ኤርምያስ ለገሠና ሲሳይ አጌና የሰሞኑን የወያኔ ጭንቅ-ወለድ ሥልጠና ተብዬ በተመለከተ ሲወያዩ በኢሳት ተከታተልኩና ይህችን ጦማር መጦመር ፈለግሁ፡፡ ጊዜው የተግባር እንጂ የጦማር መጦመሪያ እንዳልሆነ ብረዳም ለጊዜው ያለኝ ብቸኛ ምርጫ ይሄው ነውና – መጻፍ ሰልችቶኝ እየተንገፈገፍኩም ቢሆን – ትንሽ ልተንፍስ ፤ ብፈነዳስ?
በነሲሳይ አጭር ውይይት ወያኔ ለተማሪዎችና ለዩንቨርስቲ መምህራን በሥልጠና “ማንዋልነት” ያቀረባቸው ጽሑፎች ሦስት መሆናቸው ተጠቅሷል፡፡ ከሦስቱ አንዱን ተሣታፊ ጓደኛ ሰጥቶኝ እኔም አንብቤዋለሁ፡፡ ከጽሑፉ የተረዳሁት አዲስ ነገር የለም – ያው እንደወትሮው ሁሉ የወያኔን ማበድና ከድርጅትነትም ከሰውነትም ተራ መውጣት ነው የተገነዘብኩት፡፡ ይሁንና ቢያብዱም ቢሠክሩም ገፍቶ የሚጥላቸውና ከገቡበት አረንቋ የሚገላግላቸው ኃይል እስካላገኙ ድረስ እንደዚሁ እየተጃጃሉ ዓመት ዓልፎ ዓመት ይተካል፡፡ የዲያስፖራ መንጫጫት፣ የኢሳት በዜናና ሀተታዎቹ የወያኔን ገመና ራቁት ማውጣት፣ ሥርዓቱን የሚከዱ ወገኖች ወያኔን በየጊዜው ማጋለጥ፣ … በሌላ በኩልም የሕዝቡ መረገጥና የሀገሪቱ መቀመቅ መውረድ ካለአንዳች ሃይ ባይ ይቀጥላል፡፡ ቢያድለንና ፈጣ ፊቱን ቢመልስልን አሁን ጊዜው የወሬና የሀተታ መሆን አልነበረበትም፡፡ ወያኔዎች ይህን ነገራችንን ከመጠን በላይ ይወዱታል፤ ህዝቡ በዚህ የወሬና ሀተታ ቱማታ ተዘናግቶ “እሰይ፣ ችግሬን አፍረጥረጠው ነገሩልኝ! ልክ ልካቸውን ነገሯቸው” እያለ በከንቱ ሲጽናና ዋናው የነፃነት ቁም ነገር ግን ወደጎን እየተገፋ ጊዜው ይነጉዳል፡፡ የዛሬ ሃያ ሦስት ዓመት ስለወያኔ ክፋት እንጽፍና እንናገር ነበር፤ ከዚያን ጊዜ በፊትና በኋላም ከመጻፍና ከማጋለጥ ዐላረፍንም፤ ምናልባትም ይህ የጨለማ ዘመን እስኪቋጭ አናርፍም፡፡ በሌላ አቅጣጫ ግን ወደተግባር የሚገባ አካል ሊኖረን ይገባል፡፡ የፉከራና የዛቻ ወሬ ወደተግባር ካልተለወጠና ውጤታማ የኃይል አጀብ ካልደገፈው ነገረ ሥራችን ሁሉ የእምቧይ ካብ እየሆነ (እንደሆነ) ይቀጥላል፤ ወያኔ የሚፈልገውም ይህንኑ ነው፡፡ እንጂ እንደውነቱማ ወያኔ በተለይ በአሁኑ ሰዓት እፍ ቢሉት በሴከንዶች አፈር ዱቄት የሚሆን በጅማቱ ብቻ የሚኖር የሀገርና ሕዝብ ነቀርሣ ሆኗል፡፡
ወያኔ ለአፉም ሆነ ለብዕሩ ለከት የለውም – ለዕኩይ ምግባሩም እንዲሁ፡፡ ስለወያኔ ማንነት መናገር አሁን አሁን ጅልነት እየመሰለኝ መጥቷል፡፡ የማያውቀው ያለ ይመስል ስለወያኔ ማንነትና ምንነት ስንጮህ ብዙ ዘመን ባጀን፡፡ እኔም የራሴን ጩኸት ደግሜ ስሰማው ራሴን እንደሞኝ እቆጥርና “ወይ ምርጫ ማጣት!” በማለት ፈገግ እሰኛለሁ፡፡ ግን ሞኝነቴ ደግሞ አያርመኝም፡፡ እናገራለሁ፤ እጽፍማለሁ፡፡ እንዲህ እንዲህ እያጃጃሉ ያነሆልሉናል – እነሱም ሰው ሆነው፡፡
በሰሞኑ የወያኔ ስብከት “በመንግሥት ሥልጣን ላይ ተቀምጦ በትምክህትና በጠባብነት ሀገርን የሚያተራምስ ኃይል የለም” የሚል ግልጽ ቅኔ አንብቤያለሁ፤ ደጋግሜም ሰምቻለሁ፡፡ ምናልባት ይህ አባባላቸው የማይገባው ዜጋ ካለ በዚህ ላይ ትንሽ ማለት ያስፈልጋል፡፡ “ሠራዊቱን ለማመጣጠንም ብዙ ርቀት ተጉዘን ሌላውን ዘውግ እስከሻለቃ ደረጃ አድርሰናል” የሚል ወያኔያዊ ወደር-የለሽ የቸርነት ዜናም ራሱ ወያኔ እንዳሰራጨም ከኤርምያስ ሰምቻለሁ፡፡ ስላሰቡልን እግዜር ያስባቸው፡፡ ማዕረጉ የለበጣና በብሔር ተዋፅዖ ስም ሞኞቾችን የማታለያ መሆኑ ግልጽ ቢሆንም ይህንንስ ማን አየበት፡፡
በወያኔ እምነት የትምክህትና የጠባብነት ኃይሎች በሥልጣን ላይ የሉም ሲል አማራንና ኦሮሞን አከርካሪያቸውን ሰባብረን ሥልጣኑን ለሕዝብ አስረክበናል ማለቱ ነው – ሁለቱን ብሔሮች ወያኔ ክፉኛ ይፈራቸዋል – አማራን በተፅዕኖው፣ ኦሮሞን በምልዓቱ፡፡ ከኢትዮጵያ ሕዝብ አጠቃላይ ቁጥር ላይ አማራንና ኦሮሞን ስትቀንሱ የምታገኙት ቁጥር ነው እንግዲህ የወያኔ አዲሲቷ ኢትዮጵያ ቅርጽና ይዘት መሠረት – ይበል ነው፡፡ እነዚህ ወያኔዎች በርግጥም የሚሉትን በተግባር አሳይተዋል፡፡ የወያኔ ሤራ ያልገባቸውና በጠላት ኩንታል ድማሚት ላይ ፊጥ እያሉ በመፈንዳት እንደሳት እራት የሚያልቁት በአብዛኛው የተደገሰላቸውን ያላወቁ ወይም ለማወቅ ያልፈለጉ ሞኛሞኞቹ አማራና ኦሮሞ ናቸው፡፡ ዕድሜ ለሲአይኤና ለሞሣድ ይህ የራሱን ጠባብነት ቅንጣት ሳያፍር በኦሮሞ ላይ የሚለጥፍ ስድአደግ ወያኔ – ይህ የራሱን ዕብሪትና ትምክህት በራሱ በወያኔ በታወጀበት የዘር ማፅዳት ዘመቻ ሳቢያ በፍርሀትና በሰቀቀን እየተሽቆጠቆጠ በሚኖር ምሥኪን የአማራ ብሔር ላይ የሚያላክክ የፍየል ዐይን የበላ ወያኔ – ከታሪካዊ የሀገራችን ጠላቶች ምክርና የገንዘብ ድጋፍ በገፍ በማጋበስ ያሻውን እያደረገ እስካሁን በሕይወት አለ፡፡ (የኤርምያስ ለገሠን “የመለስ ትሩፋቶች” መጽሐፍ ሰሞኑን ሳነብ ማበድ ጥቅም ያለው ይመስል “ጨርቅህን ጣልና ዕበድ፤ ከዚያም ይለፍልህ” የሚል ስሜት ተፈታተነኝ – ‹ለሥራ ያልደረሱ፣ ለምግብ ያላነሱ› ኩታራዎች ባይኖሩኝ ኖሮ ለይቶልኝ ዐብጄ ያን በየቀኑ ሺዎች ኢትዮጵያውያን የሚቀላቀሉትን ነፃ ሕይወት ደግሞ በሞኮርኩት – ሊያውስ በራስ ፈቃድ የሚገኝ ቢሆን አይደል፤ የፈለጉት ነገር እኮ እንዲህ በቀላሉ አይገኝም – ሞትም ቢሆን፡፡ ለነገሩ ይህን ሁሉ ግፍና መከራ እያደረሱብን ያሉት እነሱ አይፈረድባቸውም፡፡ ጥፋተኞቹ በሣሎናችን እያቀማጠልን የያዝናቸው እኛው፣ ተጠያቂዎቹ ባጠመዱልን ወጥመድ ሁሉ ዘው እያልን ለአሰቃቂው አገዛዛቸው የተመቻቸንላቸው እኛው! ለሞተ እህል ተገዝተን ሀገርና ወገን በመክዳት ከጠላት ጋር አብረን ወንድምና እህቶቻችንን የምናሰቃይ እኛው!…)
አማራና ኦሮሞ በአሁኑ ወቅት ምንም ዓይነት ሥልጣን ላይ የሉም፡፡ ታችኛውን ቤተ መንግሥት ጠባቂውንና አምባሳደር ሸኚውን ሙላቱ ተሾመንና ቡልሃውን ደመቀ መኮንንን እንደሰው ቆጥረን እነዚህ ዘውጎች በነዚህ ሰዎች ተወክለዋል ካላልን በስተቀር አንድም አማራና ኦሮሞ ሥልጣን ላይ የለም፡፡ ስለዚህ ወያኔዎች አሁንም ሆነ ወደፊት ያሉት ቢሉ እውነታቸውን ነው፡፡ እንደቤት አሽከር እያላገጡበት ጫትና ሲጋራ የሚያስገዙትን የአማራና ኦሮሞ “ሻለቃ”ና “ኮሎኔል” እንደወካይ ከቆጠርነውም ልክ ነው እነዚህ ብሔሮች “ሥልጣን ይዘዋል፡፡” ቀልዱን ትተን የምሩን እንያዝ ይልቁናስ፡፡
አንድ የሚገርመኝን ነገር ልጥቀስና ላቁም፡፡ በመሠረቱ የጦሩንም ሆነ የሲቪሉን ሥልጣን በአሁኑ ወቅት ሙሉ በሙሉ ትግሬዎች እንደያዙት ሁሉ ይህ አያያዛቸው በብቃትና በችሎታ እንዲሁም ካለአድልዎና ካለማግለል የሚሠሩበት ቢሆኑ ኖሮ በበኩሌ ቅር ባልተሰኘሁ ነበረ፡፡ ችግሩ ይሄ በጣም ክረት እየተሰጠው መጥቶ አንድ መሠረታዊ እውነትን እየደፈጠጠ የመጣ “የብሔር ተዋፅዖ” የሚሉት ፈሊጥ ነው፡፡ ሥልጣን ሲያዝ ከመነሻው በ“ሜሪቶክራሲ” ከሆነ ችግር የለውም፤ በዴሞክራሲያዊ አገባብ ከሆነ አሁንም ችግር የለውም፡፡ ነገር ግን እነዚህን ሁለት ዋና ማኅበረሰብኣዊ የኅልውና አውታሮች አናሟላም ብለው የሚያምኑ ወገኖች በሚከተሉት የጉልበትና የተንኮል ሥልት ብዙ ጉዳት ሲከተል እናያለን፡፡ ሥልጣን በተዋፅዖ ሊያዝ አይገባም የሚል እምነት አለኝ፤ የሚታሰብም አይደለም (በዚህች ሀገር ስንት ፕሬዚደንት፣ ጠ/ሚኒስትር/ ሚኒስትር/ ኮሚሽነር/… ሊኖር? ሞኝነት ይመስለኛል፡፡ ይህን አስጠሊታ መሥፈርት ሰው በመሆን ካላስወገድነው ደምና አጥንት በማነፍነፍ የትም አይደረስም፡፡ ዕውቀቱ ካለው ለምን ዝንጀሮ አገር አይገዛም? እኛን ያስቸገረን ኩራዝ መብራት እንኳን ያላዬ መደዴ ባላገር አዲስ አበባን የመሰለ ዓለም አቀፍ ከተማ እንዲያስተዳድር በደሙ/በዘሩ ምክንያት መሾሙ ነው፡፡…) በትምህርት፣ በልምድ፣ በችሎታ፣ በዜግነትና በብሔራዊ ስሜት፣ ወዘተ. ተመሥርቶ እንጂ እንደወያኔ ሌሎችን ባለማመንና “በስንት የደም መስዋዕትነት የያዝኩት ሥልጣን ይወሰድብኛል” ከሚል ስግብግብነት በመነሣት ሁለተኛ ክፍል በቅጡ ያልጨረሰን ማይም ዜጋ ሁሉ ለትልቅ ሥልጣን ቢያበቁት ውጤቱ አሁን በግልጽ እንደምናየው የሀገር ውድመት ነው፡፡
እኔ የማውቃትን አንዲት ገጠመኝ ብቻ ላስታውስ – ወያኔዎች “ድል አድርገው” አዲስ አበባ ሲገቡ አንድ ፀጋው የሚባል ወያኔ ትግሬ አንድን ትልቅ የደኅንነት ማሠልጠኛ ተቋም በአዛዥነት እንዲያስተዳድር መመደቡን እዚያው ይሠራ የነበረ ጓደኛየ እያዘነ ነግሮኛል፡፡ ይህ ትልቅ የሀገር ንቀት ነው፡፡ በዚያ ተቋም ውስጥ ያገለግሉ የነበሩ መምህራን ከመጀመሪያ ዲግሪ እስከዶክትሬት ዲግሪ ነበራቸው፤ በኋላ እርግጥ ነው የሥርዓቱን ፋሽን ተከትሎ ግቢው የደናቁርት መፈንጫ ከመሆን አልዳነም – እንዴ፣ አንድኛውን የአፍንጫውን ቀዳዳ በሌባ ጣቱ ሰቅጦ ይዞ በኃይል በማናፋት በሌላኛው ቀዳዳ ንፍጡን ምን የመሰለ ምንጣፍ በለበሰ የቢሮው ወለል ላይ በመዘርገፍ ጉዳይ ማስፈጸም ወደቢሮው የገባ እንግዳንም “እንዳያስቀይምበት” እግሩን ከጭኖቹ ፈርከክ አድርጎ በግራ ወይ በቀኝ እግሩ የሚድጥ “ሥልጡን” የወያኔ ሚኒስትርም ነበር እኮ! ኢትዮጵያ እኮ እኮ ከወያኔ በበለጠ ያዋረዳት በታሪኳ ማንም የለም፤ ተዋርደው አዋርደውናል፡፡ ያ ትግሬ ወያኔና ሌሎቹም በየቦታው ከአቅማቸው በላይ የሆነና እንኳንስ አዝዘው ናዘውበት ሰምተውትም በማያውቁት ሥልጣን እየተቀመጡ ሀገር አስተዳደር የዕቃቃ ጨዋታ ይመስል ኢትዮጵያን በመቶዎች ዓመታት ወደኋላ ሊጎትቱ የቻሉት በዘራቸው ታማኝነት እንጂ የተማረ ሰው ጠፍቶ አልነበረም፤ ኢትዮጵያ ጥሩ የአስተዳደር ሰዎችን እንጂ የተማሩ ልጆችን አጥታ አታውቅም – ግን እነዚህኞቹን ታርቃቸዋለች፤ አታስጠጋቸውም፤ ዓለም ተኝቶ ሳለ የማንቂያ የጥሪ ደወል የነበረች አገራችን በተማረ የሰው ኃይል አትታማም፡፡ እነአክሱምና ላሊበላ ይመስክሩ፡፡ ዛሬ እንግዴ ልጆች እየተነሱና አድገውም “ለቁም ነገር” እየበቁ፣ እውነተኛ ልጆች ግን እየተቀበሩ እንዲህ ዓይነት ኪሣራ ውስጥ ተዘፈቅን እንጂ ብዙዎቻችን የምንናፍቀው የነፃነት ጎሕ ሲቀድ ደግሞ ለሁላችን እኩል የሚፈነጥቀውን የብርሃኑን ድምቀት እንደምናይ ጥርጥር የለኝም፡፡ ወላድ በድባብ ትሂድ፤ ከአንዲት እናት ልጆች ውስጥ አንዱ ሰካራም፣ አንዱ ሌባ፣ አንዱ ማጅራት መቺ፣ አንዱ ታማኝ፣ አንዱ ከሃዱ፣ አንዱ ማይም፣ አንዱ ዐዋቂ…. መሆናቸው ዱሮም የነበረ ነው፡፡ ከዘመን ምድብም አንደኛው የኩበት፣ አንደኛው የእንጨት፣ አንደኛው የብረት፣ አንደኛው የብር፣ አንደኛው የወርቅ፤ አንደኛው የተኩላ፣ አንደኛው የእስስት፣ አንደኛው የጅብ አንደኛው የሰሲት፣ አንደኛው የአንበሣ፣ አንደኛው የነብር፣ አንድኛው የፍየል … መሆናቸው የነበረ ነው፤ ይመስለናል እንጂ አዲስ ነገር የለም፤ በትግስት መጠበቅ ነው፡፡ ይህ የእስስቶችና የዓሣሞች ጉፋያ ዘመን እንዲህ እንዳልተንቀባረረብን ተንኮታኩቶ ያልፋል፤ ወደታሪካዊ ሰገባውም ገብቶ ይታሸጋል፡፡ እስኪያልፍ ግን ገና ብዙ እንደሚያለፋን ለብዙዎቻችን ድብቅ አይደለም፡፡
በሀገራችን የምናየው ዓይነቱ ታማኝነትንና ጎሰኝነትን ብቻ ማዕከል ያደረገ የመንግሥት መዋቅር የምናስበውን ያህል በቀላሉ ባይፈርስም በሂደትና በርግጠኝነት ግን በስብሶ መፈራረሱ አይቀርምና ያ ጊዜ ደርሶ ሲፈርስ ጣጣው ብዙና በየትኛውም ዘመን ጎልቶ የሚታይ ታሪካዊ ጠባሳ ትቶ የሚያልፍ መጥፎ ነቀርሣ ነው፡፡ የብዙዎቻችን ፍራቻ ይህ ነው፡፡ ዛሬ ወያኔ ትግሬዎች አለልክ ጠግበውና መሬት ጠባቻቸው የሚያደርጉትን ስናይና በምሥኪን ወገኖቻቸው ላይ እያደረሱት ያሉትን መከራና ስቃይ ስንታዘብ የሁለት አባባሎች ባለቤቶች የሆኑ አንዲት ሰውና አንዲት እንስሳ ትዝ ይሉናል፤ “አይነጋም መስሏት … “ ያለችው ገልቱ ሴትና “እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል” ያለችው አህያ፡፡ አዎ፣ ነገን ማየት አለመቻል ከአህያነትም በዘለለ ድንጋይነት ነው፡፡ ዛሬ መከራ ፍዳውን የሚያሳዩት አንዳርጋቸው ጽጌ ነገ ባለሐውልትና የስመጥር ታሪክ ባለቤት ነው፤ ዛሬ እንደዐይጥ የሚጨፈጭፏቸው ጋዜጠኞችና የሰላማዊ የፖለቲካ አራማጆች ነገ ሀገራዊ የሰማዕትነት ጽላት ተቀርፆላቸው በትውልድ ማነጫነት የሚያገለግሉን የአርዓያሰብ ምኩራቦቻችን ናቸው፡፡ ዛሬ በኢትዮጵያዊነታቸው ምክንያትና የዜግነትና የሰብኣዊነት መብታቸውን በመጠየቃቸው ብቻ ካለፍርድ የሚሰቃዩ፣ የሚታሰሩና ደብዛቸው እንዲጠፋ የሚደረጉ ዜጎች የሀገራችን የነፃነት ምሰሦና ማቶት በመሆናቸው በነገይቱ የነፃነት ጀምበር በተለይ የሚሰውት አፅማቸው የክብር አክሊል የሚቀዳጅ ኢትዮጵያውያን ጳውሎስና ጴጥሮስ ናቸው፡፡… በተቃራኒው ዛሬ ይህችን ሀገር ከላይ አስከታች እያተረማመሱ የሚገኙ ማይማኑ ወያኔዎችና ጀሌዎቻቸው በነገዋ ፀሐይ የጥቁር ታሪክ ባለቤቶችና የመጪው ትውልድ እናቶች “ዋ ማሙሽ! ወያኔን እጠራብሃለሁ!” በሚል የሕጻናት ማስፈራሪያ እንደሚሆኑ የታወቀ ነው፡፡ ተፈጥሮ በጣም ታዳላለች፤ የእነስብሃት ነጋንና ሣሞራ የኑስን አፈጣጠር ከእስክንድር ነጋና በቀለ ገርባ አፈጣጠር ጋር፣ የነልደቱ አያሌውንና ክፍሌ ወዳጆን አፈጣጠር ከነፕሮፌሰር አሥራት ወ/የስና አሰፋ ማሩ አፈጣጠር ጋር … ሳነጻጽረው ተፈጥሮ በርግጥም እንደምታዳላ ቁልጭ ብሎ ይታየኛል፡፡ ምናለ ከአንዳቸው የበዛውን ወደ ሌላኛቸው ቀነስነስ አድርጋ በማካፈል ሁላችን ሰላማዊ ሕይወት እንድንመራ …
ክፉንና ደግን መለየት የሚያስችል አእምሯዊ አቅም ሳይኖራቸው በዚህ በምናየው ወያኔያዊ የዐረመኔነትና የጭካኔ ተግባር የተጠመዱ ወንድሞቼና እህቶቼ – እውነቴን ነው የምለው – በጣም ያሳዝኑኛል፡፡ ተሰብስበው “የሚያዳምጡ” እንቅልፋም ወንድምና እህቶቼን ጨምሮ በፓርላማ ተብዬው ፊት ቀርበው እንዲዋሹ የሚገደዱ የምርና የተጋቦት ወያኔዎች ያሳዝኑኛል፤ በሌሎች ስብሰባዎችም እንደጣቃ እየተተረተሩ አለ አንዳች የሀፍረት ስሜትና አለ አንዳች የፊት ገጽታ መለዋወጥ ሲዋሹ ያሳዝኑኛል – ውሸት የተፈጥሮ ፀጋና ተውህቧቸው እስኪመስል፤ በየዲፕሎማሲ ዘመቻው ሲወሻክቱ ያሳዝኑኛል – በገማ ዕንቁላልና በቲማቲም ሲመቱም ያሳዝኑኛል (ስንት ዓመት ለሚኖሩበትነ ሥልጣንና ሀብት ነው እንዲህ መሰቃየታቸው? ሰው ጠላ እግዜር ጠላ ነውና እነውርደት ቀለቡ በዓለም ዙሪያ እንዲህ ውርደትን ሲከናነቡ በቃን ቢሉስ?)፤ በዕቅዶቻቸው አነዳደፍና አፈጻጸም እንዲሁም በሪፖርቶቻቸው አቀራረብ ያሳዝኑኛል፤ አልፎ አልፎ በትክክል ከሚናገረው የዜና ሰዓት ውጪ ካለውሸት የማይናገረው የሚዲያ ተቋማቸውና ሌሎች ብዙዎች ነገሮቻቸው ሁሉ ያሳዝኑኛል፣ በብዙ ነገራቸው ከሰውነት በታች መሆን በእጅጉ አዝንላቸዋለሁ(እንዴ! ይታያችሁ እስኪ – በርሀብ ጠኔ እያቃሰትኩ የምገኝን ሰው “ጠግበሃል! ቁንጣን ሊገድልህ ነው!” ካለኝ በደደብነቱ እንዴት አላዝንለት? የሌባ ዐይነ ደረቆቹ ልብ-አውልቅ ወያኔዎች እንዲህ ናቸው፡፡)፡፡
እንደኔ ትዝብትና ግንዛቤ ወደዚህ አዘቅት የገቡት እንዲህ ካላደረጉ መኖር አለመቻላቸውን ስለተረዱ ነው፡፡ ለጠላቴም አይስጠው እንጂ እኔም እንዲህ ያለ ቀረቀር ቢገጥመኝ እነሱ የሚያደርጉትን ከማድረግ የምመለስ አይመስለኝም – ቀድሞ አለመለከፍ ነው ወገኖቼ፤ ዐይንን ጨፍነው የገቡበት በወርቅ የተሞላ የዘንዶ ጉድጓድ መውጫው አሣር ነው – አያድርስ፡፡ የኤችአይቪ ቫይረስ በደሙ ያለበትና ወደበሽተኛነት የተለወጠ ታማሚ ዕድሜ ማራዘሚያውን ካልወሰደ እስትንፋሱ ቀጥ እንደምትልበት ሁሉ ወያኔም እንደመካከለኛው ምሥራቅ የአይሲል ቡድን በጭካኔውና በውሸት ጎዳናው ካልተመመ ሌላ የመውጫ በር ያለው አይመስልም – ያሉትን ለክፉ የማይሰጡ በሮች ሁሉ ደግሞ ራሱ ወያኔ ዘጋግቷቸዋል፡፡ ስለዚህም ከኅሊና ውጪ በሚረገዝ የሃሳብ ጽንስ ምክንያት ቀድሞውን የጨነገፉ ወያኔዎች ያሳዝኑኛል፡፡
በሌላ በኩልም ራሳቸው አንድ መሆን አቅቷቸው እርስ በርስ እየተደማሙና እየተወነጃጀሉ የጨለማውን ዘመን የሚያራዝሙ ተቃዋሚተብዬዎችም ያሳዝኑኛል፡፡ ከላይም ከታችም ከጎንም በወያኔ እሳት እየተለበለቡ ገና ለገና ወንዝ የማያሻግር የተናጠልና ፎሽፏሻ ትግላቸው ሠምሮ በሚጨብጡት ሥልጣን ከወዲሁ እየመረቀኑ – በምርቃናዊ ምናባቸውም አንዱን እየሾሙ፣ አንዱን እየሻሩ፣ አንዱን እያሰሩ አንዱን እየፈቱ፣ አንዱን እንዳሰቃያቸው እያሰቃዩ አንዱን እየገደሉ፣ አንዱን እየፎለሉበት አንዱን በሎሌነት እያሽቆጠቆጡ – ስለሚታያቸው ያን ቅዠት ተከትሎ በሚደርስባቸው ሥነ ልቦናዊ ድበታ አዝንላቸዋለሁ፡፡ በጥቅሉ በዘመኑ የኢትዮጵያዊነት መገለጫ ገጽታዎች አዝናለሁ፡፡ ይህ እንደገና ሊተነተንና ፍቺ ሊሰጠው የሚገባ ኢትዮጵያዊነት ያላሳዘነ ምን ያሳዝናል? የብዙዎቻችንን የማሰቢያ አካል የምችና ዋግ ሱናሚ ስለመታው ያም ያሳዝነኛል፡፡ አቅል ጀባ ምዕመናን!
ለማንኛውም ለሰላም ሲሉ በጣም ሩቅ መንገድ – ብዙ ሺህ ማይሎችን ተጉዘው ትግሬ ያልሆነ ሰው ሻለቃ ማዕረግ ማድረሳቸው እንዴቱን ያህል ታላቅ የክፍለ ዘመኑ የበጎ አድራጎት ተግባር – የፅድቅ መንገድን የሚያመቻች ድንቅ ድርጊት – እንደሆነ ሳልጠቁም አላልፍም – ማፈሪያዎች! ሥልጣን ከደደቢት ያመጡ ይመስል የኛኑ ሥልጣን ነጥቀው “ሩቅ ተጉዘን!” ሲሉ ትንሽ አይሰቀጥጣቸውም? ዳሩ ማፈርን ሲያውቁ አይደል፡፡ ከ60 የጦር አበጋዝም አንድ ሁለት ጭሎ ተላላኪዎችን ከሌሎች ብሔሮች በማስገባታቸው ራሱ ምሥጋናችንን ተንበርክከን ማቅረብ ያለብን ይመስለኛል፡፡ ወይ ወያኔ! ለነገሩ እነሱ ምን ያድርጉ? “ጮማና ቁርጥ አደከመን፤ መግረፍና መግደል፣ ማሰርና ማሳደድ ሰለቸን፤ እንኩ ሥልጣናችሁን ተረከቡን፣ ይህን ያህልም የሥልጣንና የሀብት ማማ ላይ እንቆያለን ብለን አላሰብንም ነበር፣ ዕድሜ ለናንተው አለመስማማትና ለአለቃችን ራዕይ…” ብለው አራት ኪሎ ቤተ መንግሥትን አያስረክቡም፡፡ ምድረ ሀበሻ ብቻ በነገር ጦርና በአሉቧልታ እንፈሳፈስ፡፡ በስደታችንም ዓለምን ከአሁን በበለጠ እናጥለቅልቃት፡፡ ዓሣ ነባሪዎችና የበረሃ እንስሳትም እንዳይርባቸው በገፍ እየተሰደድን እንመግባቸው፡፡ የዐረብ ጀማላም ይጫወትብን፡፡ “አንድ እግር በርበሬ መንቀል አቅቶን” ወያኔን እንክ እንክ እያልን ጫንቃችን ላይ እንደተሸከምን እንኑር፡፡ በረት አማሽን አደብ እንደማስገዛት ለጥቂት ኮርማዎች በረቱን አስረክበን እኛ ከብቶች ራሳችንን ሜዳ ላይ ጣልን፡፡ ጉደኞች ነን፡፡