Quantcast
Channel: Ethiopian News | ዘ-ሐበሻ | Latest News Provider | News For All
Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

ወርሃ ግንቦት ሲታወስ! – (ኢሮብ መብት ተማጓች ማኅበር የበተነው ጽሑፍ)

$
0
0

irob ethiopia ከ1990 ዓ.ም ወዲህ ወርሃ ግንቦትን በተለይ ደግሞ ግንቦት 23 ደስታና ሀዘን በተቀላቀለው ስሜት ነው የምናስታውሰው። ሀዘን የሚሆንብን ሻዕቢያ እንደሚወረን እየታወቀ የኢትዮዽያ መንግሥት ምንም ዓይንት ዝግጅት ሳያደርግ በመወረራችን ዳር ድንበራችንን ለማስከበር ከፍተኛ የሆነ የሰውና የንብረት መስዋዕትንት በመክፈላችን፣ ወረራውን ተከትሎ በሻዓቢያ ታግተው የተወሰዱ መቶ-እጥፍ ወገኖቻችን እስከ ዛሬ የደረሱበት ሳይታወቅ ይኸው አስራ ሶስት ዓመታት ማስቆጠራችንና ከሁሉም በላይ ደግሞ ታግተው የተወሰዱ ዜጎችን በሚመለከት የኢህአዴግ አገዛዝ ምንም ዓይነት እርምጃ ባለመውሰዱ፤ ወራሪው የሻዓቢያ ሠራዊት ዳር ድንበራችንን መውረሩና ህዝባችንን ለሁለት ዓመት በባርንት ቀንበር ሥር ማቆየቱ አንሶ ሉዓላዊ የኢትዮጵያ ግዛቶችን ለድርድርና ለግልግል ዳኝነት በማቅረብ ለሻዓቢያ ፍላጎት እንድንንበረከክ በመደረጉ፤ የኢትዮጵያ ሉዓላዊነትን ማስከበር በሚመለከት፡ በኢህአዴግ አገዛዝ ላይ እምነት እንድናጣ ስለሆን ሻዓቢያ በወረራ ይዟቸው የነበሩ የኢሮብ ህዝብ መኖሪያ አከባቢዎች ዛሬም የጦር ሰፈር በማድረግ በርካታ ወገኖቻችን ለልዩ ልዩ በሽታዎች መዳረግ፣ ለባህላችን ውድቀትና የበርካታ ወገኖቻችን ትዳር መፍረስ፣ እንዲሁም በአከባቢው የነበሩ ዛፎችና ደን፣ ሥሩ እየተነቀለ ለማገዶ እንጨት መዋል ወዘተ. እንጂ አከባቢያችን የልማት ማእከል ሲሆኑ ለማየት ያለመታደላችን፤ ናቸው።
በዚህ ሁሉ አሳዛኝ ሰቆቃና ቊጭት ማኸልም የምንጽናናባቸውና የምንኮራባቸው በዜጎቻችን የተፈጸሙ ጀግንነቶችና ቁምነገሮችም አሉ። ይኸውም፤ እናት ኢትዮጵያ ለሕይወቱ የማይሳሳ፤ ለነፃነቷና ለክብሯ ውድ ሕይወቱን የሚሰጥ ጀግና ህዝብ ያላት ሀገር መሆኗ ነው። እንደ ትናንቱ በሻዕቢያ የእብሪት ወረራ ወቅትም ውድ ልጆቿ ከአጽናፍ እስከ አጽናፍ ቀፎው እንደተነካ ንብ አንድ ላይ ሆ ብለው በመነሳት ለክብሯ ሲሉ ከፍተኛ መስዋእትነትን ከፍለዋልና እጅግ በጣም እናከብራቸዋለን። እነዚህ ሰማእታት የከፈሉት መስዋዕትነትም እኛ ብቻ ሳንሆን መጪ ትውልዶችም በኵራት የሚመለከቱትና የሚመኩበት ከመሆኑም በላይ ለዘለዓለም ሲዘክሩት የሚኖር ይሆናል። አመራሩ ቢክዳቹህም አገራዊ ግዳጃቹህን ተወጥታችኋልና እናከብራቹሀለን በናንተም እንኮራለን ልንላቸው እንወዳለን።
በሁለተኛ ደረጃ የኢህአዴግ አገዛዝ ህዝባችን ደም ገብሮ ወረራውን የቀለበሰ ማግስት የኢህአዴግ አመራር አልጀርስ ድረስ በመጓዝ ለአቶ ኢሳያስ እጅ ነስቶ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት የሚያስደፍር ሰነድ በመፈራረም የግልግል ፍርድ ቤት እንዲቋቋም መፍቀዳቸው የሚታወስ ነው። በዚህ ውል መሠረት የሚከራከርላት ወኪል ያልነበራት ኢትዮጵያ ሄግ ላይ የተሰየመው “የግልግል ፍርድ ቤት” ሲፈርድባት ተመልክተናል። ሽንፈቱን እንደ ድል የቆጠሩት የኢህአዴግ መሪዎች ብይኑ የተሰጠበት ዕለት ከጠየቅነው በላይ ተፈርዶልናል ብሎ በመዋሸትና በለመዱት የማጭበርበር ተግባር ዜጎችን ለማታለል በመሞከር ህዝብ ደስታውን እንዲገልጽ ጥሪ ማቅረባቸውም የሚዘነጋ አይደለም። እዚህ ላይ ከጠየቅነው በላይ አግኝተናል ሲሉ የጠየቁት ከየት እስከ የት እንደነበረ ግልጽ አለመሆኑ ልብ ሊባል ይገባል። የኢሮብ ርእሰ ከተማ ከዓሊተና ወደ ዳውሃን የተዛወረበት ሁኔታን ግምት ውስጥ በማስገባት ካየነው “ከጠየቅነው በላይ አግኝተናል” የሚለው ሐረግ ምን ማለት ሊሆን እንደሚችል እያንዳንዱ አንባቢ የራሱ ድምዳሜ ላይ እንዲደርሰ መልሱን በባዶ ሙላ ልናልፈው መርጠናል።
ዋናው ቁምነገሩና እጅጉንም የኮራንበትና ቀጣይ ትውልዶችም እጅጉን በኵራት የሚያስታውሱት ታሪካዊ ትምህርት ያገኙበታል ብለንም የምናምነው ህዝባችን የኢህአዴግ መሪዎች ዳር ድንበርን የመስጠት ውዲት ቀድሞ በመገንዘቡ ሴራውን ለማክሸፍ ዝግጁ ሆኖ መጠበቁ ነው። የህወሓት/ኢህአዴግ መሪዎች ሄግ ላይ የገጠማቸው ድል እንበለው ሽንፈት (እንደየአተረጓጕማችን ሊለያይ ይችላል) እንደ ደረሰ ለጭፈራ ካነሳሱት ህዝብና ከነባራዊ ሀቁ ጋር መፋጠጥ ነበረባቸው። በመሆኑም፤ ስለደረሰው ሁኔታ ለማስረዳት ከህዝብ ጀርባ ደባ ለመፈጸም ሰፊ ውስጣዊ ውይይት በማካሄድ ስራ ተጠመዱ። በዚህም፤ ግዛታችንን ለሻዓቢያ አሳልፈው ለመስጠት የነበራቸው ዝግጁነት ተግባራዊ ማድረግ ስለፈለጉ ህዝብን የሚያግባቡበት ሌላ ዘዴ ስላጡ መልካም አማራጭ ሆኖ ያገኙት የደረሰውን ሽንፈት ለኤርትራ በተወሰኑት አከባቢዎች ነዋሪ ለሆነው ህዝብ በየቀበሌው እየለያዩ ለማስረዳት በመወሰን አገባብ የሌለውን የክህደት ሥራውን እንዲያከናውኑ ካድሬዎቻቸውን ማንቀሳቀስ ጀመሩ። ከፍተኛ ካድሬዎቻቸውም በሄግ ብይን መሠረት የምትኖሩበት መሬት ለኤርትራ እንዲሰጥ ስለተወሰነና ኒውዮርክ የሚገኘው የተባበሩት መንግሥታትም ሊቀጣን ስለሆነ እናንተ ትነሳላቹህ መሬቱም ለኤርትራ ይሰጣል በማለት ለማስፈራራትና ተጽእኖ ለመፍጠር ሙከራ አደረጉ። በዛን ወቅት ነበር የኢሮብ ህዝብ ሄግም ሆነ የተባበሩት መንግሥታት የምትሉዋቸው ለኤርትራ የሚሰጡት መሬት ካላቸው ይስጡዋቸው፤ ይህ ግን የኛ መሬት ነውና እንኳን መሬታችንን ተንከባልሎ ወደ ኤርትራ ግዛት የሚወድቅ ድንጋይ ቢኖር እንኳን የሚከፈለውን ከፍለን እንመልሳለን ነበር ያላቸው። ይህ ህዝባችን ለመብቱ መከበር የሰጠው የእምቢተኝነት መልስ እጅጉን የሚያኮራ ነው። በመሆኑም፤ ይህ የህዝብ እምቢተኝነት ሉዓላዊ የኢትዮጵያ ግዛት እስከ ዛሬ ሳይሸራረፍ እንዲቆይ አስገድዷልና እጅጉን አስደስቶናል።
ስለሆነም፤ ትውስታችን በቊጭትና በደስታ በተደበላለቀ ስሜት የሚገለጽ ነው ስንል እነዚህን ከላይ የጠቃቀስናቸውን ጭብጦችና ስሜቶች ግንዛቤ ውስጥ በማስገባት ነው። እዚህ ላይ አንድ ልብ ሊባል የሚገባ ቁምነገር መኖሩን አንባቢ እንዲገነዘበው እንፈልጋለን። ይኸውም፤ ለኤርትራ ሊሰጧቸው ባዘጋጁዋቸው አከባብዎች የሚኖሩ ህዝቦችን በተናጠል ከቦታው እንዲነሱ ሲያዋክቧቸው ለሌላው የኢትዮጵያ ህዝብ የተገለጸ ነገር እንዳልነበረ ነው። በአቶ መለስ ዜናዊና በአቶ ሥዩም መስፍን በመገናኛ ብዙኃን ለኢትዮጵያ ህዝብ የተነገረው “የአሸንፈናል” የማጃጃል ሙከራ እንዳይከሽፍ በመስጋት ሀቁን ከኢትዮጵያ ህዝብ እንዲደበቅ የማድረግ ሙከራ እንደነበረ
መዘንጋት የለበትም። የኢሮብ ህዝብ እሺ ብሎ የህወሓት/ኢህዘዴግና የካድሬዎቹን ፍላጎት ተቀብሎ ቢሆን ኑሮ፤ ጉዳዩ እንዳለ ተሸፋፍኖ ይቀር እንደነበረ የሚያጠራጥር አይደለም። እነሱ ያሰቡት የኢትዮጵያ ህዝብ ሳያውቀው በሎህሳሳ መሬቱን ለኤርትራ በመስጠት የኢትዮጵያ ህዝብ ሳያውቀው ሸፋፍነው በደባ ሊያልፉት ነበር። የኢሮብ ህዝብ ግን እምብየው፤ ይህ የኛ መሬት ነው በማለት ለትውልዶች የሚተርፍ ኩራት አለበሱን። የህወሓት/ኢህአዴግ ፍላጎት ግቡን መትቶ ቢሆንና ህዝቡ እሺ ብሎ መሬቱን ለቆ ወጥቶላቸው ቢሆንና የኢትዮጵያ ህዝብ ጉዳዩን አጣርቶ ቢደርስበት፤ የህወሓት/ኢህአዴግ መሪዎች ያለ ምንም ሓፍረት “የኢሮብ ህዝብ በራሱ ፈቃድ ነው ቦታውን የለቀቀው። ባይሆን ኑሮ እኛ ግዛታችንን አሳልፈን አንሰጥም ነበር” ወይም ደግሞ “የኢትዮጵያ ህዝብ ዳር ድንበሩን ሳያውቀው ስለቆየ ነው እንጂ እንዲያውም የኛ ያልነበረ እነ ዓሊተናን አስመልሰናል” የሚል ራስን የመሸንገል አባዜ ይዘው ብቅ ሊሉ ይችሉ እንደነበር ሳይታለም የተፈታ ነው። ዛሬ ስለባድመ ስያወሩ ስለኢሮብ ግዙፍ መሬት ወደ ኤርትራ መካለል ማንሳት የማይፈልጉበት ምክንያትም ይህ ነው።
ስለዚህ የኢሮብ አባት እናቶች አኵርታቹሁናልና ምስጋና ይድረሳቹህ!
ይህንን እንደመንደርደርያ ካኖርን ዘንዳ፤ ግንቦት 23 ቀን 1990 ዓ.ም እሁድ ሌሊት የሻዓቢያ ሠራዊት ለመጀመሪያ ጊዜ የኢሮብን መሬት እንደወረረ ይታወቃል። የሻዓቢያ ወረራ ያተኵረው ዓይጋ ላይ ነበረ፣ዓላማውም ከኢሮብ መሬት ለጦር እቅድ ምቹ ከሆኑት አንደኛ የሆነውን የዓይጋ ከፍታዎችን በቁጥጥራቸው ሥር ማድረግ ነበር። ይሁን እንጂ ለኢሮብ ጅግኖች ምስጋን ይግባቸውና የሻዕቢያ እኩይ እቅድ በዛ ቀን አልተሳካም። በዚሁ ዕለት ንጋት ላይ መሬቱ መወረሩን የተገነዘበ የአከባቢዉ ህዝብ ከጠላት ትጥቅ እየነጠቀ በመዋጋት ወራሪውን ወደ መጣበት መለሰ። ስለዚህም ”ዕጡቃት-ሰንበት” የሚል ስያሜ አገኘ። በዚህ ምክንያት ግንቦት 23 ወይም በዚሁ ሳምነት ሌላ አብዛኛው የኢሮብ ህዝብ የተሰማማበት ቀን (24፣ 25…) ከዓይጋ ኮረብታዎች ጀምረው ከኢሮብ ዳርቻ በጣም እስክርቁ ድረስ ሻዓቢያን እያሳደዱ በመግረፍ ላይ የወደቁት ሊረሱ የማይገባ ጀግኖቻችን መታሰቢያ ቀን በየዓመቱ በዚሁ ሳምነት እንዲዘከርና እንዲከበር የኢሮብ መብት ተማጓች ማኅበር (ኢ.መ.ተ.ማ) ለኢሮብ ህዝብ ሃሳቡን ያቀርባል።
ዕለተ ሰንበት ግንቦት 23 ቀን 1990 ዓ.ም እብርተኛው የሻዓቢያ ሠራዊት የኢሮብን መሬት ለመቆጣጠር በታንኮችና በከባድ መሣርያ በመታጀብ የዓይጋ ኮረብታዎችን ለመቆጣጠር ዘመተ። በጊዜው በኢትዮጵያ መንግስት በኩል በቦታው ምንም የመከላከያ ኃይል ስላልነበረ፤ ሉዓላዊ የኢትዮዽያ መሬት የመከላከል ዕዳ በኢሮብ ህዝብ ጫንቃ ላይ ወደቀ። በመሆኑም በወቅቱ በኢሮብ ወረዳ ቀላልና ጊዜ ያለፈበት መሳሪያ የታጠቁ በጣት የሚቆጠሩ ምሊሻዎች ህዝባቸውን ከኋላቸው አስከትለው ሻዕቢያን ለመጋፈጥ ወደ ዓይጋ ከፍታዎች ተምዘገዘጉ። ምልሻዎቹ የኢሮብ ልማዳዊ የመልእክት ማስተላለፍ ዘዴን በመጠቀም የወረራውን ዜና ባጭር ጊዜ ውስጥ ህዝብ ጆሮ እንዲደርስ አደረጉ። ዜናውን የሰማ ህዝብም ቀፎው እንደተነካበት ንብ መጥረብያ ያለው መጥረብያውን፤ ገጀራ ያለውም ገጀራውን በማንሳት አገርን ለመከላከል ከየአከባቢው ወደ ዓይጋ ኮረብታዎች መትመም ጀመረ። ምልሻዎቹም ጋራ ሽንተረሩን አብጠርጥረው በሚያውቋቸው የዓይጋ ኮረብታዎችና የዘገብላ በረሃ ላይ የሻዓቢያን ሠራዊት በውግያ ያሽመደምዱት ጀመር። ለእርዳታ የመጣው ህዝብም የቆሰለና የተሰዋ የወገን ምልሻ ትጥቅ በማንሳት ብቻ ሳይሆን ከሻዓቢያ ወታደሮች ጋርም ጉሮሮ ለጉሮሮ እየተናነቀ ነጥቆ በመዋጋት ጦርነቱ ተጧጧፈ። እዚህ ላይ ጦርነቱ የተጀመረ ዕለት በጦርነቱ ጀመርያ ሰዓቶች የተፈጸመ የዕጡቓት-ሰንበት ቆራጥነት ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ታሪክ በሚገባ መዝግቦ ከትውልድ ወደ ትውልድ ማስተላለፍ ያለበት አንድ ቆራጥነታቸውን የሚመሰክር ገጠመኝን አስታውሰን እንለፍ። ይኸውም ፤ አንድ የተወሰነ ኃይል የያዘች የሻዓቢያ ቡድን በአንድ አከባቢ አድፍጣ ቆይታ አንድ ሁለት የኢሮብ ምልሽያዎችን ትከባለች በዚህ ጊዜ በጠላት የተከበቡ አርበኞች በሳሆ ቋንቋ “ታሃም ኒም ማኪክ ኖያ አዶሳይ ሳባዓየ” የሚል መልእክት ያስተላልፋሉ። ትርጉሙም “እነዚህ የኛ አይደሉምና እኛን ጨምራቹህ ምቷቸው” ማለት ነው። በዚህም፤ ዕጡቓት-ሰንበቶች ወገኖቻቸውን ለይተው በመተው ያ የጠላት ቡድንን እንዳለ እዛ አስቀርተውታል።
አሁን በውጊያው ማኸል ስለታዩ ዘርፈ-ብዙ ገጠመኞችን ማንሳት እዚሁ አቁመን ወደ ተነሳንበት የውጊያው አካሄድ እንመልሳቹህ! ይኸውም በውጊያው ያልጠበቀው ጥቃት የደረሰበት ሻዓቢያ የታጠቀውን መድፍና መትረየስን ማንጣጣት መጀመሩ ነው። ታንኮቹም የተሸከሙትን እሳት መትፋት ጀመሩ። ሆኖም እነዛ ምልሻዎችና በዛች ዕለተሰንበት የብረት ምንነት ያወቁ የዕጡቓት ሰንበት ተርቦች የሻዓቢያን ሠራዊት በታጠቁት ቀላል መሣሪያ ያጣድፉት ጀመር። በሰዓታት ጦርነት ሻዕቢያ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ቁስለኛና ሬሳውን መቊጠር ጀመረ። ያን ያህል ከባድ ጥቃት እየደረሰበት ያለው በጣት በሚቆጠሩ ምልሻዎችና የብረት ምንነትና ውጊያ ጠንቅቆ በማያውቅ ህዝብ ሊሆን ይችላል የሚል ግምት ስላልነበረውም ሽሽቱን ተያያዘው። እነዛ የዕጡቓት ሰንበት ተርቦች ግን ሸሽቷል ብለው አልቆሙም። ሻዓቢያን እየተከታተሉ አጨዱት። ሻዓቢያም የቻለውን ያህል ሬሳና ቁስለኛውን እየጫነ እግሬ አውጭኝ ሽሽቱን ተያያዘው። የኢሮብ ተርቦችም ወደ ሰንዓፈ ከተማ እስኪቃረብ ድረስ እየተከተሉ አጠቁት። በዚህ አኳሀን ከሦሰት ቀናት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ የኢሮብ ህዝብ በትዕቢት ተወጥሮ የመጣው ሻዓቢያን አስተንፍሶ ሙትና ቁስለኛ በማድረግ እየተከታተለ ወደ መጣበት መለሰው። ይህንን ታምር የፈጸሙ ጀግኖች “ዕጡቓት ሰንበት” የእሁድ ታጣቂዎች የሚል የቅጽል ስያሜ ተሰጣቸው። ዕጡቓት ሰንበት የሚል ስያሜ ያገኙት ያለምክንያት አይደለም። ከነዚህ በዛች ወቅት ጦርነቱ ውስጥ ተሳትፈው የተሰዋ ወይም የቆሰለ ወገናቸውን ትጥቅ እያነሱ እንዲሁም ከወደቀውና ከሚሸሸው ጠላት መሣርያ እየነጠቁ በጥቂት ቀናት ጦርነት ወደ ተፈለገው ምዕራፍ ካደረሱት ውስጥ የሚበዛው ከዛች ዕለት በፊት ብረት የሚባል ነገር ይዘው የማያውቁ ነበሩ። በዛች ቅጽበት ግን በጦርነቱ ማኸል የብረት አያያዝ የሚያውቁት የማያውቁትን እንዴት እንደሚተኵስ እያሳዩዋቸው ነው ሻዓቢያን ያሽመደመዱት። በዛች ዕለተ ሰንበት ታጥቀው የሻዓቢያን ሠራዊት ገጥመው በማሸነፋቸው ነው ዕጡቓት ሰንበት የሚለውን ስያሜ ያገኙት። በዚህም ኢሮብን ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያን አኩርተዋልና እንኮራባቸዋለን።
ይህ በግንቦት መጨረሻ ሳምንት 1990 ዓ.ም. በዓይጋ ኮረብቶች የተካሄደው የመከላከል ጦርነት የሻዓቢያን ትዕቢት ያስተነፈሰና የኢሮብ ህዝብ ለዳር ድንበሩ ያለው ቀናኢነት በግልጽ ያስመሰከረ ከመሆኑም በላይ የየዕለቱ ውጊያ የሻዓቢያን ሽንፈት ያበስር ነበር። ሆኖም፤ ያ ድል እንዲሁ ዋጋ ሳያስከፍል የተገኘ አልነበረም። በዓይጋ ከፍታዎች የተንጠፈጠፈው ደም የወራሪ ጠላት ብቻ ሳይሆን የተርቦቹ የዕጡቓት ሰንበት የኢሮብ ጀግኖችንም ጭምር ነው። ጀግኖቻችን ከወራሪ ጠላት ጋር ጉሮሮ ለጉሮሮ ተናንቀው ወድቋል። እንደነሱ ዓይነት ጀግኖች ባይኖሩን ኖሮ ሻዓቢያ በትእቢት እንደተወጠረ መላዋን ኢሮብ ምንም ጥይት ሳይተኵስ የመቆጣጠር ህልም ይዞ እንደተነሳው ሊሳካለት በቻለ ነበር። ጀግኖቹ ግን መስዋእትነት በመክፈል የሻዓቢያን ህልም ለማክሸፍ በቁ። የመንግስት በቂ እርዳታ ታክሎበት ቢሆን ኖሮ ለሁለት ዓመታት በሻዕቢያ ሥር በባርነት ቀንበር መማቀቅ ይቅርና ሻዕቢያ ዳር ድንበራችን ሊደፍር የሚችልበት ዕድልም አይኖረውም ነበር። ያም ሆነ ይህ እነዚህን ጀግኖቻችንን ልናስታውአቸውና ታሪካቸውም ከትውልድ ትውልድ እየተወራረሰ ለዘላለም ሲታወስ እንዲኖር ሁላችንም በጋራ ታሪካቸውን ማደስ አለብን ብሎ ኢ.መ.ተ.ማ በጽኑ ያምናል። ስለሆነም፤ እነዛን ጀግኖች ለሀገራቸው ሉዓላዊነትና ዳር ድንብር መከበር የወደቁበት ቀንን በየዓመቱ ለመዘከር እንዲቻል የኢሮብ ጀግኖች ያ እኩይ ወረራ ካከሸፉባቸው ቀናት አንደኛውን በመምረጥ የነዚህ ጀግኖች የመታሰብያ ቀን እንዲሆን ማድረግ ለሁላችንም ክብር ሲሉ ለከፈሉት ውድ ዋጋ እውቅና መስጠት ተገቢም፤ አስፈላጊም በመሆኑ የኢሮብ ተወላጆች በያሉበት ሊያስቡበት ይገባል ብሎ ኢ.መ.ተ.ማ ያምናል ጥሪም ያቀርባል።
የሰማዕታቶቻንን ቀን “ዕጡቓት ሰንበት” ድል የመቱበት ቀን እንዲሆን የሚመረጠው ያለምክንያት አይደለም። በግንቦት መጨረሻ ሳምንት 1990 ዓ.ም የኢሮብ ህዝብ በዓይጋ ላይ ያሰመዘገበው ድል በኢትዮዽያ መንግስት ተጠብቆ ቢሆን ኑሮ ሻዕቢያ ራሱን ዳግም በማደራጀት የኢሮብ መሬትን እስከ ዓሊተና ድረስ አይዝም ነበር፣ ከዛ በኋላ የተከፈለው መስዋእትነት አይከፈልም ነበር፣ ከዛም አልፎ የኢትዮጵያ ግዛቶች በአልጀርስ ስምምነት ተሳበው ለኤርትራ አይሰጡም ነበር ብሎ ኢ.መ.ተ.ማ በጽኑ ስለሚያምን ነው። እንዳለመታደል ሆኖ ግን የኢትዮጵያ መንግሥት ሓላፊነቱን ለመወጣት ባለመቻሉ ተጨማሪ መስዋእትነትና የግዛት መነጠቅን ለማስተናገድ በቅተናል። ያም ሆኖ ለውጤቱ የኢትዮጵያ መንግሥት በሓላፊነት የሚጠየቅበት ጉዳይ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ ለናት አገር ሲሉ የወደቁትን በወደቁበት ቀን እናስታውሳቸው።
መ.ኢ.ተ.ማ በዚህ አጭር መግለጫ የጦርነቱን ዝርዝር ታሪክ ለማስፈር የቃጣ አለመሆኑና ለወደፊት በጥልቀት የሚመለስበት መሆኑን እየገለጸ፤ ታሪኩ ታሪካችን በመሆኑና ተሰንዶ ለትውልዶች መተላለፍ አለበት ብሎ ስለሚያምን በዚህ የታሪክ ምዝገባ ውስጥ የበኩሉን ድርሻ ለመወጣት የሚችል ሁሉ ሓላፊነቱን እንዲወጣ ጥሪውን ያቀርባል።
ክብር ሕይወታቸውን ለከፈሉልን ጀግኖች!!
የመታሰብያው ቀን በአሸናፊነት በተወጡበት ዕለት ይዘከራል!!
ኢመ.ተ.ማ
ግንቦት 2005 ዓ.ም


Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>