ግርማ ሞገስ (girmamoges1@gmail.com)
ሰኞ ግንቦት 26 ቀን 2005 ዓ.ም. (Monday, June 3, 2013)
መንግስት ለተጠየቀው ጥያቄዎች አዎንታዊ መልሶች መስጠት ይጠበቅበታል። ሁሉም ነገር በእጁ እና በደጁ ስለሆነ አዎንታዊ መልስ ለመስጠት የሚያስቸግረው ምንም ነገር የለም። ዛሬ ብድግ ብሎ “እስከ ዛሬ ድረስ ለፈጸምኩት ጭቆና ይቅርታ ይደረግልኝ። የዜጎችን ነፃነት ከዛሬ ጀምሮ አከብራለሁ። እስረኞችን ነገ እፈታለሁ። በኢትዮጵያ በነፃ ፕሬስ ላይ የጫንኩትን ጭቆና ከዛሬ ጀምሮ አንስቻለሁ። ኢ.ቲቪ እና አዲስ ዘመን ጋዜጣ በአንድ ወር ውስጥ ከመንግስት ፖለቲካ ነፃ ሆነው እንዲደራጁ አደርጋለሁ። ህዝብ ማፈናቀል በኢትዮጵያ ዳግም አልፈጽምም። የተፈናቀሉትም ካሳ ተከፍሏቸው እና ህጋዊ ዋስትና ተስጥቷቸው ወደቀድሞ ኑሮዋቸው እንዲመለሱ በአንድ ወር ውስጥ እፈጽማለሁ። አፈናቃዮችን ፍርድ ቤት አቀርባለሁ። ሁሉም በሙስና የሚታሙ ባለስልጣኖች አዜብ መስፍን ሳትቀር ክትትል እንዲደርግባቸው አደርጋለሁ። አንድን ሙሰኛ ከሌላ ሙሰኛ ሳላበላልጥ ሁሉም ሙሰኞች ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ አደርጋለሁ። በዚህም በዚያም እያልኩ በየውሩ ከደሞዛችሁ እምቆርጠውን ከዚህ ወር ጀምሮ በማቆም የኑሮ ውድነት ያጎበጠው ትከሻችሁ እንዲያገግም አደርጋለሁ። ህገ-መንግስት አከብራለሁ።”
በስልጣን ላይ ያለው አምባገነን መንግስት ከፍ ብለው ከተዘረዘሩት ውስጥ ከፊሉን ያህል በማድረግ እንኳን ከአምባገነንነት ወደ ተሻለ የፖለቲካ ኃይል ሽግሽግ (Political Power Shift) ሊያደርግ ይችላል። ይኽን በማድረግ የነፃነት እና የዲሞክራሲ አድማሶች እንዲሰፋ ያደርጋል። በምላሹ የህዝብ ድጋፍ ሊያገኝ ይችላል። የህዝብ ድጋፍ ማግኘት ማለት ደግሞ የፖለቲካ ድጋፍ ማገኘት ማለት ነው። እነዚህን እርምጃዎች በመውሰድ መንግስት ከተቃዋሚ ዲሞክራሲ ኃይሎች ጋር የፖለቲካ ስልጣን ሽግሽግ ያደርጋል ማለት ነው። ይኽን በማድረግ መንግስት የሚያጣው ነገር ቢኖር አምባገነንነትን ብቻ ነው። ምርጫው የእርሱ ነው። በታሪክ ግን አምባገነኖች ካልተገደዱ በስተቀር በፈቃዳቸው የፖለቲካ ስልጣን ሽግሽግ ያደረጉበት ጊዜ ስለመኖሩ ተጽፎ ያየሁት መረጃ የለኝም።
መንግስት ከፍ ብለው ለተዘረዘሩት ጥያቄዎች አዎንታዊ ምላሽ ካልሰጠ በአምባገነንነት መቀጠል መርጧል ማለት ነው። እሱም ቢሆን ችግር አይሆንም ለዲሞክራሲ ሰራዊት። የዲሞክራሲ ሰራዊት በሰላማዊ ትግሉ የዲሞክራሲ ማዕከሉን መሰረት እና አቅም ያጎለምሳል። ይኽን ማድረግ እንደሚቻል ታሪክ ትመሰክራለች። ይሁን እንጂ መንግስት አምባገነንነትን ከመረጠ ስትራተጂካዊ የፖለቲካ ስህተት መፈጸሙን ልብ ሊል ይገባል። ነፃ ምክር ነው!
ሲጠቃለል፥ ግንቦት 25 ቀን 2005 ዓመተ ምህረት በኢትዮጵያ ሁለት የፖለቲካ ማዕከሎች እንዳሉ እና በመካከላቸው ሰላማዊ ትግል እንደሚካሄድ አሳይታናለች። የዲሞክራሲ ኃይሎች የሚያደርጉት የፖለቲካ ኃይል ሽግሽግ (Political Power Shift) ትግል በስልጣን ላይ ከሚገኘው አምባገነን መንግስት አንፃር የፖለቲካ መሰረታቸውን እና አቅማቸውን ሳያቋርጥ ሽቅብ ማሳደግ አለበት። በውጤቱም የፖለቲካ ኃይል ደረጃቸው ቀስ በቀስ ከበታችነት ወደ አቻነት ከዚያም ወደ በላይነት ደረጃ ይጓዛል። የበላይነት ደረጃ መያዝ ማለት የኢትዮጵያን ህዝብ የመንግስት ስልጣን ባለቤት ማድረግ ማለት ነው። መንገዱ ደግሞ ምርጫ ወይንም ግብጽ ሊሆን ይችላል።
የፖለቲካ ኃይል ሽግሽግ ትግል ሌላ ቁልፍ የሰላማዊ ትግል ጽንሰ አሳብ ነው። አፈጻጸሙን በስፋት ማወቅ ጠቃሚ ነው የተሳካ ሰላማዊ ትግል ለማድረግ። የሽግሽግ ትግልንም ከበካዮች (Contaminants) መጠበቅ ያስፈልጋል።
Golgul/ጎልጉል በፌስ ቡካችሁም (https://www.facebook.com/goolgule) ላይ በማቅረባችሁ ምስጋናዬ ከፍ ያለ ነው። አሁንም ቀጥሉበት። ዘሃበሻም እንደዚሁ። የረጅም ጊዜ የሰላማዊ ትግል ጉዋደኛዬ አብርሃ (ኢትዮሚዲያ) ምስጋናዬን ተቀበለኝ። እንዲሁም ቋጠሮ፣ ኢትዮጵያ ዛሬ፣ አቡጊዳ፣ አሲምባ፣ ECADFORM እና ያላየሁዋችሁ ድረገጾች በሙሉ ለምትለግሱኝ ትብብር ምስጋናዬ ገደብ የለውም። ትግሉ የጋራ ቢሆንም!