ከአልሸባብና ደቡብ አፍሪካ ከሚገኝ የሽብር ቡድን ጋር ግንኙነት ነበራቸው ተብሏል
መቃወሚያቸውን እንዲያቀርቡ ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጥቷቸዋል
(ዛሬ በአዲስ አበባ ታትሞ የወጣው አዲስ አድማስ ጋዜጣ እንዘገበው) በጅሃድ ጦርነት እስላማዊ መንግስት ለማቋቋም በጅማ አካባቢ ሲንቀሳቀሱ ነበር የተባሉ ተጠርጣሪዎች፤ ሰሞኑን ፍ/ቤት ቀርበው ክሣቸው ከተሰማ በኋላ የክስ መቃወሚያቸውን እንዲያቀርቡ ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጥቷቸዋል፡፡
በፌደራሉ ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ ባለፈው ረቡዕ ክሣቸው በንባብ የተሰማው 7 ተጠርጣሪዎች፡- ጃፋር መሃመድ መሃሙድ ኑር፣ መሃመድ ሣኒ፣ መህዲን ጀማል፣ መሃሙድ አባቢያ፣ አንዋር ትጃኔ እና ሼክ ከማል አባጪብሳ ሲሆኑ በዋና ወንጀል ፈፃሚነት መሠረታቸውን ጅማ አካባቢ አድርገው፣ እስላማዊ መንግስት ለመመስረት ሲንቀሳቀሱ በቁጥጥር ስር መዋላቸው ተጠቁሟል፡፡ ተጠርጣሪዎቹ ደቡብ አፍሪካ ከሚገኝ የሽብር ቡድንና በሶማሊያ ከሚንቀሳቀሰው አልሸባብ ጋር ግንኙነት ነበራቸውም ብሏል – የአቃቤ ህግ የክስ መዝገብ፡፡ 1ኛ ተከሣሽ ጃፋር መሃመድ፤ በኢትዮጵያ ውስጥ ሃይማኖታዊ ጦርነት ለማወጅና እስላማዊ መንግስት ለማቋቋም የሚያስችለውን ስልጠና ከደቡብ አፍሪካ ወስዶ በመምጣት፣ ጅማ አካባቢ ለአላማው ማስፈፀሚያ ቦታ በመምረጥ አባላትን በመመልመል ሲንቀሳቀስ ነበር ተብሏል፡፡
ተከሳሹ በደቡብ አፍሪካ ይገኛል ከተባለው አሸባሪ ቡድን የተላከለትን 80ሺህ የደቡብ አፍሪካ ራንድ ተቀብሎ ለመሣሪያ መግዣ እንደተጠቀመበት የክስ መዝገቡ አመልክቷል፡፡ በጅማ አካባቢ ኮዳ በተባለ ጫካ ውስጥ የመለመላቸው ግለሰቦች ለ6 ቀናት ስልጠና እንደወሰዱና እንቅስቃሴው በፀጥታ ኃይሎች እንደተደረሰበት ሲረዳ፣ ወደ ሶማሊያ ሄዶ ከአልሻባብ ጋር ለመቀላቀል ሙከራ ሲያደርግ በግንቦት 2006 ዓ.ም በቁጥጥር ስር መዋሉን የአቃቤ ህግ የክስ መዝገብ ያስረዳል፡፡
በመዝገቡ የተካተቱት ቀሪዎቹ 6 ተጠርጣሪዎች አባል በመሆን፣ የሽብር ተልዕኮ በመቀበልና እስላማዊ መንግስት የመመስረት አላማቸውን ለማሳካት ሲንቀሳቀሱ በፈፀሙት በሽብር ቡድን ውስጥ የመሳተፍ ወንጀል ክስ ተመስርቶባቸዋል፡፡ ባለፈው ረቡዕ ፍ/ቤቱ ክሱን በንባብ ካሰማ በኋላ፣ የተከሳሾች ጠበቃ በክሱ ላይ መቃወሚያ ካላቸው እንዲያቀርቡ ለህዳር 10 ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡