Quantcast
Channel: Ethiopian News | ዘ-ሐበሻ | Latest News Provider | News For All
Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

በዉጭ ያሉ ተቃዋሚዎችን ለማሰባሰብ የሚረዱ ነጥቦች –ክፍል አንድ

$
0
0

አማኑኤል ዘሰላም
ሚያዚያ 11 ቀን 2005 ዓ.ም
amanuelzeselam@gmail.com

በዉጭ አገር የፖለቲካ ድርጅቶች ነን የሚሉ ፣ የፖለቲካ ድርጅቶች አይደለንም ብለውም በፖለቲካዉ ጨዋታ ድምጻቸውን የሚያሰሙ ጥቂቶች አይደሉም።  የኢሳት ቴሌቭዥን አለ። በርካታ ድህረ ገጾች አሉ። ራዲዮ ጣቢያዎችማ በተለይም በዲሲ በሽበሽ ናቸው። በተለያዩ ጊዜ ፣ በተለያዩ ጉዳዮች የተለያዩ የአቋም መግለጫዎች፣ በተለያዩ ድርጅቶች ይወጣሉ። መግለጫዎቹ በሙሉ «ተቃዋሚዎች በአንድ ላይ መሰባሰብ አለብን፤ በአንድ ድምጽ መናገር መቻል አለብን፤ ከሌሎች ጋር አብሮ ለመስራት ድርጅታችን ያለዉን ቁርጠኝነት ያረጋግጣል» የሚል ይዘት ነበራቸው።

ሰሞኑን ከቤኔሻንጉል በተፈናቀሉ ወገኖቻችን ላይ የተከሰተዉን የዘር ማጥፋት ወንጀል አስመልክቶ፣ እንደለመድነዉ፣ የመግለጫ ናዳዎች ከተለያዩ በዉጭ አገር ካሉ ማእዘናት እያነበብን ነዉ።  ዜጎች፣ ድርጅቶች የተሰማቸዉን ስሜት መግለጻቸው በራሱ ችግር የለዉም። ተገቢም ነዉ። ነገር ግን ዛሬም ትግላችን፣ መግለጫዎች በማውጣት ላይ ብቻ የተወሰነ መሆኑ ግን በጣም ያሳዝናል።

እንግዲህ መግለጫዎች ከማውጣት ያለፈ ሥራ ለመስራት፣ አንዱና ዋናዉ አስፈላጊ ነገር ትብብር ነዉ። በአለም አቀፉ ማህበረሰብ ተሰሚነት እንዲኖረን፣ ዉጭ ያለዉም ሕዝባችን በኛ ላይ ያለዉ ድጋፉ እንዲበዛ፣  በሚያስማሙ ነጥቦች ላይ አብረን መስራት መቻል አለብን። ለዚህም አብረን እንዳንሰራ መሰናክል የሆኑብንን  ችግሮች ማስወገድ ይገባል።

በኢትዮጵያዉያን መካከል መሰባሰብና መስማማት እንዳይኖር ያደረጉ ሶስት ችግሮች አሉ። የመጀመሪያዉ ከሻእቢያ ጋር አብሮ የመስራቱ ሁኔታ ነዉ። «ወያኔን ለመጣል እስከረዳን ድረስ የጠላቴ ጠላት ወዳጄ ነዉ» በሚል የተሳሳተ መርህ፣ ሁለቱም የኦነግ አንጃዎች እና የግንቦት ሰባት ንቅናቄ የመሳሰሉቱ  ከአቶ ኢሳያስ መንግስት ጋር በቅርበት የሚሰሩ ናቸው።

አብዛኞቻችን ሻእቢያን ከኢሕአዴግ ያልተሻለ እንደዉም የባሰ አድርገን ነዉ የምናየዉ።  በኤርትራ በኩል የሚደረገዉንም ትግል አጥብቀን እንቃወማለን።  በዚህም ምክንያት አፍቃሪ ሻእቢያ በሆኑና በተቀረነዉ መካከል ትልቅ ገደል ተፈጥሮ ነበር።

ይሄ እንግዲህ እስከአሁን የነበረው ነዉ። ከሻእቢያ ጋር በመስራቱ ዙሪያ፣  ከአሁን በኋላ መከፋፈል ይኖራል ብዬ ግን አላስብም። ከሻእቢያ ጋር እንስራ የሚሉ ሰዎች እንደተሳሳቱ የተረዱበት ሁኔታ ነዉ ይመስለኛል። በተለይም የአርበኞች ግንባር አመራር አባላት መገደላቸዉና መሰወራቸው፤ የጀነራል ከማል ገልቹና ጀነራል ሃይሎ ጎንፋ መታሰር፣ የግንቦት ሰባት ጥቂት ሰራተኞች አስመራን ለቆ መዉጣት፣ አንጋፋ የተባሉ፣ አፍቃሪ ሻእቢያ የነበሩ፣ የኦነግ መስራቾችና የአመራር አባላት ኦነግን በአዲስ መልክ በአዲስ ስም አዋቅረዉ፣ ከሻእቢያ ጥገኝነት ነጻ የሆነ እንቅስቃሴ መጀመራቸው፣ የተባበሩት መንግስታት በኤርትራ ላይ የዘረጋዉ ማእቀብ፣ በአስመራ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየታየ የመጣዉ የፖለቲካ አለመረጋጋት፣  በኤርትራ በኩል የመታገል ፖለቲካ የማያዋጣ፣ የማያስኬድና እራስን እንደማጥፋት ያህል የሚያስቆጥር መሆኑ የሚያመላክቱ ናቸዉ።

በመሆኑም «ትግል በኤርትር በኩል ይደረግ አይደረግ» የሚል ክርክር፣  ከአሁን በኋላ ሊነሳ ይችላል ብዬ አላስብም። እንዳንስማማ ያደረገ ይሄ አንዱ ትልቁ መሰናክል ተወገደልን ማለት ነዉ።

ሁለተኛው መሰናክል የትጥቅ ትግል ወይስ ሰላማዊ ትግል የሚለዉ ነዉ። የትጥቅ ትግል ለማድረግ ቤዝ ያስፈልጋል። በርካታ የትጥቅ ትግል እናደርጋለን የሚሉ ቡድኖች አስመራ መጀመሪያዉኑ የተከሉት በዚሁ ምክንያት ነበር። መሳሪያ፣ መድሃኒት፣ ምግብ የሚያቀብላቸው፤ ወታደሮቻቸዉን የሚያሰለጥኑበት ኮሪዶር ያስፈልጋቸዋል። በኤርትር በኩል መስራቱ የማያወጣ በመሆኑ፣ ኤርትራን ካልተጠቀመን ደግሞ ሌላ ሊረዳ የሚችል ጎሮቤት አገር ባለመኖሩ፣ የትጥቅ ትግል ማድረጉ፣ ብንፈልገዉም፣ የማይቻል ነዉ።

«አይ የትጠቅ ትግሉን በአገር ዉስጥ ማካሄድ ይቻላል» የሚል ሃሳብ ሊቀርብ ይችላል። ይሄ ደግሞ በስድሳዎቹ እንደ ኢሕአፓ ያሉ የሞከሩት፣ ብዙ ወጣቶች ያሰጨረሰዉ  አይነት፣ አሁን ደግሞ በሲሪያ እያየን እንዳለነው፣  እንኳን ሊሞከር ሊታሰብ የማይገባ ነዉ።

ስለዚህ የትጥቅ ትግል ማድረጉ ዉጤት ካላመጣና ጠቃሚ ካልሆነ፣ እንቀጥለው እንኳን ብንል መቀጠል የምንችልበት ሁኔታ ከሌላ፣ ጥይት፣ መድሃኒት  የሚያቀርብለን የጎሮቤት አገር  ድጋፍ ካለገኘን፣ የትጥቅ ትግሉን እንደ አንድ አማራጭ መዉሰድ አይቻልም። በመሆኑም «ሰላማዊ ትግል ወይስ የትጥቅ ትግል» የሚል ክርክር ከአሁን በኋላ የሚነሳበት ምክንያት የለም። እንዳንስማማ ያደረገ ሁለተኛዉ ትልቁ መሰናክል በዚህ መልኩ ተወግደልን ማለት ነዉ።

ሌላዉ በዳያስፖራ ያሉ ተቃዋሚዎች እንዳይተባበሩ መሰናክል የሚፈጥረዉ ጉዳይ ቢኖር የአገር ቤቱ ትግል ነዉ። አንዳንዶቻችን በዉጭ ሆነን የአገር ቤት ትግሉን መምራት እንፈልጋለን። ይሄ ትልቅ ስህተት ነዉ። ከዉጭ በሚደረግ ትግል በኢትዮጵያ ለዉጥ ማምጣት አይቻልም። አራት ነጠብ። ዉጭ አገር ያለነዉ ማተኮር ያለብን የአገር ቤቱን ትግል በማገዙና በመርዳቱ ዙሪያ መሆን አለበት።

ኢሕአዴግ በሃያ አመታት እድሜዉ ለመጀመሪያ  ጊዜ የተነቃነቀዉ በቅንጅት እንቅስቃሴ ነዉ።  ያኔ በዉጭ አገር የሚገኘዉ ኢትዮጵያዊ  በድጋፍ ድርጅቶች በመሰባሰብ፣ የአገር ቤቱን ትግል ይረዳ ነበር። ያኔ በዉጭ ያሉ ተቃዋሚዎቾ በሕብረት ሥር በመሰባሰብ፣  የአገር ቤት ትግሉን ይረዱ ነበር። በዚህም ምክንያት ነዉ፣  ያኔ ያየነዉን ያየነዉ።

 

እርግጥ ነዉ ቅንጅት/ሕብረት መድረስ የነበረባቸው ደረጃ አልደረሱም። ነገር ግን ብዙ መንገድ ተኪዶ ነበር። እንግዲህ የሚያዋጣን በቅንጅት ጊዜ የተሰሩት መልካም ስራዎችን በመድገም ፣ የተሰሩ ስህተቶችን በማረም፣ የአገር ቤቱን ትግልና የዉጭ አገሩን ትግል አቀናጅቶ መቀጠሉ ነዉ እንጂ፣  ከዚህ በፊት በተሰሩ ስህተቶች ተስፋ ቆርጠን፣ ለዉርደት እራሳችንን አሳልፈን መስጠት የለብንም። እርግጥ ነዉ ከዚህ በፊት ወድቀናል፣ ቆስለናል። ገር ግን ከአሁን ለአሁን እንደገና እንወድቃለን ብለን፣  በፍርሃትና በጥርጣሬ ተሞልተን ለመነሳት ካልሞከርን፣ በወደቅንበት በስብሰን  ሞተን ነዉ የምንቀረዉ።

እንግዲህ በሰላማዊ የእምቢተኝነት ትግል የሚያምኑ፣ ከሻእቢያ ጋር ግንኙነት የሌላቸው ወይንም ግንኙነታቸውን በኢፊሴል የበጠሱ፣ የኢትዮጵያን አንድነት የሚያምኑ፣ ትግሉ አገር ቤት እንደሆነ ተረድተዉ፣  አንዳንዶች እንደሚያደርጉት ፣ የአገር ቤት ትግሉን ማሳነስ ሳይሆን፣  የሚደግፉ ኃይላት በሙሉ በአንድ ላይ መሰባሰብ አይቸግራቸውም። አለባቸውምም።

ድነት/መድረክ የድጋፍ ድርጅቶችና በነአቶ ኦባንግ ሜቶ የሚመራዉ የሶሊዳሪት ንቅናቄ፣ በሰላማዊ ትግል የሚንቀሳቀሱ መሆናቸዉ ይታወቃል። በነ ዶር ፍስሃ የሚመራዉ የሽግግር መንግስት ምክር ቤትም በይፋ የትግል ስልቱ ሰላማዊ እምቢተኝነት እንደሆነ አሳዉቋል። በዘጠና ሰባት ወቅት ከነዶር መራር ጉዲና ጋር በቅርበት ይሰሩ የነበሩ ድርጅቶች ያሉበት፣ ሸንጎ፣ በዉስጡ ያሉ ድርጅቶች አንዳንዴ «ሁሉ ገብ» ትግል የሚል ያለፈበት ፈሊጥ ቢኖራቸውም፣  ሸንጎ እንደ ሸንጎ በሰላማዊ ትግል የሚያምን ስብስብ ነዉ። በቀድሞ የኦነግ አመራር አባላት በቅርቡ የተቋቋመዉ፣ የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ግንባርም፣ ኦነግ ላለፉት በርካታ አመታት፣ ኦሮሞዎችን ከማስጨረስ ዉጭ በትጥቅ ትግሉ ዘርፍ ያስገኘው ዉጤት እንደሌለ በመረዳት ይመስለኛል፣ ሰላማዊ በሆነ መንገድ፣ ካስፈለገም ከገዢዉ ፓርቲ ጋር በመደራደር ለመንቀሳቀስ ፍላጎት እንዳለው ገልጿል።

እንግዲህ ከላይ የዘረዘርኳቸው አምስት ድርጅቶች ወይም የድርጅት ስብስቦች ሁሉም በሰላማዊ ትግል የሚያምኑ፣ ለኢትዮጵያ አንድነት የቆሙ፣ በሻእቢያ የማይታዘዙ እንደመሆናቸው ፣ በጋራ በሚስማሙበት ነጥቦች ላይ አብረው የሚሰሩበትን መድረክ ለማመቻቸት መሰናክሎች ያጋጥማቸዋል ብዬ አላምንም። በተለይም የዲፕሎማሲና የዉጭ ግንኑነትን በተመለከተ፣  በዳያስፖራ ያለዉን ኢትዮጵያዊ በማስተባበር ዙሪያ፣ የሚስራ አንድ ግብረ ኃይል በቀላሉ ሊያቋቅሙ ይችላሉ። እርግጠኛ ነኝ እንደ ዶር ዲማ ነግዎ፣ አቶ ኦባንግ ሜቶ፣ ዶር ፍስሃ፣ አቶ አክሎግ ልመንህ፣ ዶር አቻሜልህ የመሳሰሉ፣ የበሰሉ፣ ኢትዮጵያዉን የሚወዱ፣ የነዚህ ድርጅቶች አመራር አባላት ብቃቱ፣ ቅንነቱና  ቁርጠኝነቱ አላቸዉ ብዬ አምናለህ።

ይህ ግብረ ኃይል በዉጭ አገር የሚደረገዉን ትግል የሚመራ ይሆናል። ተቃዋሚዎችን ወክሎ ከምእራባዉያን ጋር ይነጋገራል። የተቃዋሚዉ ኃይል ተሰሚነት እንዲኖረው በአንድ ድምጽ ይናገራል። ሕዝባዊ እንቅስቃሴዎችን ፣ ሰላማዊ ሰልፎችን  ይመራል።  ከገዢው ፓርቲ ጋር መደራደር ካስፈለገ፣ አገር ቤት ካሉ ጋር በመቀናጀት፣ ዳያስፖራዉን ወክሎ ይደራደራል።  እኛም ከተለያዩ ማእዘናት የሚለቀቁ፣ አሰልቺና «እኔም ከማን አንሼ»  መግለጫዎችን ማንበባችን፣  ከተለያዩ ማእዘናትም እየተጎተትን  ግራ መጋባታችን ይቀራል።

ይህ ግብረ ኃይል፣ አገር ቤት የሚደረገዉን ትግል የሚመራ አይሆንም። ነገር ግን አገር ቤት የሚደረገዉን ትግል የሚያግዝ ይሆናል። በኢትዮጵያ የመንግስት ለዉጥ የሚመጣዉ አገር ቤት ያለዉን ሕዝብ ተደራጅቶች ሲንቀሳቀስ ብቻ ነዉ።

በፊታችን ጁላይ «የሽግግር ምንግስት ምክር ቤት»  የተሰኘው ድርጅት ሁሉንም የሚያሰባስብ ኮንፍራስ ጠርቷል። ይሄን አጋጣሚ መጠቀሙ ጥሩ ይመስለኛል። ይሄን በተመለከተ  ወደፊት በስፋት የምመለስበት ይሆናል።

 

እስከዚያዉ ሁላችንም ቸር ይግጠመን !

 


Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>