ሐራ ዘተዋሕዶ
በቅዱስ ሲኖዶስ የተወገዙ የተሐድሶ መናፍቃን (አላውያን) ድርጅቶችና ግለሰቦች አስተዳደራዊ ችግርንና ጎሳዊ ርእዮታዊ ጥላቻን ሰበብ በማድረግ ቤተ ክርስቲያናችንን ከሕዝቡ ነጥሎ ለማዳከም በኅቡእ እና በገሃድ የሚያራምዱትን የክሕደት ትምህርት ማጋለጥ ጠንካራ የጋራ መግባባትና አቋም ተይዞበታል፡፡
በምልመላና ቅበላ ክፍተት ሳቢያ ወደ ቤተ ክርስቲያናችን የትምህርት ተቋማት ሰርገው ገብተው እንጀራዋን እየበሉ ለፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ አራማጅ ድርጅቶች እንደሚሠሩ የተጠረጠሩ ተቋማቱንና ብዙኃን ደቀ መዛሙርቱን የማይወክሉ ግለሰቦች ጉዳይ ተጣርቶ ለውሳኔ የሚቀርብበት አቅጣጫ ተሰጥቷል፡፡
ብፁዕ አቡነ ኄኖክ፤ የምዕራብ ወለጋና አሶሳ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ (ፎቶ: ናሽቪል ሐመረ ኖኅ ኪዳነ ምሕረት)
ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶን ‹‹የምኒልክ ሃይማኖት›› እያሉ የአንድ አካባቢ በማድረግ ሕዝቡን ለሚከፋፍሉ የተሐድሶ አላውያን ምላሽ የሚሰጥ እና ምእመኑን በእምነቱና በአንድነቱ የሚያጸና መጠነ ሰፊ ስምሪት ይካሔዳል፡፡
በአህጉረ ስብከቱ በጥቂት አባወራዎች የሚጠበቁ የገጠር አብያተ ክርስቲያንም የሚረዱበት፤ በምዕራብ ወለጋና አሶሳ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ኄኖክ የሚመራ ሀገር አቀፍ ትብብር ይቋቋማል፤ ምእመኑን በቋንቋው የሚያስተምሩ ሰባክያነ ወንጌል ይመደባሉ፤መጻሕፍትና በራሪ ወረቀቶች ይዘጋጃሉ፡፡
ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ፤ የጋምቤላ እና ኢሉባቦር አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ
በጋምቤላ ካህናትና ማእመናን ለኅልፈተ ሕይወት በተዳረጉበትና በእርስ በርስ ግጭት ለተጎዱ ኹሉም ወገኖች ጸሎት የምታደርግበትንና የሰላም መልእክቷን የምታደርስበትን፤ ከኑሯቸው ለተፈናቀሉትም ድጋፍ የምታደርግበትን የማስተባበር ሥራ ትሠራለች፡፡