Quantcast
Channel: Ethiopian News | ዘ-ሐበሻ | Latest News Provider | News For All
Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

ሚኒስትሮች ባልተወራረደ የመንግስት ገንዘብ ጉዳይ ላይ ጎራ ለይተው ተከራከሩ

$
0
0

ኢሳት ዜና :-የፌደራል ዋና ኦዲተር፣ አባካኝ የመንግስት ተቋማት በሚል ለጠቅላይ ሚ/ር ጽ/ቤት እና ለተወካዮች ም/ክር ቤት አፈ ጉባኤ ያቀረበው ሪፖርት ለህዝብ ይፋ ይሁን አይሁን የሚለው ጉዳይ ሚኒስትሮችን አወዛግቧል።

943አቶ አባዱላ ገመዳ፣ አቶ ደመቀ መኮንን፣ አቶ አዲሱ ለገሰና አቶ ጸጋየ በርሄ፣ የፌደራል ኦዲተሩ ሪፖርት ለህዝብ በፍጹም ሪፖርት መደረግ የለበትም ብለው ሲከራከሩ፣ የመንግስት ጉዳዮች ሚኒስትር ወ/ሮ ሙፈርያት ከማል፡ ለህዝቡ ይፋ በሆነ መልኩ የማሳወቅ እርምጃ መውሰድ ይገባል የሚል አቋም አንጸባርቀዋል። አቶ በረከት ስምኦንና ጠ/ሚ ሃይለማርያም ደሳለኝ ለዘብተኛ የሆነ አስተያየት በመስጠት አቃም ለመያዝ በመቸገራቸው ጉዳዩ እልባት ሊያገኝ አልቻለም።

በውይይቱ ላይ የጥሬ ገንዘብ ሂሳብ ከመዝገብ /ሌጀር / ጋር የማይመሳከር መሆኑ፣ በበጀት ዓመቱ መጨረሻ በቆጠራ ከተገኘው ጥሬ ገንዘብ በማነስ ሪፖርት የተደረገ መሆኑ፣ የጥሬ ገንዘብ ቆጠራ የማያደርጉ ወይም የጥሬ ገንዘብ ቆጠራ አድርገናል ቢሉም ማስረጀ ያላቀረቡ መሆኑ፣ በባንክ ሂሣብ ገቢ ለሆኑ ሂሣቦች የገቢ ደረሰኝ ያለማዘጋጀትና ያለመመዝገቡ፤ የባንክ ሂሳብ ማስታረቂያ የማያዘጋጁ መሆኑ፤በበጀት ዓመቱ መጨረሻ በባንክ ሂሳብ መግለጫ ዜሮ ከወጪ ቀሪ እየታየ አላግባብ በባንክ ያለ ገንዘብ ተብሎ ሪፖርት የሚደረግ መሆኑ፣ በወጭ ምንዛሬ ባንክ ያለ ገንዘብ /41ዐ2/ ተብሎ ሪፖርት የተደረገውን ትክክለኛነት ለማረጋገጥ የባንክ ሂሳብ መግለጫ ያልቀረበበት ሆኖ መገኘቱ የሚሉት ዋና ዋናዎቹ ድክመቶች ተብለው ተነስተዋል።

ስለመንግሥት ሂሳብ አያያዝ የወጣው ደንብ የደመወዝ ሰነድ ሂሳብ የወሩ ደመወዝ በሚከፈልበት ጊዜ የሥራ ማስኬጃ የሚመለከተው ደግሞ በተለይ የግዥ ሰነድ ከተሰጠበት ቀን አንስቶ በሰባት የሥራ ቀናት ውሰጥ እንዲጠናቀቅ ቢያዝም፣ በኦዲተር መስሪያ ቤቱ ከተመረመሩ መ/ቤቶች ውስጥ በ43 የፌደራል መንግስት መ/ቤቶች ብር 7 ቢሊዮን 99 ሚሊዮን 495 ሺ 265 ብር ከ01 ሳንቲም የሰነድ ሂሳብ በደንቡ መሠረት ሳይወራረድ ተገኝቷል፡፡

ሂሳባቸውን ባለማወራረድ ከፍተኛውን ድርሻ ከያዙት መስሪያ ቤቶች መካከል የትምህርት ሚኒስቴር ብር ከ451 ሚሉዮን ብር በላይ ፣ግብርና ቴክኒክ ሙያና ትምህርት ስልጠና ብር 232 ሚሊዬን ፣የመከላከያ ሚ/ር ብር 228 ሚሊዬን ፣ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ብር 225 ሚሊዬን፣ ጎንደር ዩንቨርስቲ 89 ሚሊዬን ፣መቀሌ ዩንቨርስቲ ብር 36 ሚሉዬን ፣ግብርናና ገጠር ልማት ሚ/ር የምግብ ዋስትና ዳይሬክቶሬት ብር 23 ሚሊዬን እና ማዕከላዊ ስታስቲክስ ብር 23 ሚሊዩን ብር ይገኙበታል ።

ከገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር የተወጣጣ ኮሚቲ ተቋቁሞ ባደረገው ጥረት የብር 767 ሚሊዮን 425 ሲ ከ 04 ሳንቲም ሰነድ የሚወራረድበትን መንገድ ለማመቻቸት እየሰራ መሆኑ ቢገለጽም ፣ በሌሎች መስሪያ ቤቶች ስላለው ሁኔታ በዝርዝር አልታወቀም።

ውዝፍ ሰነዱን በወቅቱ አለማወራረድ ለመንግስት ገንዘብ መጥፋት በር የሚከፍት ስለሆነ በአስቸኳይ መወራረድ እንዳለበት ፣ ለረጅም ዓመታት ሳይሰበሰቡ የተገኙት ሂሳቦች እንዲወራረዱ አስፈላጊው ክትትል እንዲደረግ፤ ሊሰበሰቡ በማይችሉት ላይ በመንግስት መመሪያ መሠረት ከመዝገብ እንዲሰረዙ እንዲደረግ ኦዲተር መስሪያ ቤቱ አስተያየቱን አቅርቧል።

በገቢ ግብር፣ቀረጥና ታክስ እንዲሁም በሌሎች ገቢ መሰብሰብ በሚፈቅዱ አዋጆች መሠረት የመንግስትን ገቢ የሰበሰቡ መሆኑን ለማረጋገጥ ኦዲት ሲደረግ ደግሞ፣ በ1ዐ መ/ቤቶች ውስጥ 5 ቢሊዮን 492 ሚሊዮን 319 ሺ 53 ብር በተለያዩ ምክንያቶች ሳይሰበሰብ ተገኝቷል፡፡

ሂሳቡ ሳይሰበሰብ ከቀረበባቸው ምክንያቶች መካከል በትክክለኛው የታሪፍ ቁጥር (Harmonized System code) እና(custom procedure code) ባለለመደባቸው ያልታሰበሰበ ቀረጥና ታክስ ፣የመነሻ ዋጋ የተወሰነላቸው ዕቃዎች በመነሻ ዋጋው መሰረት ያልተሰተናገዱ ድርጅቶች መገኘታቸው ፣በማነፃፀሪያ ዋጋ መሰረት ቀረጥና ታክስ ባለመሰራቱ እና መ/ቤቶች ከሚፈፀሙት ግዥ ላይ ቀንሰው ማስቀረት የሚገባቸው ግብር ( Withholding tax) ፤የተጨማሪ እሴት ታክስ እና ሥራ ግብር ሳይቀነሱ መቅረታቸው የሚሉት በኦዲተሩ ሪፖርት ተመልክተዋል።
ስለሁኔታው ትኩረት ተሰጥቶት የመንግስት ህግና ደንብ ተከብሮ እንዲሰራ ፣ ያልተሰበሰበውም ገቢ እንዲሰበሰብ መስሪያ ቤቱ አሳስቧል።

በገቢ ሰብሳቢ መ/ቤቶችና አገልግሎት ሰጭ ድርጅቶች በወጣው ህግና ደንብ መሠረት የመንግስት ገቢ በአግባቡ መሠብሰባቸውን ለማረጋገጥ ኦዲት ሲደረግ ደግሞ በገቢዎች ጉምሩክ ባለስልጣን ስር ባሉ ሶስት ቅርጫፍ ጽ/ቤቶች ከወለድና ቅጣት መሰብሰብ የሚገባው ብር 323 ሚሊዮን 794 ሺ 818 ብር ከ43 ሳንቲም፤ በጉምሩክ የአዳማ ቅ/ጽ/ቤት ብር 78 ሚሊዮን 973 ሺ 321 ከ94 ሳንቲም የአዲስ አበባ ኤርፖርት ቅ/ጽ/ቤት ሊሰበሰብ የሚገባው ብር 5 ቢሊዮን 934 ሺ 794 ከ47 ሳንቲም ከ6 ወር በላይ የቆየ ውዝፍ ሂሳብ የተገኘ ሲሆን ፤ የአዲስ አበባ የወጪ ዕቃዎች ማስተናገጃ ቅ/ጽ/ቤት የተወሰነላቸው የጊዜ ገደብ ጠብቀው ባለመጓጓዛቸው ተገቢ ቅጣት ከተወሰነላቸው ሾፌሮች እና ወኪሎች ያልተሰበሰበ ብር 30 ሺ 000.00 በድምሩ ር 394 ሚሊዮን 495 ሺ 607 ከ69 ሳንቲም በወቅቱ ያልተሰበሰበ ውዝፍ ገቢ ተገኝቷል፡፡፡

የተሰበሰበውን ገቢ ትክክለኛነት ለማረጋገጥ ኦዲት ሲደረግ ፣በገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን ስር ባሉ ሶስት ቅርጫፍ ጽ/ቤቶችና በሌሎች ሶስት መ/ቤቶች በድምሩ ብር 69 ሚሊዮን 753 ሺ 608 ከ97 ሳንቲም የገቢ ደረሰኝ እና የግብር ማሳወቂያ በፋይሉ ጋር ተያይዞ ባለመገኘቱ ምክንያት ፤ከማን እንደተሰበሰበ ሳይገለጽ በኮድ በመሰብሰቡ የተሰበሰበው ገቢ መሰብሰብ በሚገባው ልክ መሆኑን ለማረጋገጥ ባለመቻሉ የተሰበሰበው ገቢ ትክክለኛነት ለማረጋገጥ ሳይቻል ቀርቷል፡፡

በበጀት ዓመቱ የተሰበሰበው ገቢ በትክክል ተመዝግቦና በሂሳብ ሪፖርታቸው ተካቶ ለገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር መቅረቡን ለማረጋገጥ ኦደት ሲደረግ ፤ 9 መ/ቤቶች ባቀረቡት ዓመታም የገቢ ሂሳብ ሪፖርት ውሰጥ ብር 659 ሚሊዮን 51 ሺ ሳይካተት ተገኝታል፡፡

ይህ ሪፖርት ለህዝብ ይፋ ቢሆን፣ ለመንግስት ከፍተኛ ኪሳራ እንደሚያመጣ የተከራከሩት የእነ አባዱላ ቡድን፣ ሪፖርቱ በታሹ ቃሎች እንዲቀርብ ይፈልጋል። ወ/ሮ ሙፈሪያ ደግሞ በመስሪያ ቤቶች ላይ እርምጃ መውሰድ ካልተጀመረ ችግሩ የከፋ እንደሚሆን ተከራክረዋል። አቶ በረከትና አቶ ሃይለማርያም አቋም ለመያዝ ተቸግረው ታይተዋል።

አቶ መለስ ዜናዊ ከዚህ ቀደም ተመሳሳይ ሪፖርት ሲቀርብላቸው ሪፖርቱ እንዲጣራ ከመጠየቅ ይልቅ፣ በጄኔራል ኦዲተሩ ላይ እርምጃ መውሰዳቸው የአንድ ወቅት መነጋገሪያ ሆኖ ነበር። መንግስት ተገቢውን ቁጥጥር ባለማድረጉ በእያመቱ በመንግስት መስሪያ ቤቶች የሚታየው የገንዘብ ጉድለትና ብክነት እየጨመረ ሲሆን፣ በአገሪቱ ለሚታየው ከፍተኛ ሙስናም አስተዋጽኦ እያደረገ ነው።


Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>