ይህ የቁም ነገር መፅሔት 13ኛ ዓመት ቅፅ 13 ቁጥር 188 የሽፋን ርዕሰ ነው፡፡
በታምራት ኋይሉ/
መነሻ
ድፍን የሀገራችን ህዝቦች አዲሱን የኢትዮጵያ ሚሊኒየም ሁለት ሺህን ለመቀበልና በድምቀት ለማክበር ሽር ጉድ በሚሉበት ዋዜማ ታላቁ የኢትዮጵያ ሙዚቃ ንጉስ የሆነው ክቡር ዶክተር ድምፃዊ ጥላሁን ገሠሠ ባዶ ቤት ብቻውን ሆኖ ነበር አዲሱን ሚሊኒየም የተቀበለው፡፡ በአዲስ አበባ ሚሊኒየም አዳራሽ የጎረቤት ሀገራት መሪዎችና ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣት በታደሙበት ዝግጅት ላይ የሀገር ውስጥና የውጪ ሀገር ታዋቂ አቀንቃኞች ተጋብዘው መድረክ ላይ ሲወጡ ታላቁን ድምፃዊ ጥላሁን ገሠሠን ያስታወሰው ሰው አልነበረም፡ ፡ አንጋፋው ሱዳናዊ ድምፃዊ መሀመድ ወርዲ ራሱን ችሎ መቆም በማይችልበት ህመም ላይ ቢሆንም ኢትዮጵያ ሚሊኒየሟን ስትቀበል ‹እንኳን አደረሰሽ!› እንዲላት በመንግስትና ያንን መድረክ ባዘጋጁ ወገኖች ተጋብዞ መድረክ ላይ ወጥቶ ነበር፡፡
ልክ በአስራ ሰባተኛው ቀን የሚከረበውን የጥላሁን ገሠሠን 68ኛ ዓመት የልደት በዓል በመኖሪያ ቤቱ በመገኘት ለማክበር ቁም ነገር መፅሔት ስትደርስ አንጋፋውና ተወዳጁ ድምፃዊ ሳሎን ቤት ብቻውን ዊልቸር ላይ ተቀምጦ፤ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥንን እየተመለከተ ሲተክዝ ነበር የደረስነው፡፡ ከሃምሳ ዓመታት በላይ ያገለገላት ሀገሩ በዚህ ባዕዳን ሳይቀሩ በተጋበዙበት መድረክ ላይ ባለመጋበዙ ስሜቱ መጎዳቱ በግልፅ በስታውቅ ነበር፡፡ አስፈላጊውን ሁሉ በማድረግ የተለያዩ አርቲስቶችን በመጥራት በመኖሪያ ቤቱ የዳመራ ችቦ በማብራት ካከበርነው የልደት በዓሉ ማግስት ለቃለ መጠይቅ ስንቀመጥ ‹እንዴት እናንተ ወጣቶቹ አስታወሳችሁኝ› ነበር ያለው እንባ ባቀረሩ ዓይኖቹ፡፡ ይህ የልደት በዓሉ በሀገር ውስጥ ሳለ የተከበረ የመጨረሻው ልደቱ ነበር፡ ፡በዛው ዓመት ለህክምና ወደ አሜሪካ ያቀናው ጥላሁን 69ኛ ዓመት ልደቱን በ2001 ዓ.ም እዛው አሜሪካ ጥቂት ወዳጆቹ ባሉበት አክብሮ በዛው ዓመት የፋሲካ ዕለት ወደ ሀገሩ የገባ ዕለት ህይወቱ ማለፉ ይታወሳል፡፡
ከጥላሁን በኋላ
የጥላሁን ገሠሠ ዜና እረፍት እንደተሰማ ህዝብና መንግስት አንድ ላይ ሆነው ሀዘን መቀመጣቸውና የቀብር ሥነ በደመቀ መልኩ ማድረጋቸው ይታወቃል፡፡ ይህም መንግስት ለአንድ ግለሰብ /በእርግጥ ጥላሁን ከአንድ ግለሰብ በላይ ነው/ አድርጎት በማያውቀው ሁኔታ ህዝባዊ ሽኝት ማድረጉ ለሀገራችን ሙያተኞች አዲስ ምዕራፍ የከፈተ መሆኑን ጠቅሰን ፅፈናል፡፡ ይህንኑ ተከትሎም ከጥላሁን ዜና እረፍት በኋላ የተለያዩ ነገሮች መደረግ እንዳለባቸውና ለመጪው ትውልድ ሊተላለፍ የሚችል ሥራ መሰራት እንዳለበት በልዩ ልዩ መድረኮች ላይ ተነገረ፤ በመገናኛ ብዙሃንም ላይ ተስተጋባ፡፡ ዘፈኖቹ በሙሉ በአንድ ሲዲ ተሰብስበው ይታተማሉ ተባለ፤ የህይወት ታሪኩን የሚያሳይ ቪዲዮም ይወጣል ተባለ፤ የተጀመረው የህይወት ታሪኩ መፅሀፍ ይታተማል ተባለ፤ በስሙ አደባባይ ይሰየማል ተባለ፤ በህይወት እያለ የመሰረተው የስኳር ህሙማን ማህበር ህንፃ ግንባታ ይጀመራል ተባለ፤የልደት በዓሉም በየዓመቱ በደመቀ ሁኔታ ይከበራል ተባለ ፤ወዘተ ወዘተ ወዘተ…
ይህ በተባለ በዓመቱ የጥላሁን ገሠሠ 1ኛ የሙት ዓመት ሲታሰብ በህይወት እያለ የተጀመረውና በኢትዮጵያ ደራስያን ማህበር የተዘጋጀው መፅሐፍ ከነጉድለቱም ቢሆን ተመረቀ፡፡ አራተኛ ክፍለ ጦር አካባቢ ያለውና እየተገነባ ያለውን መንገድ መንግስት የጥላሁን ገሠሠ አደባባይ እንዲሆን መፍቀዱ ይፋ ሆነ፡፡ በቃ፡፡ ከዚህ ውጪ ትርጉም ያለው ነገር አልተሰራም፡፡ ከዚሁ የ1ኛ ሙት ዓመት ዝክር ጋር በተያያዘ በሚሊኒየም አዳራሽ በተዘጋጀው የሙዚቃ ፕሮግራም ላይ እንዲገኙ ከተጋበዙት የሙያ አጋሮቹ መካከል ከግማሽ በላይ የሚሆኑት አርቲስቶች ሳይገኙ መቅረታቸው የወቅቱ አነጋጋሪ ጉዳይ ነበር፡፡ይህን ጉዳይ በተመለከተ በወቅቱ የታዲያስ አዲስ ፕሮግራም አዘጋጅ የነበረው ተወልደ በየነ/ተቦርነ/ በሸገር ሬዲዮ ላይ በጥላሁን ገሠሠ የሙያ ጓደኞች ዙሪያ ያዘጋጀው አስቂኝ የሙዚቃ ግብዣ በገዛ ዘፈናቸው የተተቹበት ነበር፡፡ ከአንጋፋው ድምፃዊ ማህሙድ አህመድ ጀምሮ እስከ ወጣቷ ድምፃዊት ዘሪቱ ከበደ ድረስ ‹በጥላሁን ገሠሠ የሙት ዓመት መታሰቢያ የሙዚቃ ዝግጅት ላይ ለምን አልተገኛችሁም?› ሲባሉ ሁሉም በየዘፈኖቻቸው ‹የእናቴ መቀነት አደናቀፈኝ› ነበር መልሳቸው፡፡ የጥቂቶቹ እነሆ!
አርቲስት ማህሙድ አህመድ ለጥያቄው ‹መቼ ነው ዛሬ ነው፤ ነገ ነው…› የሚለውን ዘፈን ሲያንጎራጉር፤
ኩኩ ሰብስቤ በበኩሏ ‹ከሰው የተለየ እኔ ምን አውቃለሁ፤ እኔ ምን አውቃለሁ›
ዘሪቱ ከበደ በዘፈኗ ‹አላውቀውም ምን እንደምል እኔ› ብላለች፡፡
ከዓመት በኋላ
የጥላሁን ገሠሠ የሙት ዓመት በታሰበው ደረጃ እንዳልታሰበና ዜና እረፍቱ በተሰማበት ወቅት እንዳለው አይነት የትብብር መንፈስ መጥፋቱን የተረዱት የጥላሁን ገሠሠ ቤተሰቦችና ጥቂት አድናቂዎቹ በ2003 ዓ.ም የጥላሁን ሁለተኛ የሙት ዓመት ሲመጣ የአቋም ለውጥ ማድረጋቸውን አስታወቁ፡፡ ይህም ‹የጥላሁን ገሠሠን ሙት ዓመት ከመዘከር ይልቅ የተወለደበትን ብናከብር ይሻላል› ወደሚል ተቀይሮ ሙት ዓመቱ በዝምታ ታለፈ፡፡ ይህንኑ ተከትሎም ሚያዝያ 2 ቀን 2003 ዓ.ም በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር በተጠራ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ሁኔታው ተነገረ፡፡ ‹የጥላሁን ገሠሠ ህያው የኪነ ጥበብ አደራጅ ኮሚቴ› የተሰኘ ‹ኮሚቴም› መቋቋሙን የሚገልፅ ጋዜጣዊ መግለጫ ተሰጠ፡፡ የልደት በዓሉንም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር በየዓመቱ በጀት መድቦ በድምቀት ለማክበር መወሰኑም ይፋ ሆነ፡፡ ውሳኔው በቀድሞው የቴአትር ቤቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ አዳፍሬ ተሻገር አማካይነት የተወሰነ መሆኑን መነሻ በማድረግ ‹ይህ ውሳኔ ምን ያህል ተፈፃሚነት ይኖረዋል?› በሚል በወቅቱ በተጠባባቂ ሥራ አስኪያጅነት ለተመደቡትና በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ ለነበሩት አቶ ደስታ ተስፋ ቁም ነገር መፅሄት ጥያቄ አቅርባ ነበር፡፡ ‹ለጥላሁን ብለን የምናዘጋጀው ልዩ ዝግጅት በየዓመቱ አይኖርም፤ የመስቀል በዓል የተለመደ የሙዚቃ ዝግጅት ስላለን ከዛው ጋር አንድ ላይ አድርገን እናከብረዋለን› ነበር ያሉት፡፡ በዚህ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ በአዲስ መልክ ብቅ ያለው አዲሱ ‹የጥላሁን ገሠሠ ህያው የኪነ ጥበብ አደራጅ ኮሚቴ› እሰራቸዋለሁ ብሎ የዘረዘራቸው ሥራዎች እቅድ የግብር ይውጣ ይመስሉ ነበር፡፡ ጥላሁን በህይወት እያለ ሊያስፈፅማቸው ያልቻላቸውን ነገሮች በሙሉ ሰብስቦ ‹እሰራቸዋለሁ› ብሎ ጋዜጣዊ መግለጫ መስጠቱ ብዙ ትችት ያስከተለበት ሲሆን እንደተባለውም ከአደረጃጀቱ ጀምሮ በነበረበት የህጋዊነት ጥያቄ እስከ ዛሬ ድረስ ከእቅዱ አንዱንም ማሳካት ያልቻለ ኮሚቴ ሆኖ ቀርቷል፡፡
የብሔራዊ ቴአትር ቃል ኪዳን
የጥላሁን ገሠሠን የልደት በዓል በየዓመቱ በጀት መድቤ አከብረዋለሁ ብሎ ቃል የሰጠው ብሔራዊ ቴአትር ይህንን ባለ ማግስት መስከረም 17 ቀን 2004 ዓ.ም የጥላሁን ገሠሠን 71ኛ ዓመት ልደት ለማክበር ሳይችል ቀርቷል፡፡ ያም ሆኖ በዛው ዓመት በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ሲተላለፍ የከረመው የኢትዮጵያ አይዶል የሙዚቃ ውድድር ማጠናቀቂያ ፕሮግራም ስለነበር ከቴአትር ቤቱ በቀጥታ ስርጭት በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ተላልፏል፡፡በዕለቱ የጥላሁን ገሠሠ መታሰቢያ ተብሎ ተሰይሞ የጥላሁን ፎቶ ተሰቅሎ ውድድሩ ከመካሄዱና ሴት ልጁ የሱን ዘፈን ከማቀንቀኗ በቀር ይህ ነው የሚያሰኝ ጥላሁንን የሚያስታውስና የሚዘክር ዝግጅት አልተደረገም፡፡ በዓመቱ በ2005 ዓ.ም 72ኛ ዓመቱ እና በ2006 ዓ.ም 73ኛ ዓመት የልደት በዓሉም እንደነገሩ ከመከበሩ ውጪ ያንን የኢትዮጵያ ሙዚቃ ንጉስ ደረጃውን በጠበቀ ሁኔታ ለማክበር አልተቻለም፡፡ ቴአትር ቤቱም የጥላሁንን ልደት በጀት መድቤ አከብርለታልሁ ማለቱን ረስቶ በዕለቱ ቴአትር ቤቱ የሙዚቃ ዝግጅቱን ገንዘብ ከፍለው ለሚገቡ ሰዎች የሚያቀርብ በመሆኑ ቢያንስ የ500 ሰዎችን ወንበር ክፍያ እንዲፈፅሙ በአዲሱ የቴአትር ቤቱ ሥራ አስኪያጅ በኩል ተነግሮአቸው ቤተሰቦቹ በደረሰኝ ለቴአትር ቤቱ ገቢ አድርገው ዝግጅቱ መካሄዱ ይታወሳል፡፡ ቤተሰቦቹ የከፈሉባቸው 500 ትኬቶች ለጥላሁን ገሠሠ ጓደኞች፤ወዳጆችና አድናቂዎች በነፃ ቢበተንም በቴአትር ቤቱ ተገኝቶ ዝግጅቶቹን የታደሙት ሰዎች ቁጥር እዚህ ግባ የሚባል አልነበረም፡፡
የዘንድሮው መስቀል
ብሔራዊ ቴአትር በአራት ዓመት ጊዜ ውስጥ ሶስት የአመራር ለውጥ ያደረገ ቴአትር ቤት ነው፡፡ በዚህ ዓመት ጥላሁን ገሠሠ በህይወት ቢኖር ኖሮ 74ኛ ዓመት የልደት በዓሉን ነበር የሚያከብረው፡፡ነገር ግን የዘንድሮ ልደቱም በተባለው መሠረት በቴአትር ቤቱ አልተከበረም፡፡ እንደውም በአንድ ሳምንት አራዝሞ ለማክበር ማሰቡን ተናግሯል፡፡ በየዓመቱ በመስቀል ዕለት የሚካሄደው የሙዚቃ ዝግጅት ታጥፎ ‹ቶፓዝ› የተሰኘው ቴአትር ነው ለተመልካች የቀረበው፡፡ ለዚህ ደግሞ እንደምክንያት የተሰጠው ከቀናት በፊት ከዚህ ዓለም በሞት የተለየውን የረዳት ፕሮፌሰር ሀይማኖት ዓለሙን ሀዘን ለማሰብ ነው፡፡ አንጋፋው አርቲስት ሀይማኖት ዓለሙ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር ባልደረባ እንደነበረና ልዩ ልዩ ቴአትሮች ላይ መስራቱ እንዲሁም ማዘጋጀቱ ይታወቃል፡፡ ይህንኑ መነሻ በማድረግም ህይወቱ ካለፈበት መስከረም 9 ቀን 2007 ዓ.ም በኋላ የቀብር ሥነ ሥርኣቱ በሚከናወንበት ዕለት በቴአትር ቤቱ ልዩ የሽኝት ፕሮግራም ተዘጋጅቶ እንደነበር ይታወሳል፡፡ ይህ ሁሉ ከተደረገ ከሳምንት በኋላ‹ የጥላሁን ገሠሠን ልደት ያላከበርነው በሀይማኖት ዓለሙ ሀዘን ነው ›ማለቱ አያስኬድም፡፡
በኢትዮጵያ ቴአትር ቤቶች ውስጥ በሀዘን ሳቢያ ቴአትሮች ወይም የሙዚቃ ዝግጅቶች የተቋረጡበት ጊዜ እንደሌለ ቴአትር ቤቱ ይዘነጋዋል ለማለት አይቻልም፡፡ የታሪክ ድርሳናት እንደውም የሚያወሱት የገዛ ልጆቻቸው ሞት የተነገራቸው አርቲስቶች የመድረክ ስራቸውን ጨርሰው ወደ ለቅሶአቸው እንደሄዱ ነው /የአርቲስት ሙናዬ መንበሩን ታሪክ ልብ ይሏል/ቴአትር ቤቱ ይህንን እያወቀ ወይም ሊያስታውስ እየተገባ የዚህን ታላቅ አርቲስት የልደት ቀን በቸልታ ማለፉና ማራዘሙ ያስተዛዝባል፡፡ በእርግጥም ቴአትር ቤቱ የጥላሁንን ልደት ለማክበር ከልቡ የወሰነ ከሆነ ከዚህ በተሻለና ጥላሁንን በሚመጥን መልኩ ዝግጁቱን ሊያዘጋጅለትና ክብሩን ሊጠብቅለት ይገባል፡፡ ፕሮግራሙ ተካሂዷል ለማለት ብቻ ከመደበኛው ፕሮግራም ጋር ቀላቅሎ ዝግጅቱን ማካሄድ የአፈፃፀም እቅድን ለማሟላትና ለሪፖርት ይጠቅም እንደሆነ ነው እንጂ ኢትዮጵያ ለሙዚቃ ንጉሷ የሚመጥን ዝግጅት ሲካሄድ እስከ ዛሬ ድረስ አልተመለከትንም፡፡
የቴአትር ቤቱ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ተስፋዬ ሽመልስ ግን በዚህ ሀሳብ አይስማሙም፡፡ እሳቸው እንደሚሉት ከዚህ በፊት የነበረው የጥላሁን ገሠሠ የልደት አከባበር ወጣ ገባ እንደነበረውና አልፎ አልፎም ቤተሰቦቹ መጠነኛ ክፍያ ይጠየቁ እንደነበር ገልፀው ‹ከዚህ ዓመት ጀምሮ ግን በተደራጀና በተጠናከረ መልኩ የልደት በዓሉን ቴአትር ቤቱ ሙሉ ወጪውን ሸፍኖ በቴአትር ቤቱ ሙዚቀኞችና ከተጋባዥ አርቲስቶች ጋር የሚያከብርበት ሁኔታ ተመቻቷል › ሲሉ ገልፀዋል፡፡ አቶ ተስፋዬ እንደሚሉት ዝግጅቱ ለአንድ ሳምንት የተራዘመው የአርቲስት ሀይማኖት ዓለሙ የሀዘን መዝገብ ባለመዘጋቱ እንደሆነና ሀዘኑን ለመግለፅ የሚመጣ ሰውን አስቀምጠን የጥላሁንን ልደት ለማክበር ሙዚቃ ከፍቶ መጨፈር ከባህላችን ጋር ስለማይሄድ ነው ብለዋል፡፡ የጥላሁን ገሠሠ የልደት ዝግጅት ከሀይማኖት ዓለሙ የሀዘን መታሰቢያ ዝግጅት ጋርም ምንም ግንኙነት እንደሌለው አረጋግጠዋል፡፡
የዘንድሮስ ልደቱ ?
ጥላሁን ገሠሠ በሥራው ሚሊዮን አድናቂዎችን አፍርቷል፡፡ ከነዚህ ሚሊዮን አድናቂዎች መሀከል ግን የሐረሩን ንጉሴ ታደሰን ያህል አድናቂ አለው ለማለት ያስቸግራል፡፡ መላ ህይወቱን የጥላሁን ገሠሠን ሥራዎችና ፎቶግራፎች ሲሰበስብ የኖረው የሐረሩ መምህር ንጉሴ ታደሰ ጥላሁን በሕይወት እያለም ሆነ ካለፈ በኋላ ለጥላሁን ያለው ፍቅርና አድናቆት ያልተቀየረ ሰው ነው፡፡ /ምናልባት የኪነ ጥብብ ሰዎችን እንወዳለን፤ እናደንቃለን ለምንል አፍአዊ ላልሆንን ሰዎች ንጉሴ ለዚህ ጥሩ መምህር ነው/ንጉሴ ሁሌም እንደሚያደርገው በየዓመቱ ዳመራ በዓልን የሚያከብረው ወደ አዲስ አበባ መጥቶ ነው፡፡ አንድም በዓሉን ለማክበር አንድም የሙዚቃ ንጉሱን ልደት ለማክበር፡፡ ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ መስከረም 17 ቀን 2006 ዓ.ም ጠዋት ንጉሴ እንደተለመደው የጥላሁን ገሠሠ መቃብር ያለበት ቅድስት ስላሴ ካቴድራል ተገኝቷል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ያው ግልፅ ነው፡፡ ያ የሚሊዮኖችን የሙዚቃ አፍቃሪያንን ልብ ያሸፈተውና በሚሊዮን የሚቆጠሩ አድናቂዎች ያሉት ጥላሁን ገሠሠ በልደት ቀኑ መቃብሩ ላይ የተገኘው ንጉሴ ብቻ ነበር፡፡ ‹ሁሌም እንደማደርገው መቃብሩ ላይ ሻማ አብርቼ አበባ አስቀምጩ ተመለስኩ› ይላል የንጉሱ ታሪክ ገና በሞተ በአምስት ዓመቱ እንዲህ ችላ መባሉ እያስቆጨው፡፡ ‹ወደ ብሔራዊ ቴአትር ሄጄ የልደት በዓሉ ስለመከበሩ ስጠይቅ፤ ባለቤቱም በሀገር ውስጥ የለችም፡፡ ዝግጅቱም ለአንድ ሳምንት ተራዝሟል አሉኝ› ይላል ለጥላሁን ልደት የሥራ ፈቃድ ጠይቆ መምጣቱንና ቀኑ ማለቁን በሀዘን በማሰብ፡፡›
አበበ ቢቂላ በሮም ከተማ
ጀግናው አትሌት አበበ ቢቂላ የመጀመሪያውን የአፍሪካና የኢትዮጵያ የማራቶን የወርቅ ሜዳሊያ በባዶ እግሩ ያስመዘገበው በጣሊያን ሮም ከተማ ነው፡፡ ጣሊያናውያን ለዚህ ብርቱ ጀግና አትሌት ያላቸው ፍቅር ተነግሮ የሚያልቅ አይደለም፡፡ ማንም ሰው ይፈፅመዋል ብቻ ሳይሆን ሊፈፅመው ለማሰብ ይከብደዋል የሚባለውን የ42 ኪሎ ሜትር ከ195 ሜትር ማራቶን በባዶ እግሩ ሮጦ መጨረስ ለእነዚያ ጣሊያናውያን የሚታመን አይደለም፡፡ አበበ ግን አድርጎታል፡፡ ታዲያ ይህንን በተከታታይ ትውልዶች እንኳ ሊፈፀም ያልቻለና ያልተፈፀመ ጀብዱ ለፈፀመው ጀግና አትሌት በከተማቸው መንገድ ፤አደባባይ ፤ድልድይ ሰይመውለታል፡፡ አሁን በቅርቡ እንኳ አበበ ያንን ጀብዱ ከፈፀመ ከ50 ዓመት በኋላ ድልድይ በስሙ ሰይመው ስሙንና ሥራውን ለጣሊያን ወጣቶች አርአያ እንዲሆን አድርገዋል፡፡ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የስፖርት አዘጋጅ ጋዜጠኛ ሰዒድ ኪያር በቅርቡ ወደ ጣሊያን ሮም ከተማ በተጓዘበት ወቅት ይህንኑ የድልድይ ምረቃ ሥነ ሥርዓት ለህዝብ አሳይቷል፡፡
በየተሰማሩበት የሙያ መስክ ከምንም ተነስተው በሀገር ፍቅር ወኔ ብቻ ለሀገራቸውና ለህዝባቸው ታሪክ ያኖሩ ጀግኖቻችንን የውጪ ሰዎች በዚህ ደረጃ ሲያከብሯቸውና ስማቸውን ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲተላለፍ ሲያደርጉ እኛ ግን የሲቪል ጀግኖቻችንን ታሪክና ሥራ እንረሳለን፡፡ ካለፉ በኋላም በስራቸው አዲሱን ትውልድ ከማነቃቃትና አርአያነታቸውን እንዲከተል ከማዕደረግ ይልቅ ድጋሚ እንቀብራቸዋለን፡፡ በጥላሁን ገሠሠ ስም ይሰራሉ ከተባሉና ሊሰሩ ከሚገባቸው ነገሮች መሀከል አብዛኛዎቹ አልተሰሩም፡፡ጥላሁንን በቅርብ የሚያውቀውና በመድረክ ላይ ሲጫወትም የተደሰተበት የአሁኑ ትውልድ ለጥላሁን አንዳች ነገር ማድረግ ካልቻለና ካላቆመለት አዲሱና በስም ብቻ የሚያውቀው ትውልድ ምን እንዲያደርግ ይጠበቃል?
ጥላሁን ገሠሠን ስንት ጊዜ እንቅበረው?
ጥላሁን በህይወት በነበረበት ወቅት ያቋቋመውና ለእግሩ መቆረጥ ምክንያት የሆነውን የስኳር ህመም ለመከላከል በስሙ አቋቁሞት የነበረው ‹የጥላሁን ገሠሠ የስኳር ህሙማን መርጃ ማህበር› ከእርሱ ሞት በኋላ ከስሟል፡፡ አስቀድሞም በህይወት እያለ ለማህበሩ ማጠናከሪያ በሚል በሸራተን ሆቴል በጠራው ስብሰባ ላይ ጥቂት ሰዎች ብቻ ተገኝተው ስሜቱን ጎድተውታል፡፡
በመሷለኪያ አካባቢ መንግስት ሰይሞለት የነበረው አደባባይ ላይ ሶኒ ኩባንያ የራሱን አርማ ከፍ አድርጎ መስቀሉና ጥላሁን አንሶ መታየቱ ‹አደባባዩ የማነው?› የሚል ጥያቄ ፈጥሯል፡፡ አደባባዩ በአሁኑ ወቅት ድጋሚ በባቡር ሥራ ምክንያት በመፍረሱ የተነሳ ‹አደባባይ › የሚለውን ስያሜ የማግኘት ዕድሉ ጠቦ ይገኛል፡፡ በስሙ የታተመው የህይውት ታሪኩ መፅሐፍ የመጀመሪያ እትም አሁንም ድረስ በአዟሪዎች እጅ የመገኘቱ ሚስጥር ምን ይሆን? 10 ሺህ ኮፒ ገዝቶ የሚያነብ ትውልድ መጥፋቱ ምን ይባላል?
በስሙ የኪነ ጥበብ ማዕከል ለማቋቋምና ሥራዎቹንም ሰብስቦ ለማስቀመጥ የተያዘው እቅድ የውሃ ሽታ ሆኖ ከመቅረቱም በላይ ዘፈኖቹ በተለያዩ ሰዎች ድጋሚ እየተዘፈኑ/በሴቶችም ጭምር/ የመጀመሪያ ለዛና ወዛቸውን ሲያጡ የሚቆረቆርና ‹ተው› የሚል አካል ጠፍቷል፡፡ በእርግጥ በቤተሰቡ ዘንድ የዚህ አይነት አካሄዶችን ለመከላከልና ለማስቆም ጥረቱ ባይጠፋም ጥላሁን ከቤተሰብ ጉዳይ በላይ የኢትዮጵያ ህዝብ ሀብት እንደሆነ የተዘነጋ ይመስላል፡፡ከጥላሁን ስራዎች ከሚገኘው ቤተሰባዊ ውርስ በላይ የኢትዮጵያ ህዝብ ቅርስነቱ ጎልቶ ሊታይ እንደሚገባ ለምን እንደተዘነጋ ግልፅ አይደለም፡፡
ጥላሁን የመጀመሪያ መድረክ ያገኘበትና ለተወሰነ ጊዜም ቢሆን የሰራበት አንጋፋው የሀገር ፍቅር ቴአትር ቤት በዜና እረፍቱ ማግስት የጥላሁን ገሠሠን ሐውልት በጊቢው ውስጥ ‹ከሌሎቹ አርቲስቶች ጎን አቆማለሁ› ብሎ የተናገረ ቢሆንም ቴአትር ቤቱ የሥራ አስኪያጅ ለውጥ ካደረገ በኋላ ስለ እቅዱ አንስቶ ለመነጋገር አልቻለም ወይም ረስቶታል፡፡ በአሁኑ ወቅት በቴአትር ቤቱ ግቢ ውስጥ የተለያዩ አንጋፋ አርቲስቶች ሐውልቶች ወደ ቴአትር ቤቱ ትርኢቶችን ለመመልከት በሚመጡ ተመልካቾች የሚጎበኙ ሲሆን ጥላሁን ከእነርሱ መሀል የለም፡፡
ገጣሚው እንዲህ ይላል፡-
… እንግዲህ አንች ኢትዮጵያ እኛስ ልጆችሽ ምንድነን?
አመንኩሽ ማለት የማንችል ፍቅራችን የሚያስነውረን
ዕዳችን የሚያስፎክረን
ግፋችን የሚያስከብረን
ቅንነት የሚያሳፍረን፣ ቂማችን የሚያስደስተን
ኧረ ምንድነን? ምንድነን?…
(ፀጋዬ ገብረ መድህን / እሳት ወይ አበባ/)