Quantcast
Channel: Ethiopian News | ዘ-ሐበሻ | Latest News Provider | News For All
Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

ባህል ሲባል ፣ የሚከነክኑኝ ነገሮች –በእውቀቱ ሥዩም (ቅጽ አንድ)

$
0
0

Bewketu Seyoum – Hagere Mariam (Maryland) USA [Must Listen)
ባህል ‹‹ነፍስን ማልማት›› ማለት ነው ብሏል ሮማዊ ሊቅ፣ ሲሰሮ፡፡ባህል ፣ማደግን፣ላቅ ማለትን መራቀቅን የሚያሳይ ነገር ነው፡፡

የኢትዮጵያን ባህል ያሳያሉ ተብለው ባገር ቤትና በውጭ አገር በሚገኙ ያበሻ ምግቤት ግድግዳዎች ላይ የሚሰቀሉ ሥእሎችና ምስሎችን ላንዳፍታ አስቧቸው፡፡ ግብዳ እንሥራ የተሸከመች ሴት፣ሞፈር ቀንበር ተሸክሞ በሬዎችን እየነዳ ወደ ማሳ የሚሄድ ገበሬ፣ከንፈሯን በገል የለጠጠች ሴት..ወዘተርፈ.
ብሔራዊ ሙዚየም ግቢ ውስጥ በሚገኝ ስመ-ጥር ምግቤት ውስጥ ጭነት እንደ ተሸከመ ደርቆ የቀረ አህያ ምስል ቆሞ ተመልክቻለሁ፡፡ ይህም እንግዲህ የባህል ምልክት መሆኑ ነው፡፡

በእንሥራ ውኃ መቅዳት ባንድ የዘመን ፌርማታ ላይ ትልቅ ስኬት ነበር፡፡ቢያንስ በቅጠል ጠልቆ ከመጠጣት ጋር ሲመዛዘን ትልቅ መሻሻል ነው፡፡የዚያ ዘመን አኩሪ ባህል መሆኑ አይካድም፡፡ ይሁን እንጂ ዛሬ ውኃ ‹‹ዳገት በሚወጣበት ዘመን›› በከባድ እንስራ ሥር ጎብጣ የምትታይ ሴት መከራችንን እንጅ ባህላችን የምታሳይ አይመስለኝም፡፡ከምስሏ ሥርም‹‹የኢትዮጵያ ሴቶች አበሳ››የሚል እንጅ‹‹የኢትዮጵያ ባህል››የሚል መግለጫ ሊሠፍር አይገባውም ፡፡ታሪክ ጎህ ሲቀድ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ በፈረደበት በሬ እናርሳለን፡፡ይህ ሁኔታ ከተቻለ ሊያሻሽሉት ካልተቻለ ሊደብቁት የሚገባ ውድቀት እንጅ እዩልኝ እዩልኝ የሚያሰኝ ባህል እንዴት ሊሆን ይችላል?

ብዙ ጊዜ ፈረንጆች ባህል እጥረት እንዳለባቸው እኛ ግን የተትረፈረፈ ባህል እንዳለን እንናገራለን፡፡ይህ የተሳሳተ አስተያየት ይመስለኛል፡፡የምትነጋገሪበት አይፎን ፣አሁን ይህን ጽሁፍ የምታነቢበት ኮምፒውተር የባህል ውጤት ነው-የፈጠራ ባህል፡፡ዴሞክራሲና የሰብአዊ መብትም አከባበር ፣የሚያስቀኑ ባህሎች ናቸው፡፡ የኢትዮጵያ ብሄሮች እስክስታና ጭፈራ ባህልነቱን ተጠራጥረን አናውቅም፡፡ ታድያ ፣ሮክና ሂፖፕ ባህል የማይሆኑበት ምክንያት ምንድነው?ክራር የባህል ሙዚቃ መሣርያ ሆኖ፣ጊታር የማይሆንበት ምክንያት ምንድነው?
ዓመት በአሎች ብቸኛ የባህል ማሳያ ቀን ተደርገው ይታሰባሉ፡፡ባዘቦት ቀን ባህል የሌለበት ምክንያት ምንድነው?

በዓመት በአል ያቅምን ያክል ማረድና መገባበዝ ጥልቅ ትርጉም ያለው ነገር ነው፡፡ሆኖም፣ የበግ አንገት በካራ ሲገዘገዝ በቴሌቪዝን ማሳየት፣ በደሙ ስክሪናችንን ማጠብ፣የአኩሪ ባህል ተደርጎ የሚወሰድበትን ምክንያት ባሰላው ባሰላው አልታይህ አለኝ፡፡አንዳንዴ ሳስበው፣ በበጎች ዓይን ስንታይ ሁላችንም ISIS ነን፡፡ ባህል መላቅን፣መሻሻልን ከአውሬነት ወደ መላእክትነት መሸጋገርን የሚያሳይ ነገር ነው ፡፡ ማኅበረሰብ ሲሻሻል በተቻለው አቅም የጭካኔ ምልክቶችን ይቀንሳል፡፡የርህራሄ ጠበል ከሰዎች አልፎ ወደ ሌሎች ፍጡራንም እንዲደርስ ያደርጋል፡፡በግና ዶሮ አይታረዱ ለማለት አይቃጣኝም፡፡ ብልስ ማን ሊሰማኝ!!!የመብል እንስሳት ለምን ታርዳላችሁ ማለት በበጎች ምትክ ለምን እናንተ አትሞቱም ከማለት አይተናነስም፡፡ ያም ሆኖ በግና በሬ የሚታረዱበት ቦታ የተከለለ ፣ከልጆች እይታ ራቅ ያለ ቢሆን ምን አለበት!! ወይስ ልጆች የጠቦት በግን ጣእር ካልተመለከቱ በባህል ታንጸው አደጉ ለማለት አይቻልም፡??
ለመሆኑ ስለ እንስሳት ህይወት የሚያሳስበው ባህል አለን? በሸገር መንገዶች ላይ የማያቸው፣አንካሳ እግራቸውን የሚጎትቱ ውሾች፣ዝንብ የለበሱ ገጣባ አህዮች፣ዙርያው የጨለመባቸው አይነስውር ፈረሶች መልሱን አሉታዊ ያደርጉታል፡፡
(ይቀጥላል)


Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>