(ዘ-ሐበሻ) አዲስ አበባ የሚገኘው ሲኖዶስ በዛሬው የ5ኛ ቀን ጉባኤው የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ሥራ አስኪያጅን እና የቅዱስ ሲኖዶሱን ዋናጸሐፊዎች ምርጫ አካሄደ።
ሲኖዶሱ በዛሬው የ5ኛ ቀን ጉባኤው ከዚህ ቀደም ለ3 ዓመታት አቡነ ሕዝቅኤል ይዘውት የነበረውን ሥልጣን የሰቲት ሁመራው ሀ/ስብከት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ሉቃስ ተክተው እንዲሰሩ እንደመረጣቸው የዘ-ሐበሻ ምንጮች አረጋግጠዋል። በሌላ በኩልም አቡነ ፊሊጶስ ይዘውት የነበረውን መንበረ ፓትርያሪክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅነቱን ሥልጣን ደግሞ የወላይታ ዳውሮ ሀ/ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ማቴዎስ እንዲይዙት መርጧል።
አቡነ ማቴዎስ ለ6ኛው የፓትርያርክነት ተወዳድረው ‘ተሸንፈዋል’ በሚል ቢነገርም መንግስት አቡነ ማትያስን ከ እየሩሳሌም አምጥቶ መሾሙን የሚያምኑ አስተያየት ሰጪዎች አቡነ ማቴዎስ በምርጫ ተሸንፈዋል ብለው እንደማያምኑ በተለያየ አጋጣሚ አስተያየታቸውን መስጠታቸው ይታወሳል።
ለፓትርያርክነት ምርጫ ተወዳድረው እንደነበር የሚታወሱት አቡነ ሉቃስ ጋራ ለቅ/ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊነት በዕጩነት የቀረቡት ጳጳሳት አቡነ ሔኖክ እና አቡነ ዲዮስቆሮስ መሆናቸውን የሚናገሩት የዘ-ሐበሻ ምንጮች አቡነ ሉቃስ ከፍተኛ ድምፅ አግኝተው በመመረጣቸው ለቀጣዩ ሦስት ዓመታት ቅ/ሲኖዶሱን በዋና ጸሐፊነት እንዲያገለግሉ መመረጣቸውን አስታወዋል።
አቡነ ማቴዎስ የተወለዱት ምንጃር፣ አቡነ ሉቃስ ደግሞ ትግራይ ተምቤን የተወለዱ አባቶች ናቸው።
እየተካሄደ ባለው የአዲስ አበባው ሲኖዶስ ጉባኤ ላይ አስተያየት እንዲሰጡን የጠየቅናቸው አንድ የሃይማኖት አባት “ሲኖዶሱ ከዚህ ቀደም የትግራይ አርቲስቶች በመኪና አደጋ ሲሞቱ ታቦት ተሸክመው በመሄድ ለአርቲስቶቹ ፍትሃት እንዳደረጉት ሁሉ፤ በባህርዳር ከተማ ይህ ሁሉ ሰው በጥይትና በተፈጥሮ አደጋ ሲሞት ተመሳሳይ ነገር አልተደረገም። ይልቁንም አንዳችም መግለጫ አለማውጣቱና አለመወያየቱ፤ የዋልድባ ጉዳይን አልማንሳቱ በጣም የሚያስተዛዝብ ነው” ብለውናል። እኚሁ አባት ጨምረውም “አዲስ አበባ ያሉት አባቶች ስለሙስና ትኩረት ሰጥተው መወያየታቸው የሚያሳየው ቤተክርስቲያን ምን ያህል እየተመዘበረች እንዳለች ነው። አሁንም እነዚህ አባቶች በሙስና ጉዳይ ላይ የሚነጋገሩት እከሌ ከኔ የተሻለ ሰርቋልና እኔም እንዴት ልሰርቅ እችላለሁ በሚል ነው እንጂ እውነት ሙስናን ከቤተክርስቲያኒቱ ለማጠፋት ቁርጠኝነት ኖሮ አይደለም” ሲሉ አሰታየታቸውን አጠናቀዋል።