Quantcast
Channel: Ethiopian News | ዘ-ሐበሻ | Latest News Provider | News For All
Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

ሰቆቃወ ፕ/ር መስፍን ወልደ ማርያም- ኢትዮጵያዊ

$
0
0

በዲ/ን ተረፈ ወርቁ

የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁራን እስራኤላዊውን ነቢዩ ኤርምያስን ‹‹አልቃሻው ነቢይ›› በሚል ሰቆቃና ምሬት፣ ዕንባና ኀዘን ዕጣ ፈንታው የሆነበት የመከራ ሰው ሲሉ በዚህ ቅፅል ስም ይጠሩታል፡፡ ለነገሩ ራሱ ነቢዩም ቢሆን ስለ እስራኤል፣ ስለ እናት ምድሩ የታሪክ ስብራት አሊያም ፕሮፍ እንደሚሉት ‹‹የታሪክ መክሸፍ››፣ ስለ ሕዝቦቹ ስደት፣ መከራና ውርደት አነባ ዘንድ ምናለ ዓይኖቼ ሳያቋርጥ እንደሚፈልቅ የምንጭ ውኃ በሆኑልኝ ሲል የለመነና የተመኘ፣ የአገሩ ውርደት፣ የሕዝቡ መጎሳቆልና መዋረድ በእጅጉ እረፍት የነሳው ጻድቅና እውነተኛ ነቢይ ነበር፡፡ ነቢዩ በዚህ ተማጽኖውና ሰቆቃውም፡-
ስለ እስራኤል የታሪክ ስብራት/መክሸፍ፣ ስለ ሕዝቦቿ፣ ነገሥታቶቿ፣ ካህናቶቿና ሐሰተኛ ነቢያቶቿ ኃጢአትና ዓመፃ፣ በደልና ግፍ፣ የትውልዱ ውርደትና ጉስቁልና እንዲህ ሲል አንብቷል፣ ‹‹… ስለ ወገኔ እስራኤል ሴት ልጅ ቅጥቃጤና መከራ ዓይኔ በእንባ ደከመች፣ አንጀቴም ታወከ፣ ጉበቴም በምድር ላይ ተዘረገፈ፡፡›› በማለት ስለ ወገኑ፣ ሕዝቡና ምድሩ ነቢዩ ኀዘኑ ምን ያህል የከፋና የአገሩ ዕጣ ፈንታም ልቡን ምንኛ ክፉኛ ሰብሮት እንደነበር ‹‹የሰቆቃወ ኤርምያስ›› መጽሐፍ ይተርክልናል፡፡
ፍርድን በሚያዛቡ፣ ድሀን በሚበድሉና በሚያጎሳቅሉ፣ መበለቲቱንና ድሀ አደጉን በሚገፉ፣ ፍትሕን በሚያዛቡ አድር ባይ ሙሰኞቿ፣ የሕዝባቸውን ደም በከንቱ በሚያፈሱ ጨካኝ ነገሥታቶቿ፣ ኃጢአትን እንደ ውኃ በሚጨልጡ ካህናቶቿ፣ ሐሰተኛና ለባጭ በሆኑ ነቢያቶቿ፣ እውነትን በአደባባይ በሚረግጡ ገዢዎቿና ፈራጆቿ ምክንያት የአምላኳ ቁጣና መዓት በፈሰሰባት በእስራኤል፣ በአይሁዳውያኑ ሕዝቦች ‹‹የታሪክ መክሸፍ›› ታላቅ የትውልድ ኪሳራና ውርደት የተነሣ ነቢዩ ኤርምያስ የዕንባ፣ የሰቆቃ ሰው ‹‹አልቃሻው ነቢይ›› የሚል ስያሜ እንደተሰጠው የመጽሐፍ ቅዱስ ሊቃውንት ያስረዳሉ፡፡
በዚህ አጭር መጣጥፌ ፕ/ር መስፍንን እንደ እስራኤላዊው ነቢዩ ኤርምያስ የዕንባና የሰቆቃ ሰው ስላልኩበት ጉዳይ ወይም የታሪክ ተመሳስሎ አንዳንድ እውነታዎችን ላነሣ ወደድኹ፡፡ ለዚህ አጭር ጽሑፌ መነሻ የሆነኝ ከጥቂት ሳምንታት በፊት ፕ/ር መስፍን ወ/ማርያም ከሸገር 102.1 ሬዲዮ የቅዳሜ ጨዋታ ዝግጅት ላይ ከመዓዛ ብሩ ጋር ያደረጉት ለሰባት ሳምንታት የዘለቀ ቆይታቸው ነው፡፡

Prof. Mesfin Woldemariam

Prof. Mesfin Woldemariam


በሸገር 102.1 ሬዲዮ በቅዳሜ የጨዋታ እንግዳ ዝግጅት ላይ ጋዜጠኛ መዓዛ ብሩ ከእውቁ ምሁር፣ የሰብአዊ መብት ተሟጋች፣ ታሪክ ተመራማሪ፣ ፖለቲከኛ፣ ጸሐፊና ገጣሚ ከሆኑት ከአዛውንቱ ከፕ/ር መስፍን ጋር ያደረገችውን ቃለ መጠይቅ በታላቅ ጉጉትና ስሜት ውስጥ ሆኜ ነበር የተከታተልኩት፡፡ ፕ/ር መስፍን ለተከታታይ ሰባት ሳምንታት ከሸገር ሬዲዮ ጋር ያደረጉት ቆይታ አስደሳች፣ አስተማሪ፣ መካሪ፣ አዝናኝ፣ በአንጻሩ ደግሞ አሳዛኝ፣ የሚያስቆጭ፣ የሚያናደድ፣ በኀዘን፣ በቁጭትና በጸጸት ብግን የሚያደርግ፣ ቀቢጸ ተስፋ የተጫነው ባለ ብዙ ኅብር፣ ባለ ቡዙ መልክ ነበር ማለት ይቻላል፡፡
ፕሮፌሰሩ ከመዓዛ ጋር በነበራቸው ቆይታ ከልጅነት እስከ አሁን ዕድሜያቸው ድረስ ያሳለፉትንና የሚያስታውሱትን ትዝታቸውን ለዛ ባለው አንደበት ከገጠመኛቸው ጋር አዋዝተው ሊያጋሩን ሞክረዋል፡፡ ፕሮፌሰር እምነታቸውን፣ የሕይወት ፍልስፍናቸውን፣ ጽናታቸውን፣ ትዕግሥታቸውን፣ ወኔያቸውን፣ ውስጣዊ ስሜታቸውን፣ ኀዘናቸውን፣ ጸጸታቸውን፣ ብሶታቸውንና… እንዲሁም በማይጠፋና ሕያው በሆነ የፍቅር ማኅተም በውስጣቸው ለታተመችው ለውድ አገራቸው ኢትዮጵያና ለሕዝባቸው እንዲሆን የሚመኙለትን ሕልማቸውንና ምኞታቸውን ኀዘንና ብሶት እያበስለሰላቸው ቁጭትና ጸጸት በተቀላቀለበት ስሜት የልባቸውን አውግተውናልና እናመሰግናቸዋለን!!
ፕ/ር መስፍን ከሸገር ሬዲዮ ጋር በነበራቸው ቆይታቸው ለዕንባ፣ ለለቅሶ ቅርብ የሆኑ፣ አሁንም ድረስ የሰቆቃና የትካዜ ሰው መሆናቸውን በሚገባ እንድገነዘብ አድርጎኛል፡፡ ፕ/ር በዚህ የጨዋታ እንግዳ ቆይታቸው እንደ አይሁዳዊው የእግዚአብሔር ነቢይ ኤርምያስ በተለያዩ ጊዜያት በጸጸትና በቁጭት ዕንባቸው እንዲፈስና ነፍሳቸው ትካዜ ውስጥ እንዲገባ ያደረጋቸው ግላዊና አገራዊ የሆኑ ትዝታዎቻቸው፣ አገራችን በረጅም ዘመን ታሪኳ ያለፈችበትና አሁንም ገና በቅጡ ያልተላቀቅናቸው ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ቀውሶቻችን ለዚህች አጭር መጣጥፌ ዐቢይ ምክንያት ኾኖኛል፡፡
እኚህ ኢትዮጵያዊ ምሁር ሦስት መንግሥታትን ባፈራረቁባት እናት ምድራቸው ያሳለፉት፣ አሁንም በዘመናቸው እያዩትና እየሰሙት ያለው ማለቂያ የሌለው የሚመስለውና መፍትሔውን አገኘነው ስንለው እየራቀን ያስቸገረን የኢትዮጵያችን ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ፣ በየቤተ እምነቶች የነገሠው የሞራል ውድቀትና ዝቅጠት፣ የመንፈሳዊነት ድርቅ፣ ዘርኝነቱ፣ በሥልጣን መባለጉ፣ ሙሰኝነቱ፣ የፍትሕ እጦቱ፣ ከቀን ወደ ቀን እየተባባሰ የቀጠለውና ድኃውን ኅብረተሰብ ግራ ያጋባው የኑሮ ውድነቱ… ወዘተ ለፕሮፌሰሩ የሰቆቃና የእንጉርጉሮ፣ የብሶትና የትካዜያቸው ምክንያት የኾናቸው ይመስላል፡፡
ፕ/ር መስፍንን ባሳለፉት የሕይወት ዘመናቸው ክፉኛ ውስጣቸውን በኀዘን ጦር የወጋውና ዛሬም ድረስ ሲያስታውሱት ውስጣቸውን የሚረብሻቸውና ብርቱ ኀዘን ካጫረባቸው አገራዊ፣ ታሪካዊ ክስተት መካከልም የትውልድ እልቂት፣ የአገር ውርድት ወይም የፕሮፍን አገላለጽ ልዋስና የኢትዮጵያችን ‹‹የታሪክ መክሸፍ›› አንዱና ዋንኛ መለያ ተብሎ ሊጠራ የሚችለው እራሳቸው ፕሮፌሰር በዓይናቸው ዐይተው ምስክር የሆኑበትና የታዘቡት በአገራችን በተለይም በሰሜኑ ኢትዮጵያ ግዛት እንደ እርሳቸው አገላለጽ ‹‹ችጋር›› ያስከተለው ዘግናኝ እልቂትና ዓለምን ሁሉ እንባ ያራጨው የ፲፱፻፷፮ቱ ራብ ነው፡፡
ፕ/ር በዚህ አገራችን ኢትዮጵያ በዓለም ሁሉ ፊት ስሟን የቀየረውና የራብ፣ የእልቂት ምድር፣ አኬል ዳማ- የደም ምድር ተብላ እንድትጠራ፣ ሕዝቦቿም በኼዱበት ዓለም ሁሉ አንገታቸውን እንዲደፉ ምክንያት ስለሆነው የችጋር ርእሰ ጉዳይ ላይ በአገር ውስጥና በውጭ አገር በሚገኙ ስመ ጥር በሆኑ እንደ ሀርቫርድ ባሉ ዩኒቨርስቲዎች ሳይቀር ሰፊና ጥልቅ የሆነ ምርምርና ጥናት እንዳደረጉ አጫውተውናል፡፡
ይህ ክፉ ዘመን፣ ይህ ክፉ ራብ የሠራልኝ ሥራ፣
አባቴን ለስደት እናቴን ለአሞራ፡፡

የወንድ ልጅ እናት ታጠቂ በገመድ
ልጅሽን አሞራ እንጂ አይቀብረውም ዘመድ፡፡
ተብሎ አገሬው በታላቅ ኀዘንና ብሶት የተቀኘለት የራብና የእርስ በርስ ጦርነት የደም ታሪካችን ዛሬም ድረስ በጸጸትና በቁጭት የምናስታውሰው ነው፡፡ ይህ አሳፋሪ፣ ዘግናኝና አሳዛኝ የታሪክ ስብራትና የትውልድ እልቂት ፕ/ሩን አገሪቱን ‹‹የከሸፈ ታሪክ ባለቤት›› እስከ ማለት አደርሷቸዋል፡፡ እናም ዛሬም ድረስ በአዛውንቱ በፕ/ር መስፍን ልብ ውስጥ እማማ ኢትዮጵያ በውስጣቸው በምሬትና በብሶት የሚያነቡላት፣ ሙሾ የሚደረድሩላት የነፍሳቸው ስብራት፣ ሕመምና ስቃይ ሆና እንደዘለቀች ነው፡፡ ዛሬም በእኚህ አዛውንት ስለ እናት ምድራቸው ኢትዮጵያ ያላቸው ተስፋ ያለቀ፣ የተቆረጠ ነው የሚመስለው፡፡
ሌላኛው ፕሮፌሰር ከመዓዛ ጋር ባደረጉት የመጀመሪያው ሳምንት ቆይታቸው እስካሁንም ድረስ ውስጣቸውን በቁጭትና በጸጸት የሚያንገበግባቸው የዘጠኝ ወር ቤታቸው ለሆኑት፣ በመልካም ሥነ- ምግባር ተቀርጸው እንዲያድጉ ትልቅ መሠረት ለጣሉላቸው ለወላጅ ለእናታቸው የሚገባቸውን ውለታ ሳያደርጉላቸው በሞት የመለየታቸው ጉዳይ እንደሆነ እንባና ሳግ በተቀላቀለ ስሜት አጫውተውናል፡፡
እኚህ ዕድሜ ባለጠጋ በሆኑ አዛውንትና አንጋፋ ምሁር ስለ እናታቸው ባሰቡ ቁጥር ዓይናቸውን በሚሞላው እንባቸውና ውስጣቸውን በሚያብሰለስላቸው ጸጸትና ኀዘን ውስጥ በፕሮፌሰሩ የልባቸው ዙፋን ላይ የነገሠችውና የትካዜያቸውና የሰቆቃቸው ምክንያት የኾነችው የትልቋና የሁላችንም እናት የሆነችው የምድራችን፣ የእማማ ኢትዮጵያ ኀዘንና ትካዜ፣ ብሶትና ሰቆቃ የሞላበት የተዥጎረጎረ የታሪኳ ገጽ ተራ በተራ፣ ምዕራፍ በምዕራፍ እየተገለጸ ከፊታችን ድቅን እንደሚልብን አስባለሁ፡፡
እናም ፕሮፍ ለሰባት ሳምንት በዘለቀ የቅዳሜ ጨዋታቸው ይኸውን የተዥጎረጎረ፣ በደም የቀላ የኢትዮጵያን ታሪክ እያነሡ፣ እየፈተሹና እንያንገዋለሉ ‹‹የታሪካችንን መክሸፍ››፣ የሕዝባችንን ውርደትና ጉስቁልና እንደ አይሁዳዊው ነቢዩ ኤርምያስ በእንባ፣ በኀዘንና በሰቆቃ ተውጠው ተረኩልን፡፡
ፕሮፌሰር መስፍን አክለውም የራብና የእርስ በርስ ጦርነት፣ የእልቂት ምድር-አኬል ዳማ በሚል ስያሜ የጠለሸውን የትናንትና መልካም ታሪኳን፣ ስሟንና ክብሯን ለመመለስና ለተሻለ ነገ ጉልበቴ በርታ በርታ እያለች ያለችውን እናት ኢትዮጵያን የእግር እሳት ሆኖ እየለበለባትና አላንቀሳቅሳት ያለ ሌላ የዘረኝነት/የጎሰኝነት ክፉ አደጋ እንደተጋረጠባት በስጋት ስሜት ሆነው ነገሩን፣ ውስጣቸውን ክፉኛ ፍርሃት፣ ቁጭትና ሥጋት እያረሰው፡፡ እናም ከዚህ ዙሪያችንን ከከበበን ክፉ አደጋ አገሪቱን ይታደጉ ዘንድ በሥልጣን ላይ ላሉት ሰዎች አስተዋይና ይቅር ባይ ልቦናን ፈጣሪ ይቸራቸው ዘንድም ፕሮፌሰር በሸገር የቅዳሜ እንግዳ ቆይታቸው ከልብ ለምነዋል፣ ተማጽነዋል፡፡
ለፕሮፌሰሩ ከወዲሁ ስለ ነገይቱ ኢትዮጵያ የታያቸው ምስል ዝብርቅርቅ ያለ፣ ጥፋትን ያዘለ፣ የማይስብ፣ አንዳች ውብና አዲስ ተስፋ የማይንጸባረቅበት፣ አሳሳቢና ድንግዝግዝ ይመስላል፡፡ እናም በፕሮፌሰር ልብ ውስጥ ብዙ ሐዘን፣ የማያቋርጥ ጭንቀት፣ በቃላት ሊገለጽ የማይችል ቁጭትና እልህ የሚንጠው ብርቱ የነፍሳቸው ጩኸት ስለ እናት ምድራችን ኢትዮጵያ በቃለ ምልልሳቸው ውስጥ በለሆሳስ ተሰማኝ፣ አሊያም ቁጭታቸውንና ሐዘናቸውን ለምንጋራ ሁሉ እንዲያ እንደሚሰማን ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ እኔም የኸው የፕሮፌሰሩ ሰቆቃና ብርቱ ኀዘን ነው ብዕሬን እንዳነሳ የገፋፋኝም፡፡
በእርግጥም እኚህ የዕድሜ ባለጠጋ፣ ምሁር አዛውንት የዕድሜያቸውን ግማሽ ማለት ይቻላል ስለ እናት ምድራቸው፣ ኢትዮጵያ ልባቸው በኀዘን ጦር እንደተወጋ፣ ዓይናቸው ዘወትር እንዳነባ፣ እንደ አይሁዳዊው የእግዚአብሔር ነቢይ ኤርምያስ የምሬትና የብሶት፣ የትካዜና የሰቆቃ ሰው ሆነው አብዛኛው ሕይወታቸውን ዘመን እንደፈጁ ነው በቃለ ምልልሳቸው የነገሩን፣ ያጫወቱን፡፡
እናም ፕሮፌሰር ታሪኳ ሁሉ የከሸፈ ነው፣ የልማት፣ የዕድገትና የብልጽግና ጎዳናዎቿ ሁሉ በእሾህ የታጠሩባት ናት፤ እንዲያም ሲል ደግሞ ‹‹በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ›› እንዲሉ ሌላ ውስጥ ለውስጥ እየነደደ ያለ ሞትን፣ ጥፋትንና እልቂትን የደገሰልን የዘረኝነት፣ የመለያየት አደጋ ተጋርጦባታል ለሚሏት አገራቸው ኢትዮጵያ ሥጋታቸውና ጭንቀታቸው እጅጉን የበረታ፣ ያየለ ነው የሚመስለው፡፡
ይህች በፕሮፌሰሩ ሕሊና ውስጥ የዘመናት ታሪክ ልቃቂት ውሏ ሲተረተር፣ ሲገለጽ ከከሸፈ ታሪክና ገድል በቀር ሌላ ታሪክ የሌላት፣ እድገትና ብልጽግናን ያዝኳቸው ስትላቸው የሚያመልጧት ነጻነትና ሰላም፣ ፍትሕና ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ብሎ ነገር ሕልም የሆነባት፣ በእርስ በርስ እልቂት፣ በፍጅትና በራብ የምትታወቅ፣ በአብራኳ ክፋዮች፣ በገዛ የማኅፀኗ ልጆቿ ደም የምትዋኝ፣ በደም ሸማ፣ በደም ሰንደቅ የደመቀች፣ በደም ታሪክ የተንቆጠቆጠች የተባለች ኢትዮጵያ- ምስሏም፣ ገጽታዋም ይኽው ነው በፕሮፌሰር መስፍን ልብ፣ እይታና የረጅም ዓመታት ትዝታቸው ትርክት ውሰጥ፡፡
በማብቂያዬም ይህን ሰቆቃወ ፕ/ር መስፍን-ኢትዮጵያ ብዬ የሰየምኩትን አጭር መጣጥፌን በእንዲህ ቀቢጸ ተስፋ ባየለበት የጨለምተኝነት መንፈስ ልደምድመው አልወደድኩም፡፡ በፕሮፌሰር መስፍን እይታ የረጅም ዘመን ታሪክ መዝገቧ ሲከፈት በአብዛኛው ‹‹የከሸፈ ታሪክ›› ባለቤት ናት ብለው ስለሚጠሯት ኢትዮጵያ ታሪክ አንድ የሚግረን ትልቅ ሐቅ እንዳለ ለማንሣት እወዳለኹ፡፡
ይኸውም ይህች አብዛኛው ታሪኳ የከሸፈ ነው፣ ሞተች በቃ፣ ከአሁንስ ወዲያ ተስፋም የላት የተባለች ኢትዮጵያ፣ በተለያዩ ዘመናት ከመውደቅ፣ ከውርደት፣ ከሽንፈት ታሪኳ እንደገና የተቀበረችበትን አፈር አራግፋ ዳግም በአዲስ የዘመን ብስራት ትንሣኤ ብድግ ያለችበት ወርቃማ የታሪክ ዘመንም እንደነበራት ማሰብ፣ ማስታወስ ያለብን ይመስለኛል፡፡
ይህን አሳቤን የሚያጠናክርልኝ አንድ የጥናት ወረቀት እዚህ ላይ ማነሣቱ ተገቢ ይመስለኛል፡፡ ራሳቸው ፕ/ር መስፍን ተሳታፊ በነበሩበት በ1997 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ኢኮኖሚክስ ባለሙያዎች ማኅበር ባዘጋጀው ‹‹Vision 2020›› በ2020 ልናያት የምንፈልጋት ወይም የምንመኛት ኢትዮጵያ በሚል የውይይት መድረክ ላይ የታሪክ ምሁሩ ፕሮፌሰር ባሕሩ ዘውዴ፡- ‹‹ምን አለምን? የት ደረስን? ወዴትስ እያመራን ይሆን?›› በሚል ርዕስ ባቀረቡት የጥናት ወረቀታቸው እንዲህ ብለው ነበር፡-
… ከኢትዮጵያ ታሪክ የምንገነዘበው አንድ ሐቅ ቢኖር፣ ካንዴም ሁለቴ አለቀላት፣ ፈረሰች ተብሎ ከተደመደመ በኋላ እንደገና እንዴት እንዳሰራራችና አዲስ ሕይወት እንደዘራች ነው፡፡ በአክሱም ዘመን ፍፃሜ፣ በ፲፮ኛው መቶ ዓመት፣ በዘመነ መሳፍንትና በዘመናችንም በአብዮቱ ወቅትና በደርግ ውድቀት ጊዜ የታየው ሁኔታ ይኸው ነው፡፡ ይህ የኢትዮጵያ እንደገና የማንሰራራት ችሎታ ሀገሪቱ በዘመናት የታሪክ ሂደት ያካበተችው ሰብዓዊና ባሕላዊ እሴቶች ውጤት ይመስለኛል፡፡
ፕሮፌሰር ባሕሩ ተስፋዋ የተቆረጠ፣ የጨለመ ነው የተባለችው ኢትዮችጵያችን ከአሁን ወዲያ አበቃላት፣ በቃ፣ ሞተች፣ ተረሳች ስትባል ዳግም ያንሰራራችበት የትንሣኤ/የሕዳሴ ታሪክ ዘመናት እንደነበሯትም ማስታወስ አለብን፡፡ ፕ/ር ባሕሩ መጪው ዘመን ለኢትዮጵያችን የተሻለና ብሩህ ዘመን እንዲሆን የምንመኝ ሁሉ ብሩህ ተስፋን ሰንቀን በአንድነት እጅ ለእጅ በመያያዝ መነሳት እንደሚገባን የሚያሳስበን ምሁራዊ አስተውሎት የታከለበት ትንታኔ ነው በዚህ ጥናታዊ ጽሑፋቸው ያስቀመጡት፡፡
ስለሆነም በዚህች አጭር መጣጥፌ መደምደሚያዬም ይህችን የሁላችንም የሆነች ኢትዮጵያችንን ለመጪው ትውልድ እንደተከበረች፣ እንደታፈረችና እንደተፈራች በክብር ማስተላለፍ አገራችንን እንወዳለን፣ ለወገን እንቆረቆራለን የምንል ኢትዮጵያን ሁሉ ግዴታና ሓላፊነት እንደሆነ ነው የማስበው፡፡
ስለዚህም እንደ አገርም፣ እንደ ሕዝብም ለረጅም ዘመናት በአንድነት አስተሳስሮ ያቆየንን ታሪካዊ፣ ሃይማኖታዊ፣ ባህላዊ እሴቶቻችንና ቅርሶቻችንን ጠብቀን፣ ያለፈውን የታሪክ ጠባሳችንን/ቁርሾአችንን በይቅርታ ልብ ሽረን፣ እያመረቀዘ ያስቸገረንን የትናንትና ስብራታችንን፣ ቁስላችንን በፍቅር ዘይት አለስልሰንና አክመን እጅ ለእጅ በመያያዝ- የሰላምና የአንድነት፣ የልማትና የዕድገት ጮራዋ፣ ጸዳሏ የሚደምቅባትን ታላቋን ኢትዮጵያን ዕውን ለማድረግ በአንድነት ሆነን በፍቅርና በይቅርታ ልብ ቃል ኪዳናችንን ማደስ እንደሚኖርብን ማስታወስ፣ ማሳሰብ እወዳለኹ፡፡
እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ!!


Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>