በዶ/ር ብርሃኔ ረዳኢ
- የቲማቲም ሶስ
ቲማቲም፣ የቲማቲም ሶስ ወይም ፒዛ አዘውትረው የሚመገቡ ወንዶች ራሳቸውን ከፕሮስቴት ካንሰር በጥሩ ሁኔታ እየተከታተሉ እንደሆነ በሃርቫርድ ተመራማሪዎች የተደረገ ጥናት አረጋግጧል፡፡ በጥናቱ ላይ 47ሺ ወንድ የጤና ባለሙያዎች ተካተዋል፡፡ በውጤቱም በሳምንት ከሁለት እስከ አራት ጊዜ ቲማቲም ነክ ምግቦችን የሚመገቡ ወንዶች በፕሮስቴት ካንሰር የመጠቃት እድላቸው በ35 ከመቶ ቀንሶ ተገኝቷል፡፡ ቲማቲም በከፍተኛ መጠን ይዞት የሚገኘው carotenoid ለዚህ ውጤት መገኘት ወሳኝነት አለው ተብሏል፡፡ ተመራማሪዎቹ ካሮቲኖይድን የያዘው ላይኮፔን የተሰኘ ንጥረ ነገር በቶሎ ከሰውነት ጋር እንዲዋሃድ ቲማቲሙ ከቅባት ጋር አብሮ መብሰል አለበት ያሉ ሲሆን ለዚህ ደግሞ ፒዛ ተመራጭ ሆኖ ተገኝቷል፡፡
- ኦይስተር
ይህ ከባህር ውስጥ የሚገኝ ምግብ በኛ ሃገር(ኢትዮጵያ) ብዙም የሚታወቅ አይደለም፡፡ ይህ ግን ጠቀሜታውን ከመንገር አያግድም፡፡ በጥንት አፈ ታሪክ ኦይስተር የፍቅር ምግብ ይባል ነበር፡፡ ሳይንስም ከዚህ ጋር ሳይስማማ አይቀርም፡፡ በቀን ሁለት ወይም ሶስት አይስተር ለተመገቡ ወንዶች ለእለቱ የሚያስፈልጋቸውን ዚንክ ይሰጣል፡፡ ይህ ሚነራል የወንድ የመራቢያ ክፍል የተለመደ ስራውን በአግባቡ እንዲወጣ ያስችላል፡፡ ሳይንቲስቶች ‹‹ባለፉት 50 ዓመታት የወንዶች ስፐርም ቁጥር (sperm count) አሽቆልቁሏል፡፡ ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ የአካባቢያዊ ሁኔታዎች መበላሸት ነው›› በሚለው ነጥብ ላይ የተከፋፈለ አቋም አላቸው፡፡ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት በአንዳንድ ጥናቶች ላይ የቴስቶስትሮን መቀነስን አሳይቷል፡፡ በቂ ዚንክ ማግኘት ለዚህ መልስ ነው፡፡ ለወንዶች በቀን 11 ሚሊ ግራም ዚንክ በቂ ሲሆን ከ40 ሚሊግራም በላይ ከሆነ ግን ጉዳት ያመጣል፡፡ የቴስቶስትሮንና የስፐርም መጠናቸው ቀንሶ የተገኙ 22 ሰዎችን ያሳተፈ አንድ የሙከራ ጥናት ተካሂዶ ነበር፡፡ እነዚህ ሰዎች በየእለቱ 45-50 ቀናት ዚንክ እንዲወስዱ ከተደረጉ በኋላ የቴስቶስትሮንና የስፐርም መጠናቸው ጨምሮ ተገኝቷል፡፡
- ብሮኮሊ
በሃርቫርድ የተደረገ አንድ የቅርብ ጊዜ ጥናት እንደ ብሮኮሊ ያሉ ባለ አበባ አትክልቶች የሽንት ፊኛ ካንሰርን ሊከላከሉ ይችላሉ ብሏል፡፡ ይህ የካንሰር አይነት አሜሪካ ውስጥ ከሚታዩ ካንሰሮች ዋነኛው ሲሆን ወንዶች ላይ በስፋት ይታያል፡፡ በ50 ሺ ወንዶች ላይ ጥናት ያደረጉ ሳይንቲስቶች ባወጡት ሪፖርት ላይ በሳምንት አምስት ጊዜና ከዚያ በላይ ባለ አበባ አትክልቶችን የሚመገቡ ሰዎች ከማይመገቡት ጋር ሲነፃፀር በካንሰር የመጠቃት እድላቸው በግማሽ ቀንሶ ተገኝቷል፡፡
- የኦቾሎኒ ቅቤ
ልብዎ ጤናማ እንዲሆንልዎ ከፈለጉ ቁርስዎን ከኦቾሎኒ ቅቤ ይጀምሩ ይላል፡፡ በፔንስልቫኒያ ስቴት ዩኒቨርስቲ ተመራማሪዎች የተካሄደ አንድ ጥናት፡፡ የልብ በሽታ ፆታ ሳይመርጥ ሁሉንም ያጠቃል፡፡ ወንዶች በአረጋዊ እድሜያቸው ላይ በስፋት ይጠቃሉ፡፡ ተመራማሪዎቹ በአሜሪካ የልብ ማህበር የተዘጋጀውን step 11 የተሰኘ የአመጋገብ መመሪያንና በከፍተኛ ቅባት የበለፀገውን ኦቾሎኒን በሁለት ምድብ ለከፈሏቸው ሰዎች በመስጠት ለውጡን መዝግበውታል፡፡ የልብ ማህበሩ እቅድ ብዙ ካርቦሃይድሬትስን በመጠቀም ላይ ያተኩራል፡፡ የኦቾሎኒው እቅድ ደግሞ 36 ከመቶው ስብ ነበር፡፡ ከ24 ቀናት በኋላ በተገኘው ውጤት ሁለቱም መጥፎ (ጎጂ) የሚባለውን LDL ተሰኘ ኮሌስትሮል ቀንሰው ተገኝተዋል፡፡ ኦቾሎኒው በዚህም አላቆመም፡፡ የደም ስቦች (blood fats) ተብለው የሚጠሩትን (triglycerides) መጠን በመቀነስ ጠቃሚውን HDL ኮሌስትሮል ሳይነካ ቀርቷል፡፡ ተመራማሪዎች የኦቾሎኒ ቅቤው ጥቅሙ በእጅጉ ያመዘነ በመሆኑ አዘውትረን እንድንመገበው መክረዋል፡፡
- ሃብሃብ
ወንዶች እስከ 55 ዓመታቸው ድረስ ከሴቶች በበለጠ በከፍተኛ የደም ግፊት ይጠቃሉ፡፡ ጥናቶች እንደሚያሳዩት ከሆነ በፖታሲየም የበለፀጉ ምግቦች በከፍተኛ የደም ግፊትና በልብ ድካም የመጠቃት እድልን ይቀንሳሉ፡፡ ሃብሃብ በፖታሲየም የበለፀገ ነው፡፡ በአንድ ተለቅ ያለ የሃብሃብ ቁራጭ ላይ 644 ሚሊ ግራም ፖታሲየም ይገኛል፡፡ ይህ ከሙዝ ወይም ከብርቱካን ጭማቂ ውስጥ ከሚገኘው ይበልጣል፡፡