የዛሬው እድሜ ጠገብ አንጋፋ ፖለቲከኛና ምሁር በየካቲት 1966 እና ከዚያም በፊት የፖለቲካ አፈንፋኝ የነበረው ትውልድ ድርጅት መሥርቶ በድርጅት ደረጃ የታገለና ያታገለ እንደነበረ ይታወቃል። ያ ትውልድ በለስ ቀንቶት ሥልጣን የያዘበትና በለስ ሳይቀናው ቀርቶ ደግሞ ዛሬም የድርጅቱን ስም ሳይቀይር መሠረታዊ ለውጥ ሳያሳይ ቀጥሎበት ይገኛል።የዚያ ጊዜ አመራሮች ዛሬም የእነዚያ ድርጅቶች አመራር ሆነው ቀጥለዋል።አብዛኛው በኢትዮጵያ መንግሥትና የሕዝብ ሀብት ለመማር እድል ገጥሞት ወደ ውጭ ሄዶ ዓላማውን በመቀየር የመንግሥት ሥልጣንን ለመጨበጥ አልሞ የነበረው ሲሆን የቀረው ደግሞ ከየዩኒቨርስቲዎችና ሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎችና አስተማሪዎች የወጣ የየካቲት ሕዝባዊ አብዮት ያነሳሳው፤ የኃይለሥላሴ መንግሥት ቤተሰብና ባለሥልጣናትን ያካተተውና ከወታደራዊ ካምፕ ውስጥ የነበረው ነው።(በስም ሲገለጡ፦ ሻእብያ፤ ህወሃት፤ ጀብሐ፤ኢዲዩ፤ደርግ፤መኢሶንና ኢህአፓ ማለት ነው)
እነዚህን ድርጅቶች የኢትዮጵያ ህዝብ ተገፍቼና ተደፍቻለሁ ዋስ ጠበቃ ሁኑኝ በደል በዛብኝ ብሎ ተማጽኖ እንዲታገሉለት አልመረጣቸውም በመንፈሳዊና ብሔራዊ ሞራል ለሕዝብ በመቆርቆር አለመሆኑም ይታወቃል ዋና ዓላማውና ግቡ የነበረው የሥልጣን ባለተራ ከመሆን ውጭ የሚታሰብ አልነበረም አሁንም ከዚያ የተሻለ ራእይ አላቸው ማለት በፍጹም አዳጋች ነው።እነዚህ ኃይሎች ወይም የድርጅት አመራሮችና አባላት ይበልጡ በየሥርዓቱ አገልጋይና ሹመኛ የነበሩ ባለሥልጣናት ቤተሰብ እንደነበሩ ግልጽ ነበር።አንግበውት የተነሱት መፈክር ግን የሕዝቡ ቁስል የነበረውንና ዛሬም እልባት ሊያገኝ ያልቻለውን ጥያቄ ነበር፡፡
በኋላ ላይ እርስ በርሳቸው ተባልተው ጀብሓ ቢከስምም የሻእብያና ጀብሓ አነሳስ ኤርትራ በጣሊያን ግዛት ሥር ለ50፤በእንግሊዝ ግዛት ሥር ለ10ዓመታ የቆየችበትን ምክንያትና ችግር ወደ ጎን በመተው ከዚያ በፊት ኤርትራ የኢትዮጵያ አካል አልነበረችም ብሎ ሸምጥጦ በመካድ ኢትዮጵያ ኤርትራን ከእንግሊዝ ግዛት ወደ ራሷ በማድረግ እንደ አንድ የኢትዮጵያ ክፍለሀገር(ጠቅላይ ግዛት)ማስተዳደር በጀመረችበት ወቅት ኢትዮጵያ ኤርትራን በቅኝ ግዛት ነው ይዛ ያለች በሚል ደረቅ ፖለቲካዊ አስተሳሰብ ተነሳስተው ኤርትራን ከኢትዮጵያ ለመገንጠል ታገሉ ተሳካላቸው።ዛሬ ኢትዮጵያንና የኢትዮጵያን ሕዝብ እያመሰ ያለው በሻእብያ ፊታውራሪነት በዐረብ ፊውዳሎችና ምዕራባውያን ተኮትኩቶ ያደገው ህወሃትም የሻእብያ ጉዳይ አስፈጻሚና ተላላኪ በመሆን ጠንክሮ የሰራ ሲሆን እንደ መነሻ ያደረገው ግን የትግራይ ሕዝብ ከሌላው የኢትዮጵያ ሕዝብ በተለየ ሁኔታ በአማራው ገዥ መደብ የተጨቆነ ስለሆነ ነፃ ማውጣት አለብን የሚል መፈክር ይዞ የተነሳ ሲሆን ሌሎች ሕብረ-ብሔራዊ ድርጅቶችን ከሻእብያና ጀብሓ ጋር በመሆን ያዳከመና በ1976 ዓ/ም ትግራይን ከኢትዮጵያ በመገንጠል “ ታላቋን ትግራይ ትግርኝት ሪፐብሊክ” መመሥረት ይገባል በማለት በማነፌስቶ (manifesto)ላይ ይፋ በማድረግ የተንቀሳቀሰና ዛሬም ከዚያ ጭንብል አስተሳሰብ ያልተላቀቀ ድርጅት ነው። አንዳንድ ወገኖች ህወሃት የመንግሥትን ሥልጣን በመያዙ ከመገንጠል አባዜው ድኗል ብለው ሳይሞግቱኝ አልቀሩም ጥሬ ሀቁ ግን የህወሃት አመራርና አባላቱ በኢትዮጵያ የሚገኘው የፖለቲካ ምሕዳር ሲጠብ የህወሃት ምርጫ መገንጠል ሊሆን እንደሚችል በአራት ነጥብ መደምደም ይቻላል።ለዚያ ሲባልም ነው ህወሃት የኢትዮጵያ ሕዝብ በጎሣ ተለያይቶ የየራሱ የተከለለ መንደር ተበጅቶለት አንዱ ሌላውን እንዳያምነውና በጥርጣሬ ዓይን እንዲተያዩ ለዘመናት አብሮ ያኖራቸውን ባሕላዊና ታሪካዊ ትሥሥር የአንድነታቸውን ማሰሪያ ገመድ ለመቁረጥ አዛዥና አናዛዥ በመሆን እየሠራ የሚገኘው።
ሌሎች የየካቲት 1966 ሕዝባዊ አብዮት ያስገኘውን ድል ነጥቆ ሥልጣን የጨበጠውን የወታደራዊ ጁንታ ጨምሮ ኢህአፓና መኢሶን የማርክሳዊ ሌሊናዊ ርዕዮትን የተከተሉ ሲሆን ማሌን በኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታው ሳይፈቅድ ለማስረጽ ነበር የተንቀሳቀሱት በውጤቱ ምን እንዳተረፉ ተመልክተናል።ከዚህ ለየት የሚለው የየካቲት ሕዝባዊ አብዮት የተናደውን የፊውዳላዊ ሥርዓት ለማስመለስ የተንቀሳቀሰው ኢዲዩ ጉዳይ ነበር።ኢዲዩ ከላይ እስከ ታች ያለው መዋቅሩ አንድ ወጥ የሆነና በሥነ-ሥርዓት የታነጸ አመራርና አባላት የነበረው ባይሆንም ከሌሎች ባልተናነሰ መልኩ ሕዝብን የማነሳሳትና ደርግን የማደናገጥ አቅም ፈጥሮ ነበር። ህወሃትና ኢህአፓ ከውስጡ ሠርጎ በመግባትና በውጊያም አዳክመው እንዲንኮላሽ አደረጉት።
እንደመግቢያ ወደ ኋላ ሄጀ አንዳንድ ቅድመ ሁኔታዎችን የነካካሁት በብዙ መንገድ ምክንያታዊ ነው ህወሃት በለስ ቀንቶት የመንግሥት ሥልጣን ከጨበጠ በኋላ አካሄዱ ያላማራቸው ተደራጅተው ትግል የጀመሩትን በሚመለከት ጊዜ ወስዶ ስለሁኔታቸው ማየት የሚያስፈልግ በመሆኑ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ላይ ግድፈቶች ናቸው ብየ የማምንባቸውን በዚህ ጹሑፌ ስለነሱ የምለው አይኖረኝም።የታገሉኝንና ያታገሉኝን ድርጅቶች ግን ከታች በነበረው የአባላቱ እርከን ሆኘም ስለማውቃቸው ለምን እርስ በርስ ከመናከስና ከመዘረጣጠጥ እርቀ-ሰላም አውርደው(ይቅር-ለእግዚአብሔር)ተባብለው በአንድነት ጠንካራ ክንድ ፈጥረው ይህን “ተውሳክ የኅዳጣኖች ድርጅት ህወሃትን”አይታገሉም?በሚለው ጉዳይ ዙሪያ የተጠየቅ ሀሳቤን ከመሰንዘር ወደ ኋላ እንደማልል ልገልጽላቸው እወዳለሁ።
ሁላችንም የምንስማማበት የሁላችን የሆነ የጋራ ችግር እንደገጠመን ግልጽ ነው። ይኸውም “ውሃ እያሳሳቀ ይወስዳል” እንዲሉ ቅጥረኝነትን እንደ ሥልጣኔ ቆጥረው በኢትዮጵያና በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ የጥፋት ዘመቻ የሚካሄዱና እያካሄዱ ያሉ የዘር ሀረገጋቸው ኢትዮጵያዊ የሆኑ በተልዕኮ ግን ድርቡሽ (መሐዲስት)፤ ዮዲት ጉዲት፤ግራኝ መሐመድና ጣሊያን በቅርቡም ደርግ ከፈፀመው ፀረ-ሕዝብ ተግባር የከፋ አመለካከትና ዓላማ አንግበው አጀንዳቸውን ደብቀው በኢትዮጵያዊነት ስም የመንግሥት ሥልጣን በመጨበጥ ሀገርንና ሕዝብን እያጠፉ የሚገኙ ከአንድ ነገድ የተሰባሰቡ ጠባብና ጎጠኛ የሆኑ የትግራይ ተወላጆች የሚመሩት እንዲሁም ከሌሎች ነገዶች የተሰባሰቡ አድርባዮችና ሆዳሞች የያዙት ሥልጣን እያደረሰብን ያለው ጉዳይ ነው።
ይህን ዓይነቱን ችግር በምን ሁኔታ ማስወገድ እንደሚቻል እንኳን እንደ ድርጅት ቆመውና የፖለቲካ ፕሮግራም ነድፈው የሚንቀሳቀሱት በግብርና የሚተዳደር የትግራይ ወይም ወለጋ የሚገኝ አርሶ አደር እስከ መፍትሔው ሊያስቀምጠው ይችላል። ለዚያም ነው ሕዝባችን አንድ ሆናችሁ ተጋሉ እኛንም አታግሉን የሚለው። ልብ አድርጉ የኢትዮጵያ ሕዝብ ታገሉልን አላለም አታግሉን ነው ያለው።ይህ እጅግ በጣም የባሰ ችግር እንዳለና ሕዝብ ለትግል ቆርጦ መነሳቱን ሲያሳይ ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች ግን አንድ ርምጃ ወደፊት ሄደው መገኘት ሲገባቸው አንድ ርምጃ ወደ ኋላ ሄደው ጭራ ሆነው የሚገኙበት ወቅት ነው። ሀገሬንና ሕዝቤን እወዳለሁ የሚል ግልጽ ዓላማና ፕሮግራም ያለው ድርጅት ቅድሚያ ማድረግ ያለበት የሕዝብ ተገዥነቱን ፤ ተአማኒነቱን ማረጋገጥ ነው። ይህን ማድረግ ሲቻል ነው ያ ድርጅት ወይም እነዚያ ድርጅቶች በሰው ኃይል ሊጠናከር ወይም ሊጠናከሩ የሚችሉት። በሰው ኃይል የተጠናከረ ድርጅት ደግሞ ድል ማድረጉ የማይቀር ነው።እንግዲህ ይህን መራራ እውነት ለመቀበል አለመድፈር የሚያመላክተው እያንዳንዱ ድርጅት ያነገበው ድብቅ አጀንዳ አለ ወይም በድርጅት ደረጃ መንቀሳቀስ አንድምታው ምን እንደሆነ ሳያውቁ የተዘፈቁበት ጉዳይ ነው ማለት ይቻላል።
በርግጥ በርከት ያሉት ድርጅቶች እንደ የካቲቱ ዓይነት ሕዝብ የሚያስገኘውን ድል ለመንጠቅ የሚጠባበቁና በአቋራጩ የሥልጣን ማማ ላይ ለመቀመጥ የሚያስቡ ናቸው። አንዳንዶቹ ደግሞ የህወሃቱ አይነት የውሸት ግንባርና ህወሃት የተጠቀመባቸውን አይነት አሻንጉሊት ድርጅቶችን በማስመራት ህወሃት በሄደበት መንገድ ሄዶ በኃይል ገብቶ ሥልጣን ለመጨበጥ የሚጓዙም አሉ። ሌሎች ደግሞ ትክክለኛ የሕዝብና ሀገር ፍቅር ያላቸው በኢትዮጵያ የሕግ የበላይነት፤ ነፃነት ፤ እኩልነት፤ ዴሞክራሲ እንዲሰፍን የሚዋደቁ ሞልተዋል።ቢሆንም ግን ሕዝብ ምን እያለን ነው? ነባራዊ ሁኔታው ምንን እያሳየ ይገኛል? የሕዝቡ ለትግል የመነሳሳት ጉዳይ እለታዊ ነው ወይስ ሥር ነቀል ለውጥ እስኪመጣ ድረስ የሚዘልቅ ነው? በሚለው ዙሪያ መግለጫ ከማውጣትና በተደጋጋሚ ከማውራት ተሻግሮ ተገቢ እንቅስቃሴ ማድረግ የተሳናቸው ናቸው።
ዲሞክራሲ የሰፈነበት፤የሕዝቦች ነፃነትና እኩልነት የተከበረበት፤የሕግ የበላይነት የሰፈነበት ሥርዓት ሲገነባና በተገነባበት አገር በሕዝብ ላይ የግድያ የእሥራት፤የድብደባና የአፈና ወንጀል፤የሕዝብን ሀብት የዘረፈ የሀገርን ሉዓላዊነት ያስደፈረ በወንጀል ወይም በፍትሐብሔር ሕግ ይጠየቃል። የወሰደውን ይመልሳል፤ የበደለውን ይክሳል እንደ ጥፋቱ ክብደት እየታየ የእሥራትና የሞት ቅጣት እስከመውሰድ የሚያደርስ ሕጋዊ ርምጃ በመንግሥት ይወሰዳል።የትኛውም ዜጋ በዜግነቱ ተከብሮ የሕግ ጥበቃ ይደረግለታል።ሕጉን ጥሶ በዜጋ ላይ አግባብ የሌለው ርምጃ የወሰደ ማንኛውም ባለሥልጣን ይከሰሳል ፤ ይቀጣል፤ሥራውን እንዲያጣ ይደረጋል።በኢትዮጵያችን እንዲህ ያለውን ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት፤ የሕዝቦች በጋራ መፈቃቀድና መከባበር የተገነባ ነፃነትና እኩልነት፤ የሕግ የበላይነት ታይቶ አያውቅም። ግለሰቦች ከሕግ በላይ ሆነው በቡድን ተደራጅተው የሕግ ከለላ የሌላቸውን ሲያሰድዱ ሲገድሉ፤ሲያስሩ፤ሲዘርፉ ኖሩ አሁንም ይህ የሰብአዊ መብት አፈናና ረገጣ፤ፋሽስታዊ ዱላ በዜጎች ላይ እየተፈፀመ ይገኛል። የዘውዳዊው ሥርዓት መጥፎ ባህሪያት ደርግ አሻሽሎና አጠናክሮ ቀጠለ፤ከዚያ የተረከበው የህወሃት ቡድን ደግሞ እጅግ በጣም አጠናክሮ ሕዝብና አገር እያጠፋ ይገኛል። እዚህ ላይ ቁም ድምበሩን ዘለሃል የሚል በመጥፋቱ በማናለብኝነት አካላዊ ግፍ ከመፈፀማቸው ባሻገር ስነ-አእምሮን የሚያውኩ አፀያፊ ቃላትን በመጠቀም በአንድ ነገድና የክርስትና እምነት ተከታይ ሕዝብ ላይ ሰፊ ዘለፋ አካሄዱ አሁንም እየገፉበት ሄደዋል።
በዘውዳዊ አገዛዝ ዘመን የነበሩ የመንግሥት ባለሥልጣናት ላይ ደርግ በወሰደው ፋሽስታዊ ርምጃ ያበቃ በመሆኑ በዚህ ዙሪያ የምለው አይኖረኝም። በደርግ ዘመን የነበረው የመንግሥት ባለሥልጣን፤ካድሬ፤ደህንነት ወደ ዘመነ ወያኔ(የትግራይ ወመኔዎች) ተላልፏል።በወመኔዎች የሥልጣን ዘመን ደግሞ ለየት ባለና ባልተለመደ መልኩ በአንድ ጐሣ ጥርቅሞች የሚመራው ደህንነት፤ፖሊስ፤ካድሬ ከላይ እስከ ታች ባለው የመንግሥት መዋቅር የሚገኘው ኃይል ሕዝብን እያስለቀሰ ፤እየዘረፈና እየገደለ ይገኛል።የሰላማዊ በሩ ተዘግቷል።የወጣቱን ትውልድ እጣ ፈንታ አጨልመነዋል። የእነዚህ ሁሉ ማጠንጠኛው በቡድንም ሆነ በተናጠል በሕዝብ ላይ የፈጸሙት ግፍ በኃይል ተጠናክረው ካልቆሙ በስተቀር በሰላም ቀን የተጠያቂነት ጉዳይ ስለሚነሳ እየተረበሹ እንዲኖሩ የግድ ሆኗል።ሕብረት ፈጥረው በጋራና በአንድነት የማይታገሉት የተቃዋሚ ኃይሎችም ተመሳሳይ ቁስል ያላቸው ስለሆኑ እርቀ- ሰላም ማውረድና ይቅር ለእግዚአብሔር ተባብሎ የበደሉትን ሕዝብ ይቅርታ ጠይቀው ወደ ድሮው ሰውነታቸው መመለስ አልፈለጉም።ችግራችን ያለው እዚህ ላይ በመሆኑ ሁላችንም ተባብረን መፍትሄውን ልናበጅለት ይገባል የሚል እምነትና አመለካከት ስለአለኝ ከሕዝቡ ይሁንታና መሠረታዊ ፍላጎት ውጭ የሚሄዱትን የተቃዋሚ ኃይሎች በጋራ እንዲታገሉ ማድረግ የወመኔዎችን ቡድንም የፕሮፓጋዳ፤የኢኮኖሚና የፖለቲካ ሥሩ የሚደርቅበት ሥራ እንሥራ እነዚህ የደደቢት ወመኔዎች እቤትህ ድረስ ሳይመጡ አንተ እቤታቸው ሂድባቸው።