የስኳር ህመም ከበድ ብለው ከሚታዩ ህመሞች አንዱ ነው፡፡ በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ህመሙ በኢትዮጵያም ሆነ በመላው ዓለም በከፍተኛ ሁኔታ ከመስፋፋቱ አንጻር የተለያዩ ባለሞያዎች በየጊዜው የመከላከያና ቁጥጥር ስልቶችን በተለያዩ አጋጣሚዎችና ብዙኃን መገናኛዎች እየገለጡ ይገኛሉ፡፡ መከላከሉ እና ማራቁ ሳይሆን ቀርቶ የስኳር ህመምተኛ መሆንዎ በቅርቡ የተነገረዎ ከሆነ ሊከተሉና ሊወስዱ የሚገባዎትን ቁልፍ እርምጃዎች በዛሬው የሚዲካል ፊቸር ተዳስሰዋል፡፡
የስኳር ህመም በዋናነት የሚከሰተው በሰውነት ውስጥ የስኳር መጠናችንን የሚቆጣጠረው የኢንሱሊን ሆርሞን መጠን ምርት ማነስ ወይም ጨርሶ አለመመረት ሊሆን ይችላል፡፡ በተለይ ሁለተኛው አይነት የስኳር ህመም የያዛቸው አዲስ ህሙማን በሽታው ይህ ነው የሚባል እክል በህይወታቸው ላይ ሳያደርስ መቆጣጠር የሚችሉባቸውን ስልቶች ኤክስፐርቶች ይጠቁማሉ፡፡ ሁለተኛው የስኳር ህመም አይነት ሲከሰት ይዟቸው የሚመጣቸው እንደ ልብ ህመም፣ የኩላሊት ድክመት እንዲሁም የጭንቅላት ውስጥ ደም መፍሰሰ ወይም ኦክስጅን እጦት (ስትሮክ) ህመሞች ጠንቆች ስጋት ብዙዎችን ያሳስባል፡፡ ለዚህ ነው ባለሞያዎችም እዚህ ላይ ገና ህሙማኑ ችግሩ እንዳለባቸው እንዳወቁ ሊወስዱ የሚገባቸውን እርምጃዎች አጥብቀው የሚያስረዱት፡፡
1. በእርግጥ የስኳር ህመም ይዞዎታል? ያረጋግጡ
አንዳንድ ጊዜ በተለያዩ የምርመራ ተቋማት የሚሰሩ ስህተቶች የብዙ ሰዎችን ህይወት የሚለውጥ ውጤት ሊያወጡ ይችላሉ፡፡ ይህ ሲከሰት የባለሞያዎች ወይም የማሽኖች ስህተት ሊሆን ይችላል፡፡ እርስዎም ለዚህ ስህተት ምክንያት ሆነው ሊሆን ይችላል፡፡ ምግብ ሳይበሉ ናሙና መስጠት እንዳለብዎት ቢያውቁም በመዘናጋት ወይም ባለማወቅ ከምግብ በኋላ ሰጥተው ሊሆን ይችላል፡፡ ይህ የሌለብዎትን የስኳር ህመም ሊሰጥዎት ይችላል፡፡ ስለሆነም ሁልጊዜ በመጀመሪያው ምርመራ ውጤት ብቻ የስኳር ህመም እንዳለብዎ የሚነግርዎትን ውጤት አይቀበሉ፣ የማረጋገጫ ምርመራን ዳግም ይውሰዱ፡፡
2. ያስፈራል፤ ቢሆንም ግን መድኃኒት ይጀምሩ
ብዙ ሰዎች በመጀመሪያ የስኳር ህመም እንዳለባቸው ሲነገራቸው መድኃኒት መጀመርን በእጅጉ ይፈራሉ፡፡ ከመድኃኒት ይልቅ በምግብ መቆጣጠርን ያስቀድማሉ፡፡ በእርግጥ አመጋገብን ማስተካከል ለስኳር ህሙማን በጣም ቁልፍ ጉዳይ ነው፡፡ ይሁንና በምግብ ብቻ ስኳሩ የሚስተካከልላቸው ሰዎች ብዙ አይደሉም፡፡ ስለሆነም የመጀመሪያውን ቀለል ያለ መድኃኒት በመውሰድ መጀመሪያ በሐኪሞች ይመከራል፡፡ ገና አዲስ የስኳር ህሙማን የጎንዮሽ ጉዳቶቹ በጣም አነስተኛ የሆነውን መድኃኒት መውሰዳቸው ተመካሪ ነው፡፡ ይህን መድኃኒትም ሐኪምዎ ሊያዝልዎት ይችላል፡፡ ይህ የመጀመሪያ ደረጃ መድኃኒት ስኳሩን ወደ ጤናማው ምጣኔ የመመለስ ብቃት አለው፡፡ ይሁንና በዚህ መድኃኒት ለውጥ ካልመጣ ሌላ ጠንከር ያለ መድኃኒት ሊሰጥዎት ይችላል፡፡ ከዚህ ውጪ የኮሌስትሮል ማስተካከያ እንዲሁም የልብ ህመም መድኃኒቶችን ቀድመው የሚወስዱ ከነበረ ይህን መረጃ ለሐኪምዎ መንገርዎን መዘንጋት የለብዎትም፡፡ ምክንያቱም ስኳር ህመም በራሱ ኮሎስትሮል መጠንን የመጨመር ጠባይ ስላለው ይህን ሐኪሙ መረዳትና አስፈላጊውን እርምጃ መውሰድ ያስችለዋል፡፡
3. ምግብዎ ላይ ለውጦችን ያድርጉ
የስኳር ህመምን በማባባስ በኩል የካርቦሃይድሬት ምግቦች ተጽዕኖዋቸው ከፍ ያለ ስለሆነ ከቀድሞ አበላልዎ ቀነስ ማድረግን ባለሞያዎቹ ይመክራሉ፡፡ ኃይልና ሙቀት ሰጪዎቹ ምግቦች ስኳርን ሲጨምሩ ቅባት ነክ ምግቦቹ ደግሞ የኮሌስትሮል መጠንን ይጨምራሉ፡፡ ሁለቱም በስኳር ምጣኔ ላይ አስተዋጽኦዋቸው የጎላ በመሆኑ ለውጦችን ማድረግ አስፈላጊ ይሆናል፡፡ ነገር ግን የሚወዷቸውን ምግቦች ሁሉ እርግፍ አድርገው ይተዋቸው ማለት አይደለም፡፡ መጠነኛ ለውጦች በቂ ናቸው፡፡ የሚወስዱትን መጠን ማሳነስ እና የስኳር መጠናቸው አነስተኛ የሆኑ አማራጮቻቸውን መጠቀም ይችላሉ፡፡ ለስላሳ መጠጦችን እና ቅባት የበዛባቸውን ምግቦች በስኳር ይዘታቸው አነስተኛ በሆኑና የስኳር ልካቸው አነስተኛ በሆኑ የምግብ እና መጠጥ አይነቶች መቀየር ይቻላል፡፡ ቅድሚያው ጤናዎት በመሆኑ ይህ ይቀድማል፡፡
4. እንቅስቃሴ ይጀምሩ
እንቅስቃሴ ማድረግ ክብደትዎን ከመቀነስና ከማስተካከል በላይ የስኳር መጠንዎትንም በከፍተኛ ሁኔታ በመቀነስ ወደ ጥሩ ልኬት ያደርስዎታል፡፡ የስኳር ህሙማን በሳምንት ቢያንስ ለ3 ቀናት ለ30 ደቂቃ የሚዘልቅ ቋሚ የአካል እንቅስቃሴን ማድረግ እንዳለባቸው ባለሞያዎች ያሳስባሉ፡፡ ይሁንና የስፖርት እንቅስቃሴ እጅግም የማይሆንልዎት ከሆነ በሌሎች ይህን በሚተኩ እንቅስቃሴዎች ጥቅሞቹን ሊያገኙ ይችላሉ፡፡ ለምሳሌ የግቢዎን አትክልቶች በቋሚነት ቢኮተኩቱና ውሃ ቢያጠጡ፣ ፈጣን የእግር ጉዞን ቢያደርጉ እንዲሁም የህንጻ ደረጃዎችን በእግርዎ መውጣት እና የመሳሰሉት እንቅስቃሴዎች አማራጮች ናቸው፡፡ በዚህም የስኳር ህመምን ክፉ ጎኖች መቆጣጠርና ሰላማዊ ህይወትን መምራት ይችላሉ፡፡
5. ከቋሚ የሐኪም ምርመራ ብዙ ያተርፋሉ
የስኳር ህመም ቋሚ ክትትልን የሚፈልግ ህመም ነው፡፡ በርካታ ጥንቁቅ ሰዎች ለዓመታት መድኃኒትና ምግባቸውን እየተከታተሉ ከስኳር ህመም ጠንቆች ተጠብቀው ይኖራሉ፡፡ ለዚህ ደግሞ ወሳኙ በባለሞያ የታገዘ የቁጥጥር ስትራቴጂ መከተላቸው ነው፡፡ በየጊዜው የስኳሩ መጠን በምን ሁኔታ ላይ እንዳለ ቀላል ምርመራዎችን በማድረግና በአጠቃላይም የአመጋገብ፣ መድኃኒትና እንቅስቃሴ ምክሮችን በመተግበር አንድ ሰው ስኳር ሲይዘው ተያይዘው የሚመጡ የአካል መጉደልና የመደበኛ ህይወት እንቅስቃሴ መዛባትን በሩቁ ማድረግ እንደሚቻል ባለሞያዎቹ ይመክራሉ፡፡ አመታዊ የአይን ምርመራ የኩላሊት ምርመራ እና የእግር ጤና ምርመራ ቢደረጉ የሚመከሩ ሁነኛ ተጨማሪ ምርመራዎች ናቸው፡፡
6. የአመለካከት ለውጥ ተአምር ያመጣል
የስኳር ህመም እንዳለብን ማወቅ በመጀመሪያ ጊዜ በእርግጥም አስደንጋጭ ሊሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን የህይወት ፍጻሜን የሚያመለክትና ተስፋን የሚያሳጣ ችግር አይደለም፡፡ ከባለሞያዎች ጋር በመመካከር ህክምና እስከወሰዱና ጤናማ አኗኗርን እስከተከተሉ ድረስ ጫናው አያሳስብም፡፡ ስለሆነም ቀና አመለካከትን በማዳበር ሁኔታውን በድል መወጣት ደስተኛ ህይወትንም መምራት እንደሚቻል የበርካታ ሰዎች ተሞክሮ ያሳያል፡፡