ቅንብር በኢሳያስ ከበደ
‹‹ቡዳ›› በባህልና እምነት ውስጥ ለረዥም ዘመን ማህበራዊ አስተሳሰብና እምነት ይዞ የዘለቀ ትርጓሜ አለው፡፡ በአውሮፓና ኤዥያ ሀገራትም የዚህ የቡዳ አስተሳሰብን በሰፊው የሚያራምዱት የማህበረሰብ ክፍሎች አሉ፡፡ በሀገራችን በአውሮፓውያን ዘንድ ያለውን ይሄን አመለካከት የተሰሩ ጥናቶችን ዋቢ አድርገን እንደሚከተለው አቅርበነዋል፡፡
…ህጻኗ ቤቲ ከእኩዮቿ ጋር ትጓተታለች- ትጫወታለች፡፡ የልጅነት ጨቅላ ዘመን… የእምቦቀቅላ አሻራዋ መጫወት ነው- አፈር መፍጨት- ውሃ መራጨት፡፡ አራት ዓመት… እያለችም ነፍሷ የጨዋታ ነው- የቡረቃ፡፡
የፀሎት መፅሐፉን ከማህደሩ አኑሮ አንገቱ ላይ እንዳጠለጠለ ደብተራ፣… እሷ አንገት ላይም በአራት መአዘን ክብ የተዘጋጀና በቆዳ የተሰፋ ትንሽዬ የቡዳ መከላከያ እንደ መስቀል አንገቷ ላይ አንጠልጥላለች፡፡ ‹‹ቡዳ እንዳይበላት›› ተብሎ ነው፡፡ ከፍ እያለች ስትመጣ ነው አንገቷ ላይ የታሰረላት የቡዳ መድኃኒት መሆኑን ያወቀችው፡፡ ቡዳ ማለት ምን እንደሆነ እየተረዳች የመጣችውም አምስተኛ ዓመቷን በተሻገረች ማግስት ነበር፡፡
…ቤቲ እያደገች መጣች፡፡ እየበሰለች ሄደች፡፡ ያን ጊዜ ግን አንገቷ ላይ ተንጠልጥሎ የቆየው የቡዳ መድኃኒት አልነበረም፡፡ ለምን? ብዙ ጊዜ የቡዳ መድኃኒት ተቀምሞና በቆዳ ተሰፍቶ አንገታቸው ላይ የሚታሰርላቸው ነፍስ የማያውቁ ህፃናት ናቸው፡፡ ስለምን? እነሱ ከቡዳ መጠንቀቅ አይችሉም… ይደነገጥባቸዋል… በቅናት አይን ይታያሉ፡፡ ቡዳ ህፃናት ስለሚቆነጁ… አይጠነቀቁም ይበሏቸዋል- ነፍስ አያውቁምና፡፡ ነፍስ ቢያውቁ ይጠነቀቃሉ፡፡ መንገድ ላይም እየበሉ ሊሄዱ ይችላሉ… ያን ጊዜ ቡዳ ያያቸዋል… ስለሚባል በተለይ ለነሱ መከላከያው ይታሰርላቸዋል፡፡ የቡዳ መከላከያው ከቅጠላ ቅጠሎችና ቡዳን ሊያርቁ ይችላሉ ተብለው ከሚታሰቡ ነገሮች ስብስብ ተዘጋጅቶ እንደሚታሰርም እየበሰለች ስትሄድ አወቀች፡፡
ቤቲ ስለ ቡዳ ትኩረት መስጠት የጀመረችውና ግን በቡዳ ተበሉ የተባሉ ሰዎች ‹‹ሲቀባጥሩ… ጭሳጭስ እየታጠኑ ሲያስቀባጥሯቸው ፀበል እየተጠመቁ ሲያጓሩና ሲለፈልፉ… ኋላም ሲሻላቸው ነው፡፡ ‹‹በዚህ መልኩ ተጨባጭ ነገሮችን እያየሁ ሰዎችም ስም እየጠሩ እየለፈለፉ እከሌ በሉኝ እያሉ ሲጮሁ ሲሻላቸው ማየት የልጅነት ዘመን ትውስታዬ ነው›› የምትለው የዛሬዋ ወጣት ቤቲ፣ ‹‹ቡዳ በላው…›› የሚሉት ነገሮች ተጨባጭ መሆኑን በዚያ ዘመን አረጋገጥኩ›› ትላለች፡፡ በቡዳ መበላት… ለፍልፎ የማስወጣት ትዕይንት መኖሩን አሁንም ታምናለች- ቤቲ፡፡
ነገር ግን ቤቲ ደቡብን ለቅቃ አዲስ አበባ ስትገባ ‹‹ቡዳ›› የሚለው ነገር ትዝ ያላት እኔ ለዚህ ፊቸር ጥንቅር ግብአት እንዲሆን ጥያቄ ብቅ ሳደርግላት ነው፡፡ አዲስ አበባ ለእንደዚህ አይነት ባህላዊ ወይም ልማዳዊ አስተሳሰብ ‹‹ክብር›› ስለማትሰጥ ይሁን… በቴክኖሎጂ ውጥንቅጧን ያጣች ከተማ ስለሆነች ይሁን… ጥሞና ስላጣ- መረጋጋት ስለሌላት ይሁን እሷ አልገጠማትም፡፡ ቢገጥማት የምትተማመንበትን ቁንጅናዋን እንደ ኤግዚቢሽን ከማሳየት ትቆጠባለች እንደሷ አነጋገር፡፡ በዚህ ጉዳይ አዲስ አበቤ እንደ ክፍለ ሀገሩ ሲያወራና ሲሰጋ ቢገጥማት ዛሬ ከቤት ወደ ካምፓስ አይስክሬም እየላሰች ባልሄደች ነበር፡፡ ግን ዝም ብላ እየኖረች ነው፡፡
…የዚህ ፊቸር ፀሐፊም ወደ ኋላ መለስ አለ- መለስ አለና የስብ ስቴውን ዘመን አገኘ- ጨቅላ ጊዜውን… ከዚያ የታዳጊነት ዘመን ጀምሮ ወተትና የወተት ተዋፆ ምግቦችን አይወስድም፡፡ ወላጆቹ ምክንያቱን የገለፁት ‹‹ቡዳ በልቶት› ነው የሚል ነው፡፡ ወተት የሚባል ነገር በዓይኑ ሊያይ ያንገፈግፈዋል፡፡ ‹‹ውይ ቡዳ በልቶት ነው!›› ይላል – የአካባቢው ማህበረሰብም፡፡ በዚህ አሰተሳሰብ ውስጥ ቅንጣት ጥርጣሬ ስለሌለ ‹‹ቡዳ ስለበላኝ ወተት አልጠጣም!›› የሚል ድምዳሜ ላይ ደረስኩ- ከጠጣሁ የምሞት ያህል ነው የሚሰማኝ፡፡ ግን ወተትና የወተት ተዋፅኦ ምን ያህል ለጤንነት ጠቃሚ እንደሆኑ እያወቅሁ ስመጣ ‹‹መበደሌ›› አሳዘነኝ፡፡ ‹‹የጠጣሁ ቢሆን እላለሁ!…›› ግን አልጠጣም፡፡ ምክንያቱም ቡዳ በልቶኛል- ወተት ስጠጣ፡፡
የትውልድ አገሬን ለቅቄ ከወጣሁ ዘመናት ነጎዱ፡፡ አሁንም ወተት አልጠጣም፡፡ ቡዳ በልቶኛል፡፡ ሃያ አምስት ዓመቴ ተጠግቶ ነበር- አሁን በቅርብ ወዳጆቼ አንድ ወተት ቤት ይዘውኝ ገቡ፡፡ መኖሪያ ቤት ነው፡፡ በጣም እርቦኝ ነበር- እነሱ እርጎ እኔ ደግሞ ከወተት ውጪ ሌላ ቁርስ ባገኝ ብዬ ነበር፡፡ በኩባያ ከመጣው እርጎ እጅግ ጽዱና ቀዝቃዛ ነው፡፡ ከመርጋቱ የተነሳ እንደማዘቅዘቅ ቢሉትም አይደፋም- እርጋታው! ይሄንን ዳቦ እየገመጡ ሲጠጡ ለምን እንደሆነ አላውቅም በጉጉት አያቸው ነበር- አለመታደሌ እያልኩኝ፡፡ አለመጠጣቴ ግራ ያጋባው ወዳጄ ‹‹አትጠጣም እንዴ?›› አለኝ፡፡ የአገሬ ልጅ አብሮአደጌ (የይርጋ ጨፌው ጎታ እንግድነት መጥቶ) ከኔ ፈጥኖ ‹‹ቡዳ በልቶታል!›› አለና- መለሰለት፡፡ ‹‹ዝም ብለህ ጠጣ ምንም አያደርግህም!›› አለኝ- ወዳጄ፡፡ እኔም አብሯደጌም ተሳሳቅን፡፡
‹‹እየውልህ ሚጥሚጣ አብዛበትና ግጥም አድርግ ስነ ልቦና ነው!›› አለኝ፡፡ ስነልቦና ሲል ራሴን ጠየቅሁ፡፡ እርግጥ ሞክሬ ባየውስ? አይገለኝ! ደፍሬ ብገባበትስ? ብዬ ራሴን ሞገትሁ፡፡ የጥፋት ነገር ስላልሆነ መጣልኝ፡፡ ወዳጄ እንዳለኝ በርበሬ አበዛሁበትና የወተቱ ጣዕም እንዲጠፋ አደረግሁ፡፡ ከዚያም ግጥም አድርጌ ጠጣሁት፡፡ እውነቱን ለመናገር በጣም ተመቸኝ፡፡ ነፃነት ተሰማኝ፡፡ በሁለተኛ ጊዜ በሶስተኛ ጊዜ የፍርሃት ደመናውን ለመግለጥ በበርበሬ ብዛት ተወጣሁት! እነሆ ዛሬ እርጎ ያለበርበሬ እጠጣለሁ፡፡ (መጀመሪያም አልተበላው ይሆን? አላውቅም) ወዳጄ ምስጋና ይግባው! (የሳሪሱ ይሄይስ ታሪክ ሰርተኻልኮ) ትኩስ ወተት ለመጠጣት አሁን የምፈልገው እንደ ይሄይስ አይነት ቀስቃሽ ወዳጅ ይመስለኛል፡፡
በሀገራችን በቡዳ መበላት ላይ ያለው ባህልና እምነት ረዥም ዘመን ያስቆጠረ እምነት ነው፡፡ በቡዳ የተበሉ ሰዎች በቡዳ የበሏቸውን ሰዎች እንደሚለፈልፉም ይታመናል፡፡ ሰለሞን ገ/ጊዮርጊስ በአንድ ወቅት የገጠመውን ይናገራል፡፡
‹‹አንድ ወቅት ላይ ከአዲስ አበባ ወጣ ባለ አካባቢ በእንግድነት ሄድን፡፡ እህታችን እጅግ በጣም ቆንጆ ናት፡፡ ከተማ ውስጥ ረፋድ ላይ ገብተው ሌሊት ላይ ኡኡ… ማለት ጀመረች›› ‹‹ምን አድርጌህ ነው!…›› ትላለች፡፡ ታለቅሳለች ትስቃለች- በጣም ትለፈልፋለች፡፡ ሁላችንም ተደናግጠን ተሰባሰብን፡፡ መለፍለፏን ግን ቀጠለች፡፡ በኋላ ቡዳ መሆኑን አወቅን- ቡዳ እንደበላት አረጋገጥን፡፡ ወዲያውኑ በጭሳጭስ እንድትታጠን አደረግን፡፡ መለፍለፍ ጀመረች፡፡ ቄሱ ‹‹ማነህ ውጣ!… ውጣ!!!…›› እያሉ እየታጠነች በመስቀል አናቷን ይደባብሱታል…
‹‹የት ነው የያዝካት! አንተ ማነህ!››
‹‹እያስተናገድኳት እያለ ነው ደስ ብላኝ ነው የበላኋት!›› ማለት ጀመረ፡፡ ስሙንም ጠቀሰ፡፡
‹‹እሺ አሁን ትወጣለህ አትወጣም! ውጣ!… ውጣ!!…››
‹‹እሺ እወጣለሁ! እወጣለሁ…››
‹‹እኮ ውጣ!… ውጣ…›› ቄሱ አቀርቅራ እየታጠነች አናቷን በመስቀል ይመቱታል፡፡
‹‹በቃ ወጥቻለሁ!›› መስከረም ይሄን ጊዜ በላብ ተጠምቃ-ሰውነቷ ዝሎ ነበር፡፡ ወደ ማንነቷ የመመለስ ሁኔታ ውስጥ መግባቷን እየተረዱ የሄዱት ቄሱና ቤተሰቡ አረፍ አሉ፡፡
‹‹የሚገርምህ ነገር›› ይላል- ሰለሞን ገ/ጊዮርጊስ፤
‹‹…ሌሊቱን ሻል ብሏት አደረችና ጠዋት ወደ ከተማ ወጣ እንዳለን የበላትን ሰውዬ አየነው፡፡ ሲያየን በጣም ነው ድንግጥ ያለው…›› ይላል፡፡
በተለምዶ ቡዳ (evil eye) እየተባለ የሚጠራው በማህበራዊ ህይወታችን ውስጥ የራሱ የሆነ ቦታና መልክ የተሰጠው ጉዳይ ነው፡፡ በቡዳ የሚመሰሉ ሰዎች አይናቸው ከፍተኛ ሀይል (power) ስላለው ነው… በጣም በሚስባቸውና በሚወዱት ነገር ላይ በተለየ ሁኔታ ስለሚደነግጡ ያን ጊዜ ነው በግለሰቡ ውስጥ የሚያድሩት…›› የሚሉት አስተሳሰቦች ከመላምትም በላይ በአብዛኛው አካባቢ ዘንድ የሚታመንባቸው ናቸው፡፡
የተወሰኑ የማህበረሰብ ክፍሎች ብቻ ‹‹ቡዳ›› ተብለው እንደሚፈረጅም የሚናገሩ አሉ፡፡ ለዚህም በዚህ መልኩ በማህበረሰቡ ‹‹ቡዳ›› ናቸው ተብለው የተፈረጁ የማህበረሰብ ክፍሎች ህብረተሰቡ በተለየ ሁኔታ ስለሚመለከታቸው ስለሚያማቸው… ስለሚሸሻቸው… ስለሚያገላቸው ቤተሰባዊ ህይወታቸው በስነ ልቦና የተሸነቆጠና ሰላማቸው የጠፋባቸው እንደሆኑ ይታሰባል፡፡ ሌላው ቀርቶ በዚህ መልኩ ይታወቃሉ የሚባሉት የማህበረሰብ ክፍሎች ተሰብስበው በሚኖሩበት ወይንም ባለበት መንደር ውስጥ ለመኖር ጥርጣሬና ፍራቻ የሚፈጠርባቸው ሰዎች እንዳሉ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡
ቡዳ ቅናትና ጥላቻ?
በአማርኛ ቋንቋ ‹‹ቡዳ›› ተብሎ የሚጠራውና የሚታወቀው ከዓይን የሚመነጭ ኃይል (evil eye) በተለያዩና በብዙ ባህሎች (ህዝቦች) እንደሚታመንበት ከሆነ ይህ ጎጂ የማየት ኃይል የታለመበት ሆነም የተሰነዘረበት ሰው (ሰለባ) ላይ አንድ አይነት ጉዳትን ወይንም መጥፎ ዕድልን ያስከትልበታል፡፡ በአብዛኛው እንደሚታመንበት ከሆነ ይህን ጎጂ የእይታ ኃይል የሚያመነጨው ‹‹ቡዳ›› ከቅናትና ከጥላቻ የመነጨ የዕይታ ኃይሉን ሌላው ሰው ላይ በሚያሳርፍበት ጊዜ መጥፎ ጉዳትን ያስከትልበታል፡፡
ቢያንስ ከአንድ ሚሊኒየም (አንድ ሺህ ዓመት) በላይ የሚያልፈው ይህ አመለካከትና እምነትም አያሌ ባህሎች (የተለያዩ ማህረበሰቦችና ህዝቦች) የየራሳቸውን የቡዳ መከላከያ ዘዴዎች እንዲሹ መነሻ ሆኗቸዋል፡፡
ስለ ቡዳ ዓይን ካሉት እምነቶች ውስጥ አንዱ ‹‹አንዳንድ የቡዳነት ኃይል ያላቸው ሰዎች ምትሃታዊ ከሆኑት ዐይኖቸው የሚያመነጩት ከጥላቻ የመነጨው የማየት ኃይላቸው በሰለባዎቻቸው (ተጠቂዎቻቸው) ላይ ጎጂ የሆነ እርግማን እና አሉታዊ ተፅዕኖን (ህመም፣ ስቃይና ሞትን) የመሳሰሉ ጉዳቶችን ያስከትላሉ›› (some people can bestow a course on victims by the malevolent goze of thiren magical eye) የሚል ነው፡፡ ከዚህ እምነት ውስጥ በስፋት ተቀባይነት ያለው አመለካከት እንደሚለው ከሆነ ቡዳው በሰለባው ላይ ጎጂ የሆነ አደጋን በማየት ኃይሉ የሚያደርስበትን ሳያውቀው፤ ሳይፈልግ ወይንም ሆን ብሎ እንዳልሆነ ይነገራል፤ ይታመናል፡፡ በተጠቂዎች ወይንም በቡዳ ዓይን ጥቃት የሚደርስባቸው ሰዎችም የተለያዩ ‹‹ጉዳት›› እንደሚያደርስባቸው ይታመናል፡፡ አንዳንድ ማህበረሰቦች አስረግጠው እንደሚዘግቡት የቡዳ ዓይን መጥፎ እድልን (ክፉ ነገርን) ያስከትላል፡፡ ሌሎች ባህሎች እንደሚሉት ደግሞ የቡዳ ዓይን (መጥፎ የማየት ኃይል) ህመምን መክሳትና መመንመንን ብሎም ሞትን ያስከትላል፡፡ በብዙ ማህበረሰቦች ውስጥ ያለው እምነት ደግሞ በአብዛኛው የቡዳ ዓይን ተጠቂዎች የሚሆኑት ጨቅላዎች እና ህፃናቶች ናቸው፡፡ ምክንያቱም ህፃናቶች በተለያዩ እንግዳ ‹‹ፀጉረ ልውጥ›› ሰዎችና ልጅ አልባ (መሃን) በሆኑ ሴቶች ስለሚደነቁና በቅናት አይን ስለሚታዩ በቀላሉ ለጉዳት ይጋለጣሉ፡፡ የበርክሌይ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪ ፕሮፌሰር አለን ደንዴስ በበርካታ ባህሎች ውስጥ ስለ ቡዳ ያሉትን እምነቶች አስሰውና አበጥረው በማጥናት እንዳረጋገጡት ከሆነ ጥብቅ የሆነው የ‹‹ቡዳ ዓይን›› የማየት ኃይል የሚያስከትላቸውን ጉዳቶች የሚገልፁት ምልክቶች (symptoms) ውስጥ ድርቀት፣ መክሳትና መመንመን በስፋት የሚታዩት የህመም ምልክቶች ናቸው፡፡ ለምሳሌ በብዙ የአውሮፓ ማህበረሰቦች ውስጥ ዓሳ የቡዳ መከላከያ ሆኖ የሚታመነው እርጥብ (ውሃ ውስጥ ነዋሪ) ከመሆኑ ጋር በተያያዘ ነው፡፡
‹‹እርጥብና ደረቅ የቡዳ ዓይን›› በሚል ርዕስ ፕሮፌሰሩ ያወጡት የምርምር ፅሑፍም በዚህ ጉዳይ ዙሪያ የተዘጋጀ ጥናታዊ ዘገባ ነው፡፡ እኛም የሌሎችን ሀገራት እምነትና አመለካከት የምናስነካባችሁ ጥናት ላይ ተመስርተን ነው፡፡ የቡዳ ዓይን አዋቂዎች ህፃናት፣ የቤት እንስሳት እና ሌሎችም ንብረቶች ላይ ሁሉ የቅናት አስተያየት በማየት ብቻ አደገኛና የተለየዩ ጉዳቶችን የጥናት ዘገባ ያሳያል፡፡
ታሪክ
በቡዳ ዓይን ላይ የተመሰረቱ ትውፊታዊ፣ ስነ ፅሑፋዊና አርኬኦሎጂያዊ መረጃዎች መነሻቸው ወይንም ምንጫቸው ከምስራቃዊው የሜድትራኒያን ባህር ክልሎች አካባቢ ከሺህ ዓመት በፊት የተፃፉት የፕላቶ፣ ዲዮዶርስ ሲክለስ፣ ቴዎክራተስ፣ ፕሉታሮች እና የፕሉኒ ሰነዶች ናቸው፡፡ ፒተር ዋልኮት ‹‹ቅናት እና ግሪኮች›› በተባለው መፅሐፍ (1978) እነዚህንና ሌሎችም ከመቶ የበለጡ ጥንታዊ የታሪክ ፀሐፊዎች ስለ ቡዳ ዓይን የፃፉትን መረጃ ጠቅሷቸዋል፡፡
የሶቅራጠስ የቡዳ ዓይን
በጥንቱ ዘመን ስለ ቡዳ ዓይን የነበሩት እምነቶችን በተመለከተ ምንጮቹ የአሪስቶ ፌነስ፣ አቴኒየስ፣ ፕሉተሮችና የሄሉ ኦዲረስ ጽሑፎች ሲሆኑ የዘመኑ ፈላስፋ ሶቅራጠስ ራሱ የቡዳ ዓይን (evil eye) ኃይል እንደነበረውና ደቀመዛሙርቱም በሶቅራጠስ ዓይኖች የፈጠጠና ሰርሳሪ (glaring) የሆነ የማየት ኃይል ይደነቁ እንደነበረ ተዘግቧል፡፡ የሶቅራጠስ ተከታዮችና ተማሪዎች በግሪክኛው ‹‹ብለፔዳይመንስ›› ተብለው ይጠሩ ነበር፡፡ ትርጉሙም ‹‹እርኩስ፣ አመለካከት›› ማለት ሲሆን ደቀመዛሙርቱ ቡዳነታቸውን ሳይሆን በመምህራቸው ሶቅራጠስ የቡዳ አይኖች ተፅዕኖ ስር መውደቃቸውን ለማመልከት የተሰጠ አጠራር ነው፡፡
ስለ ቡዳ ዓይን የተቀመሩ ሳይንሳዊ ማብራሪያዎች ለምሳሌ ፐሉታሮች ያቀረበው ሳይንሳዊ ማብራሪያ…
‹‹የቡዳ ዓይን›› ያለው ሰው ከውስጡ የሚያፈልቀውን እና እንደ መርዛማ መርፌዎች አደገኛና ጎጂ የሆኑ ጨረሮችን የሚረጭባቸው ዋነኛ መሳሪያዎቹ ዓይኖቹ ናቸው!›› ብሏል፡፡ ይህንን የቡዳ ዓይን ‹‹ክስተትን›› ፐሉታርች የሚያቀርበው ማብራሪያ የለሽና አስደናቂ ክስተት አድርጎ ነው፡፡
የቡዳ ዓይን እምነት ታሪክ
ስለ ቡዳ ዓይን (evil eye) በርካታ መጽሐፍትና ድርሳናት ተጽፈዋል፡፡ ከእነዚህም ውስጥ በ19ኛው ክፍለ ዘመን ፍሬደሪክ ቶማስ አልዎርዙ የፃፈው ‹‹የቡዳ ዓይን የአል እምነቶች ምንጭና ተግባር›› (Terrors of the evil eye exposed) የተሰኘው መፅሐፍ አንዱ ነው፡፡ በዚህ የቡዳ ዓይን እምነት ላይ እኔ ካገኘኋቸውና ከሁሉም በላይ ለምርምር የሚጋብዘው አካዳሚያዊ ጽሑፍ ‹‹እርጥብና ደረቅ የቡዳ ዓይን›› (wet and dry) የተሰኘው የፕሮፌሰር አለን ዱንዴስ መጽሐፍ ዋነኛው ነው እላለሁ፡፡ አለን ዱንዴስ በካሊፎርኒያው በርክሌይ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ መምህር ነው፡፡
ስለ ቡዳ ዓይን ፕሮፌሰር ቡንዴስ የሚያቀርበው ንድፈ ሀሳብ (Logic) የተመሰረተው በምስራቅ ሜዲትራኒያን፤ በአሜሪካ በፓሲፊክ ደሴቶች፣ በኢሲያና በአውስታራሊያ የተስፋፋና የአውሮፓውያን ባህል እስከመጣበት ዘመን ድረስ የዘለቀ እምነት መሆኑን ያብራራል፡፡ ከላይ በተጠቀሱት ባህሎች ውስጥ የተንሰራፋው እምነት መሰረቱ ወይንም ምንጭ ያደረገው መርህ ‹‹ውሃ የህይወት ምንጭ-ድርቀት የሞት ምንጭ›› (water equating to life and dimes equating to death) በሚል እሳቤ ላይ የተመሰረተ ነው ይልና ‹‹በቡዳ ዓይን (evil eye) የሚደርሰው ክፉ፣ እርኩስ ጉዳት ህይወት ያላቸውን ነገሮች ያደርቃል፣ በተለይም ህፃናት፣ የሚጠቡ እንስሳት፣ የደረሱ የፍራፍሬ ዛፎች እና የሚያጠቡ እናቶች ዋነኛዎቹ ተጠቂዎች ናቸው›› ይላል፡፡
በቡዳ ዓይን የሚደርሱ ጉዳቶችና አሉታዊ ህመሞች ምልክቶቻቸውም (symptoms) በህፃናት ላይ የሚከሰቱ ድንገተኛ ትውኪያዎችና ተቅማጥ፣ የአጥቢ እናቶችና እንስሳት ጡት (ወተት) መንጠፍ መድረቅ፣ የፍራፍሬ ዛፎች መጠውለግና መድረቅ እና በወንዶች ላይ የሚከሰት ስንፈተ ወሲብ ናቸው፡፡ ባጭሩ ፕሮፌሰር ዱንዴስ ስለ ቡዳ ዓይን ያቀረበው ምርምሩ ‹‹የቡዳ ዓይን እርጥበትን ወይንም ፈሳሽ ነገሮችን ያደርቃል!›› የሚል ነው፡፡
ዱንዴስ ይህንኑ ንድፈ ሀሳቡን የበለጠ ማጠናከሪያ አድርጎ የሚያቀርበው መረጃው እንደሚለው ከሆነ… ‹‹የቡዳ ዓይን እምነት የመነሻ ስፍራው የሆነውን ጥንታዊውን የሱሜር ምድር (ግዛት) ማዕከል ባደረገ ጂኦግራፊያዊ ቀለበት የተሰራጨ ነው›› (Evil eye belief is geographically spread out in a reediting from ancient summer) ይላል፡፡ (የማጅራት ገትር፣ ማኔንጃይትስ ቀለበት ወይንም ለበሽታው የተጋለጡ አገሮች ክልል እንደሚባለው አይነት መሆኑን ልብ ይሏል)
የቡዳ ዓይን በእርግጠኝነት ስለመኖሩ በብሉይ ኪዳን መጽሐፍት ከመጠቀሱም ሌላ በዘመናዊ (የወቅታችን) አይሁዶች፣ አረቦችና ክርስቲያኖችም እውቅና የተሰጠው ጉዳይ ነው፡፡ (በዚህ ጉዳይ ምሁራን ጥናትና ምርምር ያድርጉ እንጂ ሳይንሳዊ እውቅና አልተገኘለትም) ይህ እምነት ከመካከለኛው ምስራቅ በመነሳት በስተ ምስራቅ እስከ ህንድ፣ በስተምዕራብ ስፔይን፣ ፖርቹጋል፣ በስተሰሜን እሰከ ስካን ዲኔቪያን እና እንግሊዝ እና ወደ ደቡብ እስከ ሰሜናዊ አፍሪካ ግዛቶች ድረስ ተሰራጭቷል፡፡
የቡዳ ዓይን እምነት በተንሰራፋባቸው ስፍራዎች ሁሉ ‹‹ከመደበኛው የበለጠ ወይንም የጋለ የቅናት ወይንም የአድናቆ ስሜትና አመለካከት ጎጂ ተፅዕኖ ያሳድራል›› ተብሎ ይታመናል፡፡
ሃራ-ሃራ!
በጣም የተለመደ ‹‹የቡዳ ዓይን›› መገለጫ (በብዙ አገሮችና ባህሎች ማለት ነው) ‹‹ልጄን አዲስ ልብስ አልብሼው ወደ ከተማ ወሰድኩትና አንዲት ልጅ የሌላት ሴት አይታው አቤት! እንዴት የሚያምር ህፃን ነው! ስትል አደነቀችው፡፡ እቤት ተመልሰን እንደገባን ወዲያውኑ ማስመለስ ጀመረ!›› የሚለው ትረካ በጣም የተለመደ ነው፡፡
ከዚህ አባባል የምንረዳውም ‹‹የቡዳ ዓይን (evil eye)›› ቅናትን መቆጣጠር ካለመቻል የሚመነጭ ጎጂ ተፈጥሯዊ ክስተት መሆኑን ነው፡፡ በመፅሐፍ ቅዱስ ውስጥ ቡዳን ዓይንን ‹‹ዓይን eyin ሃራ ሃራ hara›› ሲል ይጠራውና መንስኤውም ቅናትና ምቀኝነት እንደሆነ ያብራራል የሚለው የፕሮፌሰሩ የጥናት ፅሑፍ በአይሁዶች አካባቢ ህፃናትና ከቡዳ ዓይን ወይንም በቡዳ ‹‹ከመበላት›› ለመከላከል ሲባል ፀጉራቸው ላይ የተለያዩ ጨሌዎችን እና ዶቃዎችን ያስሩላቸዋል፡፡ በብዙ ባህሎች ውስጥ የቡዳ ዓይን (ኃይል) ያለው ሰው በሌላው ሰው ላይ ጉዳት የሚያደርሰው ሆን ብሎ ወይንም ለመጉዳት ፈልጎ ሳይሆን ሳያውቀው ወይንም ከፍላጎቱ ውጪ ነው ተብሎ ቢታመንም ከዚህ በተለየ መልኩ በደቡብ ኢጣሊያና በሲሲሊ ግዛቶች ብቻ አንዳንድ ሰዎች ሆነ ብለው በሌሎች ላይ የቡዳ አይናቸውን ይጥላሉ (በሀገራችን አባባል በቡዳ ይበሏቸዋል!) ተብሎ ይታመናል፡፡ በእነዚህ ግዛቶች ዙሪያ የሰፈነው እምነት እንደሚለው ከሆነ ‹‹አንዳንድ ሰዎች፣ የቡዳ ዓይን ኃይልን ይዘው ይወለዳሉ፡፡ ሳያውቁትም በሌሎች ላይ ያንፀባርቁታል (ያሳርፉታል) ወይንም በእንግሊዝኛው ‹‹ፕሮጀክት›› ያደርጉታል ይባላል፡፡ ከዚህም በመነሳት ነው ቡዳዎች ወይንም የቡዳ ዓይን ኃይል ያላቸው ሰዎች ‹‹ፕሮጀክተሮች›› ተብለው የሚጠሩት፡፡
የቡዳ ዓይንን በቃል እና በአካል መከላከል
የቡዳ ዓይን በግልፅ እና በዝርዝር የተገለፁ ጉዳይ በመሆኑ ቡዳን መከላከያ የሆኑ ድምግምቶችና ክትባቶች የመከላከያ መሳሪያዎችም በዝርዝር ተቀምጠዋል፡፡ በአንዳንድ አገሮች አንድ ሰው ወደ ህንድ ህፃን የፍሬ ዛፍ ወይንም የወተት እንስሳ ላይ የአድናቆት ስሜትና አስተያየት ከሰጡ አድናቆቱን ወይንም ሙገሳውን ተከትሎ ወዲያውኑ በአደነቀው ነገር ላይ ምራቁን እንትፍ እንትፍ ይልበታል፡፡ (በአገራችንም ይህ በጣም የተለመደ ነው) በሌሎች ባህሎች ውስጥ ደግሞ ከአድናቆት በኋላ ወዲያውኑ የህፃኑን ራስ ወይንም የተደነቀውን ነገር በእጅ በመንካት ‹‹የቡዳ ዓይንን መልሶ መውሰድ›› ወይንም መከላከል ከተመልካቹ ይጠበቅበታል፡፡ አድናቂው ሰው ይህንን የማክሸፊያ ተግባር ሳያደርግ ከቀረ ግን የህፃኑ እናት በልጇ ላይ ሊደርስ የሚችለውን ‹‹ቡዳ የመበላት አደጋ›› ለማክሸፍ ወይንም ለማርከስ ወዲያውኑ ኃይማኖታዊ የሆኑ ድግምቶችና መነባንቦችን በአዋቂች በማስደገም ትታደገዋለች፡፡ በአንዳንድ ባህሎች ደግሞ አንድ ህፃን በሌላ ሰው ሲደነቅና ሲታይ ወዲያውኑ ልጁ ላይ ምራቅን እንትፍትፍ ይሉበታል ድርቀትን ለመከላከል፡፡ መምህር አስፋው ይልማ ደምሴ በአንድ ወቅት ለዘፈን ግጥም ቢሆን ብለው የሰጡኝ ስንኝ ይሄኔ ነው ብቅ የሚልብኝ፡፡
‹‹ዓይኔ ሲንከራተት በድንገት ታምሜ
ቡዳ በላት በቃ ይለኛል አዳሜ
ተበላች አትበሉ ንክተኝ ዓለሜ
ቢጥመው ይሆናል ያበሻነት ደሜ…››