Quantcast
Channel: Ethiopian News | ዘ-ሐበሻ | Latest News Provider | News For All
Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

ኢትዮ ቴሌኮም ከዜድቲኢ ጋር የገባውን የ800 ሚሊዮን ዶላር ውል አፈረሰ

$
0
0

-በውሉ መሠረት ፕሮጀክቱ ሳይጀመር ዓመት አልፎታል

ethio_telecom_corp101371252571በአዲስ አበባና ከአዲስ አበባ ውጪ ያለውን የቴሌኮም ማስፋፊያ ፕሮጀክት ለመተግበር የ800 ሚሊዮን ዶላር ኮንትራት የወሰደው የቻይናው ዜድቲኢ ኩባንያ ኮንትራት ተሰረዘ፡፡

እ.ኤ.አ. ኦገስት 18 ቀን 2013 ዜድቲኢ የማስፋፊያ ፕሮጀክቱን ውል ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር የተፈራረመ ቢሆንም፣ በውሉ መሠረት በሁለት ዓመታት መጠናቀቅ የነበረበት ፕሮጀክት፣ እስካሁን ባለመጀመሩ ለኮንትራቱ መፍረስ ምክንያት መሆኑን የሪፖርተር ምንጮች ተናግረዋል፡፡

ኢትዮ ቴሌኮም በደብዳቤ ቁጥር ET/CEO/63/2014 በጻፈው የማስጠንቀቂያ ደብዳቤ እንደገለጸው፣ ዜድቲኢ ፕሮጀክቱን ከማጓተት ተቆጥቦ በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ሥራ ገብቶ እንዲያጠናቅቅ አሳስቧል፡፡

ዜድቲኢ ለተጻፈለት የማስጠንቀቂያ ደብዳቤ ተዛማጅነት የሌለውና ግራ የሚያጋባ ምላሽ ከመስጠት ባለፈ፣ በገባው የኮንትራት ውል መሠረት ሥራውን ሊጀምር አለመቻሉን፣ ኢትዮ ቴሌኮም በሥራ አስፈጻሚው በአቶ አንዱዓለም አድማሴ ተፈርሞ የወጣው የኮንትራት ውል ማፍረሻ ደብዳቤ ቁጥር ET/CEO/71/2014 ይጠቁማል፡፡

‹‹እልህ አስጨራሽ ከሆነ ድርድር በኋላ የተደረሰበትን ስምምነት በዜድቲኢ ቁርጠኝነት ማጣት ምክንያት ስምምነቱ ጥያቄ ውስጥ ገብቷል፤›› የሚለው በሥራ አስፈጻሚው ተፈርሞ የወጣው ደብዳቤ፣ የኢትዮጵያ መንግሥትም ሆነ ኢትዮ ቴሌኮም በከፍተኛ ፍላጎት ሲጠብቁት የነበረውን የፕሮጀክቱን መጀመር ተስፋ አስቆራጭ እንዳደረገው ያስረዳል፡፡

ኢትዮ ቴሌኮም ከዜድቲኢ ጋር በገባው የፕሮጀክት ስምምነት አንቀጾች መሠረት ለመሥራት የመልካም ፍላጎት አለመኖር፣ የኮንትራት ስምምነቱን እንደመጣስ ተደርጎ እንደሚቆጠር በአቶ አንዱዓለም ተፈርሞ የወጣው ደብዳቤ ያስረዳል፡፡ በተጨማሪም ‹‹ይህ ኮንትራት ማቋረጫ ደብዳቤ ለዜድቲኢ ከደረሰበት ከሰላሳ ቀናት በኋላ ኩባንያው ወደ ሥራ መግባት ካልቻለ በፍቃዱ ኮንትራቱን እንዳቋረጠ ይቆጠራል፤›› ሲል ደብዳቤው ያስጠነቅቃል፡፡

ፕሮጀክቱን ተግባራዊ ለማድረግ ስምምነት ላይ የተደረሰባቸውን አንቀጾች ዜድቲኢ ጠብቆ ካለመጓዙም በተጨማሪ፣ ኩባንያው የኢትዮጵያ መንግሥትና ኢትዮ ቴሌኮም ፕሮጀክቱ በፍጥነት እንዲጠናቀቅ በሰጡት ትልቅ ትኩረት ላይ ጉዳት ማድረሱም ተጠቁሟል፡፡ በመሆኑም ኢትዮ ቴሌኮም በፕሮጀክቱ አለመጀመርና በተባለው ጊዜ አለመጠናቀቅ ምክንያት የደረሰበትን ጉዳት በሕግ የሚጠይቅ መሆኑ እንዳለ ሆኖ፣ የፕሮጀክት ኮንትራት ስምምነቱ የፈረሰ መሆኑን አስታውቋል፡፡

ዜድቲኢ በደብዳቤ ቁጥር ዜድቲኢ/CEO/14 0909/01 እ.ኤ.አ. ሴፕቴንበር 9 ቀን 2014 ለኢትዮ ቴሌኮም በጻፈው ምላሽ፣ ፕሮጀክቱን በፍጥነት እንደሚጀምርና በተባለው ጊዜ እንደሚያጠናቅቅ ገልጾ፣ ይህ እንዲሆንም ሁለቱ አካላት ተገናኝተው እንዲወያዩ ጠይቋል፡፡

ኢትዮ ቴሌኮም በጻፈለት ደብዳቤ መሠረት ፕሮጀክቱን የሚያቋርጥ ከሆነ በተናጠል የወሰነው ውሳኔ መሆኑን ለማስታወስ እንደሚወድ ዜድቲኢ በምላሽ ደብዳቤው ገልጿል፡፡

ጉዳዩን በተመለከተ የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ አንዱዓለም አድማሴ ማብራሪያ እንዲሰጡ ሪፖርተር የተጠየቃቸው ቢሆንም፣ ጉዳዩን ሳያስተባብሉ ምላሽ ከመስጠት ተቆጥበዋል፡፡ በተመሳሳይ የዜድቲኢ የሕዝብ ግንኙነት ሠራተኛ ወ/ሮ የምሥራች ብርሃኑ ውሉ አለመቋረጡን ገልጸው፣ ዜድቲኢ ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር እስካሁን በድርድር ላይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ዜድቲኢ የመጀመርያውን የአገር አቀፍ ቴሌኮም ማስፋፊያ ፕሮጀክት በ1.5 ቢሊዮን ዶላር ብድር የሠራ መሆኑ ይታወሳል፡፡ ይህ ኩባንያ ለረዥም ዓመታት ኢንዱስትሪው ውስጥ ቆይታ ቢያደርግም፣ የኢትዮጵያ መንግሥት በቅርቡ ይፋ ያደረገውን የ1.6 ቢሊዮን ዶላር ሁለተኛ ዙር የቴሌኮም ማስፋፊያ ፕሮጀክት ከባላንጣው የቻይናው ኩባንያ፣ ሁዋዌ ጋር እንዲጋራ መገደዱን መዘገባችን ይታወሳል፡፡ በተለይ 4G የተባለውን ዓለም የደረሰበትን የቴሌኮም ቴክኖሎጂ በአዲስ አበባ እንዲዘረጋ የኢትዮጵያ መንግሥት ሁዋዌን መምረጡ ለዜድቲኢ ያልተዋጠለት እንደነበርም ዘግበናል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ ዜድቲኢ በሚሳተፍበት የ800 ሚሊዮን ዶላር ማስፋፊያ ፕሮጀከት ላይ የሚያስፈልጉ ማይክሮዌቭ መሣሪያዎችን ከባላንጣው ሁዋዌ ኩባንያ እንዲገዛ መገደዱ ላለመግባባቱና ለፕሮጀክቱ መቋረጥ ምክንያት ሳይሆን እንደማይቀር ምንጮች ገልጸዋል፡፡

በቅርቡም የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ዜድቲኢ 500 ሚሊዮን ብር የትርፍ ግብር ታከስ አልከፈለም በሚል ውዝግብ ውስጥ መግባቱንና ኢትዮ ቴሌኮምም ምንም ዓይነት ክፍያ እንደማይፈጽም ማስታወቁን መዘገባችን ይታወሳል፡፡

Source:: Ethiopian Reporter


Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>