የጋራ ንቅናቄ መድረክ
የጅማሬው መሠረት ስለ ሌላው መነጋገር ሳይሆን እርስበርሳችን መወያየት ነው!
ቀኑ፤ ቅዳሜ ኅዳር 6 ቀን 2007ዓም / November 15, 2014
ሰዓቱ፤ 10:00 AM እስከ 7:00 PM – ውይይቱ በሁለት የተከፈለ ነው
ቦታ፤ Sheraton Pentagon City Hotel,
900 S Orme St., Arlington, VA
አገራችን ካለችበት ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታ አንጻር በዓለምአቀፍ መድረክ ያላት ተፈላጊነት የሚካድ አይደለም፡፡ ይህም በራሱ የኢትዮጵያን ተፈጥሮ ሃብት ለመጠቀም ከመፈለግ አኳያ የፖለቲካ ገመድ ጉተታ መፍጠሩ አይካድም፡፡ በዚህ ውስጥ የሚሳተፉት ክፍሎች የሕዝብን ድምጽ ችላ በማለት ጭቆናው እንዲበረታ በማድረጋቸው በኢትዮጵያ ተጻራሪ ኃይላት ጽንፍ እንዲይዙ አድርጓቸዋል፡፡
በእነዚህ ኃይላትና ተባባሪዎቻቸው የሚቀርበው ሥዕላዊ መግለጫ የኢኮኖሚ ብልጽግናው ባስደናቂ ሁኔታ እያደገ መሄዱ ሲሆን በተግባር የሚታየውና ከሕዝቡ የሚሰማው ደግሞ ከዚህ በተቃራኒ መልኩ እንደሆነ፣ ስደተኞች አሁንም አገር ጥለው እንደሚሄዱ፣ በአገር ውስጥ ኑሮን ለማሸነፍ ያቃታቸው ቤተሰቦች በውጭ ባሉቱ በሚልኩላቸው እየተደገፉ እንደሆነ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም እኤአ ከ2000 እስከ 2009ዓም ባሉት ዓመታት ከአገር ውስጥ በህገወጥ መንገድ እያፈተለከ የወጣው ሃብት 11.7ቢሊዮን ዶላር እንደሆነ መረጃዎች ሲጠቁሙ እኤአ በ2009ዓም ብቻ አኻዙ 3.6ቢሊዮን ዶላር እንደነበር ተገልጾዋል፤ የኪሳራው ቁጥር እያሻቀበ እንጂ እየቀነሰ አልመጣም፡፡
የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች በበርካታ ቦታዎች የሰብዓዊ መብቶች ረገጣ እንደሚካሄድና ዜጎች ከቤትና መሬታቸው በግዳጅ እየተፈናቀሉ ለመኖሪያ አልባነት መዳረጋቸውን ይዘግባሉ፡፡ የነጻነትና የእውነት ድምጾች በጸረ አሸባሪነት ሕግ እየተመካኘባቸውና “አሸባሪ” እየተባሉ በእስር ቤቶች እየማቀቁ ነው፡፡ ከዚህም ባሻገር ነጻነትን፣ ፍትሕንና ሰላማዊ ኑሮን በሚያሳዩ መለኪያዎች መሠረት ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ብቻ ሳይሆን ከዓለምም በመጨረሻዎቹ ደረጃ ላይ የምትገኝ አገር ሆናለች፡፡
የመያዶች ሕግ ተብሎ የተደነገገው፤ ነጻ ድምጽ እንዳይኖር በማድረግ ተቋማትን አሽመድምዷል፤ አስወግዷል፤ እንዳይኖሩ አድርጓል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በሥልጣን ላይ ያለው አገዛዝ የሕዝብና የግል ተቋማትን በቁጥጥሩ ሥር በማድረግ የራሱን ዓላማ ለማራመድ ወይም እንዳስፈላጊነቱ ተቃዋሚዎቹን ለማፈን የሚጠቀምበት መሣሪያ አድርጎታል፡፡ ፓርላማው፣ የፍትሕ አሠራሩ፣ ጦር ሠራዊቱ፣ የደኅንነት ኃይሉ፣ ሚዲያው፣ የገንዘብና ፋይናንስ ተቋማቱ፣ ቴሌኮሙኒኬሽን፣ የሃይማኖት ድርጅቶች፣ እንዲሁም የትምህርት፣ የኢኮኖሚና ሌሎች ተቋማት በሙሉ በቁጥጥሩ ሥር ውለዋል፡፡
እነዚህ ከላይ የተገለጹት ሁሉ መረን ከለቀቀ ሙስና እና በእርዳታ ከውጭ የሚመጣውን ገንዘብ ከማባከን ጋር ተዳምረው ችግሩን እጅግ አብሰውታል፡፡ የአገዛዙ ልዩ ምልክት የሆነው የዘር እና የሃይማኖት ቁርቋሶ ሌሎችን ከሰብዓዊነት ተራ ውጪ እንዲሆኑ አድርጓል፡፡ በሥልጣን ላይ ያለው የአናሳዎች ቡድን መግዛት ለመቀጠል እንዲያስችለው የከፋፍለህ አሸንፍ ፖሊሲውን አጠናክሮ በመቀጠሉ ኢትዮጵያውያን በአሁኑ ጊዜ እርስበርሳቸው እንደ ጠላት የሚተያዩና የሚናቆሩ ሆነዋል፡፡ በመሆኑም ሃይማኖትን ወይም ዘርን መሠረት ያደረገ ግጭት በኢትዮጵያ ውስጥ ለመፈንዳት ጊዜውን እየቆጠረ እንዳለ ቦምብ መሆኑን ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡ ካሁኑ እርምጃ ሳይወሰድ ቀርቶ ይህ ከተከሰተ በሩዋንዳ፣ በዩጎዝላቪያ፣ ወይም በደቡብ ሱዳን የሆነውን ዓይነት ዓመጽ፣ ግድያና ሁከት ይከሰታል የሚለውን አስተያየት ይሰጣሉ፡፡
በአሁኑ ጊዜ ኢትዮጵያውያን እነዚህ ሁሉ አደጋዎች ያንዣበቡባቸው መሆኑን ቢረዱም ስለ መፍትሔው እርስ በርስ ከመነጋገር ይልቅ ስለሌላው መናገርና ማውራት የብዙዎች ቀዳሚው ተግባር ሆኗል፡፡ በመሆኑም “እያንዳንዱ ተራ ኢትዮጵያዊ ጥላቻ የረገበበትና ሰላማዊ ኢትዮጵያ መፍጠር የሚችለው እንዴት ነው?” የሚለው መጠየቅ ያለበት የወቅቱ ጥያቄ ሆኗል፡፡ በተለያዩ ኢትዮጵያውያን መካከል ዘንድ መተማመን ለመፍጠር የአንድ ለአንድ/የሕዝብ ከሕዝብ ውይይትና ምክክር የዚህ ስብሰባ ዋንኛ ዓላማ ነው፡፡
በዕለቱ በሚደረገው ስብሰባ የመጀመሪያው ክፍል “በኢትዮጵያ ያሉት ተቋማት እንዴት እንደመከኑ” ከኢትዮጵያውያን ከሌሎች ባለሙያዎች ማብራሪያ የሚሰጥበት ነው፡፡ ይህም የሚያተኩረው አገዛዙ የዕርዳታ ገንዘብ እንዴት ለራሱ ጥቅም እያዋለ እንደሆነ፣ የመረጃ ፍሰቱን እንዴት በቁጥጥሩ ሥር እንዳደረገ፣ የድርብ አኻዝ የኢኮኖሚ ዕድገት ተመዝግቧል እያለ እንዴት በቁጥር ጨዋታ እንደሚያምታታ፣ መረን የለቀቀው ሙስና በነጻነት፣ ሰብዓዊ መብቶች እና ዕድገት ላይ እያደረሰ ያለው ቀውስ ምን እንደሚመስል ዝርዝር ማብራሪያ ይደረጋል፡፡
በሁለተኛው ክፍለጊዜ “በልዩነታችን በመከባበር አዲሲቷን ኢትዮጵያ ለመገንባት” በሚል ውይይት የሚደረግበት ይሆናል፡፡ በዚህ የውይይት ሰዓት ከተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች፣ ሃይማኖት፣ ጾታ፣ … የመጡና ሌሎች ባለሙያዎች ስለ ዕርቅ፣ ትርጉም ያለው ተሃድሶ፣ እንዲሁም ፍትሕ ዙሪያ ሃሳባቸውን የሚያቀርቡበትና ተግባራዊነቱን በተመለከተ ተሰብሳቢው ግልጽ ውይይት የሚያደርግበት ይሆናል፡፡ ደካማ ተቋማት የመኖራቸው ሁኔታ አሁን ያለው አገዛዝ የጀመረው ጉዳይ አይደለም፤ በታሪካችን ሥር የሰደደ ነው፤ ይህንን ተጠቅሞ አገዛዙ የበለጠውን ውድመት አስከትሏል፤ ተቋማቱን ለራሱ መጠቀሚያ አድርጓቸዋል፤ የሽምግልና ጉባዔ የመሳሰሉትን ቅድስናቸውን አርክሷል፡፡ ስለዚህ ሁላችን እንደ ግለሰብና በአንድነት ደግሞ እንደ ሕዝብ አለመግባባትን አስወግደን ጠንካራ ተቋማት መገንባት ካልቻልን ይህ አገዛዝ ከሥልጣን ቢወርድ እንኳን የናፈቅነውን ለውጥና ነጻነት ለማየት አንችልም፡፡ አለመግባባትን ሰብረን ጠንካራ ተቋማትን የምንገነባበት ወቅት አሁን ነው!
ስለዚህ እንገናኝና እንወያይ! አዲሲቷን ኢትዮጵያ ለመመሥረት የሚያስችሉ ተቋማት እንገንባ!
በቀጣይ በሚወጣው ማስታወቂያ አወያዮቹ ይገለጻሉ፤ ይህ ስብሰባ ለሕዝብ ክፍት ሲሆን ስፖንሰር ለማድረግም ሆነ ለሌሎች ጥያቄዎችና ጉዳዮች ማነጋገር ለሚፈልጉ ሁሉ ኦባንግ ሜቶን በዚህ ኢሜይል ማግኘት ይችላሉ፡- obang@solidaritymovement.org