የተለያዩ የመንግሥት ቤቶችን የኪራይ ዋጋ በመቀነስና በዜጎች መካከል ልዩነት በመፍጠር፣ መንግሥት 370,476 ብር ጉዳት እንዲደርስበት ለማድረግ ሥልጣናቸውን ያላግባብ በመጠቀም የሙስና ወንጀል የተከሰሱት፣ የቀድሞ የመንግሥት ቤቶች ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ጥቅምት 4 ቀን 2007 ዓ.ም. ጥፋተኛ ተባሉ፡፡
ዋና ዳይሬክተሩ አቶ ተፈሪ ፍቅሬ ጎሳዬ የፌዴራል የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ባለፈው ዓመት የመሠረተባቸውን ክስ ሲመረምር የከረመው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አንደኛ ወንጀል ችሎት ነው ጥፋተኛ የተባሉት፡፡
አቶ ተፈሪ በሥልጣን ላይ እያሉ፣ በቀድሞ ወረዳ 23 ቀበሌ 12 የቤት ቁጥር 106 የሆነውና በውጭ ምንዛሪ ተከራይቶ የነበረን ቤት፣ የኤጀንሲውን መመርያ አንቀጽ 13 (5) ውድቅ በማድረግ ለኢትዮጵያዊ ማከራየታቸው፣ በቀድሞ ወረዳ 21 ቀበሌ 01 የቤት ቁጥር 112/40 ባሰፋ ትሬዲንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር፣ ለንግድ በጨረታ አሸንፎ የነበረውን ቤት በመመሳጠር ወደ መኖሪያ ቤት በመቀየርና ኪራዩን በመቀነስ፣ በቀድሞ ወረዳ 18 ቀበሌ 05 የቤት ቁጥር 008/14 ውስጥ ተከራይ የነበሩትን የምክር ቤት አባል ከጠቅላይ ሚኒስትሩ የተጻፈ የድጋፍ ደብዳቤ ሳይኖር በመመሳጠርና በምክር ቤት አባላት ላይ ልዩነት በመፍጠር እንዲከራዩ በማድረግና ሌሎችንም ተጨማሪ ቤቶች ሥልጣናቸውን በመጠቀም ኪራይ ቀንሰው እንዲከራዩ በማድረግ በመንግሥት ላይ ጉዳት ማድረሳቸውን ክሱ ያብራራል፡፡
ከሳሽ ዓቃቤ ሕግ እንደ ክሱ የሰነድና የሰዎች ምስክሮችን በማቅረብ ለፍርድ ቤቱ ማስረዳቱን ፍርድ ቤቱ በብይኑ ገልጾ፣ አቶ ተፈሪ እንዲከላከሉ በማዘዝ ተከላክለዋል፡፡
በአሁኑ ጊዜ የጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካሪ የሆኑት ዶ/ር ካሱ ኢላላና የምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካሪና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል አቶ አማኑኤል አብርሃን ጨምሮ ሌሎች መከላከያ ምስክሮችን ያቀረቡት አቶ ተፈሪ፣ የቀረበባቸውን ክስ በከፊል ሊከላከሉ እንዳልቻሉ ፍርድ ቤቱ ገልጾ፣ ጥቅምት 4 ቀን 2007 ዓ.ም. ጥፋተኛ ብሏቸዋል፡፡
ፍርድ ቤቱ በፍርዱ እንደገለጸው አቶ ተፈሪ የቀረበባቸው ክስ በሥልጣን ያላግባብ የመገልገል ወንጀል ሲሆን፣ ክሱ አንድ ሆኖ በአራት ጭብጥ የተከፋፈለ መሆኑን አብራርቷል፡፡
አቶ ተፈሪ የዓቃቤ ሕግን ክስና ማስረጃ የተወሰነ ክፍል በበቂ ሁኔታ መከላከላቸውንም ፍርዱ ይገልጻል፡፡ የግል የንግድ ድርጅት የሆነውን ባሰፋ ትሬዲንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበርና ወ/ሮ ሶሻል ይልማ የተባሉት ግለሰብ የተከራዩትን ቤት በተመለከተ የኪራይ ተመናቸው እንዲቀንስ ያደረጉት አቶ ተፈሪ በመሆናቸው፣ ይኼንን ለማድረግ የተሰጣቸው ሥልጣን እንደሌለ ፍርድ ቤቱ አስታውቋል፡፡ በመሆኑም በዚህ በኩል ጥፋተኛ እንዳላቸው ፍርድ ቤቱ አስታውቆ ቅጣት ለመወሰንም ለጥቅምት 18 ቀን 2007 ዓ.ም. ቀጥሯል፡፡
Source:: Ethiopian Reporter