ሰማያዊ ፓርቲ ጥቅምት 18/2007 ዓ.ም በሰጠው መግለጫ የኢትዮጵያ ህዝብ አፋኙን ስርዓት በመቃወምና ከስርዓቱ ጋር ባለመተባበር በብሔራዊ ደረጃ የሚደረገው ትግል አካል እንዲሆን ጥሪ አቀረበ፡፡
‹‹የሀገራችን አስተዳደራዊና ፖለቲካዊ ችግሮች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሱና እየከፉ የመምጣታቸውን ያህል ገዢው ፓርቲ ቆም ብሎ ከማሰብ ይልቅ ወደ ማይወጣው አዘቅት ውስጥ ሀገሪቷን ጭምር እያንደረደራት ይገኛል›› ያለው የሰማያዊ ፓርቲ መግለጫ ገዥው ፓርቲ ከዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ሂደት ፍፁም በማይጣጣም መልኩ አፋኝ መዋቅሩን በማናለብኝነት እያስፋፋ እንደሚገኝ አብራርቷል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ለማናቸውም አስተዳደራዊም ይሁን ፖለቲካዊ ጥያቄዎች ሀይልን በመጠቀም ለመደፍጠጥና ለማጥፋት ቆርጦ በመነሳት ፍፁም አምባገነንነቱን ገፍቶበት የበርካቶች ህይወት እየቀጠፈ እንደሆነ ገልጾአል፡፡
መግለጫው ለስርዓቱ አፋኝነት በምሳሌነት ካነሳቸው መካከል በአለፈው ክረምት ወራት ጀምሮ ለተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች የሚሰጠው የግዳጅ ስልጠና የሚገኝበት ሲሆን በስልጠናው ስነ ምግባር በጎደለው መልኩ የጥላቻ ዘመቻ በማካሄድ የሃሳብ ልዩነትን የማስተናገድ ፍላጎቱ ሙሉ ለሙሉ እንደተዳፈነ ያሳየ ነው ብሎታል፡፡ ሰማያዊ ፓርቲ እነዚህን ስልጠናዎች እጅግ በቅርበት ሲከታተላቸው የቆየ መሆኑንና ከጅማሬውም ተቃውሞውን በይፋ መግለጹንም መግለጫው አውስቷል፡፡
ፓርቲው በጋዜጠኞች ላይ የተወሰደው የማሳደድ እርምጃ፣ በነጻው ፕሬስ ላይ የተፈጸመው አፈና የስርዓቱን መበስበስ እና አፋኝ አምባገነንነትን ብቸኛ አማራጭ አድርጎ መቀጠል መምረጡን ግልጽ አመላካች ነው ብሏል፡፡
‹‹እጅግ የከፋውና እየተባባሰ የመጣው ከፍተኛ አደጋ ያዘለ ችግር ያለው አስተዳደራዊ እና ፖለቲካዊ ጥያቄ እያነሱ ያሉ የሕብረተሰብ ክፍሎችን በሀይል ለመግዛት ቆርጦ መነሳቱ ነው›› ያለው መግለጫው በተለይ በኦጋዴን በርካታ ዜጎች በመንግስት ሀይሎች ህይወታቸው መቀጠፉ ሳያንስ ሬሳቸው እንኳን ክብር በሌለው ሁኔታ መሬት ለመሬት እየተጓተተ ባደባባይ ሰብአዊ መብት ሙሉ ለሙሉ መጣሱን አውስቷል፡፡ በተጨማሪም በጋምቤላም የህወሓት ሰዎች መሬት በሕገ-ወጥ መንገድ መቀራመታቸውን የተቃወሙ በርካታ የሰው ህይወት የተቀጠፈበት ሁነት ሀገሪቱ ወደ ከፋ ሁኔታ እያመራች ለመሆኑ አመላካች ነው ሲል ገልጾአል፡፡
ሰማያዊ ፓርቲ ገዥው ፓርቲ በህዝብ ላይ የሚፈጽመውን በደል በቅርበት እየተከታተለ መሆኑን ያስታወቀው መግለጫው ‹‹የሀገሪቱን ወቅታዊ ሁኔታ ከግምት በማስገባት መላው የሀገሪቱ ህዝብ፣ በውጪ የምትኖሩ ኢትዮጵያውያን እና ለሀገር ተቆርቋሪ ተቋማት እንዲሁም በገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ ስር ሆናችሁ ለውጥን የምትሹ ወገኖች ሀገራችንን ወደ አደጋ እየወሰዳት ያለውን አፋኝ ስርዓት በቻላችሁት ሁሉ በመቃወምና ከስርዓቱ ጋር ባለመተባበር በብሔራዊ ደረጃ የሚደረገው ትግል አካል እንድትሆኑ›› ሲል ጥሪ አቅርቧል፡፡