Quantcast
Channel: Ethiopian News | ዘ-ሐበሻ | Latest News Provider | News For All
Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Sport: የቶሬስ መጨረሻ!!

$
0
0

በ2011 ኤፕሪል መጨረሻ በስታምፎርድ ብሪጅ የስታዲየሙ ድባብ ቀዝቅዞ ነበር፡፡ የተጨዋቾቹ እንቅስቃሴም ፍጥነት ይጎድለዋል፡፡ ድንገት ኒኮላ አኔልካ ድንቅ ኳስ ለፈርናንዶ ቶሬስ አሾለከለት፡፡ በመላው ዓለም ጨዋታውን ለመከታተል ላይ የነበሩ የቼልሲ ደጋፊዎች ትንፋሻቸውን ውጠው ዝም አሉ፡፡ በእርግጥ በቂ ምክንያት አላቸው፡፡ 50 ሚሊዮን ፓውንድ ወጥቶበት ሰማያዊዎቹን የተቀላቀለው ስፔናዊ ለ734 ደቂቃዎች ኳስ እና መረብ ማገናኘት አልቻለም ነበር፡፡ ሳምንታት ባለፉ ቁጥር የውድድር ዘመኑ ከመጠናቀቁ በፊት ለአዲሱ ቡድኑ ጎል ላያስቆጥር ይችላል የሚለው ግምት እያደገ መጥቷል፡፡
ጥበቃው አበቃ፡፡ ቶሬስ ወደ ኳሷ ተንደረደረ፡፡ ወደ ጎል አክርሮ ለመምታት ያደረገው ሙከራ አልተሳካም፡፡ ኳሷ ከእርሱ ብዙም ሳትርቅ በሮበርት ግሪን ግብ ፊት ለፊት በጭቃ ተይዛ ቆመች፡፡ አጋጣሚው ዕድለኝነት ታክሎበታል፡፡ ቶሬስን በዓይነ ቁራኛ ሲጠባበቁ የነበሩ ተከላካዮች ተሸወዱ፡፡ ኳሷን ለመጠቀም ቀዳሚ ሆነ፡፡ በጥሩ ሁኔታ በግራ እግሩ መረብ ላይ አሳረፋት፡፡ እጆቹን ወደ ላይ ከፍ አድርጎ ሜዳው ላይ በመንሸራተት ደስታውን ገለፀ፡፡ ስታምፎርድ ብሪጅም በአንድ እግሩ ቆመ፡፡ ፈርንናዶ ቶሬስ ‹‹ተመለሰ!››
Fernando Torres spain

ቶሬስ ከክብር ማማ የወረደበት ፍጥነት እና አስገራሚነት በዘመናዊው እግርኳስ ከተከሰቱት ሁሉ ይለያል፡፡ በአንድ ወቅት ከዓለማችን ምርጥ አጥቂዎች አንዱ ነበር፡፡ አሁን ግን በእግርኳስ ዓለም መቀለጃ ከሆኑ ጎል አግቢዎች ግንባር ቀደሙ ነው፡፡ ቶሬስ በቼልሲ ውጤታማ ያልሆነበትን ምክንያት የሚተነትኑ በርካታ ንድፈ ሃሳቦች በእግርኳሱ ዓለም ተንሸራሽረዋል፡፡ አብዛኞቹ እውነት አላቸው፡፡ አንድ እና ሁለት ሃሳቦች ነቅሶ በማውጣት ለውድቀቱ እንደ ምክንያት ማቅረብ ያስቸግራል፡፡ ቀድሞ የነበረውን ፍጥነት ማጣቱ፣ የቼልሲ የአጨዋወት ስታይል፣ ለዝውውር የወጣበት ገንዘብ የፈጠረበት ተፅዕኖ አልያም በራስ መተማመኑ በከፍተኛ ሁኔታ መንኮታኮቱ እንደ ምክንያት ሊጠቀሱ ይችላሉ፡፡ እየተከታተሉ የተከሰቱት አሳፋሪ አጋጣሚዎች ጎድተውታል፡፡ ውጤታማነቱን የቀነሱት እነዚህ ሁሉ ነገሮች ተደማምረው ነው፡፡ እንደዚያም ሆኖ አጥቂው በሰማያዊዎቹ መንደር ሶስት ዓመት ከስድስት ወር ቆይቷል፡፡ በሂደቱም በ172 ጨዋታዎች ላይ ተሰልፏል፡፡ አብዛኞቹ ግን ከክብር ይልቅ ያጎናፀፉት ውርደት ነበር፡፡ በመጨረሻ የቶሬስ የቼልሲ ቆይታ የተጠናቀቀ ይመስላል፡፡ ስፔናዊው በውሰት ውል ለሚላን ተሰጥቷል፡፡

ቶሬስ ውጤታማ ያልሆነበትን ምክንያት ለመመርመር ትክክለኛ መነሻ ነጥብ የሚሆነው በወቅቱ የቼልሲ አሰልጣን የነበሩት ካርሎ አንቼሎቲ ተጫዋቹ የስኳዳቸው አካል እንዲሆን ይፈልጉ ነበር ወይ? ለሚለው ጥያቄ ምላሽ መስጠት ነው፡፡ አንቼሎቲ በ2009/10 የውድድር ዘመን ከቼልሲ ጋር የድርብ ድል ባለቤት ሆነዋል፡፡ ዲዲዬ ድሮግባ፣ አኔልካ እና ፍሎሮ ማሉዳን የያዘው የፊት መስመር በፕሪሚየር ሊጉ ብቻ 103 ጎሎችን አስቆጥሯል፡፡ ይህ አሃዝ አሁንም ድረስ የፕሪሚየር ሊጉ ሪከርድ ነው፡፡ ምንም እንኳን በ2010 መጨረሻ አካባቢ መቀዛቀዝ ቢታይበትም የቼልሲ የፊት መስመር ጥገና የሚያሻው አልነበረም፡፡ ቶሬስ ሰማያዊዎቹን እንዲቀላቀል በግላቸው የገፋፉት እና ያሳመኑት የቼልሲ ባለቤት ቢሊየነሩ ሮማን አብራሞቪች እንደሆኑ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

በክለቡ ባለቤት ፍላጎት 50 ሚሊዮን ፓውንድ ወጥቶበት የፈረመ ተጨዋች መዘዙ ብዙ ነው፡፡ ተወደደም ተጠላ አንቼሎቲ በቋሚ አሰላለፍ ውስጥ እንዲያካትቱት ይጠበቅ ነበር፡፡ እንደተፈራውም የቶሬስ ወደ ስታምፎርድ ብሪጅ መውጣት በድሮግባ፣ አኔልካ እና ማሉዳ መካከል ተፈጥሮ የነበረውን መግባባት ማናጋቱ አልቀረም፡፡ አንቼሎቲ የሚመርጡት 4-3-3 ድሮግባን እና ቶሬስን በአንድ ጊዜ ለመጠቀም አይመችም፡፡ ለዚህ ምክንያቱ ሁለቱ ተመሳሳይ ሚና የሚወጡ አጥቂዎች መሆናቸው ነው፡፡ ይህም የአንቼሎቲን ፈተና ድርብ አደረገው፡፡ ማንቸስተር ዩናይትድ ለወጥ አቋም እያደረገ የነበረውን ግስጋሴ መግታት ቀዳሚው ሲሆን ከሁለቱ ዋነኛ አጥቂዎቻቸው ጥሩ ግልጋሎት ሊያገኙ የሚችሉበትን ሲስተም መንደፍ ደግሞ ሌላኛው ነበር፡፡

የቶሬስ እስከ 14ኛ ጨዋታው ድረስ ጎል አለማስቆጠር ሁኔታውን አባባሰው፡፡ ጣልያናዊው አሰልጣኝም ሚዲያው ስፔናዊው አጥቂ ባጋጠመው የጎል ድርቅ ላይ ያሳረፈውን ትኩረት እንዲያነሳ ለማድረግ ያልፈነቀሉት ድንጋይ የለም፡፡ ቼልሲም የውድድር ዘመኑን ያለ ዋንጫ አጠናቀቀ፡፡ ኤል ኒኖም ለክለቡ ባደረጋቸው 18 ጨዋታዎች ኳስ እና መረብን ማገናኘት የቻለው አንድ ጊዜ ብቻ ነበር፡፡

ሮማን አብራሞቪች ቼልሲን የግላቸው ካደረጉ በኋላ ከተፈፀመው ስህተቶች ግንባር ቀደሙ የቶሬስ ዝውውር መሆኑ አያጠያይቅም፡፡ ብዙዎችን ያስገረመው ስህተቱ ሌላ ጥፋት ማስከተሉ ነበር፡፡ በ2011 ክረምት የምዕራብ ለንደኑ ክለብ አንቼሎቲን አሰናበተ፡፡ ይህም ቢሆን ቶሬስን አልጠቀመውም፡፡ በቼልሲ ባሳለፈው ሶስት ዓመት ከስድስት ወር ጊዜ ውስጥ ከአምስት አሰልጣኞች ጋር ለመስራት ተገድዷል፡፡

በጁን 2011 አንድሬስ ቪያስ ቦአስ ቼልሲን ተረከቡ፡፡ ክለቡ እዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰው ማራኪ እግርኳስ ለመጫወት ከነበረው ፍላጎት ነው፡፡ ወጣቱ ፖርቹጋላዊም በፕሪሚየር ሊጉ አሻራቸውን ለማሳረፍ ተንቀሳቀሱ፡፡ በቼልሲ ይተገበር የነበረውን 4-3-3 ወደ 4-2-3-1 ፎርሜሽን ቀየሩ፡፡ ቶሬስ በሊቨርፑል ሳለ ከአጨራረስ ብቃቱ በተጨማሪ ቁልፍ መሳሪያው ፍጥነቱ ነበር፡፡ አዲሱ አሰልጣኝ የተገበሩት አጨዋወት ጨዋታን ከኋላ መስርቶ ወደ ፊት መንቀሳቀስን ይጠይቃል፡፡ ይህንን የገንዘቡ አብዛኞቹ የሰማያዊዎቹ ተጋጣሚዎች ደግሞ ወደ ኋላ አፈግፍገው መከላከልን ይመርጡ ነበር፡፡ ይህም ቶሬስ ከተከላካዮች ኋላ በቂ ክፍተት እንዳያገኝ አደረገው፡፡ በዚያ ላይ ቼልሲ ስቲቭን ዤራርድ አልያም ዣቢ አሎንሶን የመሰለ ተጨዋች አልነበረውም፡፡ እነዚህ ተጨዋቾች ልኬታቸውን የጠበቁ ረዥም ኳሶችን በመጣል የታወቁ ናቸው፡፡ በማጥቃት ሽግግር ወቅት ኳሷን ከተከላካዮች ጀርባ በመጣል ቶሬስ እንዲጠቀምበት በማድረግ በኩል እንከን አይወጣላቸውም፡፡

ለውጡ ቶሬስ ክፍተቶችን ለመጠቀም ወደ ፊት እንዲገሰግስ ከማድረግ ይልቅ በተደጋጋሚ ጀርባውን ለጎሉ ሰጥቶ እንዲጫወት አስገደደው፡፡ ይህ ሲባል ግን ቶሬስ በጭራሽ ከሲስተሙ ጋር መላመድ አልቻለም ማለት አይደለም፡፡ ተከላካዮች ዓይናቸውን ከእርሱ ላይ ሳይነቅሉ በጥብቅ እንዲከታተሉት የሚያግዳቸው ፍጥነቱ እና የአጨራረስ ብቃቱ እንዲዋዥቅ ማድረጉ ግን አይካድም፡፡ ቼልሲ የብሪታኒያ የዝውውር ሪከርድ በሆነ ዋጋ ሲያስፈርመው በ2009/10 የውድድር ዘመኑ መጨረሻ ላይ ያደረገውን የጉልበት ቀዶ ጥገና ተከትሎ በአካል ብቃቱ በኩል መንሸራተት እያሳየ እንደነበር ይታሰባል፡፡ ምንም እንኳን ያጣውን ፍጥነት እና የአጨራረስ ብቃት በመጠን መግለፅ አስቸጋሪ ቢሆንም የችግሩ መንስኤ ሊሆኑ እንደሚችሉ አያጠራጥርም፡፡

ቪያስ ቦአስ ታክቲኩን በግትርነት መተግበራቸውን መቀጠላቸው እና ያስመዘገቡት ደካማ ውጤት በውድድር ዘመኑ አጋማሽ ስራቸውን እንዲያጡ አደረጋቸው፡፡ የቀድሞው የቼልሲ ተጨዋች ሮቤርቶ ዲ ማቲዮም በምትካቸው ተሾመ፡፡

ዲ ማቲዮ 2011/12 የውድድር ዘመንን ያጠናቀቀበት መንገድ አስገራሚ ነበር፡፡ ኤፍካፕን አሸነፈ፡፡ ቼልሲ በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የቻምፒዮንስ ሊግ ባለድል እንዲሆን አደረገ፡፤ ይህ ሁሉ ሲሆን የቴሮስ ሚና ውሱን ነበር፡፡ ቼልሲ በተለይ በቻምፒዮንስ ሊግ በመከላከል ላይ የተመሰረተ አጨዋወት መተግበሩ ከቶሬስ ይልቅ ድሮግባ ቅድሚያ እንዲያገኝ አስቻለ፡፡ በዚህ ምክንያቱ የአየር ላይ ኳሶችን በመተቀም እና ጀርባውን ለጎል ሰጥቶ በመጫወት ረገድ ከስፔናዊው ይልቅ አይቮሪኮስታዊው የተሻለ መሆኑ ነው፡፡ ቶሬስም ቢሆን በውድድር ዘመኑ መገባደጃ አካባቢ የእርሱ አስተዋፅኦ የተገደበ እንደነበር ተረድቶታል፡፡ ‹‹ቻምፒዮንስ ሊግን ዳግመኛ ማሸነፍ እፈልጋለሁ፡፡ ነገር ግን ከአሁኑ ለየት ባለ መልኩ ቢሆን እመርጣለሁ›› ሲል ከቻምፒዮንስ ሊግ ድል በኋላ የተናገረው ይህንን እውነታ በመረዳቱ ነው፡፡

ድሮግባ በሙኒክ በተደረገው የቻምፒዮንስ ሊግ የፍፃሜ ጨዋታ ላይ ድንቅ ብቃቱን ካስመሰከረ በኋላ የምዕራብ ለንደኑን ክለብ ለቅቆ ሄደ፡፡ ቶሬስም የቡድኑን የፊት መስመር በቋሚነት የሚመራበትን ዕድል አገኘ፡፡ ራፋ ቤኒቴዝ በኖቬምበር 2012 ዲ ማትዮን ተክተው የቼልሲን ኃላፊነት በመረከባቸው ኤል ኒኖ ከቀድሞ አሰልጣኙ ጋር ዳግም ተገናኘ፡፡ ቼልሲ የዩሮፓ ሊግ አሸናፊ ሆኖ ባጠናቀቀበት የውድድር ዘመን ቶሬስ በንፅፅር ጥሩ የሚባል ጊዜን አሳለፈ፡፡ የጎሉን መንገድም ማግኘት ቻለ፡፡ በፍፃሜው ጨዋታ ቤንፊካ ላይ ያስቆጠራትን ድንቅ ጎል ጨምሮ በርካታ ጎሎችን በስሙ አስመዘገበ፡፡ ስኬቱ ግን ቀጣይነት አልነበረውም፡፡ በ2013 ክረምት ቼልሲን ዳግመኛ የተረከቡት ጆዜ ሞውሪንሆ የመጀመሪያ ምርጫቸው ያደረጉት ወደ ቡድኑ የቀላቀሉትን ሳሙኤል ኤቶ ሆነ፡፡ ፖርቹጋላዊው አሰልጣኝም የውድድር ዘመኑን በሙሉ አጥቂዎቻቸውን ሲያብጠለጥሉ ከረሙ፡፡ የሰውዬው አስተያየት የቶሬስ በራስ መተማመንን ከማጠንከር ይልቅ አኮሰሰው፡፡
Fernando Torres

የወጣበት ከፍተኛ ወጪ እና በቼልሲ ያደረገው ዘገምተኛ አጀማመር በቶሬስ ላይ ከፍተኛ ጫና ፈጥሯል፡፡ በራስ መተማመኑን ከማጣቱ በተጨማሪ ለተደጋጋሚ ጉዳት መጋለጡ ብቃቱን አወረደው፡፡ ይህም በበርካታ ጨዋታዎች ላይ ወረደ አቋም እንዲያሳይ አደረገው፡፡ ይህም ሆኖ ግን ቶሬስ ከቼልሲ ደጋፊዎች ጋር ያጣጣማቸው ጥቂት የደስታ ጊዜያት አይጠፉም፡፡ በመጨረሻዋ ደቂቃ ባርሴሎና ላይ ጎል አስቆጥሮ ቼልሲን ለቻምፒዮንስ ሊግ ፍፃሜ ያበቃበትን አጋጣ የቼልሲ ታማኝ ደጋፊዎች ለዘለዓለሙ አይረሱትም፡፡ ስታምፎርድ ብሪጅ ላይ በመጨረሻዋ ደቂቃ ያስቆጠራት የማስነፊያ ጎል ማንቸስተር ሲቲዎችን ከማበሳጨት በተጨማሪ ጆዜ ሞውሪንሆ በደስታ እንዲዘልሉ አድርጋለች፡፡ በኦልድ ትራፎርድ ከማንቸስተር ጋር ሲጫወቱ ያመከነው ኳስ የሚያስቆጭ እንደነበር አይካድም፡፡ ከቡድኑ ተለይቶ በተጓዘበት በዚህ ወቅት ግን የቼልሲ ደጋፊዎች አጋጣሚውን የሚያስታውሱት በመልካም ነው፡፡
የፈረናንዶ ቶሬስ የቼልሲ ቆይታ ውጤታማ እንዳልነበር ግልፅ ነው፡፡ የቼልሲ የቦርድ አባላት እና ሮማን አብራሞቪች ግን ትልቅ ትምህርት ገብይተውበታል፡፡ ለዚህ እንደ አብነት ሊጠቀስ የሚችለው ከቶሬስ ዝውውር በኋላ በቼልሲ የዝውውር ፖሊሲ ላይ የተደረገው ለውጥ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት አብራሞቪች በግላቸው የሚወድዱትን ተጨዋች ለማስፈረም ከፍተኛ ገንዘብ ከማውጣታቸው በፊት ቆም ብለው ሁለት ጊዜ ያስባሉ፡፡

የቼልሲ ደጋፊዎች ቶሬስ ቡድኑን ሲቀላቀል እጅጉን ተደስተው ነበር፡፡ ስፔናዊው ወደ ሚላን ማምራቱ ሲሰማ የተፈጠረው ደስታ ግን መጀመሪያ ወደ ቡድኑ ሲመጣ ከተፈጠረው ይበልጣ፡፡ አሁን ኤል ኔኖ ወደ አዲስ ሊግ ለአዲስ ፈተና አምርቷል፡፡ ምናልባትም በለንደን የራቀውን ስኬት እና ደስታ በሚላን ያገኝ ይሆናል፡፡


Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>