ከሥርጉተ ሥላሴ 09.11.2014 /ዙሪክ – ሲዊዘርላንድ።/
በቅድሚያ ዬጸሐፊ አቶ ጌታቸው ሽፈራው “ጥቁሩ አብዮት›› እንዲሁም ዬጸሐፊ ዮፍታሔ „ስምንት ዋና ነጥቦች ከእስራኤላውያን“ ጭብጦቹ በሚሉ እርእሰ ጉዳዮች የተጻፉት የፍላጎታችን ፍሬ ነገር፤ የመንፈስ መርህና መሪ ከመሆናቸውም በላይ መንገድ ጠራጊም ናቸው። አስፈላጊነታቸውም የዓይን ያህል ናቸው። እንደዚህ መስል ጹሑፎች ናቸው „የአሻም ፈሎች“ ሆነው በቃኝን አምርተው ድምጽ የሚመራት የርትህ ሀገር የሚፈጥሩት። ስለሆነም አመሰግናለሁ ከልብ – ጸሐፍትን። ለነገሩ የጸሐፊ ጌታቸው ሽፍራውን ጹሁፍ ሌላ መጻፍ ሳያስፈልግኝ በ07.11.2014 በነበረኝ የቅኔው ልዑል የጸጋዬ ራዲዮ ፕሮግራም /Radio Tesgaye/ ሙሉን ተጠቅሜበታለሁ። የጸሐፊ ዮፍታሄም ለቀጣዩ ዝግጅት ታጭቷል። በተያያዘ ሁኔታ ስለ ኢቦላ ባይረስና ስለ ህዝብ ጉዳይ ግድ ስለማይሰጠው የወያኔ አስተዳደር „ጀብደኝት ..“ የተጻፈውም ወርቅ ነበር – እግዚአብሄር ይስጥልኝ።
ሰሞኑን አዲስ ዜግነት ደግሞ ተስጥቶናል ሰምታችኋል አይደል የእኔ ውዶች „የአፍሪካ ቀንድ ዜጎች“ ወይ ማላገጥ። እንዴት ተቀለደ … „ከአፍሪቃ ቀንድ ዜጎች ጋር በአካባቢያችን የፖለቲካ ጉዳዮች ላይ፣ እንዲሁም በስነፅሁፍ ነክ ርእሰ ጉዳዮች፣ ካደረግሁዋቸው ውይይቶች እጅግ ብዙ ትምህርት ቀስሜያለሁ።”
የዛሬው ጸሐፊ ገዳ ገብራብ ነገ ደግሞ ተሰፋዬ አክራም በመባል ወደ ሳውዲ ወይንም ተስፋዬ ሮቬርቶ በመባል ወደ ጣሊያን እንደ ሽንብራ ቂጣ መገላበጡን እንጠብቃለን። እንዲህ በሚጸዬፈውና ግማሽ ዕድሜውን በጨረሰበት የጥላቻ መግል ውስጥ ሆኖ ስለምን በተገፋውና በተረገጠው፤ በተገለለውና በተናቀው አማርኛ ቋንቋ መጻፍ እንዳስፈለገውም ፈጽሞ አልገባኝም። ለነገሩ እኔ ለወደቀ እንጨት ብዙም ቁብ ስለማይሰጠኝ ሰው ከፍቅር ሃፍትነቱ ወደ መፏከት ሲያሰኘው እምለው አልነበረኝም። ለቡጀሌ ለምን ጊዜ ይቃጠል?! ነገረ ግን ዛሬ የተጠላውና አጥብቆ በጥርሱ በያዘው – በተፀዬፈውም የኢትዮጵያዊነትን ሰንደቅን ከፍ ባደረገው ዬምልዕተ ቤት በዘሃበሻ የካህዲ ጹሑፍ አቅም አግኝቶ ገልባጤን እንዲህ ሲያቀናጣ በማዬቴ ዝም ብዬው ማለፍን መንፈሴ አላስቻለውም።
በቅድሚያ እጅግ የማከብራችሁ የፁሁፌ ታዳሚዎች እና እንዲሁም ልጅነቱን ፈቅደው ለተቀበሉት „አባወራ ኦቦ ሉቤ“ የቤት ሥራ መስጠቱን ወሰንኩ። እናንተም ውዶቼ ብታነቡት አይከፋም። እርእሱ ብቻ ይበቃል። አንዲት የትውልድ ዕንቁ ብቻ አይደለም ብልህ ወጣት መሪ ክብርት ዳኛ ብርቱካንን „ከባህር የወጣች አሳ“ ሲል ቅብጥ ሲል ያዛላጠውን ጨቀጨቅ እሳቤ ለኩት … እንሆ በትሁት ቅናዊ መንፈስ ሊንኩን https://www.facebook.com/ethiopiazare/posts/535876466438109
http://www.ethiopiazare.com/art-56/short-story/2565-birtukan-mideksa-by-tesfaye-gebreab ጹሑፉን ከማንበባቸሁ በፊት ግን የክብርት ዳኛ ብርቱካን ሜዲቅሳ ዬለጠፈውን ፎቶውን እንዴት አበልቆ እንዳወጣው ተመልከቱት። በወቅቱ እኔ እንዲነሳ እጅግ ለማከብረው ወንድሜ ጽፌለት ነበር። ከዚህ በኋላም ነበር በአንድ ቀን ሌሊቱን አክዬ በጉጉት አንብቤ የጨረስኩት „ዬጋዜጠኛው ማስታወሻ“ ክፍል አንድ መጸሐፉ ብዕርና የእኔ ፍቅር ተምሶ የተቀበረው። ለማንኛው ውስጡን በሚገባ ጎብኘት አድርጋችሁ ከእነብልቱ – ፈትሹት። ጠረኑም ጠጋ አድርጋችሁ አሽቱት። በተረፈ ቀጣዩ የህሊና ፍርዱን ለክብረቶቼ ለአንባብያን ትቼ ልጅነቱን የተቀበሉለትን „አባወራ ኦቦ ሉቤ“ ከክብርት ዳኛ ብርቱካን ሜዲቅሳ እና ከጸሐፊ ገዳ ገብረመድህን የትኛው ለደማቸው እንደሚቀርብ እራሳቸውን ይለኩት ዘንድ በአጽህኖት አሳስባለሁ። እንዲህ የተረገጠ – የተጠቀጠቀ – የተወቀጠ – የተናቀ – የተጣለ – የተቃለለ – የተሳለቀበት አካላዊ እትብትና ሥጋ እንደ ገና ደጅ ጥናት ተሄዶለት እውቅና ሰጠኝ አስብሎ በአታሞ ያሳዳከረው ይሄው ገማና ነው። ብልሃት የሌለው ቅላት።
„ከአሜሪካ መልስ እነሆ! በህግ ኦሮሞ ሆኛለሁ። ኦሮሞ መሆን “ኢትዮጵያዊ መሆን” ማለት ግን አይደለም። ወደፊት የኦሮሞ ህዝብ ስለማንነቱ በነፃነት ሲወስን ያን ጊዜ የሚታይ ይሆናል። ኢትዮጵያዊነትን በመተው ኦሮሞ ብቻ ሆኖ መቆየት እንደሚቻል ግን ቀደም ሲል በሞጋሳ ባህል ኦሮሞነትን ከወሰዱ ግለሰቦች ተረድቻለሁ።“
ጸሐፊ ተስፋዬ ጥሩ አብሾ ተጎንጭቶ ብቻ ሳይሆን አብሾው መሥራቱን ያመለከተው መሰረታዊ ነገር የኢትዮጵያ ጠላትነቱን ዝርግፍግፍ አድርጎ ቄጤማ ማድረጉ ነው። እንዲህ ይልናል በግልጽና በስውር ሴራ በገደል ለተወረወሩ፤ ለተገደሉ፤ በስለት ለታረዱ፤ አድራሻቸው ሳይታወቅ ለቀሩ ለተፈናቀሉ ሚሊዮኖች ሥቃይ፤ ለጥላቻ አምራችነቱ፤ ተጠያቂነቱን ብዕሩ ቁማ እንሆ መሰከረች። የተከደነው ተዘሎ እንዲህ አለን „ግማሽ የህይወቱን ክፍል የታገለለት አላማ በመጨረሻ በኦሮሞ ህዝብ ፊት ዋጋና ሞገስ ማግኘቱ በትክክለኛው መስመር ላይ ሲጓዝ እንደቆየ ማረጋገጫ ሆኖለታል።” የስለላ ተግባሩ፤ በ6ቢላዋ መብላቱ፤ ደም እዬተጎነጨ በደም ሰብቶ መኖሩን፤ ፍንትው አድርጎ ከነመግሉ አሳይቶናል። „ኢትዮጵያዊነት“ ሲገፋ እንዲህ ያንደፈድፋል። እንዲህ ያስቃዣል። እንዲህ ቅብጥብጥ ያደርጋል። ኢትዮጵያዊነት የመንፈስ ሥነ ህይወት ነው። ኢትዮጵያዊነት ልዕቅናው ሆነ ልዕልናው ዕውቅናው ጥበቡ የመረቀው የአባቱ የአደኖይ ነው። አሁን እንኳን ከሃብቱ ለመውጣት ጋዳ ሆኖ አማርኛ ቋንቋ አስጎንብሶ ያስደገድጋል። ተመስገን!
ስለነገው ቀለበጡሊ ትረካ ደግሞ „አዳማ ላይ ከብቶችን አርብቶ ለመኖር መቋመጡን“ አንብበናል። ሲያምርህ ይቀራል እንላለን። ወንዱ ቀበቶ ከሌለው አንስቶች እምናደርገውን እናውቃለን። በተረገጠና በተናቀ መሬት መልሶ መፈንጨት አይፈቀድም። „ኢትዮጵያዊነቴን ማንም ሊሰጠኝ ወይንም ሊነሳኝ አይችልም“ ባልክበት አንደበት ደግሞ ዛሬ „በህግ ኦረሞ ሆኛለሁ“ ትለናለህ። ያልሆንከውን ልትሆን እንደማትችል ታውቃዋለህ – ጌታው። „እንግዲህ በሞጋሳ ስርአት መሰረት ኦሮሞነትን በኩራት የተቀበልኩ በመሆኑ በኦሮሚያና በአካባቢያችን ጉዳዮች ላይ የመፃፍ ብቻ ሳይሆን፣ የመሳተፍ ጭምር ግዴታ አለብኝ።„ አባ አዋጉ ያው ለማንኮር። ያው ለማተራመስ – ዬአረም አጥሚት። ኦሮሞ ሲከበር ልጁንም ነው። ሲወዱ እስከ ንፍጥ ልጋጉ … ብርቴ ከዬት የመጣች መሰለችህ? የቅኔው ልዑል ጸጋዬ ገ/መድህን ምንጩ ማን መሰለህ? ለልዑሉ አክብሮት ካለህ ለእትብቱም …. „ትንሽ ሥጋ በመርፌ ትውጋ“ ይህን ለአቶ በረከት ንገራቸው – ከኑዛዜያቸው በፊት__ ያው በመስመራችሁ እዬተገናኛችሁ የሰብዕና ዘረፋችሁን አና ብላችሁት የለ። ለማንኛውም አራባና ቆቦ እዬረገጡ አምታቶ መኖር – አላጋጦ መኖር፤ በደም ቋንጣ ንግድ እንዲሁም መዘባነን ህልም ነው።
ሌላው የተነሳው ነገር የእኛን ልቦና ፈታሽና ነገር አዋቂ ሆነህ መገኘትህ ደግሞ የሚገርም ገደል ነገር ነው። „ኢትዮ አማሮች ደግሞ ከወያኔ በከፋ ደረጃ የኦሮሞን ህዝብ መብቶች ለማፈን ጊዜ የሚጠብቁ መሆናቸውን የኦሮሞ ህዝብ ጠንቅቆ ሊረዳው ይገባል። በመሆኑም ከወያኔ መውደቅ ቀጥሎ የኦሮሞ ህዝብ ከባድ ፈተና የሚገጥመው ከእነዚሁ እላዩ ላይ መጥተው ቁጭ ካሉበት ሰፋሪዎች ነው።” ቃሬዛ የዋኘበት ዝልቦ ትንተና …..
እንዲህ ለዛቀጠ ለወረደ ሰብዕና፤ ተፈጥሮ ለሚያረግርግ እንዳንተ ላለ ሊሆን ይችላል። ይህ ስንጥቅና ትርትር ፈት ግልቢያ። ለጥንቁቁ የኢትዮጵያ ህዝብ አካል ለሆነው አማራ ግን የሚበልጥበት እናት ሀገሩና ሰንደቅዓላማዋ ነው። በእኔ ውስጥ ያለው ነገር እኔን እንጂ ሌላውን ሊወክል አይችልም። ትናንትም ዛሬም ማንነት ችግር ያለበት በወደቀ በተነሳ – በፈረጠ በዘለለ ቁጥር ማተባችን አንበጥስም። ተግባባን?! መስመራችን አፈራችን መሆኑን ስለምናወቅ እንደማተባችን ኖረን እንደ ማተባችን እናልፋለን። እኔን ለመተርጎም ኢትዮጵያዊነትን የማንበብ ሆነ የመተርጎምና የማመሳጠር አቅም የተሰጠው ብቻ ይሆናል ስለ እኔ ስለ ሥርጉተ ስሜት ፍላጎት ራዕይ የውስጥ አዋቂ ሊሆን የሚችለው። …. ስለዚህ የእኛን ለእኛ ተወው። አንተ የተፈጠርክበትን በደም አላባ ተዘፍቆ ውሎ ማደር፤ በሴራና በተንኮል በክቶ ቁርሾን ታቅፎ ለቂም ሰግዶ በቋሳ ዘልቦ መኖሩን ለመረጠከው ስለራስህ እንዲህ ዘርግፍ …. ዝርግፍ —-
ግን ክብሮቼ የእኔዎቹ የሀገሬ ልጆች ደሞቼ „አለቀት“ ታውቃላችሁን? አለቀት ውሃን ተግን አድርጎ ውሃን መስሎ የሚኖር ተውሳክ ነው። ከብቶች ውሃ ሲጠጡ ሰለል ብሎ ውሃን ተመሳስሎ ገብቶ ወይ አይወጣ ወይ ወደታች አይወርድ ጉሮሮ ላይ ተሰንቅሮ ከብቶችን አሰቃይቶ ይገድላል። ለዚህ ሙያ የተካኑ ሀገረሰብ ሃኪሞች አሉ። ከብቱ ከመሞቱ በፊት የባህል ሃኪሞች ከደረሱ አለቅቱ ሲወጣ ደም ጎርሶ ነው የሚወጣው። ከወጣ በኋላ ደግሞ እንደ ቅል ተነፍቶ በደም ተቀብሮ ይገኛል። የዘመናችን አለቅት ለዛውም የቁርሾና የቋሳ ቀንዳሙ ደግሞ ፀሐፊ ገብረ ጉንዳን ነው።
ሌላው ደግሞ ምንድን ነው የተባለነው? „ጉዳይ ሳይኖረኝ ወደ ምጽዋ ሄድኩ። ሰላምታ ላቀርብ“ አዬ ትዕቢት። „ትናንት ወደ ምፅዋ ሄጄ ነበር። ምፅዋ የሚያስኬድ ምንም ጉዳይ አልነበረኝም። የተጓዝኩት ለቀይባህር ደረት የሞቀ ሰላምታ ለማቅረብ ብቻ ነበር። የቀይባህር የምሽት ማእበል ናፍቆኝ ነበር። የምፅዋ ሙቀት በጣም ናፍቆኝ ነበር። የጀበና ቡና እና ፈንዲሻ – ባህሩ ዳርቻ ናፍቆኝ ነበር።” …. ድንቄም ቡና “ወደሽን ቆማጤ ንጉሥ ትመርቂ” አሉ …
አላስችልህ አለህ? ግን ለመሆኑ የጤፍ ጠላ ጠጥተህን ታውቃለህ? ታቅፈው ወይንም አሽኮኮ አድርገኸው ዙር። አባቶቻችንና ወንድሞቻችን እንደ ክረምት እንጨት አካላቸው ተደርድሮ በበቀል – ታጭደው – የተቃጠሉበት – የነደዱበት – አመድ የሆኑበት ነው። የሰው ልጅ የማገዶ መሬት ነው። የአካላችን ጢሱ ከመንፈሳችን ውስጥ አለ። ለአንተ ግን እንኳን ለዚህ አበቃህ ክክክክክክክከ —- ከውስጡ ገብተህ ብትጠመቅ ምን አልባት መላ አሳጥቶ የሚያስለፈልፍ ጉድህ ይለቅህ ይሆን? እስኪ ሞክረው?
ሌላ ምን ነበር የተደስኮረልን ደጎስ ያለውን ልበወለድ ትልም „የአሜሪካ ቆይታዬን በተሳካ ሁኔታ አጠናቅቄ ቀጣዩን ዳጎስ ያለ ታሪክ ቀመስ ልቦለድ ድርሰት ለመፃፍ ወደ ኤርትራ ተመልሻለሁ።” ሪፖርቱ ለዬትኛው ታዳሚህ ነው? ጉብራህን የተረገጠኽ ከቶ ይኖር ይሆን? ማን ጠዬቀኽ?! ከተሳካልህ ለአማርኛ ተነጋሪዎች ሳይሆን ለመረጥከው ቋንቋ አወራርደው … አይመስልህም? ይመስለህ። …. „ስለክብርት ዳኛ ብርቱካን የጻፍከው እርእስ ለአንተ ነበር እኮ የተነበይከው? „ከባህር የወጣ አሳ“ ይህ የሚስማማው እንደ አንተ ላሉ ማንነታቸው ጠፍቶባቸው በበታችንት ስሜት ለሚወዛወዙ ዝልቦች ይመስለኛል። የችግርህ ቁንጮው በለው ጅራቱ ማንነትህን የሚመልስልህ መንፈስ አላገኘህም ምን አልባት ብትተረተር ልታገኘው ትችል ይሆናል። ተሰንጠቅ እና እስኪ የቀረህ ይኸው ነውና እዬው —–
„ኢትዮጵያዊ ነኝ“ ያልከን አንተው። እኛ የትኛውን አማላጅ ይሆን ዬላክንልህ? ናልን እባክህ ብለን ደጅ አልጠናነኽ? ዛሬ ደግሞ ከረፋኝ የምትለን አንተው ነህ። ትዋዥቃለህ ማህለቋ እንደተሰበረ መርከብ። ቀድሞ ነገር ለጥበብ ሰው „ሰው መሆኑ ብቻ ይበቃው በነበር“ ጥበብ የሰማይ ሥጦታ ስለሆነ ድንግልናው ቅድስናው ቤተ መቅደስ ነው። ጥበብ ታቦት ነው። የሚወደድ የሚከበር ለሥነምግባሩ በፍቅር ፈቅደው የሚገዘሉት ድንበር ወሰን ያልተሰራለት ፍጥረት ለተባለ ቀርቶ ለድንጋይ ቅሬቶች ለግዑዛን ሳይቀር እንደ ተፈጥሯቸው ብርቱ ጥንቃቄ የሚያድርግ የሰብዕና ልዩ መለያ ሰማያዊ ጸጋ ነበር። አዳካርከው … አንቦጨራቅከው …. ይብላኝላት አንተን አግብታ ለምትኖር ብዕርና ብርና …. መጥኔ! ….. ፈርዶባት … ያተረፈቸውን ፍቅር በቤንዚን አርክፍክፎ ከሚያቃጥል ግልብ ተጠግታ መለመላዋን ቀረች ….
አንተ በገዢው ፓርቲ ውስጥ ሆነህ የሰራኸው ደባ፤ ዛሬም አንተን አምነው የተጠጉትን የበላህ የቀን ጅብ ነህ። ስለላና ጥበብን እንዴት አድርገህ አጋብታሃቸው ኖርክ ከቶ … ?! ይገርማል አካልህን መክሊትህ ተሸክሞት መኖሩ … እራሱ አንድ የጨለማ መጸሐፍ ያጽፋል። ዳፍንት ነህና —
ሌላው ድሉም ቅርብ እንደሆነ ተንብዬሃል። ዘለልክ …. የፈጣሪንም ሥልጣን ቀማኸው። ልክ ይኑርህ። በእጅህ ምን እንዳለ እናውቃለን። ግን እሳቱ ከዚህም አለ። የምትፎክርበት ይህ ከንቱ ዓለም በሰው ሰራሽ ጥበብ ሰክኖ አያውቅም። የፈጣሪ ታምር ብቻ ነው ደምን አርግቶ ሰውን አቁሞ የሚያስኬደው፤ መሬትን ካለ ካስማ ሰማይን ካለባላ ያቆመ አምላክ አላት … ክብርት ልዕልት ኢትዮጵያ …. አይመስለህ ወድቃ የማትወድቅ ደክማ የማትደክም አላዛር ናት።
አሁን ግራ ቀኙ እሳት ነው። የአባ ገብርህይወትና የእማማ ብሬ ልጅ ጠ/ሚሩ እሱ ነው ያው እትብትህ። … ጽጌ መልስ ይኖራታል ብዬ ነበር … አቮይም ተዛው ናቸው ዘሃ ግራው ተጀምሮ እስኪጨርስ ድረስ በጠላት የታጠረች ሀገር ናት ጥንታዊቷ ቀደምት ሀገር ንግሥት ኢትዮጵያ። … ግን አምላክ አላት። የማያንቀላፋ – የማይተኛ … ከቶውንም የማይረሳት …. 90 ሚሊዮን ህዝብ ከተነሳ ደግሞ የግራ ቀኙን ትዕቢቱን ሁሉ ያስተነፍሳል። የቆመ የሚመስለው ሁሉ በቁሙ ነቅዞ … ከንቱነት ይጨፍርበታል ….
ሽልማት ደግሞ ሰጠህ። ተቀናጣህ – ካለልክህ ተወጣጠርክ – ተወራጨህም። እራስህ በምናብህ በምትፈጥረው ጥያቄ ተጠይቀህ መልስ እንደሰጠኽበት ታወራለህ። „ወሎ …. ምን?“ መብቱ ያለን ሰዎች ነው የመናገር መብት ያለን። ሰባራ ገል ለምን ነበር አገልግሎት የሚውለው? እቴ አምጡልኝ እባካችሁ? ኣህ መጣልኝ … ለእሳት መጫሪያነት … አዎን የአግልግሎት ጊዜህ መጠናቀቁን እወቀው …. ደሙ አስክሮ እራሱ ይደፋሃል … መጣፊያ – መለበጃ የድሪቶህ ማግኘትህ እያወሩ ብቻን ከመሄድ ይታደግኽ ይሆን?!
መቋጫ ለዳርቻ —- ከገለባ ጋር። እንደራስህ ኖረህ አፈር ለመሆን ያብቃህ ልበልህ ወይንስ ማንነትህን ሳታገኝ እንደባዘንክ ስንብት ይሁንልህ? የተሻለህን ውስድ። ከዜሮ በታች —
ውዶቼ የሞተ ውይብ መንፈስ ሊንክ ካስፈለጋችሁ ይኼው ነው። http://www.zehabesha.com/amharic/archives/35970
ለእኔዎቹ ብቻ … አብረን በመቆዬታችን ደስ አለኝ። መለዬቴ ደግሞ ጊዜያዊም ቢሆን ከፋኝ። በሌላ ጉዳይ እስንገናኝ ድረስ ሁሉንም ውስጤን በልግስና ሸልሜ ልሰናበት። መሸቢያ ሳምንት።
ለእኔስ ሰው መሆኔ ብቻ ይበቃኛል።
እግዚአብሄር ይስጥልኝ።