Quantcast
Channel: Ethiopian News | ዘ-ሐበሻ | Latest News Provider | News For All
Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

ለአንዳንድ ጥያቄዎች መልስ (ከፕ/ር መስፍን ወ/ማርያም)

$
0
0

ከፕ/ር መስፍን ወልደ ማርያም

ግንቦት 2005

Pro Mesfinበጽሑፎቹ ላይ የቀረቡት አስተያየቶች በመሠረቱ ሁለት ዓይነት ናቸው፤ አንዳንዶቹ እንደምክር ያለ ነገር፣ አንዳንዶቹ ጽሑፎቹን መውደዳቸውን ወይም አለመውደዳቸውን በመግለጽ ጽፈዋል፤ በነዚህ ላይ ምንም አስተያየት የለኝም፤ መውደድም ሆነ መጥላት፣ መንቀፍም ሆነ ለወደፊት የምሻሻልበትን ምክር መስጠት መብታቸው ነው፤ በግድ እኛ የምንልህን ተቀበል ሲሉኝ ከመብታቸው ያልፋሉ፤ ቢሆንም መልስ አያስፈልጋቸውም።

ሌሎች አስተያየት ሰጪዎች ወደፍሬ-ነገሩ ውስጥ ገብተው ለመሞገት ይሞክራሉ፤ ግልጽ የሆነ የሁነት ግድፈት ሲያገኙ ቢያመለክቱኝ በደስታና በምስጋና እቀበላቸዋለሁ፤ ሁነቱ ለእነሱ በሚጥም መንገድ ባለመገለጹ ወይም ሁነቱን እነሱ የሚወዱት ባለመሆኑ ሙግት ውስጥ የሚገቡ ሲሆን የማይጠቅም መሆኑን ስለተረዳሁ አንድ ዘዴ አቀረብሁ፤ ሁነቱ እኔ ከገለጽሁት ውጭ ሆኖ ከተገኘ አምስት መቶ ብር እከፍላለሁ ብዬ ጻፍሁ፤ እስከዛሬ ብሩን የጠየቀኝ የለም፤ ሊሞግተኝ የሞከረውም አዋቂ ነኝ-ባይ ከዝምታ አልወጣም፤ ፍሬ-ነገሩ ሙግት የሚያቀርቡ ሰዎች ሁለት ዓይነት ይመስሉኛል፤ በቅን መንፈስ በውይይቱ ላይ አስተዋጽኦ ለማድረግ የሚፈልጉ አሉ፤ ሌሎች ደግሞ ሌላ ሰው ሲጽፍ እየጠበቁ ‹‹እኛ የተሻለ አለን›› እያሉ የሚጮሁ አሉ፤ ዓላማቸው ውይይቱን ለማዳበር ሳይሆን ራሳቸውን አብጧል ከሚሉት ሰው እኩል ማሳበጥ ቢቻልም መብለጥ ነው፤ በራሳቸውም ሆነ በሀሳባቸው እምነት ስለሌላቸው የሚናገሩት ራሳቸውን በመቃብር ውስጥ ከትተው ነው፤ በመቃብር ቤት ውስጥ ማበጥ ለምስጦች እንደሆን እንጂ ለሌሎች ‹‹የጭቃ እሾህ›› የሚል ስያሜን ከማትረፍ አያልፍም።

በተከታታይ በቀረቡት ጽሑፎች ላይ ሁለት አንባቢዎች በተቸገሩባቸው ሀሳቦች ላይ አስተያየቴን ልስጥ፤ በመጀመሪያ አርበኛና ባንዳ የሚባሉትን ቃላት የማይወዳቸው አንባቢ ችግሩ አልገባኝም፤ ስገምተው ከቅን መንፈስና ከኢትዮጵያዊ ይሉኝታ ጋር የተያያዘ ይመስለኛል፤ አርበኞችና ባንዶች መኖራቸውን የካደ አይመስለኝም፤ አርበኞች ነበሩ፤ አሁንም አሉ፤ ባንዶችም ነበሩ፤ አሁንም አሉ፤ አርበኛም የለም፤ ባንዳም የለም ለማለት አልችልም፤ ባንዳነት ሲነሣ ኅሊናቸውን የሚቆረቁራቸውና የሚያፍሩ ባንዳዎችና የባንዳ ልጆች ከአሉ፣ ይቆርቁራቸው፤ ይፈሩ፤ የሚያሳፍር ሥራ ውጤት ነው፤ አርበኝነት ሲነሣ ልባቸው የሚያብጥና የሚኮሩ ካሉ፣ ይበጡ፤ ይኩሩ፤ የሚያኮራ ሥራ ውጤት ነው፤  ምንድን ነው ስሕተቱ? የታሪካችን መክሸፍ አንዱ ምክንያት በይሉኝታ ዓይኖችን ሸፍኖ ፍሬውንና አንክርዳዱን ለመለየት አለመፈለግ ነው፤ (በአሥራ ዘጠኝ መቶ አርባዎቹ አጋማሽ ላይ በጾም ጊዜ በምግብ ቤቶች የሚቀርብ የፍስክ ወጥ ነበረ፤ ሽፍንፍን ይባል ነበር፤ ሳይጾሙ የሚጾሙ መስሎ ለመታየት፤) እንክርዳዱንና ፍሬውን እኩል አድርጎ ለማየትና ለማሳየት መፈለግ ነው፤ የኢትዮጵያ አርበኞች ታሪክ ተዳፍኖ የቀረው በአጼ ኃይለ ሥላሴ መንግሥት ውስጥ ባንዶች ተሰግስገውበት ስለነበረ ነው፤ በዚህም ምክንያት ፍሬና እንክርዳዱ ሳይለይ አንዱ ትውልድ ለሚቀጥለው ትውልድ እያስተላለፈ መማርና መሻሻል ያቅተናል፤ አንባቢው ይህንን ይመኛል ብዬ አልገምትም፤ እውነትን የሚገፋ፣ እውነትን የሚያደበዝዝ፣ እውነትን የሚያጨልም ነገር ሁሉ በአገርም ሆነ በግለሰብ ደረጃ መጨረሻው ገደል ነው።

ሁለተኛው ምንም አንኳን በጎ ፈቃድ ከሌለው ሰው የተሰነዘረ ቢሆንም ሌሎችን ሰዎች ሆን ተብሎ ከሚረጨው መርዝ ለመጠበቅ ባጭሩ በአንድ ሀሳብ ላይ ብቻ የሰውዬውን ጤናማ ያልሆነ ዓላማ ላሳይለት፤— እኔ የሚከተለውን ጻፍሁ፤–

የኢሳት መክሸፍ የኢትዮጵያውያንን ተስፋ ያጨልማል፤ አንፈራጥጠው ከላይ ቤት እታች ቤት እየቀላወጡአካላቸውን፣ አእምሮአቸውንና መንፈሳቸውን የሚያባልጉ ሰዎችን ያበራክታል፤ የድብቅብቆሽ ዓለምን እየፈጠሩየጠራውን ከደፈረሰው፣ የጸዳውን ከአደፈው፣ ሳይለዩ ለሚያወሩት ደካሞች ሜዳውን ያሰፋላቸዋል፤የወያኔ/ኢሕአዴግን ፍርሃት ወደመርበድበድ ይለውጠዋል፤ የጦርነት ጥሩምባ ለሚነፉትም ሜዳውን እያሳየ  የቀረርቶበር ይከፍትላቸዋል፤ ይህ ሁሉ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ሰላምንና ስምምነትን፣ እድገትንና ብልጽግናን፣ ኩራትንና ክብርንአያስገኝም።

በነዚህ አምስት መስመሮች ላይ የሰፈረው ሀሳብ አስቸጋሪ አይደለም፤ ማንበብና መጻፍ እችላለሁ ለሚል ሰው ቀላል ነው፤ ዋናውና መሪው ሀሳብ የኢሳት መክሸፍ የኢትዮጵያውያንን ተስፋ ያጨልማል፤ የሚለው ነው፤ አራት የሚሆኑ አጫፋሪ ሀሳቦች ተከታትለው ቀርበዋል፤ የኔን ጽሑፍ ሲያነብ አንጎሉ እያጠናገረ የሚመዘግብለት ሰው ሲጽፍም አንጎሉ አጠናግሮ የመዘገበለትን ስለሚያቀርብለት የተወላገደ መደምደሚያ ላይ ይደርስና ያንኑ ለሌሎች አዋቂ መስሎ ያስተላልፋል፤ ላንዳንዶች ሰዎች ይህ አገላለጼ የከረረ ይመስላቸው ይሆናል፤ በአውነት ይህ አገላለጽ ከበጎ መንፈስ የመነጨ ነው፤ በጎ መንፈስ የሌለበት አገላለጽ ብመርጥ የበለጠ የሚያስከፋ ይሆን ነበር፤ የእውነት ውበት የሚታየው ጨለማውን ሲገልጠው ነው፤ አንዱ አስተያየት ሰጪ እንዳለው ‹‹የጭቃ እሾሁን›› ማየት መቻል ነው፤ እንግዲህ ከላይ የተጻፈውን ሰውዬው እንዴት አወላግዶ እንደተገነዘበውና እንዴት አወላግዶ እንዳወጣው እዩት፤ –

“የኢሳት መክሸፍ የኢትዮጵያውያንን ተስፋ ያጨልማል፤ ………………………………የጦርነት ጥሩምባ ለሚነፉትም ሜዳውን እያሳየ የቀረርቶ በር ይከፍትላቸዋል፤ ይህ ሁሉ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ሰላምንና ስምምነትን፣ እድገትንና ብልጽግናን፣ ኩራትንና ክብርን አያስገኝም። ”እኔም ‹ለሃገራችን ችግር መፍትሄው አንድ መንገድ (የእርሶ መንገድ) ብቻ አይደለም› ያልኩት ኢሳት ነጻ ሚዲያ እንዲሆን የምንሻ ከሆነ ከመርህ አኳያ ሁሉንም በእኩል መድረክ መስጠት እንዳለበት ለመግለጽ ፈልጌ ነው፡፡ ከተሳሳትኩ ለመታረም ዝግጁ ነኝ።››

እግዚአብሔር ያሳያችሁ! ከላይ በትክክል የጠቀስሁትና ይህ ተቆራርጦና ተወላግዶ የቀረበው አንድ ናቸው? እኔ ከጻፍሁትስ እንዴት ብሎ ከውልግድግዱ የተሰጠው መደምደሚያ ሊወጣ ይችላል? ‹‹የጭቃ እሾህ›› ለምን ይጠቅማል? ለማን ይጠቅማል? በዚህ ጽሑፍ ውስጥ ለኢትዮጵያ ችግር መፍትሔው አንድ መንገድ ብቻ ነው (የኔ ብቻ) ያልሁት የት ነው? ተከታታይ ጽሑፎቹን ሁሉ ያነበበ ሁሉ የተለያዩ አመለካከቶች በእኩልነት ይስተናገዱ የሚል እንደሆነ ከዚህ ሰው በቀር የተረዳው ይመስለኛል።

‹‹ከተሳሳትሁ ለመታረም ዝግጁ ነኝ›› የምትለዋ አስቂኝ ነች!  የተሞከረው ማታለል አልሠራ ሲል ወደሌላ ማታለል! አውቆ የተኛ ቢቀሰቅሱት መች ይሰማል!


Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>