Quantcast
Channel: Ethiopian News | ዘ-ሐበሻ | Latest News Provider | News For All
Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

ሁነኛ። (ሥርጉተ ሥላሴ)

$
0
0

ከሥርጉተ ሥላሴ 17.10.2014 /ሲዊዘርላንድ – ዙሪክ/

sr1ይቅርታ በመጠይቅ ጡሑፌን ብጀምር ይሻላል ብዬ ወሰንኩኝ። ባለፈው ወር በጀግና አበራ ሃይለመድህን ዙሪያ ወርሃዊ ተግባሬን አልከወንኩም ነበር – ባለመቻል። ስለሆነም ለአድናቂዎቹ – ለአክባሪዎቹ ፈለጉን ለመከተል ለቆረጡ ወጣት የነፃነት አርበኞች ይቅርታ ዝቅ ብዬ – እጠይቃለሁ። ዛሬ ግን በተለመደው አኳኋን ትንሽ ነገር ቆጣጥሬ እንሆ ከች ብያለሁ።

ዕንባ ከውስጥ ቁስለት የሚፈላ የሃዘን መግለጫ ርቁቅ ቋንቋ ነው። ዕንባ የመከፋት ድምጽ አልባ ዬእግዚዎታ ድምጽ ነው። ስለዚህም ዕንባ ጥሩ ተናጋሪ፣ እንዲሁም የውስጥን ስሜትን የሚቀበል የወጣለት ቅን አድማጭ ነው። ዕንባ የአሳር መግለጫነቱ የጭካኔ ግፋዊ አስተዳደር ማዬልን የሚያብራራ የሥጋ ጠብታ ልዩ ሰነድ ነው።

ዕንባ የመከራው ዘመን ልዩ የፍዳ ማዕዋለ ዜና ነው። ዕንባ ሙቀቱ ከተቃጠለ ጭስ ጋር ተዋህዶ ሲፈስ ምህረት፣ ሰላም፤ ትፈስህትን ፈጣሪ አምላክ ያዝ ዘንድ በፅኑ እዬለመነ ነው። ዕንባ የበቀለ ተሰፋን ለማዬት ናፍቆቱን ሰንቆ ነው የሚወርደው። ዕንባ የተዘጋ ነገን ለማስከፈት – የሱባኤ ወንዝ ነው። “የወንድ ልጅ ዕንባው በሆዱ” ያለው የብላቴ ሎርዬት ጸጋዬ ገ/መድህን ቅኔ ዛሬ ቢያው ምን ይለው ይሆን?! ተብዕት ወገኖቹ ከውስጣቸው ዕንባ መራስ የተነሳ ገደቡን ጥሶ ፈንድቶ – ዘልቆ አደባባይ ሲውል …. ከቶ ምን ብሎ ይቃኝ በነበር ያ የቅኔ ልዑል?~!

ዕንባ ስለተፈለገ አይገኝም። ወይንም አይመጣም። ድርቅ ብለው የሚፈጠሩ ፍጥረቶች ሊኖሩ ይቻላሉ። አብሶ ጨካኞች በጭካኔያቸው ክፋት ምክንያት ዕንባን ሲዩ መደሰቻቸው – መዝናኛቸው – መፈንጠዣቸው ስለሆነ ዕንባቸውን ፈጣሪ አምላክ አምክኖ – ወይንም አድርቆ ነው የሚፈጥራቸው። ጨካኞች ሲገድሉ – ሲያስሩ – ሲበድሉ – ሲያሳድዱ ዕንባን እዬረገጡ ወይንም እዬጠቀጠቁ ነው። የሚጠቀጠቀው ዕንባ ደግሞ መገፋቱን – መገለሉን – በትዕቢተኞች ፊት መነሳቱን፤ የተፈጥሮ አካልነቱ በገዢዎች ዘንድ ሰሚ ማጣቱን፤ የአምላክ ሥጦታነቱ በጉልበተኞች ሆነ በዘመናዮች መሰረዙን ስለሚያውቅ፤ ለሁሉ ጌታ ለፈጣሪ አምላክ ስሞታውን በፆም – በፀሎት ያሳውቃል – ያብራራል። ዕንባ ከማናቸውም በላይ ውስጡን በተደራጀ አኳዃን የማሳዬት፤ – ሙሉዑ ስሜቱን የመግለጽ ቋሚ ፍጽምና አለው። እንደ እኛ መከራ ሳያቋርጥ በሚመረትባት ሀገረ ኢትዮጵያ ኑሮውን የመሰረተ ዕንባ ገንፍሎ “በቃኝ” ብሎ ሲወጣ የተጣራ የእምታ፤ የምሬት ሬት ጭማቂ ነው። ከቶ የጭንቅ የተጣራ ዬምጥ ውስኪ ልበለው ይሆን ….?!

ዕንባ ዋጋው እጥፍ ድርብ ነው። ዕንባ የመፍትሄ ቀኑ ምን ቢረዝም፤ ነገር ግን የገፋው ወይንም የገፈተረው ጨካኝ የእጁን ማግኘቱ አይቀሬ መሆኑን ስለሚያውቅ፤ ከትጋቱ ለአፍታ ተግ አይልም። ሰው እንደ ወጣ በሰላም ስለ መመለሱ እርግጠኛ በማይሆንባት እናት ምድር ኢትዮጵያ የዕንባ ጅረት በዬትኛውም አቅጣጫና ሁኔታ ሊወረድ ይችላል። የዕድሜ ሆነ የፆታ፤ የዕምነት ሆነ የፖለቲካ አቋም ፤ የቀለም ዕውቀት ሆነ የሙያ ደረጃ ሳይወስነው በጋ ከክረምት ይዘንባል፤ በተፈጥሮ ሁለቱ መስኮቶቹም በፍሰቱ ልክ መልዕክቱን ሆነ ተልዕኮውን ሳያባራ ወደ ላይ እዬላከ አቤቱታውን በአጽህኖት ያሰማል – ይማጸናል። በእናት ሀገር በኢትዮጵያ የዕንባ የችርቻሮ ወይንም የጀምላ ትልቅ ፕሮጀክት ማስከፈት እስኪያስችል ድረስ ዙሪያ ገባው ከውስጥ መራዊ ቁስለት – ነበልባላዊ ብግነት – ቋያዊ ስቅዛት በመነጨ አኳኋን ሌትና ቀን ሳይታክት ይፈሳል ….

ለጉሮሮው ማርጠቢያ ያጣው ዕልፉ፤ ሊለምን ያፈረው ብዙኃኑ፤ በሀገሩ በባይታወርነት የሚገፋው ቀን ጠበቂው – በጥጋበኛ ታጣቂ ዱራ የሚደበደበው ፍትህ ፈላጊ፤ የነገ ተስፋ ዕንቡጦች ሳይቀሩ በናፍቆትና በተስፋ ማጣት ተከዝነው፤ የወላጆቻቸው ድብደባ – መደፈር – እስር – ስደት – ሞት – ሐዘናዊ መርዶ ለጋ መንፈሳቸውን ያለ ርህራሄ ሲቀጥፈው የሚወርደው የቀንበጥ ቅድስና ያልተለዬው ዶፍ፤ ከመደበኛ የሥራ ገበታው በዘሩ ብቻ ተነጥሎ የሚባረረው አባ እና እማ ወራ፤ ትክክለኛ ብይን አጥቶ ዓመት እስከ ዓመት ዶሴ ስንቁ የሆነው ለፍቶ አደር፤ የቀረጡ ንረት ከገብያ ውድድር ያወጣው ባተሌ ጥሮ አዳሪ፤ ጥግ አጥቶ ሰኔን ሲናፍቅ ከማሳው የተፈናቀለው የበሬ ጌታ፤ ወጥቶ ሳይመለስ ወይንም ወጥታ ሳትመለስ የቀረች /የቀረ/  የሰብዕዊ መብት ተሟጋች፤

በግራጫ ዘመናቸው ተከብረው ለምርቃት ወይንም ለሽምግልና ሊበቁ የሚገባቸው አዛውንታት ክብራቸው ተመልጦ በክርኒ የሚገፉት ባለግራጫወች፤ ከጸሎት ምኩባራቸው የተለዩት የምዕመናን አባቶች ፍዳ ወዘተ …  በተናጠል ሆነ በጅምላ በገባሩ ሆነ በዋና ወንዝ የሚፈሰው የዕንባ መጠን ከባህር ወላል በላይና በታች ልግምተው በማልችለው መጠን ማዕለተ – ተሌሊት ይፈሳል። …. ነገ እንዲነጋለት ….. አምላኩን አዘውትሮ ሳይታክትም ይለምናል።

… ዓለም ለሽ ብላ የሰላም ህይወቷን በምታጣጥምበት ወቅት፤ ዓለም ከደላው መኖር ጋር ቅብጥ ቅልጥ ስትል፤ ዬእልፈተ ቢሷ የኢትዮጵያ ልጆች ግን ትክን፣ ኩምትር ብለው አንገታቸው ቀና ሳይል እንደ ተከዙ ድፍት ሲሉ እያዬ ዝም እንዳይል አዶናይን ዕንባ አብዝቶ ሳይደክም ይወተውተዋል። ስለሆነም ዕንባ ለተገፉት ስንቅና ትጥቅነቱን በተግባር የኳለ ድንቅ የድርጊት አርበኛ ነው። የአሳረኛው ዘመን ጽኑም አጋር ጠበቃም፤ ሊቀ ትጉኽ – የጭቁን ተሟጋችም፤ በዘመነ ህማማት ያለተለዬ ቁርጠኛ አስራት ሆደ ባሻ ነው ደራሹ ሩኽሩሁ ዕንባ።

ይህመራር የዕንባ ዘመን ማደመጥ የሚችሉ፤ ማንበብ የሚችሉ፤ ማናገር የሚችሉ፤ ማመሳጠር የሚችሉ ወገኖች ደግሞ የበለጠውን መከራ በመሸከም ፊት ለፊት ወጥተው የግንባር ሥጋ – ማገዶ ይሆናሉ። ይቀቀላሉ – ይሾቃሉ። ውስጣቸውም ደም ዕንባ ሳያርጥ ያምጣል ….

እንሆ ደምን አቆርዝዞ የዕንባ ቀለበት ብሄራዊ ጥሪ  – የመከራው ዘመን የትውልዱ ዕጣ ፈንታ ሆኗል – በዘመነ ወያኔ ኃርነት ትግራይ። ዕልፈተ ቢሱ ሰፊው የኢትዮጵያ ህዝብ፤ እልቀተ – ቢስ በሆነ ሁኔታ መከራን ከወቅት – ወቅት እዬበላ፤ ያልፋልን ጠብቆ ግን ቀን ተዘግቶበት ይኸው አለ፤ እንደ ትናንቱ ዛሬም በሲቃ እያነባ በዘርፈ – ብዙ ራህብ እዬተንገረገበ – እዬተገረፈ። እናቱም ማቅ ለብሳ ገመድ – አደግድጋ ታጥቃ ኤሉሄ – ኤሉሄ ትላለች እንደ ራሄል ….። ያልፍላት ይሆን?

የእኔ ጌጦች የፁሑፌ ታዳሚዎች – ዘመናችን ለትውልዱ የሰጠው የቤት ሥራ በባህሬው እጅግ ትብትብ – ውስብስብ – በበዛ ሁኔታ ረቂቅ ከመሆኑም በላይ ዝንቅንቅ ነው። ስለሆነም የበሰለ ትዕግስትን፤ የለማ ማስተዋልን፤ የፋፋ አርቆ አሳቢነትን፤ የተሟላ ሥነ ምግባርን ከክህሎተ – ብቃት ጋር ይጠይቃል። ሙሉ ሰብዕናን ምራቅ ከመዋጥ ጋር ይሻል። ይህ መክሊት የሁሉ ላይሆን ይችላል። ባለጸጋዎች ግን አሉን። ከእነዚህ ዘመንና ጊዜ አብዝቶ ዕንባን የማዳመጥ ልዩ ብቃት ሆነ አቅም ከሰጣቸው፣ ከተባረከላቸው አንዱ ጀግናዬ ካፒቴን አበራ ሃይለመድህን ነው። ሰው መሆን እንዲህ ለሰብዕዊ መብት ህልውና በውጤታማ ጉልህ ተግባር ዋቢነቱን ያሰክናል።

ይህ ወጣት፤ ይህ ሳታና፤ ይህ ትንታግ፤ ይህ ታታሪ፤ ይህ ብርቅ ሙሑር፤ ይህ የነፃነት ድንቅ አርበኛ ሳይተጓጎል የሚፈሰው የተገፉ ወገኖቹን ዬዕንባን ውስጡን ፈትሾ – መርምሮ ዘንበል ብሎ በተደሞ አዳመጠ። በአርምሞ አነበበ። በአንድምታ መሰጠረ። እሱ እራሱ ከነተፈጥሮው ሚስጢር ነው። ጠቅላላ ጉዞውና ሁኔታው አምላካዊ ጥበቃና ፈቃድ ያለበት በመሆኑ ይኸው ከብጥቅጣቂ ተባራሪ መረጃዎች ውጪ ጉልበታም መረጃ እሱ ስላለበት ሁኔታ ለማወቅ አቀበት ሆነ። ሚስጢር ተመሳጥሮ በኪዳን የመንፈስ ቋሚ ውል መቋሚያ የሆነበት ጀግንነት እንሆ በዘመናችን አዬን። ተመስገን!

ጀግና አበራ ሃይለመድህን ዬዕንባን ህዋሳዊ አካልን አድምጦ በትክክለኛው ወቅትና ጊዜ መተርጎሙ የዕንባ ሁነኛ ብቁ አድማጭ ያሰኘዋል። እርምጃው ሆነ ሂደቱ በማሸነፍ ድልን ያሰበለ፤ ጥቃትን ያወጣ፤ አለሁ ባይነትን ያመሳከረ፤ ሆደ ባሻነቱን ሆነ እናት አንጀቱን የተረጎመ፤ ከተከፋ ጎን የመቆምን አይነታ ድርጊት የከወነ ነው። ጀግናዬ ካፒቴን አበራ ሃይለመድህን የትውልዱን አብሶ የወጣቱን የማድረግ አቅምና ብቃት በድርጊት ያነጠረ፤ ጠላትን ለይቶ በማወቅ የሚከፈለው መስዋዕትነትና የሚያሰገኘው ተጨባጭ ውጤትን ለክቶ የሆነበት። “አልገዛም ባይነትን” በድርጊት ያቀለመ – ያዘመረ የድንቅ ተግባር መጠሪያ – ልዩ አብነት ነው።

መቋጫ። ውዶቼ – የእኔዎቹ ዛሬ ዕለቱ ነው – የድል ቀን መታሰቢያ ወይንም ማጠሪያ። ስለዚህም የቻላችሁ በአካውንታችሁ ዘመን የሰጠንን ወጣት ጀግና አስባችሁት ትውሉ ዘንድ በትሁት ቅን መንፈስ እያሳሰብኩ፤ አብራችሁኝ በመቆዬታችሁ ደግሞ ውስጤን በልግስና ሸልሜ፤ ፍቅሬንም የንብ ዓውራ በመሰለ ሽንጣም ናፍቆት አጉርሼ ልሰናበት። ኑሩልኝ የእኔ ጸጋዎች። መሸቢያ – ሰንበት።

ጀግኖቻችን መንገዶቻችን ናቸው!

ጀግኖቻችን ማተቦቻችን ናቸው!

እግዚአብሄር ይስጥልኝ።

 

 


Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>