የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለመኖሪያ ቤት ግንባታ ደካማ የሥራ አፈጻጸም ከፍተኛ አስተዋጽኦ አላቸው ያላቸውን ጠጠር አምራቾች አስጠነቀቀ፡፡ አስተዳደሩ ጠጠር አምራቾቹ በሕጋዊ መንገድ ሥራቸውን የማያካሂዱ ከሆነ ዕርምጃ እወስዳለሁ ብሏል፡፡
አስተዳደሩ ይህንን ማስጠንቀቂያ የሰጠው በጠጠር አቅርቦት ላይ የተከሰቱ ችግሮችን ለመፍታት፣ ጥቅምት 11 ቀን 2007 ዓ.ም. በጠራው ስብሰባ ላይ ነው፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ አቶ አባተ ስጦታው በስብሰባው ላይ እንዳሉት፣ በጠጠር አቅርቦት ላይ እየተፈጠሩ ባሉ ችግሮች እጃቸው ያለበት አካላት ወደ ሕጋዊ መስመር መግባት አለባቸው፡፡ አቶ አባተ አስተዳደሩ የማጣራት ሥራ ሠርቶ አፋጣኝ ዕርምጃ እንደሚወስድ አስገንዝበው፣ በዚህ ተግባር የተሰማሩ የአስተዳደሩም ሆነ አቅራቢ ኩባንያዎች ወደ ሕጋዊ መስመር እንዲገቡ አሳስበዋል፡፡
‹‹በእኛ ሠራተኞች ጭምር ማጭበርበርና ሌብነት አለ›› በማለት አቶ አባተ የጉዳዩን አደገኝነት አስታውቀዋል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር 200 ኩባንያዎች የማዕድን ፈቃድ በማውጣት 370 ሔክታር መሬት ለጠጠር ማምረቻ ወስደዋል፡፡ አስተዳደሩ ለእነዚህ ኩባንያዎች በቂ መሬትና የኮንስትራክሽን ማሽኖችን ጨምሮ ለተለያዩ ሥራዎች ብድር አመቻችቶ መስጠቱን ገልጿል፡፡
አስተዳደሩ እነዚህን ድጋፎች ለአምራቾቹ ያቀረበው በከተማው እየተካሄዱ ላሉት ሦስት የመኖሪያ ቤት ፕሮግራሞች የሚያስፈልገውን ጠጠር ለማግኘት መሆኑን ገልጾ፣ ነገር ግን ይህ ዕቅድ በሕገወጦች ምክንያት እየተስተጓጎለ መሆኑን አስረድቷል፡፡
ስብሰባውን የመሩት አቶ አባተ እንደገለጹት፣ ከእነዚህ ኩባንያዎች ውስጥ አብዛኛዎቹ የወሰዱትን የማምረቻ ቦታ ለሦስተኛ ወገን አሳልፈው ሰጥተዋል፡፡ አምራቾቹ ለቤቶች ግንባታ ጠጠር ማቅረብ ሲገባቸው ለሌሎች ፕሮጀክቶች ቅድሚያ እንደሰጡና ‹‹በተለይም ሰው ሠራሽ ዋጋ በመፍጠር የዋጋ ንረት እንዲከሰት አድርገዋል፤›› ሲሉ ወቅሰዋል፡፡
በዘርፉ ወደ ሦስተኛ ወገን ማስተላለፍ፣ ከወሰዱበት ዓላማ ውጪ ለሆነ ተግባር ማዋል አስተዳደሩ ያነሳቸው ችግሮች ሲሆኑ፣ ከተሰብሳቢዎች ውስጥ ‹‹መሬትን ከነግዳጁ ለሦስተኛ ወገን ማስተላለፍ ችግሩ ምንድነው?›› የሚል ጥያቄ ቀርቧል፡፡
አቶ አባተ እንዳሉት መሬት እየያዙ ወደ ሦስተኛ ወገን ማስተላለፍ በፍፁም አይቻልም፡፡ ‹‹እኛ የምንፈልገው ኪራይ ሰብሳቢ ሳይሆን ልማታዊ ባለሀብት ነው፤›› በማለት ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ የአስተዳደሩ መሥሪያ ቤቶች በመቀናጀት የወሰዱትን መሬት ላልተገባ ተግባር ያዋሉ አምራቾች ላይ ዕርምጃ እንዲወሰዱ አቶ አባተ መመርያ ሰጥተዋል፡፡
በተሰብሳቢዎቹ ሥራቸውን ለማካሄድ የመሠረተ ልማት አለመሟላት ችግር እንደሆነ ተነስቷል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም አስተዳደሩ ግዥ የሚፈጽምበት ዋጋ ከማምረቻ ዋጋ ንረት ጋር እንደማይገናኝ የሚጠቅሱም አሉ፡፡ ይህንን የዋጋ ንረት ለመቀነስ የትራንስፖርት ሥራ ውስጥ ለመግባት እንዲፈቀድላቸው ጥያቄ አቅርበዋል፡፡ የመሠረተ ልማት ችግሮች ተብለው ከቀረቡት ውስጥ የመንገድ አውታር፣ የኤሌክትሪክና የውኃ መስመር አለመኖር ተጠቅሰዋል፡፡
በተለይ በኤሌክትሪክ በኩል ያለው ችግር ጎልቶ የወጣ ሲሆን፣ ባለሀብቶቹ ከሁለት ዓመት በፊት ክፍያ ፈጽመው የኤሌክትሪክ ኃይል ይለቀቃል ብለው ቢጠብቁም አለመለቀቁን ተናግረዋል፡፡
አስተዳደሩ በኤሌክትሪክ ኃይል በኩል ያለውን ችግር ለመፍታት ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ጋር እየሠራ መሆኑን ጠቅሶ፣ ውኃና መንገድ ግን በተቻለ መጠን ባለሀብቶቹ ራሳቸው መሥራት እንደሚኖርባቸው አስገንዝቧል፡፡
የአዲስ አበባ አስተዳደር በተያዘው የበጀት ዓመት 125 ሺሕ ቤቶችን እየገነባ መሆኑን ገልጾ፣ ለእነዚህ ግንባታዎች 1.3 ሚሊዮን ሜትር ኩብ ጠጠር እንደሚያስፈልግ አስታውቋል፡፡
ባለሀብቶቹ ይህንን ጠጠር ማቅረብ የማይችሉበት አሠራር ከቀጠለ፣ የራሱን ማሽኖች በመግዛት ወደ ሥራ ሊገባ እንደሚችል አስተዳደሩ ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል፡፡ የአዲስ አበባ ኮንስትራክሽንና ቤቶች ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ጌታቸው ኃይለ ማርያም እንደገለጹት፣ አስተዳደሩ ወደ ጠጠር ምርት የሚገባው የባለሀብቶች የሥራ አፈጻጸም ደካማ ከሆነ ብቻ ነው፡፡
Source:: Ethiopian Reporter