ብፁዓን አባቶቻችን !
እኛ ስማችንም ሆነ ምግባራችን ከንቱ የሆነ፣ በቅዱስ ሲኖዶስ ፊት የሚያቀርብ አንዳች በጎ ምግባር የሌለን፣ ይልቁንም ይህን ሃገራዊ አጀንዳ ለማንሳት የማይገባን ታናናሾች ስንሆን፤ ይሁን እንጂ እንደ ማንኛውም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ምዕመን በፈጣሪያችንና በመድሃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ህያው ቃል በአደራ የተሰጠናችሁ ደካማ ልጆቻችሁ ነን፡፡
እኛ በማርቆስ ወንጌል በም. ፭ ከቁ. ፳፭-፴፬ እንደምናነባት አንዲት በደሟ ስትታጠብ እንደኖረችው ሴት፤ እንዲያ የተጨናነቀው የህዝብ ብዛት ሳያቆማት፤ ተሽሎክሉካ የመድሃኒቷን ልብስ በእምነት በመንካት ለ፲፪ አመታት ሲያሳቅቃትና ሲያሰቃያት ከነበረው ሸክሟ እንደነፃችው እንስት ያለን፤
አዎ! እኛ የሃገራችን እና የወገናችን ለዘመናት በትውልዶች የደም ጎርፍ መታጠብ ያሳቀቀን፣ መጭው ዘመን በእጅጉ ያስፈራንና ያስጨነቀን፣ በአንፃሩ ደግሞ በፈጣሪያችን እና በመድሃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ መንበር ለተሰየማችሁት፣ በቅዱሳን ሐዋርያት እግር ለተተካችሁት፣ በቅዱሱ የእግዚአብሔር መንፈስ ወደ ምትመሩቱ ወደ ብፁዓን አባቶቻችን በማሳስባችን፤ ብሎም ጩኸታችንም ሰሚ ጆሮና እሩሩህ ልቦና ሲያገኝ ይህቺ በንፁሃን ልጆቿ የደም ጎርፍ የጨቀዬችው እናት ሃገራችንና ኢትዮጵያዊነታችን በፍፁም ሃገራዊ እርቅና የይቅርታ ምህረት እንደ አመዳይ እንደምትነፃ ፍፁም ተስፋ እና እምነት በልቦናችን የሰነቅን የዛች እንስት አምሳያዎች ነን፡፡
ብሔራዊ እርቅና መግባባት ለምን?
ብፁዓን አባቶቻችን !
በአለፉት ጥቂት ዓመታት እዚህ በስደት ሆነን ተለይተናቸው የኖርነውን የወላጆቻችንን ትውልድ በቅርበት ሆነን ለማወቅ እና በስደት የሚገፉትን የእርጅና ዘመናቸውንም ለመጋራት እግዚአብሔር እድሉን ሰጥቶናል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ለዘመናት ከእናቶቻችን እቅፍ ሳንወርድ ጀምሮ ስንኮመኩመው ያደግንበትን የዚያን ትውልድ እርስ በእርስ የመጠፋፋት ጀብዱ ከአፈ-ታሪክነት በአለፈ ደረጃ፤ የዚያን ዘመን የፖለቲካ እንቅስቃሴ በተለያዩ ተፃፃራሪ ጎራዎች ተሰልፈው ይዘውሩት የነበሩት “ታላላቅ” ሰዎች ያለፉበትን የታሪክ ጎዳና በመዋዕለ ዜናዎቻቸው ለአደባባይ በማዋላቸው፣ እኛም እነዚህን በንፁሃን ኢትዮጵያውያን ሰቆቃና የደም ጩኸት የታጨቁ ድርሳናት እንደዋዛ የማግኘትና የማንበብ እድል ለማግኘት ችለናል፡፡ በተጨማሪም አሁን ስልጣን ላይ ያለው የኢህአዴግ ባለስልጣናት በተለያዩ ምክንያቶች ከስርአቱ ተለይተው ከወጡ በኃላ የከተቧቸውን ዘገባዎች በቅርብ የማግኘት እድል ገጥሞናል፡፡
ከእነዚህ ህለቆ መሳፍርት በሌላቸው የንፁሃን ወገኖቻችን የሰቆቃ ጩኸቶች ከተሞሉ መዛግብት በተለይ የተረዳነው አንድ አብይ ጉዳይ አለ፡፡ ይሃውም በተለይም ከ፲፱፻፶ዎቹ ወዲህ እከሌ ከእከሌ ሳይባል እኛ ኢትዮጵያውያን እንደ ህዝብ እጆቻችን በገዛ ወገኖቻችን ንፁህ ደም እንደ ተጨማለቀ እና ምድሪቱም በግፍ በፈሰሰው በልጆቿ ደም በእጅጉ እንደ ጨቀዬች ተረድተናል፡፡ ስለዚህም እኛና ምድሪቱ በአንድነት እንደረከስን፣ የወላጆች ቀሪ የእርጅና ዘመን በመሪር ሃዘን እንደተኮማተረ፣ የአእላፍትን ወገኖች የትዳር ጎጆ በሰቆቃ እንደተዘጋ፣ የንፁሃን ታዳጊ ህፃናትን ህይወት ከጅምሩ እንደጨለመ፣ ይልቁንም በዚህ ሁላችን በምናፍርበት እኩይ ምግባራችን በሰማይ በቅዱሳኑ ዘንድ ፍፁም እንደታዘነብን ይሰማናል፡፡
ቅዱሱ እግዚአብሄር በነብዩ በዮናስ መፅሃፍ በም. ፬ ከቁ. ፱-፲፩ “ . . . እኔስ ቀኛቸውንና ግራቸውን ከማይለዩ ከመቶ ሃያ ሺህ የሚበልጡ ሰዎችና ብዙ እንስሶች ላሉባት ለታላቂቱ ከተማ ለነነዌ አላዝንምን? ” ይላልና ነው፡፡
ብፁዓን አባቶቻችን !
ለዚህም ሰቆቃና በደል ተጠያቂ የማይሆን ወይም አይመለከተኝም የሚል ኢትዮጵያዊ ማግኘት የሚቻል አይመስለንም፡፡ ከደሙ ንፁህ ነኝ የሚል ከተገኘም “ግመል በመርፌ ቀዳዳ…” ነው የሚሆንብን፡፡
ታዲያ ሁሉም በዳይና ተበዳይ በሆነበት ሁኔታ ለሁሉም ፍትህን በሚዛናዊነትና በርዕቱነት መስጠት የሚችል ምድራዊ ህግም ሆነ የፍትህ ተቋም ወይም ምድራዊ ዳኛ የምናገኝ አይመስለንም፡፡ በፍፁም እውነት የሚፈርድ እውነተኛ ዳኛ እንኳን ቢገኝ ማን ከሳሽ፣ ማን ተከሳሽ፤ ማን በዳይ ማንስ ተበዳይ ሊሆን ይሆን? እዚህ ላይ በዩሐንስ ወንጌል በም. ፰ ከቁ. ፩-፲፩ በተፃፈው የአመንዝራዩቱ ሴት ፍርድ ታሪክ ላይ ሁሌም የምናነባትንና ወደ እውነተኛው ፈራጅ ወደ ኢየሱስ ክርሰቶስ ፊት ለፍርድ የቀረበችውን እንስት እና ሊወግሯት የነበሩትን የከሳሾቿን ታሪክ ልብ ይሏል፡፡
እኛ ግን በአንድ የቀደመ ሃሳብ እንስማማለን፡፡ ይኃውም አስቀድሞ የገባንበት ታሪካዊ ፈተና የተገለጠላቸው ወገኖች ያለመታከት ደግመው ደጋግመው እንደሚያነሱት ሁሉ ብሔራዊ እርቅና ሃገራዊ መግባባት ከሁሉም የተሻለው የችግራችን መፍቻ መንገድ እንደሆነ እንረዳለን፡፡ ስለዚህም እኛም እንደ እነርሱ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ብሔራዊ እርቅ ይቅደም እንላለን፡፡
ማን ከማን ጋር ይታረቅ?
ብፁዓን አባቶቻችን !
ታራቂዎቹ እኛ ኢትዮጵያውያን ስንሆን የምንታረቀውም ከእራሳችንና ከፈጣሪያችን፣ ከምድር እና ከሰማይ ጋር ነው ብለን አናምናለን !
ሂደቱም ከሴት እስከ ከወንድ፣ ከትልቅ እስከ ትንሽ፣ ከጨዋ እስከ ምሁር፣ ከደሃ እስከ ባለፀጋ፣ ከፖለቲከኛ እስከ ገበሬ ወዘተ ሁላችንንም ያካተተ ሊሆን ይገባል የሚል ፅኑ እምነት አድሮብናል፡፡
ይሁንና ሁላችንም እንደምናውቀው ኢህአዴግን ወደ መንግስታዊ ስልጣን መምጣት ተከትሎ በነበረው ለውጥ ተስፋ የሰነቀው በውስጥም በውጭም የሚገኘው ህዝባችን በሃገራችን ብሔራዊ እርቅ እንዲወርድና ሁላችንም ወደ አንድ ሃገራዊ መግባባት እንድንደርስ፣ ሂደቱንም በወቅቱ በስልጣን ላይ ያለው አካል በቅንነት እንዲቀበለው እና ድጋፍ እንዲያደርግ ከፍተኛ የሆነ ጥረት ሲደረግ ቆይቷል፡፡
ነገረ ግን ሃገሪቱን እየመራ ያለው መንግስት ይቀርብለት ለነበረው ጥያቄ አሉታዊ እይታ ያለው እና ምላሹም ተስፋ የሚያስቆርጥ ስለነበረ እነሆ ሂደቱ በትንሹ ለአለፉት ፳፫ ዓመታት ምንም እመርታ ሳያሳይ በእንጥልጥል የሚገኝ እና ምንም አይነት ተስፋ ሰጪ ምልክቶች የማይታዩበት ለመሆን ተገዷል፡፡
ምንም እንኳ ዛሬም ድረስ ለዚህ ሃገራዊ አጀንዳ ተግባራዊነት በመትጋት እንቅልፍ የማይወስዳቸው ወገኖች እንደሚኖሩ ብንረዳም ከላይ በተገለፀው እንቅፋት ምክንያት ይህ ታሪካዊና ቅዱሱ የእርቅ እና የሰላም መንፈስ በጊዜ ህዝባችንና ሃገራችንን እንዳይታደግ ለጊዜው ስለተገታ ሌላ አማራጭ መፍተሄ የግድ መፈለግ እንዳለበት እናምናል፡፡ የእኛም አላማ አማራጭ የመፍትሄ አቅጣጫ ሊሆን ይችላል ያልነውን መንገድ ለመጠቆም ነው፡፡
መቼና የትስ ሆነን እንታረቅ?
ብፁዓን አባቶቻችን !
እዚህ ላይ “ማን ከማን ጋር ይታረቅ ከሚለው” ቁምነገር ጋር በዋናነት አብሮ መታሰብ የሚኖርበት ጉዳይ ሂደቱን አሁኑኑ የመጀመር አንገብጋቢነት ነው፡፡ ለምን ቢባል ጊዜን በመቅደም አላፊውን ትውልድ ከፍፁም የህሊና ሰላም ጋር ከመሸኘት፣ ወጣቱን አፍጦና አግጦ ሊውጠው ከሚጠብቀው የመጠፋፋት አዙሪት ለመታደግና፣ መጭውን ትውልድ ከደም ውርሱ ከማዳን አንፃር ሂደቱ ነገ ዛሬ ሳይባል በጊዜ መጀመር እንዳለበት በፅኑ እናምናለን፡፡
በሌላ መልኩ ደግሞ ሃገራችንን በቀደሙት ፲፯ ዓመታት ከመሩት ከቀድሞው የኢትዮጵያ ፕሬዘደንት መንግስቱ ሃ/ማርያም እና ጓዶቻቸው ጀምሮ እስከ ዋነኛ ተቀናቃኞቻቸው ከነበሩት የመኢሶን ፣ የኢህአፓ ፣ የኢዲዮ ፣ የኦነግ፣ ወዘተ እስከ ዛሬዎቹ የኢህአዴግ አሳዳጆችና ተሳዳጆች ከነጓዶቻቸውና ደጋፊዎቻቸው በብዛት ከሃገራቸው ውጭ በስደት እንደሚኖሩ ተገንዝበናል፡፡
ስለሆነም ይህ የብሔራዊ እርቁ እና የሃገራዊ መግባባቱ የመጀመሪያ ምዕራፍ እዚሁ በስደት ቢጀመር በመተላለቅ ዘመናቶቻችን ከመሪነት እስከ ተራ አባልነትና ደጋፊነት፣ በከፍተኛ ሁኔታ በብዛትና በንቃት ይሳተፍ የነበረውን የህብረተሰብ ክፍል በቀላሉ መድረስ የሚቻል ስለሚሆን፤ የመጀመሪያው ታሪካዊ ምዕራፍ በመላው ዓለም ተበትነን የምንገኝ ሁላችንም ኢትዮጵያውያን ያካተተ ሆኖ ሊከናወን ይችላል ብለን እናምናለን፡፡ ከዚያም እግዚአብሔር ሲፈቅድ እና ጊዜው ሲደርስ ሂደቱ ወደ ሃገራችን ተሸጋግሮ በሃገር ውስጥ የሚገኘውን መላውን ህዝባችንን የሚያሳትፍ በመሆን ይጠናቀቃል የሚል ታላቅ ተስፋ አለን፡፡ በዚህም ጅማሮ በሃገር ቤት የሚገኘው ወገናችን ሂደቱ እንዲፋጠንና እርሱም ዘንድ እንዲደርስ ከፍተኛ ግፊትና አስተዋፅኦ እንዲያደርግ ያበረታታዋል እንላለን፡፡
ታላቁ የእግዚአብሔር ነብይ ነህምያ በመጽሐፉ በም.፪ ከቁ. ፳ “ የሰማይ አምላክ ያከናውንልናል፤ እኛም ንጹሓን ባሪያዎቹ ተነስተን እንሠራለን ” እንዲል፡፡
ይህን ታላቅ ሃገራዊ አጀንዳ ማን ይምራው?
ብፁዓን አባቶቻችን !
ምንም እንኳ የችግራችን መነሻና መድረሻ የየዘመናቱ የፖለቲካ አሰላለፎች በመሆናቸው መፍትሄውም ፖለቲካዊ ቢሆን እና ሂደቱንም ሃላፊነት ወስዶ የሚሳተፈውም ሆነ የሚያስተባብረው/የሚተባበረው ፖለቲካዊ የበላይነት የያዘው የወቅቱ አሸናፊው ቡድን ቢሆን ሂደቱን እጅግ ያቀለው ነበር (የታለቁን መሪ የማዲባን ሃገር እና የANCን ታላቅ አስተዋፅኦ ልብ ይሏል)፡፡ ነገር ግን በአሁኑ ሰአት ኢህአዴግ በያዘው አቋም ይህን ታላቅ የእፎይታ መንገድ ለማግኘት የምንችል አልመሰለንም፡፡ በመሆኑም እነሆ ይህ አብይ አጀንዳ እስከ ዛሬ ድረስ ባለቤት ሊያገኝ ሳይችል ቀርቷል የሚል እምነት ይዘናል፡፡
ብፁዓን አባቶቻችን !
ከሁሉም በላይ የሚያሳዝነው ደግሞ ኢህአዴግ ሂደቱን ካልተቀላቀለውና ካልመራው ተብሎ በይደር የሚቆይና በጊዜ መራዘም ብቻ ችግሩ የሚወገድ ያለመሆኑ ጉዳይ ነው፡፡ ይልቁንም ጊዜ በሰጠንና በተዘናጋን ቁጥር ይህ የደም ውርስ በፍጥነት እየተንከባለለ እኛ ዘመን ላይ እንደደረሰብን ሁሉ ወደቀጣይ ትውልዶች በቀላሉ እንዲተላለፍ ምቹ ሁኔታን እያመቻቸን የምንገኝ ይመስለናል፡፡ ስለሆነም ይህ ዘግናኝ የመጠፋፋት ሂደት ወደ ቀጣዮቹ ዘመናት ከመተላለፉ በፊት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እልባት እንዲያገኝና ዳግመኛ እንዳይመለስ ሆኖ እንዲሸኝ ያሻል፡፡ ስለዚህ ይህን ሃገራዊ ሸክም ሊሸከምልን በሚችል አካል አማካኝነት ይህ ታላቅ ሃገራዊና ትውልዳዊ የመፍትሄ ጎዳና በጊዜ አንድ ቦታ ላይ መጀመር እንዳለበት ፅኑ እምነት ይዘናል፡፡
በመሆኑም ይህንንም ሂደት ሃላፊነት ወስዶ ለመምራት ለማስተባበር ከህዝቦቿ ጋር በስደት ከምትገኘው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያንና ከቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ የተሻለ አንዳች አካል ያለ አይመስለንም፡፡ ይህንንም ለማለት ያስደፈሩንን ብዙ ምክንያቶቻችንን ማቅረብ በወደድን ነበር፡፡ ነገር ግን የእናንተን የብፁዓን አባቶቻችን ጊዜ መሻማትና በከንቱ ማድከም እንዳይሆን በማሰብ ለአብነት ያህል አንዷን ብቻ እናቅርብ፡፡ ይኃውም እናንተ ማለት ለእኛ ፡-
ከሁሉ አስቀድሞ ከመረጣችሁ፡ ከለያችሁና፣ በቀደሙት አባቶቻችን እግር ካስቀመጣችሁ በሃያሉ በእግዚአብሔር አብ ፀጋ፣ ቅድስት ቤተክርስቲያኑን በከበረ ደሙ በዋጃትና በመሠረታት በቅዱሱ በእግዚአብሔር ወልድ ፍቅር ፣ እናንተም ዘወትር በመካከላችሁ ሆኖ በሚያፅናናችሁና በሚያፀናችሁ በቅዱሱ የእግዚአብሔር መንፈስ በመመራት ስለ ፍቅር፣ ሠላምና፣ አንድነት በመትጋት መንጋውን ከክፉው ሁሉ የምትጠብቁ መልካም እረኛዎቻችን እንደሆናችሁ እናምናለን፡፡
ቅዱስ ዩሐንስ በወንጌል በም. ፳፩ ከቁ. ፲፭ -፲፰ “. . . ጴጥሮስም ሶስትጊዜ ትወደኛለህን? ስላለው ተከዘ፤ “ጌታዬ ሆይ አንተ ሁሉን ታውቃለህ፤ እኔም እንደምወድህ አንተ ታውቃለህ” አለው፤ “እንኪያስ ግልገሎቼን ጠብቅ” አለው . . . ” ብሎ እንደ መሰከረው፡፡
ሂደቱ እንዴት ሊተገበር ይችላል?
ብፁዓን አባቶቻችን !
እንግዲህ የእኛ ተማፅኖ ቅድስት ቤተክርስቲያናችን እና ቅዱስ ሲኖዶሱ እንደ ተቋም ሃላፊነቱን ወስዳችሁ ሂደቱን እንድትመሩ እንጂ ከዚህ በዘለለ መልኩ በዝርዝር ጉዳዮችና አፈፃፀሙ ላይ ሃሳብ ለማቅረብ አይደለም፡፡ ይህም ከእውቀትና ከልምድ ማነስ የተነሳ ነው፡፡ ይልቁንም ኢትዮጵያ ሃገራችን የሊቃውንትና የደጋግ ልጆች ደሃ አይደለችምና አጠቃላይ ሃላፊነቱን ቅዱስ ሲኖዶሱ በመውሰድ፤ የሚመራውና የሚቆጣጠረው አንድ አካል በመሰየም በመላው አለም እንደ ጨው ዘር ተበትነው የሚገኙ ታዛዥ ልጆቻችሁን በማስተባበርና ቡራኬ በመስጠት ይህንን ታሪካዊና ትውልዳዊ መርገም በተሰጣችሁ ፀጋ እግዚአብሔር በመታገዝ በፍቅርና በይቅርታ ታፀዱልን ዘንድ በሃያሉ በልዑል እግዚአብሔር ስም ልባዊ ተማፅኗችንን እናቀርባለን፡፡
በዚሁ አጋጣሚም መላው ወገናችን ለዚህ ታላቅ የይቅርታ ህይወት እራሱን ከወዲሁ እያዘጋጀ፣ የብፁዓን አባቶቹን የፍቅር፣ የሰላምና፣ የእርቅ ጥሪ በንቃት እንዲጠባበቅና፣ ለስኬታማነቱም ተግቶ እንዲታዘዝ እና እንዲረባረብ ወገናዊ ጥሪያችንን ከታላቅ አክብሮት ጋር እናቀርባለን፡፡
በመጨረሻም ነገራችን ሁሉ ያለዕውቀትና ማስተዋል የተዘበዘበ “ልጅ ያቦካው” አይነት ነውና አንዳች እናንተንና ህዝባችንን የሚያሳዝንና የሚያስከፋ ነቀፋ ቢገኝብን ፍፁም የሆነው አባታዊ ይቅርታችሁ ከወዲሁ ይደረግልን ዘንድ የአማላጃችንና የእናታችንን የቅድስት ድንግል ማርያምን ጣፋጭ ስም ጠርተን እጅ ነስተናል፡፡
ወስብሃት ለእግዚአብሔር
ልጆቻችሁ
ከሰሜን አሜሪካ – ጥቅምት ፳፻፯ ዓ.ም
ግልባጭ ፡-
ለብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆርዮስ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ
ለብፁዕ አቡነ መልከፄዴቅ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ፀሐፊ
ለብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት በሙሉ (በየሃገረ ስብከታቸው)