(ዘ-ሐበሻ) የኢትዮጵያ ሕዝብ የጋራ ትግል ሸንጎ (ሸንጎ) በዛሬው እለት በሰማያዊ ፓርቲ ጠሪነትና በተለያዩ ድርጅቶች ተባባሪነት በአዲስ አበባ ለተካሄደው ሰላማዊ ሰልፍ ያለውን አድናቆትና የትግል አጋርነት በድጋሜ እንደሚገልጽ ዛሬ ባወጣው መግለጫ አስታወቀ። ድርጅቱ ለዘ-ሐበሻ በላከው መግለጫ “ይህ በሽዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ጎሳ፣ዕድሜ፣ጾታና እምነት ሳይነጥላቸው በአንድ ሆነው የሀገራችንን ህብር በሚያንጸባርቅና በታላቅ ሥነስርዓት የጋለ ስሜታቸውን በይፋ የገለጡበት ህዝባዊ ሠልፍ ፣ በሕዝባችን ላይ የተጫነው የፍርሀት ድባብ እየተሰበረ መምጣቱን የሚያመለከት ታላቅ እርምጃ ነው።” ብሎታል።
“ይህ እጅግ ብዙ ወጣቶችን ያሳተፈ፣ ስሜት ቀስቃሽና ታላቅ ወኔ የታየበት የህዝብ ቁጣ፣ ህዝባችን ለዓመታት የተጫነበትን የግፍ ቀንበር ሊሸከም የሚችልበት ጀርባ እንደሌለው በግልጥ ያሳየበት ቀን ነው።” የሚለው የሸንጎ መግለጫ “ይህ ስላማዊ ሰልፍ የኢትዮጵያ ህዝብ መሰረታዊ መብቶች ሙሉ በሙሉ እንዲከበር፣ ጎሳ ተኮር የህዝብ ማፈናቀል እንዲያበቃ፣ የኑሮ ውድነት እንዲወገድ፣ በፖለቲካ ጉዳይ በእስር ላይ ያሉ የፖለቲካ ድርጅት መሪዎችና ነጻ ጋዜጠኞች በአስቸኳይ እንዲፈቱ፣ የመደራጀት መብት ሙሉ በሙሉ እንዲከበር፣ በየሃይማኖቶች የውስጥ ጉዳይ የመንግሥት ጣልቃ ገብነት እንዲቆምና የታሰሩት የሙስሊሙ ተወካዮች እንዲፈቱ በመጠየቅ የሀገሪቱን ሕዝብ ብሶት በሚገባ አንፀባርቋል።” ካለ በኋላ “የኢትዮጵያ ሕዝብ የጋራ ትግል ሸንጎ (ሸንጎ) እነዚህና ሌሎች መሰረታዊ የመብት ጥያቄዎች ባሰቸኳይ እንዲመለሱና ከዚህም አልፎ የአምባገነንነትና የጎጠኛ ስርዓት አክትሞ ህዝብ በምርጫ የራሱን መንግሥት የመመስረት መብቱ እንዲረጋገጥ ለማስቻል ከተለያዩ ኢትዮጵያዊ ሀይሎች ጋር ተባብሮ ትግሉን እንደሚቀጥል አሁንም ያረጋግጣል።” ሲል አቋሙን አስታውቋል።
“በሀገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን፣ ከሀገር ውጭም፣ ዓለምአቀፉ ህብረተሰብ፣ ያለውን ሁኔታ ይበልጥ ተረድቶ፣ በመፍትሄ ፍለጋው አንጻር፣ አወንታዊ ሚና እንዲጫወት፣ ሸንጎው የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን አጠናክሮ ይቀጥላል።” ሲል አቋሙን ያጠናከረው ሸንጎ “የተባበረ የህዝብ ትግልን ሊመክት የሚችል ምንም ሀይል የለምና፣ መብታችንን ለማሰከበር ትግላችን ተጠናክሮ ይቀጥል። ዛሬ የተካሄደው ሕዝባዊ የተቃውሞ ሰልፍ፣ ለተከታታይ ሕዝባዊ ንቅናቄዎች በር ከፋች እንጂ መደምደሚያ እንደማይሆን ሸንጎው ይተማመናል።” ብሏል።
ሸንጎው በመግለጫው ማጠናቀቂያ ላይም “ሰላማዊው ትግሉ እንዳይቀጥል የሕወሓት/ኢሕዴግ አሸባሪ አገዛዝ ብዙ ጥረት እንደሚያደርግና ደፍረው በወጡትና ባዘጋጁት ላይም ስበብ እየፈጠረ የሽብር ክንዱን ከመሰንዘር ስለማይመለስ ከወዲሁ ነቅቶ መጠበቅና በጋራ መከላከል የሚቻልበት ዘዴ እንዲፈጠር፣ ተደናግጦና በርግጎም የተጀመረው የነጻነት ጉዞ እንዳይከሽፍና እንዳይቆም ሸንጎ ያሳስባል። ሁሉም ዜጋ የተቻለውን ሁሉ እንዲያደርግም ጥሪ ያደርጋል።” ብሏል።
↧
ሸንጎ በአ.አ የተደረገውን ሰልፍ “በሺዎች የተጀመረው እንቅስቃሴ የሚሊዮኖች ይሆናል”አለ
↧