መስከረም 25 ቀን በአዲስ አበባ ከተማ፣ ሰላማዊ ሰልፍ ለማድረግ የአንድነት ፓርቲ አዲስ አበባ ምክር ቤት ወጣቶች፣ ለአዲስ አበባ አስተዳደር የእውቅና ደብዳቤ ማስገባታቸው ይታወቃል። አስተዳደሩ ደብዳቤው በደረሰው በ48 ሰዓት መልስ ሳይሰጥ ዛሬ መስከረም 22 ቀን፣ በቂ ቅስቀሳ ሳይደረግ፣ «ነገ መጥታችሁ፣ የእውቅና ደብዳቤ አስገቡና ሰልፍ ማድረግ ትችላላችሁ» የሚል መልስ እንደሰጠ ለማረጋገጥ ችለናል።
የአዲስ አበባ አንድነት ምክር ቤት ወጣቶች ግን « ነገ ዓርብ መስከረም 23 ቀን እንደገና ፍቃድ አስገብተን ፣ የእውቅና ደብዳቤ እስክናገኝ ቀኗ ታልፋለች። ለቅስቀሳ የሚኖረን መስከረም 24 ቀን፣ አንድ ቅዳሜ ቀን ብቻ ናት» ሲሉ ፣ አስተዳደሩ ሆን ብሎ ሕዝብ በበቂ ሁኔታ ስለለልፉ አውቆ፣ በነቂስ እንዳይወጣ ለማከላከል ያደረገው እኩይ ተግባር እንደሆነም ይናገራሉ። አምስት ሚሊዮን ሕዝብ ይኖርባታል ተብላ በምትገመተው በአዲስ አበባ፣ አንድ ቀን ብቻ ተቀስቅሶ ሰልፍ እንዲደረግ አስተዳደሩ መጠየቁ አሳፋሪ መሆኑ የገለጹት የአንድነት ወጣቶች በተባለው ቀን ሰልፉን ለማድረግ ፍቃደኛ እንዳልሆኑም ገልጸዋል።
ከሌሎች ድርጅቶች ጋር በመተባበር፣ በቅርቡ፣ ድርጅቶቹ በመረጡት ቀን እና ቦታ፣ ሰልፊ በጋራ እንደሚደረግም የገለጹት የአንድነት ወጣቶች፣ የሰማያዊ ፓርቲ፣ የመኢአድ እና የትብብር አመራሮችን አነጋገረው ፍቃደኛና ደስተኛ መሆናቸውን ይናገራሉ። በጋራ ሊጠራ የታሰበዉን ሰልፍ በተመለከተ ለመድረክም ጥሪ እንደቀረበም የደረሰን መረጃ ያመለክታል።
ትላንት መስከረም 21 ቀን የአንድነት፣ የሰማያዊና የአራና አመርር አባላት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ፣ ገዢው ፓርቲ በወጣት ፖለቲከኞች ላይ እየፈጸመ ያለውን ግፍ በማዉገዝ « ይህን አይነት ተግባር መላው ኢትዮጵያዊ ተገንዝቦ ለምናደርገው ሰላማዊ ትግል ከፓርቲዎቹ ጎን እንዲቆሙ እንጠይቃለን። በቀጣይ ድርጊቱን የምናወግዝበት ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ደረጃ በደረጃ እናሳውቃለን» ሲሉ መናገራቸው ይታወቃል።
ወጣቶቹ ከስብሰባና ከመግለጫ ያለፈ እንቅስቃሴ እያደረጉ ባለበት ወቅት፣ የፓርቲዎቹ አመራሮች ከቢሮ ፖለቲካና መግለጫ ከማወጣት አልፈው ፣ ወጣቶቹ የጀመሩትን በመደገፍ፣ በአስቸኳይ ለሕዝባዊ ሰላማዊ ሰልፎችና እንቅስቃሴዎች ህዝቡን ማስተባበር እንዲጀምሩ፣ ብዙ አባላትና ደግፊዎች እየጠየቁ ነው። «የመግለጫና የስብሰባ ጋጋታ ለዉጥ አያመጣም። የአሁኑ የአንድነት ሊቀመንበር እንደሚፈልጉት ገዢውን ፓርቲ መለመን የትም አያደርስም» ሲሉ አስተያየት የሰጡት በጉዳዩ ላይ ያነጋገርናቸው ተንታኝ ፣ አንድነት፣ መኢአድ ሰማያዊ እና ትብብር እንዲሁም መድረኮች ሰልፉን ለመቀላቀል ፍቃደኝነት ካሳዩ፣ በዋና ዋና ከተሞች፣ ሕዝቡ ድምጹን ያሰማ ዘንድ ሰልፎችን በጋራ ማዘጋጀት እንዳለባቸው ይናገራሉ። «ሕዝብን የማያንቀሳቀስና ወደ ሜዳ ያልወጣ ትግል፣ ጊዜ ማጥፋት ነው” ያሉት እኝሁ ተንታኝ በተለይም ትልቁ የሚባለው የአንድነት ፓርቲ በዚህ ጉዳይ አስቸኳይ ዉሳኔዎች መዉሰድ እንዳለበት ይናግራሉ።