱን ሀብት እየዘረፉ በውጭ ባንኮች የእራሳቸውን ሂሳብ እየከፈቱ በብዙ ቢሊዮን የሚቆጠር ዶላር የሚያጭቁበትን እኩይ ምግባር ማስታወስ አለብኝ፡፡
የመለስ ዜናዊ እና የህወሀት የአፈና እና ጭራቃዊ አገዛዝ የህያወት ሰለባ የሆኑትን ማስታወስ አለብኝ፡፡ ዓለም አቀፋዊ ዕውቅና እና ዝና ያለውን እና ከዋናው ከተማ በስተደቡብ በኩል በጥቂት ኪሎ ሜትሮች ወጣ ብሎ በሚገኘው በመለስ የማጎሪያ እስር ቤት ውስጥ ለብቻው ከሰው ተነጥሎ ታስሮ በመማቀቅ ላይ የሚገኘውን ኢትዮጵያዊ ጋዜጠኛ ወንድሜን እስክንድር ነጋን አስታውሳለሁ፡፡ ስለእርሱ የውሸት ፐሮጀክቶች እውነታውን በማፍረጥ ደፍራ በመጠየቋ እና በመጻፏ ምክንያት ብቻ በጨካኙ በመለስ ዜናዊ እስር ቤት ተወርውራ በመማቀቅ ላይ የምትገኘውን ወጣት እህቴን ርዕዮት ዓለሙን አስታውሳለሁ፡፡ ወንድሞቼን አንዷለም አራጌን፣ በቀለ ገርባን፣ አቡባከር አህመድን፣ ውብሸት ታዬን፣ ወጣቶቹን የዞን 9 ጦማሪያንን፣ ተመስገን ደሳለኝን እና ሌሎች በርካታዎቹን ሁሉ አስታውሳለሁ፡፡
ለምንድን ነው የማስታውሰው?
ማስታወስ ካልቻልኩ እነርሱን ሊያስታውስ የሚችል እዚያ ያለ ማን ነው? አስታውሳቸዋለሁ ምክንያቱም የምረሳቸው ከሆነ ተንሰራፍተው የቆዩት ወንጀሎች እና አረመኔ እና እብሪተኞቹ ወንጀለኞች ይረሳሉ፡፡ እኔ ከረሳኋቸው እንዴት አድርጎ ነው ታሪክ ሊያስታውሳቸው የሚችለው? ታሪክ ሊያስታውስ የሚችለው የሚያስታውስ ሰው ሲያገኝ ብቻ ነው፡፡ ስለሆነም ማስታወስ አለብኝ፡፡ የምስክርነት ቃሌን ሁልጊዜ ሰኞ እየሰጠሁ በህዳር፣ በታህሳስ እና በጥር… ውስጥ ማስታወስ አለብኝ፡፡ በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ ላሉ ወጣቶች እና ወደፊትም በኢትዮጵያ ለሚወለዱ ልጆች ማስታወስ አለብኝ፡፡ የኤሊ ውሰልን አባባል በመዋስ “ያለፈው ጊዜ የወደፊት ህይወታቸው እንዲሆን አልፈልግም፡፡”
በህዳር ውስጥ ለእኔ ምንም ዓይነት ደስታ ነገር የለኝም፡፡ እውነት ነው ህዳር ጨካኝ ወር ነው፡፡ የቶማስ ሁድ የሀዘን እንጉርጉሮ እንዲህ ይገልጸዋል፡
ምንም ሙቀት የለም፣ ምንም ደስታ የለም፣ ምንም ጤናማ ህይወት የለም፣
ማንም አባል የሚሰማው ምቹ ሁኔታ የለም፣
ምንም ጥላ የለም፣ ምንም ብርሀን የለም፣ ቢራቢሮዎች የሉም፣ ንቦች የሉም፣
ፍራፍሬዎች የሉም፣ አበባዎች የሉም፣ ቅጠሎች የሉም፣ ወፎች የሉም፣
ህዳር!
በእራሴ ነጻ ስንኝ ደግሞ “የመለስ የእልቂት ሰለባ ለሆኑ ወገኖቻችን ፍትህ የለም“
መለስ ላሰፈጃቸው በመቶዎች ለሚቆጠሩ ወገኖቻችን ፍትህ የለም፣
ቁጥር ስፍር ለሌላቸው ወንዶች፣ ሴቶች እና ልጆች ካሳ የለም፣
ከሞት ለተረፉት ወይም የጉዳት ሰለባ ለሆኑት ቤተሰቦች የሚሰጥ የጉዳት ከፍያ የለም፣
በህገወጥ መልክ ለእስር ለተዳረጉ በአስር ሺዎች ለሚሆኑ ዜጎች የፍርድ ማቅለያ ምህረት የለም፣
በህገወጥ አፈና የተሰወሩትን ዱካ የሚፈልግ የለም፣
በመስከረም፣ በጥቅምት እና በህዳር ለተፈጸሙት ወንጀሎች የተሰጠ ካሳ ወይም የተደረገ የኃጢአት ኑዛዜ የለም፣
የመለስ የህዳር እልቂትን አስመልክቶ የተጠየቀ ይቅርታ የለም፣
ህዳርን መድገም የለም፣
ህዳር መታወስ ያለበት ነው፡፡
እ.ኤ.አ የ2005 የወሮበላ ቡድኑ የእልቂት ሰለባ የሆኑትን ንጹሀን ዜጎች መርሳት በእነዚህ ዜጎች ላይ የተፈጸመውን ዘግናኝ እልቂት እና እነዚያን ኋላቀር አውሬ ወንጀለኞች የሰሩትን ወንጀል ይቅርታ እንደማድረግ ያህል ነው፡፡ እልቂቶችን መርሳት ለወንጀለኞች ምንጊዜም ተጠያቂ እንደማይሆኑ እና ደረታቸውን ነፍተው እየገደሉ፣ እያሰቃዩ እና ሰብአዊ ክብርን እያዋረዱ እንዲኖሩ ዋስትና የመስጠት ያህል ነው ምክንያቱም ወንጀሎቹ ተረስተዋል የሚል ትረጉም ስለሚያሰጠው፡፡ በመጨረሻ መርሳት ማለት በስልጣን ወንበር ላይ ተፈናጠው ለሚገኙ ወንጀለኞች ደግመው እና ደጋግመው ወንጀል እንዲሰሩ የግብዣ ወረቀት በመስጠት እብሪተኞቹ ያለምንም የወንጀል ተጠያቂነት እንዲኖሩ እንዲያውም ቀደም ከነበረው እልቂት በበለጠ መልኩ እንዲፈጽሙ ማደፋፈር ማለት ነው፡፡
አስታውሳለሁ ምክንያቱም ልረሳ አልችልም እናም አልረሳም! በፍጹም!
የ2005ን የእልቂት ሰላበዎች አስታውሳለሁ፡፡ እያንዳንዱን/ዷን እና እያንዳንዳቸውን አስታውሳለሁ፡፡ ለእኔ ቁጥር አይደሉም ይልቁንም ከዚያ በላይ በአዕምሮዬ ጓዳ ውስጥ አሉ፡፡ አሁን በህይወት የሌለው መለስ ዜናዊ እና የእርሱ የህወሀት ወሮበላ ቡድን የእነርሱን የግፍ ሰለባ የሆኑ ንጹሀን ዜጎች ስምየለሾች፣ መልከየለሾች፣ ሰውነት አልባዎች፣ ጓደኛ የለሾች እና ቤተሰብ የለሾች እንዲሁም ወገን አልባዎች ሊያደርጓቸው ይፈልጋሉ፡፡ መለስ የእልቂት ሰለባ እና አካለ ስንኩል ሽባ ያደረገው እያንዳንዱ/ዷ ዜጋ ለእኔ ልዩ ነው/ናት፡፡ እናት ለመሆን እንዳይችሉ የተደረጉትን ወጣት ሴቶች የተገደሉትን አስታውሳለሁ፡፡ አባት እንዳይሆኑ የተደረጉትን ወጣት ወንዶች የተገደሉትን አስታውሳለሁ፡፡ ወላጆቻቸው የእልቂት ሰለባ እንዲሆኑ የተደረጉባቸውን ወላጅ ያጡ ህጻናትየተገደሉትን አስታውሳለሁ፡፡ ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ ልጆቻቸውን ማየት ላልቻሉ አባቶች እና እናቶች እንዲሁም የልጅ ልጆቻቸውን ለማየት ያልቻሉትን አስታውሳለሁ ምክንያቱም ሁሉንም መለስ እንዲያልቁ እና እንዲፈጁ አደርጎባቸዋልና፡፡
እነዚህን ጭራቅ ወሮበላ ወንጀለኞች አልረሳቸውም፡፡ በወገኖቻችን ላይ ጭፍጨፋውን ሲያካሂዱ የነበሩ 237 የድሁር አስተሳሰብ ባለቤት የሆኑትን ነፍሰ ገዳይ ቅጥረኛ ፖሊስ ተብዮዎች፣ እንዲሁም ዋነኛ የወንጀሉ አቀናባባሪ መሀንዲሶች እና አውራ ወንጀለኞች አንድ በአንድ በስም አስታውሳቸዋለሁ፡፡ ምንጊዜም ቢሆን በህዳር ውስጥ አስታውሳለሁ፣ እንዲሁም በታህሳስ እና በጥርም፣ እንደዚሁም ደግሞ በየካቲት እና በሚያዚያም…
አስታውሳለሁ…
ሬቡና እርገጤ፣ የ34 ዓመት እድሜ እና ግንበኛ፣ መልሳቸው አለምነው፣ የ16 ዓመት እድሜ እና ተማሪ፣ ሀድራ ኡስማን፣ የ22 ዓመት እድሜ እና ስራዋ የማይታወቅ፣ ጃፋር ኢብራሂም የ28 ዓመት እድሜ እና የንግድ ባለሙያ፣ መኮንን፣ የ17 ዓመት እድሜ እና ስራው የማይታወቅ፣ ወልደሰማያት፣ የ27 ዓመት አድሜ እና ስራ የሌለው፣ ባህሩ ደምለው፣ እድሜው እና ስራው የማይታወቅ፣ ፈቃደ ነጋሽ፣ የ25 ዓመት እድሜ እና መካኒክ፣ አብረሀም ይልማ የ17 ዓመት እድሜ እና የታክሲ ሾፌር፣ ያሬድ እሸቴ የ23 ዓመት እድሜ እና የንግድ ባለሙያ፣ ከበደ ገብረ ህይወት፣ የ17 ዓመት እድሜ እና ተማሪ፣ ማቴዎስ ፍልፍሉ የ14 ዓመት እድሜ እና ተማሪ፣ ጌትነት ወዳጆ፣ የ48 ዓመት እድሜ እና የንግድ ባለሙያ፣ እንዳልካቸው ሁንዴ፣ የ18 ዓመት እድሜ እና ስራው የማይታወቅ፣ ቃሲም ረሺድ፣ የ21 ዓመት እድሜ እና መካኒክ፣ ኢማም ሸውሞሊ፣ የ22 ዓመት እድሜ እና የንግድ ባለሙያ፣ አልዬ ኢሳ፣ የ20 ዓመት እድሜ እና የቀን ሰራተኛ፣ ሳምሶን ያዕቆብ፣ የ23 ዓመት እድሜ እና የህዝብ ማመላለሻ ሰራተኛ፣ አለበለው አበበ፣ የ18 ዓመት እድሜ እና ተማሪ፣ በልዩ ቢ. የ18 ዓመት እድሜ እና የትራንስፖርት ረዳት፣ ዩሱፍ ጀማል፣ የ23 ዓመት እድሜ እና ተማሪ፣ አብረሀም አገኘሁ፣ የ23 ዓመት እድሜ እና የትራንሰፖርት ረዳት፣ መሀመድ በቃ፣ የ45 ዓመት እድሜ እና አርሶ አደር፣ ረደላ አወል፣ የ19 ዓመት እድሜ እና የታክሲ ሾፌር፣ ሀብታሙ ኡርጋ፣ የ30 ዓመት እድሜ እና የንግድ ባለሙያ፣ ዳዊት ጸጋዬ፣ የ19 ዓመት እድሜ እና መካኒክ፣ ገዛኸኝ ገረመው፣ የ15 ዓመት እድሜ እና ተማሪ፣ ዮናስ አበራ፣ የ24 ዓመት እድሜ እና ስራው የማይታወቅ፣ ግርማ ወልዴ፣ የ38 ዓመት እድሜ እና ሾፌር፣ ወ/ሮ ደስታ ብሩ፣ የ37 ዓመት እድሜ እና የንግድ ባለሙያ፣ ለገሰ ፈይሳ፣ የ60 ዓመት አዛውንት እና ግንበኛ፣ ተስፋዬ ቡሽራ፣ የ19 ዓመት እድሜ እና ጫማ ሰፊ፣ ቢኒያም ደገፋ፣ የ18 ዓመት እድሜ እና ስራ የሌለው፣ ሚሊዮን ሮቢ፣ የ32 ዓመት እድሜ እና የትራንስፖርት ረዳት፣ ደረጀ ደኔ፣ የ24 ዓመት እድሜ እና ተማሪ፣ ነብዩ ኃይሌ፣ የ16 ዓመት እድሜ እና ተማሪ፣ ምትኩ ዋለንዳ፣ የ24 ዓመት እድሜ እና የአገልግሎት ሰራተኛ፣ አንዋር ሱሩር፣ የ22 ዓመት እድሜ እና የንግድ ባለሙያ፣ ንጉሴ ዋበኝ፣ የ36 ዓመት እድሜ እና የአገልግሎት ሰራተኛ፣ ዙልፋ ሀሰን፣ የ50 ዓመት እድሜ እና የቤት እመቤት፣ ዋስሁን ከበደ፣ የ16 ዓመት እድሜ እና ተማሪ፣ ኤርሚያስ ከተማ፣ የ20 ዓመት እድሜ እና ተማሪ፣ መለያ ቁጥሩ 00428 የሆነ፣ የ25 ዓመት እድሜ እና ስራው የማይታወቅ፣ መለያ ቁጥሩ 00429 የሆነ፣ የ26 ዓመት እድሜ እና ስራው የማይታወቅ፣ መለያ ቁጥሩ 00430 የሆነ፣ የ30 ዓመት እድሜ እና ስራው የማይታወቅ፣ አዲሱ በላቸው፣ የ25 ዓመት እድሜ እና ስራው የማይታወቅ፣ ደመቀ አበበ፣ እድሜ እና ስራው የማይታወቅ፣ መለያ ቁጥሩ 00432 የሆነ፣ የ22 ዓመት እድሜ እና ስራው የማይታወቅ፣ መለያ ቁጥሩ 0045 የሆነ፣ የ20 ዓመት እድሜ እና ስራው የማይታወቅ፣ መለያ ቁጥሩ 13903 የሆነ፣ የ25 ዓመት እድሜ እና ስራው የማይታወቅ፣ መለያ ቁጥሩ 00435 የሆነ የ30 ዓመት እድሜ እና ስራው የማይታወቅ፣ መለያ ቁጥሩ 13906 የሆነ፣ የ25 ዓመት እድሜ እና ስራው የማይታወቅ፣ ተማም ሙክታር፣ የ25 ዓመት እድሜ እና ስራው የማይታወቅ፣ በየነ በዛ፣ የ25 ዓመት እድሜ እና ስራው የማይታወቅ፣ ወሰን አሰፋ፣ የ25 ዓመት እድሜ እና ስራው የማይታወቅ፣ አበበ አንተነህ፣ የ30 ዓመት እድሜ እና ስራው የማይታወቅ፣ ፈቃዱ ኃይሌ፣ የ25 ዓመት እድሜ እና ስራው የማይታወቅ፣ ኤሊያስ ጎልቴ፣ እድሜው እና ስራው የማይታው፣ ብርሀኑ ወርካ፣ እድሜው እና ስራው የማይታወቅ፣
አስታውሳለሁ…
አሸብር መኩሪያ እድሜው እና ስራው የማይታወቅ፣ ዳዊት ሰማ፣ እድሜው እና ስራው የማይታወቅ፣ መርሀጽድቅ ሲራክ፣ 22 ዓመት እድሜ እና ስራው የማይታወቅ፣ በለጠ ጋሻው ጠና፣ እድሜው እና ስራው የማይታወቅ፣ በሀይሉ ተስፋዬ፣ የ20 ዓመት እድሜ እና ስራው የማይታወቅ፣ መለያ ቁጥሩ 21760 የሆነ፣ የ18 ዓመት እድሜ እና ስራው የማይታወቅ፣ መለያ ቁጥሩ 21523 የሆነ፣ የ25 ዓመት እድሜ እና ስራው የማይታወቅ፣ መለያ ቁጥሩ 11657 የሆነ፣ የ24 ዓመት እድሜ እና ስራው የማይታወቅ፣ መለያ ቁጥሩ 21520 የሆነ፣ የ25 ዓመት እድሜ እና ስራው የማይታወቅ፣ መለያ ቁጥሩ 21781 የሆነ፣ እድሜው እና ስራው የማይታወቅ፣ ጌታቸው አዘዘ፣ የ45 ዓመት እድሜ እና ስራው የማይታወቅ፣ መለያ ቁጥሩ 21762 የሆነ፣ የ75 ዓመት አዛውንት እና ስራቸው የማይታወቅ፣ መለያ ቁጥሩ 11662 የሆነ የ45 ዓመት እድሜ እና ስራው የማይታወቅ፣ መለያ ቁጥሩ 21763 የሆነ፣ የ25 ዓመት እድሜ እና ስራው የማይታወቅ፣ መለያ ቁጥሩ 13087 የሆነ የ30 ዓመት እድሜ እና ስራው የማይታወቅ፣ መለያ ቁጥሩ 21574 የሆነ የ25 ዓመት እድሜ እና ስራው የማይታወቅ፣ መለያ ቁጥሩ 21761 የሆነ፣ እድሜው እና ስራው የማይታወቅ፣ መለያ ቁጥሩ 21569 የሆነ፣ የ25 ዓመት እድሜ እና ስራው የማይታወቅ፣ መለያ ቁጥሩ13088 የሆነ፣ የ30 ዓመት እድሜ እና ስራው የማይታወቅ፣ እንዳልካቸው ገብርኤል፣ የ27 ዓመት እድሜ እና ስራው የማይታወቅ፣
አስታውሳለሁ…
ኃይለማርያም አምባዬ፣ የ20 ዓመት እድሜ እና ስራው የማይታወቅ፣ መብራቱ ዘውዱ፣ የ27 ዓመት እድሜ እና ስራው የማይታወቅ፣ ስንታየሁ በየነ፣ የ14 ዓመት እድሜ እና ስራው የማይታወቅ፣ ታምሩ ኃይለሚካኤል፣ እድሜው እና ስራው የማይታወቅ፣ አድማሱ አበበ፣ የ45 ዓመት እድሜ እና ስራው የማይታወቅ፣ እቴነሽ ይማም፣ የ50 ዓመት እድሜ እና ስራዋ የማይታወቅ፣ ወርቄ አበበ፣ የ19 ዓመት እድሜ እና ስራዋ የማይታወቅ፣ ፈቃዱ ደግፌ፣ የ27 ዓመት እድሜ እና ስራው የማይታወቅ፣ ሸምሱ ካሊድ፣ የ25 ዓመት እድሜ እና ስራው የማይታወቅ፣ አብዱዋሂብ አህመዲን፣ የ30 ዓመት እድሜ እና ስራው የማይታወቅ፣ ተክሌ ደበሌ፣ የ20 ዓመት እድሜ እና ስራው የማይታወቅ፣ ታደሰ ፈይሳ፣ የ38 ዓመት እድሜ እና ስራው የማይታወቅ፣ ሰለሞን ተስፋዬ፣ የ25 ዓመት እድሜ እና ስራው የማይታወቅ፣ ቅጣው ወርቁ፣ የ25 ዓመት እድሜ እና ስራው የማይታወቅ፣ እንዳልካቸው ወርቁ፣ የ25 ዓመት እድሜ እና ስራው የማይታወቅ፣ ደስታ ነጋሽ፣ የ30 ዓመት እድሜ እና ስራው የማይታወቅ፣ ይለፍ ነጋ፣ የ15 ዓመት እድሜ እና ስራው የማይታወቅ፣ ዮሃንስ ኃይሌ፣ የ20 ዓመት እድሜ እና ስራው የማይታወቅ፣ በኃይሉ ብርሀኑ፣ የ30 ዓመት እድሜ እና ስራው የማይታወቅ፣ ሙሉ ሶሬሳ፣ የ50 ዓመት እድሜ እና የቤት እመቤት፣ ቴዎድሮስ ግደይ ኃይሉ፣ የ23 ዓመት እድሜ እና ጫማ ሻጭ፣ ደጀኔ ይልማ፣ የ18 ዓመት እድሜ እና የመጋዘን ሰራተኛ፣ ኡጋሁን ወልደገብርኤል፣ የ18 ዓመት ተማሪ፣ ደረጀ ማሞ ሀሰን፣ የ27 ዓመት እድሜ እና አናጺ፣
አስታውሳለሁ…
ረጋሳ ፈይሳ፣ የ55 ዓመት እድሜ እና የልብስ ንጽኅና መስጫ ሰራተኛ፣ ቴዎድሮስ ገብረዎልድ የ28 ዓመት እድሜ እና የግል ንግድ፣ መኮንን ገብረእግዚአብሄር፣ የ20 ዓመት እድሜ እና መካኒክ፣ አሊያስ ግብረጊዮርጊስ፣ የ23 ዓመት እድሜ እና ተማሪ፣ አብርሀም መኮንን፣ የ21 ዓመት እድሜ እና የቀን ሰራተኛ፣ ጥሩወርቅ ገብረጻድቅ፣ የ41 ዓመት እድሜ እና የቤት እመቤት፣ ሄኖክ መኮንን፣ የ28 ዓመት እድሜ እና ስራው የማይታወቅ፣ ጌቱ መረሳ፣ የ24 ዓመት እድሜ እና ስራው የማይታወቅ፣ ወ/ሮ ክብነሽ መኬ ታደሰ፣ የ52 ዓመት እድሜ እና ስራዋ የማይታወቅ፣ መሳይ ስጦታው፣ የ29 ዓመት አድሜ እና የግል ንግድ፣ ሙሉዓለም ወይሳ፣ የ15 ዓመት እድሜ እና ተማሪ፣ አያልሰው ማሞ፣ የ23 ዓመት እድሜ እና ስራው የማይታወቅ፣ ስንታዬሁ መለሰ፣ የ24 ዓመት እድሜ እና የቀን ሰራተኛ፣ ወ/ሮ ጸዳለ ቢራ፣ የ50 ዓመት እድሜ እና የቤት እመቤት፣ አባይነህ ሳራ ሰዴ፣ የ35 ዓመት እድሜ እና ልብስ ሰፊ፣ ፍቅረማሬም ተሊላ፣ የ18 ዓመት እድሜ እና ሾፌር፣ አለማየሁ ገርባ፣ የ26 ዓመት እድሜ እና ስራው የማይታወቅ፣ ጆርጅ አበበ፣ የ36 ዓመት እድሜ እና የግል ማመላለሻ፣ ሀብታሙ ዘገዬ ቶላ፣የ16 ዓመት እድሜ እና ተማሪ፣ ምትኩ ገብረስላሴ፣ የ24 ዓመት እድሜ እና ተማሪ፣ ትዕዛዙ መኩሪያ፣ የ24 ዓመት እድሜ እና የግል ንግድ፣ ፍቃዱ ዳልጌ፣ የ36 ዓመት እና ልብስ ሰፊ፣ ሸዋጋ ወልደጊዮርጊስ፣ የ38 ዓመት እድሜ እና የቀን ሰራተኛ፣ አለማየሁ ዘውዴ፣ የ32 ዓመት እድሜ እና የጨርቃጨርቅ ሰራተኛ፣ ዘላለም ገብረጻዲቅ፣ የ31 ዓመት እድሜ እና የታክሲ ሾፌር፣ መቆያ ታደሰ፣ የ19 ዓመት እድሜ እና ተማሪ፣ ኃይልዬ ሁሴን፣ የ19 ዓመት እድሜ እና ተማሪ፣ ወ/ሮ ፍስኃ ግብረጻዲቅ፣ የ23 ዓመት እድሜ እና የፖሊስ ተቀጣሪ፣ ወጋየሁ አርጋው፣ የ36 ዓመት እድሜ እና ስራ የሌለው፣
አስታውሳለሁ…
መላኩ ከበደ የ19 ዓመት እድሜ እና ስራው የማይታወቅ፣ አባይነህ ኦራ፣ የ25 ዓመት እድሜ እና ልብስ ሰፊ፣ ወ/ሮ አበበች ሆለቱ፣ የ50 ዓመት እድሜ እና የቤት እመቤት፣ ደመቀ ጀንበሬ፣ የ30 ዓመት እድሜ እና አርሶ አደር፣ ክንዴ ወረሱ፣ የ22 ዓመት እድሜ እና ስራ የሌለው፣ እንዳለ ገብረመድህን፣ የ23 ዓመት እድሜ እና የግል ንግድ፣ አለማየሁ ወልዴ፣ የ24 ዓመት እድሜ እና መምህር፣ ብስራት ደምሴ፣ የ24 ዓመት እድሜ እና መኪና አስመጭ፣ መስፍን ኃይለጊዮርጊስ፣ የ23 ዓመት እድሜ እና የግል ንግድ፣ ወሊዮ ዳሪ፣ የ18 ዓመት እድሜ እና የግል ንግድ፣ በኃይሉ ገብረመድህን፣ የ20 ዓመት እድሜ እና የግል ንግድ፣ ሲራጅ ኑርሰይድ፣ የ18 ዓመት እድሜ እና ተማሪ፣ እዮብ ገብረመድህን፣ የ25 ዓመት እድሜ እና ተማሪ፣ ዳንኤል ሜሉጌታ፣ የ25 ዓመት እድሜ እና የቀን ሰራተኛ፣ ቴዎድሮስ ደገፋ፣ የ25 ዓመት እድሜ እና በጫማ ፋብሪካ ውስጥ የሚሰራ ሰራተኛ፣ ጋሻው ሙሉጌታ፣ የ24 ዓመት እድሜ እና ተማሪ፣ ከበደ ኦርኬ የ22 ዓመት እድሜ እና ተማሪ፣ ሌችሳ ፋታሳ፣ የ21 ዓመት እድሜ እና ተማሪ፣ ጀጋማ በሻ፣ የ20 ዓመት እድሜ እና ተማሪ፣ ደበላ ጉታ፣ የ15 ዓመት እድሜ እና ተማሪ፣ መላኩ ፈይሳ፣ የ16 ዓመት እድሜ እና ተማሪ፣ ወ/ሮ እልፍነሽ ተክሌ፣ የ45 ዓመት እድሜ እና ስራዋ የማይታወቅ፣ ሀሰን ዱላ፣ የ64 ዓመት እድሜ እና ስራቸው የማይታወቅ፣ ሁሴን ሀሰን ዱላ፣ የ25 ዓመት እድሜ እና ስራው የማይታወቅ፣ ደጀኔ ደምሴ፣ የ15 ዓመት እድሜ እና ስራው የማይታወቅ፣ ሌላ ስሙ የማይታወቅ፣ አሁንም ሌላ ስሙ የማይታወቅ፣ አሁንም ሌላ ስሙ የማይታወቅ፣ ዘመድኩን አግደው፣ የ18 ዓመት እድሜ እና ስራው የማያታወቅ፣ ጌታቸው ተረፈ፣ የ16 ዓመት እድሜ እና ስራው የማይታወቅ፣ ደለለኝ አለሙ፣ የ20 ዓመት እድሜ እና ስራው የማይታወቅ፣ ዩሱፍ ኡመር፣ የ20 ዓመት እድሜ እና ስራው የማይታወቅ
አስታውሳለሁ…
መኩሪያ ተበጀ የ22 ዓመት እድሜ እና ስራው የማይታወቅ፣ ባደመ ተሻማሁ፣ የ20 ዓመት እድሜ እና ስራው የማይታወቅ፣ አምባው ጌታሁን፣ የ38 ዓመት እድሜ እና ስራው የማይታወቅ፣ ተሾመ ኪዳኔ፣ የ65 ዓመት እድሜ እና የጤና ሰራተኛ፣ ዮሴፍ ረጋሳ፣ እድሜው እና ስራው የማይታወቅ፣ አብዩ ንጉሴ፣ እድሜው እና ስራው የማይታወቅ፣ ታደለ በሀጋ እድሜው እና ስራው የማይታወቅ፣ ኤፍሬም ሻፊ እድሜው እና ስራው የማይታወቅ፣ አበበ ሀማ፣ እድሜው እና ስራው የማይታወቅ፣ ገብሬ ሞላ፣ እድሜው እና ስራው የማይታወቅ፣ ሰይዲን ኑሩዲን፣ እድሜው እና ስራው የማይታወቅ፣ እነዬው ጸጋዬ፣ የ32 ዓመት እድሜ እና የህዝብ ማመላለሻ ረዳት፣ አብዱራህማን ፈረጅ፣ የ32 ዓመት እድሜ እና የእንጨት ስራ ሰራተኛ፣ አምባው ብጡል፣ የ60 ዓመት እድሜ አዛውንት እና በቆዳ ፋብሪካ ውስጥ የሚሰራ ሰራተኛ፣ አብዱልመናን ሁሴን፣ የ28 ዓመት እድሜ እና የግል ንግድ፣ ጅግሳ ሰጠኝ፣ የ18 ዓመት እድሜ እና ተማሪ፣ አሰፋ ነጋሳ፣ የ33 ዓመት እድሜ እና አናጺ፣ ከተማ ኡንኮ፣ የ23 ዓመት እድሜ እና ልብስ ሰፊ፣ ክብረት እልፍነህ፣ የ48 ዓመት እድሜ እና የግል የጥበቃ አባል፣ እዮብ ዘመደኩን፣ የ24 ዓመት እድሜ እና የግል ንግድ፣ ተስፋዬ መንገሻ፣ የ15 ዓመት እድሜ እና የግል ንግድ፣ ካፒቴን ደበሳ ቶሎሳ፣ የ58 ዓመት እድሜ እና የግል ንግድ፣ ትንሳኤ ዘገዬ፣ የ14 ዓመት እድሜ እና ልበስ ሰፊ፣ ኪዳና ሽኩሮው፣ የ25 ዓመት እድሜ እና የቀን ሰራተኛ፣ አንዷለም ሺ በለው፣ የ16 ዓመት እድሜ እና ተማሪ፣ አዲሱ ተስፋሁን፣ የ19 ዓመት እድሜ እና የግል ንግድ፣ ከሳ በየነ፣ የ28 ዓመት እድሜ እና ልብስ ሻጭ፣ ይታገሱ ሲሳይ፣ የ22 ዓመት እድሜ እና ስራው የማይታወቅ፣ ሌላ ስሙ የማይታወቅ የ22 ዓመት እድሜ እና ስራው የማይታወቅ፡፡
አስታውሳለሁ…
የፖሊስ እና የደህንነት ኃላፊዎች የእርስ በእርስ በተደረገ የመሳሪያ ተኩስ የተገደሉ የሚከተሉት ናቸው፡ ነጋ ገብሬ፣ ጀበና ደሳለኝ፣ ሙሊታ ኢርቆ፣ ዮሀንስ ሰለሞን፣ አሸናፊ ደሳለኝ እና ፈይሳ ገብረመንፈስ ናቸው፡፡
እ.ኤ.አ ኖቬምበር 2/2005 በቃሊቲ እስር ቤት ግቢ በእስር ቤቶቻቸው ውስጥ እያሉበጥይትተደብድበው እንዲያልቁ የተደረጉ እስረኞች ስም ዝርዝር፣
አስታውሳለሁ…
ጠይብ ሸምሱ መሀመድ፣ እድሜው አይታወቅም፣ ጾታ ወንድ፣ የጦር መሳሪያ ደብቀሀል ተብሎ ክስ የተመሰረተበት፣ ሳሊ ከበደ፣ እድሜው አይታወቅም፣ ጾታ ወንድ፣ ምንም ዓይነት የተመሰረተበት ክስ የለም፡፡ ሰፊው እንድሪስ ታፈሰ ወረደ፣ እድሜው አይታወቅም፣ ጾታው ወንድ፣ በአስገድዶ መድፈር ወንጀል የተከሰሰ፣ ዘገዬ ተንኮሉ በላይ፣ እድሜው የማይታወቅ፣ ጾታ ወንድ፣ በዘረፋ ወንጀል የተከሰሰ፣ ቢያድግልኝ ታመነ፣ እድሜው የማይታወቅ፣ ጾታ ወንድ፣ የክሱ ምክንያት ያልታወቀ፣ ገብሬ መስፍን ዳኘ፣ እድሜው የማይታወቅ፣ ጾታ ወንድ፣ ስራው የማይታወቅ፣ በቀለ አብርሀም ታዬ፣ እድሜው የማይታወቅ፣ ጾታ ወንድ፣ ሁከት በመፍጠር ወንጀል የተከሰሰ፣ አበሻ ጉታ ሞላ፣ እድሜው የማይታወቅ፣ ጾታ ወንድ፣ የክሱ ምክንያት የማይታወቅ፣ ኩርፋ መልካ ተሊላ፣ በማስፈራራት ወንጀል የተከሰሰ፣ በጋሻው ተረፈ ጉደታ፣ እድሜው የማይታወቅ፣ ጾታ ወንድ፣ ሰላም በማደፍረስ የተከሰሰ፣ በዱልወሀብ አህመዲን፣ እድሜው የማይታወቅ፣ ጾታ ወንድ፣ በዘረፋ ወንጀል የተከሰሰ፣ ተስፋዬ አብይ ሙሉጌታ፣ እድሜው የማይታወቅ፣ ጾታ ወንድ፣ የጦር መሳሪያ ደብቀሀል ተብሎ የተከሰሰ፣ አዳነ ቢረዳ፣ እድሜው የማይታወቅ፣ ጾታ ወንድ፣ በነፍስ ግድያ ወንጀል የተከሰሰ፣ ይርዳው ከርስማ፣ እድሜው የማይታወቅ፣ ጾታ ወንድ፣ የክሱ ምክንያት ያልተገለጸ፣
አስታውሳለሁ…
ባልቻ ዓለሙ ረጋሳ፣ እድሜው የማይታወቅ፣ ጾታ ወንድ፣ በዘረፋ ወንጀል የተከሰሰ፣ አቡሽ በለው ወዳጆ፣ እድሜው የማይታወቅ፣ የክሱ ምክንያት ያልተገለጸ፣ ዋለልኝ ታምር በላይ፣ እድሜው ያልታወቀ፣ ጾታ ወንድ፣ በአስገድዶ መድፈር ወንጀል የተከሰሰ፣ ቸርነት ኃይሌ ቶላ፣ እድሜው የማይታወቅ፣ ጾታ ወንድ፣ በዘረፋ ወንጀል የተከሰሰ፣ ተማም ሸምሱ ጎሌ፣ እድሜው የማይታወቅ፣ ጾታ ወንድ፣ የክሱ ምክንያት ያልታወቀ፣ ገበየሁ በቀለ አለነ፣ አድሜው የማይታወቅ፣ ጾታ ወንድ፣ የክሱ ምክንያት ያልታወቀ፣ ዳንኤል ታዬ ልኩ፣ እድሜው የማይታወቅ፣ ጾታ ወንድ፣ የክሱ ምክንያት የማይታወቅ፣ መሀመድ ቱጂ ቀኔ፣ እድሜው የማይታወቅ፣ ጾታ ወንድ፣ የክሱ ምክንያት ያልተገለጸ፣ አብዱ ነጅብ ኑር፣ እድሜው የማይታወቅ፣ ጾታ ወንድ፣ የክሱ ምክንያት ያልተገለጸ፣ የማታው ሰርቤሎ፣ በአስገድዶ መድፈር ወንጀል የተከሰሰ፣ ፍቅሩ ናትናኤል ሰውነህ፣ እድሜው የማይታወቅ፣ ጾታ ወንድ፣ በማስፈራራት ወንጀል የተከሰሰ፣ ሙኒር ከሊል አደም እድሜው የማይታወቅ፣ ጾታ ሁከት በመፍጠር የተከሰሰ፣ ኃይማኖት በድሉ ተሾመ፣ አድሜው የማይታወቅ፣ ህግ በመጣስ ወንጀል የተከሰሰ፣ ተስፋዬ ክብሮም ተክኔ፣ እድሜው የማይታወቅ፣ በዘረፋ ወንጀል የተከሰሰ፣ ወርቅነህ ተፈራ ሁንዴ፣ እድሜው የማይታወቅ፣ ጾታ ወንድ፣ የክሱ ወንጀል ያልተገለጸ፣
አስታውሳለሁ…
ሲሳ ምትኩ ሁነኝ፣ በማጭበርበር ወንጀል የተከሰሰ፣ ሙሉነህ ዓይንዓለም ማሞ፣ እድሜው የማይታወቅ፣ የክሱ ምክንያት ያልተገለጸ፣ ታደሰ ሩፌ የኔነህ፣ በማስፈራራት ወንጀል የተከሰሰ፣ አንተነህ በየቻ ቀበታ፣ እድሜው የማይታወቅ፣ ጾታ ወንድ፣ የጦር መሳሪያ ደብቀሀል በሚል ወንጀል የተከሰሰ፣ ዘሪሁን መረሳ፣ እድሜው የማይታወቅ፣ ጾታ ወንድ፣ በንብረት ላይ ጉዳት በማድረስ ወንጀል የተከሰሰ፣ ወጋዬሁ ዘሪሁን አርጋው፣ በዘረፋ ወንጀል የተከሰሰ፣ በከልካይ ታምሩ፣ እድሜው የማይታወቅ፣ ጾታ ወንድ፣ የክሱ ምክንያት ያልተገለጸ፣ የራስወርቅ አንተነህ፣ እድሜው የማይታወቅ፣ ጾታ ወንድ፣ በማጭበርበር ወንጀል የተከሰሰ፣ ባዝዘው ብርሀኑ፣ እድሜው የማይታወቅ፣ ጾታ ወንድ፣ በግብረሰዶማዊነት የድርጊት ወንጀል የተከሰሰ፣ ሰለሞን እዮብ ጉታ፣ እድሜው የማይታወቅ፣ ጾታ ወንድ፣ በአስገድዶ መድፈር ወንጀል የተከሰሰ፣ አሳዩ ምትኩ፣ እድሜው የማይታወቅ፣ ጾታ ወንድ፣ በማስፈራራት ወንጀል የተከሰሰ፣ ጋሜ ኃይሉ ዘገዬ፣ እድሜው የማይታወቅ፣ ሁከት በመፍጠር እና ጸጥታ በማደፍረስ የተከሰሰ፣ ማሩ እናውጋው ድንበሬ፣ እድሜው የማይታወቅ፣ ጾታ ወንድ፣ በአስገድዶ መድፈር ወንጀል የተከሰሰ፣ እጅጉ ምናለ፣ አድሜው የማይታወቅ፣ ጾታ ወንድ፣ በግድያ ሙከራ የተከሰሰ፣ ኃይሉ ቦስኔ ሀቢብ፣ አድሜው የማይታወቅ፣ ለወንጀለኛ መጠለያ በመስጠት ወንጀል የተከሰሰ፣ ጥላሁን መሰረት፣ እድሜው የማይታወቅ፣ ጾታ ወንድ የክሱ ምክንያት ያልተገለጸ፣ ንጉሴ በላይነህ እድሜው ያልታወቀ፣ በዘረፋ ወንጀል የተከሰሰ፣ አሸናፊ አበባው፣ እድሜው የማይታወቅ፣ ጾታ ወንድ፣ የክሱ ምክንያት ያልተገለጸ፣ ፈለቀ ድንቄ፣ እድሜው የማይታወቅ፣ ጾታ ወንድ፣ የክሱ ምክንያት ያልተገለጸ፣ ጀንበሬ ድንቅነህ ቢለው፣ እድሜው የማይታወቅ፣ ጾታ ወንድ ጸጥታ በማደፍረስ ወንጀል የተከሰሰ፣ ቶሎሳ ወርቁ፣ አድሜው የማይታወቅ፣ ጾታ ወንድ፣ በዘረፋ ወንጀል የተከሰሰ፣ መካሻ በላይነህ ታምሩ፣ እድሜው የማይታወቅ፣ ጾታ ወንድ፣ ሁከት በመፍጠር ወንጀል የተከሰሰ፣ ይፍሩ አደራው፣ እድሜው የማይታወቅ፣ ጾታ ወንድ፣ የክሱ ምክንያት ያልተገለጸ፣ ፋንታሁን ዳኘ፣ እድሜው የማይታወቅ፣ ጾታ ወንድ፣ የክሱ ምክንያት ያልተገለጸ፣ ጥበበ ዋከኔ ቱፋ፣ እድሜው የማይታወቅ፣ ጾታ ወንድ፣ ሰለሞን ገብረ አምላክ፣ እድሜው የማይታወቅ፣ ጾታ ወንድ፣ ሁከት በመፍጠር ወንጀል የተከሰሰ፣ ባንጃው ቹቹ ካሳሁን፣ እድሜው የማይታወቅ፣ ጾታ ወንድ፣ በዘረፋ ወንጀል የተከሰሰ፣ ደመቀ አበጀ፣ እድሜው የማይታወቅ፣ ጾታ ወንድ፣ እድሜ 58፣ የመግደል ሙከራ በማድረግ ወንጀል የተከሰሰ፣ እንዳለ እውነቱ መንግስቴ፣ እድሜው የማይታወቅ፣ ጾታ ወንድ፣ የክሱ ምክንያት ያልተገለጸ፣ አለማየሁ ገርባ፣ እድሜው የማይታወቅ፣ ጾታ ወንድ፣ እ.ኤ.አ በ2004 የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ካደረጉት ሰላማዊ ሰልፍ ጉዳይ ጋር በተያያዘ የታሰረ፣ መርኮታ ኢዶሳ፣ እድሜው የማይታወቅ፣ ጾታ ወንድ፣ የክሱ ምክንያት ያልተገለጸ፣
ለታሪክ ምዘገባ፡ በእነዚህ ከላይ በተዘረዘሩት የግድያ እልቂቶች ሙሉ በሙሉ እና በቀጥታ የተሳተፉ እጃቸው በደም የተጨማለቀ ቢያንስ 237 ስማቸው እና ማንነታቸው በውል የተረጋገጠ የፖሊስ እና የደህንነት ኃላፊዎች ስምዝርዘር አለ፡፡
የኔሰው ገብሬን አስታውሳለሁ፡፡
እ.ኤ.አ በ11/11/11 የኔሰው ገብሬ የሚባል የ29 ዓመት እድሜ የነበረው ኢትዮጵያዊ የትምህርት ቤት መምህር እና የሰብአዊ መብት ተሟጋች በደቡብ ኢትዮጵያ ዳውሮ ዞን በተርጫ ከተማ ከህዝብ የመሰብሰቢያ አዳራሽ ወጣ ብሎ በሚገኝ በአንድ ቦታ ላይ በእራሱ ላይ እሳት በመለኮስ እራሱን አቃጠለ፡፡ ለሶስት ቀናት ቁስለኛ ሆኖ ከቆዬ በኋላ ህይወቱ ሊያልፍ ችሏል፡፡ በእራሱ ላይ ያንን የመሰለ አሰቃቂ እርምጃ ከመውሰዱ በፊት የኔሰው ከመሰብሰቢያ አዳራሹ ውጭ ተሰብስቦ ለነበረው የአካባቢው ህዝብ እንዲህ የሚል ንግግር አድርጎ ነበር፣ “ፍትህ እና ፍትሀዊ አስተዳደር በሌለባት ሀገር፣ ሰብአዊ መብቶች በሚደፈጠጡባት እና በማይከበሩባት ሀገር እራሴን መስዋዕት በማድረግ እነዚህን ወጣቶች ነጻ አወጣለሁ፡፡“
የ2005 ምርጫ ሁከትን ተከትሎ ያለቁ ሰላማዊ ዜጎች
ህወሀት እና አመራሮቹ በስልጣን እርካብ ላይ ተቆናጥጠው ለመቆየት ሲሉ እልቂት ከማድረስ፣ ከመምታት እና ከማቃጠል ወደኋላ እንደማይሉ ለጥያቄ የሚቀርብ ጉዳይ አይደለም፡፡ እ.ኤ.አ በ2015 ይካሄዳል እየተባለ የሚደሰኮርለትን ምርጫ ተብዮ ቢያንስ 99.6 በመቶ እንደሚያሸንፉ አስቀድመው ያውቃሉ፣ ሆኖም ግን በፍርሀት እና በጭንቀት ውስጥ ተዘፍቀው በመራድ ላይ ይገኛሉ፡፡ ነጻ ጋዜጠኞችን ሰላማዊ አመጸኞችን ያስራሉ፣ የነጻው ፕሬስ ጋዜጦችን በሙሉ ዘግተዋል፡፡ የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችን እና አባላትን ያስራሉ፡፡ ለምንድን ነው እንደዚህ በፍርሀት እየራዱ በነጭ ላብ ተዘፍቀው የሚገኙት?
እነዚህ ግፈኞች ይፈራሉ ምክንያቱም ከኢትዮጵያ ህዝብ ምንም ዓይነት ድጋፍ እንደሌላቸው ያውቃሉ፡፡ የያዙት ስልጣን መሰረት የሌለው እና ትንሽ የሚገዳደር ነገር ቢያጋጥመው እንደ እንቧይ ካብ በቀላሉ እንደሚፈራርስ ያውቃሉ፡፡ በአንድ ወቅት ህዝቡ ፊቱን እንደሚያዞርባቸው እና ከስልጣናቸው ላይ እንደ መጥፎ አረም እየነቀለ እንደሚጥላቸው ያውቃሉ፡፡ በስልጣናቸው ላይ እንደመዥገር ተጣብቀው ለመቆየት ብቸኛው አማራጭ አደገኛ የሽብር ሁኔታዎችን በመፍጠር የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎችን (ተቃዋሚ ፓርቲዎችን እና ሰላማዊ አመጸኞችን) ማጥፋት፣ በመንግስት ላይ የሚደረግን ትችት (ነጻውን ፕሬስ) መዝጋት እና ነጻ እና ፍትሀዊ ምርጫ እንዳይካሄድ ማድረግ እንደሆነ ጽኑ እምነት አላቸው፡፡ በፍርሀት፣ በሽብርተኝነት ተዘፍቀው እና ኃይልን እንደብቸኛ አማራጭ በመጠቀም መግዛት ይፈልጋሉ፡፡ ህወሀት አሁንም በስልጣን ላይ ተጣብቆ ለመቆየት እልቂትን መፈጸም፣ መምታት እና ማቃጠልን እንደተለመደው እንደ ስልት ሊጠቀም ይችላልን? የለመደች ጦጣ ሁልጊዜ ሽምጠጣ አይደል ነገሩ! ሲኦል ውስጥ የሚያስገባ እና አጠራጣሪ ጉዳይ ነው! እ.ኤ.አ በ2005 በመቶዎች የሚቆጠር እና ያን ይህል ብዛት ያለው ህዝብ ሲገድሉ እና በሺዎች የሚቆጠሩትን ደግሞ ሲቆስሉ እና ወደ እስር ቤትም በመውሰድ ሲያጉሩ ምንም ዓይነት መጥፎ ነገር ያልገጠማቸው ስለነበር አሁን በ2015 ይደረጋል እየተባለ የሚደሰኮርለትን የይስሙላ ምርጫ በማስታከክ ደግሞ ያንን ሰይጣናዊ ልምዳቸውን ከፍ ወዳለ ደረጃ በማድረስ በሺዎች የሚቆጠሩትን ሊገድሉ፣ ሊያቆስሉ፣ ሊያስሩ እና ሊያሰቃዩ ይችላሉ፡፡ እንደዚህ ያለውን ነገር ነው እንግዲህ ወሮበሎች እና ዘራፊዎች ደጋግመው የሚሰሩ!
እ.ኤ.አ በ2005 የተፈጸሙት ጭራቃዊ ወንጀሎች በ2015 እንዳይደገሙ ከፈለግን በአንድነት ተነስተን በአንድ ላይ ቆመን ለኢትዮጵያውያን/ት ወንድሞች እና እህቶች መብት መከበር መታገል አለብን፡፡ በዲያስፖራ የሚገኘው እና የምትገኘው እያንዳንዱ/ዷ እና ማንኛውም/ዋም ኢትዮጵያዊ/ት የወያኔን የሸፍጥ ወንጀሎች ለማምከን በአንድ ላይ መቆም፣ በአንድነት መናገር፣ ፈትለፊት መጋጠም፣ መደጋገፍ፣ መተባበር፣ በአንድ ላይ መናገር መቻል አለባቸው፡፡
አጠቃላይ የመርሳት ችግራችንን እናስወግድ፣ የመለስን የእልቂት ሰለባዎች እናስታውስ…
የእልቂቱን ሰለባዎች እንደማልረሳ፣ የእልቂቱ ፈጻሚዎችን እና ቅጥር ነፍሰ ገዳዮችን እንደማልረሳ እያደረግሁት ላለው ጥረት ወደ ትግሉ ተቀላቀሉ፡፡ በትግሌ ውስጥ ለድል እንደምንበቃ አንድ ሺህ አንድ ያህል ምክንያቶችን በመደርደር ተስፋዎቼን ሰንቂያለሁ፡፡ ምክንያቱም አስታውሳለሁ፡፡ ተስፋቢስ አልሆንም:: ምክንያቱም አስታውሳለሁ፡፡ ተስፋቢሰነትን ለማስወገድ የሞራል ግዴታ አለብኝ፡፡ ከተስፋ ማጣት በኋላ ተስፋን ማለምለም ይቻላል”፡፡ ኤሊ ዊሰል
የመለስ ዜናዊን የህዳርን እና የታህሳስን እንዲሁም የ….ን እናስታውስ!
======================
በመለስ እልቂቶች ላይ ተጨማሪ መረጃ ካስፈለገ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ጉባኤ የሰብአዊ መብት ተሟጋች የነበረው ያሬድ ኃይለማርያም ለአውሮፓ ህብረት ድንገተኛ የጋራ ጉባኤ የልማት እና የውጭ ጉዳይ እና የሰብአዊ መብት ንኡስ ኮሚቴ የፓርላማ አባላት ፊት በግንባር ቀርቦ “በኢትዮጵያ በሰብአዊነት ላይ የተፈጸመ ወንጀል፡ የሰኔ እና የህዳር 2005 የአዲስ አበባ ህዝብ እልቂት/CRIMES AGAINST HUMANITY IN ETHIOPIA: THE ADDIS ABABA MASSACRES OF JUNE AND NOVEMBER 2005“ በሚል ርዕስ እ.ኤ.አ ሜይ 15/2006 የሰጠውን ምስክርነት መመልከት ይቻላል፡፡
**አጣሪ ኪሚሽኑ የእልቂቱ ሰለባ የሆኑትን ዜጎች ሙሉ በሙሉ ነጻ በማውጣት ወንጀሉን ሙሉበሙሉበፖሊስ እና በምልምል የፖሊስ ኃይሎች ላይ ደፍድፎታል፡፡ ኮሚሽኑ እንዲህ የሚልመደምደሚያ ሰጥቷል፣“በሰላማዊ አመኞች የተፈጸመ የንብረት ውድመት የለም፣ ጥቂት አመጸኞችጠብመንጃ እና ቦምብ የታተቁነበሩ በማለት በመንግስት ቀጥጥር ስር ባሉት መገናኛ ብዙሀንእንደተዘገበው ሳይሆን አንድም ጠብመንጃያነገተ ወይም ደግሞ የእጅ ቦምብ የያዘ ሰላማዊ አመጸኛአልነበረም፡፡ በመንግስት ታጣቂ ኃይሎች ሲደረጉየነበሩት የጥይት ተኩሶች የሰላማዊ አመጸኞችንስብስብ በመበተን ዓላማ ላይ ያነጣጠሩ አልነበሩም፡፡ ሆኖምግን የሰላማዊ አመጸኞችን ጭንቅላትእና ደረቶች እያነጣጠሩ በመበርቀስ ህይወት አልባ ማድረግ ነበር“
የኮሚሽኑ የ193 የእልቂት ሰለባዎች ስም ዝርዝር እ.ኤ.አ ከሰኔ 6 እስከ 8 እና ከህዳር 1 እስከ4/2005ኮሚሽኑ በእነዚህ ውሱን በሆኑ ቀናት ብቻ እንዲያጣራ በታዘዘው መሰረት አጣርቶያቀረባቸው የተገደሉንጹሀን ዜጎችን ብቻ ያካተተ ነው፡፡ ኮሚሽኑ ከዚህ በተጨማሪም በገዥውአካል የፖሊስ እና የደህንነትኃይሎች ከህግ አግባብ ውጭ በዘፈቀደ የተገደሉ ንጹሀን ዜጎች ስምዝርዝር አለው፡፡ ሆኖም ግን ኮሚሽኑአጣርቶ እንዲያቀርብ የታዘዘው ከላይ በግልጽእንደተቀመጠው የሌሎች ቀናትን ብቻ ሰለነበር በዚህምክንያት እነዚህን ከህግ አግባብ ውጭበዘፈቀደ የተገደሉትን ዜጎች በዘገባው ይፋ ማድረግ ሳይችልቀርቷል፡፡
የወገኖቻችን ሬሳ የውሻ ሬሳ ሆኖ ደመከልብ ሆነው አይቀሩም!
ፍትህ አንድ ቀን የርትዕ ሰይፏን በመምዘዝ በግፈኞች ላይ ታሳርፋለች!
የማይሳነው ቸሩ አምላክ ያለቁትን ወገኖቻችንን ነፍስ በገነት ያኑርልን! አሜን!
ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር!
ህዳር 2 ቀን 2007 ዓ.ም