ፌዴሬሽኑ ተጫዋቾች አይወክለንም ባሉት ግለሰብ ስር ተመዝግበው እንዲመጡ ውሳኔ ወስኗል
<<ይሔ ችግር የፌዴሬሽናችንን ህልውና ሳያጠፋ ቦርዱ ውሳኔ እንዲሰጥ እጠይቃለሁ>> አቶ ተካበ ዘውዴ
የፌዴሬሽኑ የውድድር አስተባባሪና የቀድሞ ብሔራዊ ቡድን ግብ ጠባቂ
የሰሜን አሜሪካ ስፖርት ፌዴሬሽን አንዳንድ አመራሮች ከፌዴሬሽኑ ሕግና ደንብ ውጭ ቦርዱን ስብሰባ ሳይጠሩ ለነሱ ስልጣን ማራዘሚያ ድምጽ ለሰጡዋቸውና ከየከተማው ውክልና የሌላቸውን ግለሰቦች የቡድን መሪዎች እነሱ ካልሆኑ ተጫዋቹ ራሱ የመረጠው ተወካይ አንቀበልም በማለት ኢትዮጵያውያንን ሊያቀራርብ የተቋቋመውን ፌዴሬሽን የግል መጠቀሚያ አድርገው መብታችንን ገፈዋል ያሉ የቬጋስ የኢትዮ ስታር ፋሲለደስ አባላት ትላንት በከተማው ከፌዴሬሽኑ ተወካይ ጋር ተወያይተው መፍትሔ ባለማግኘታቸው መብታቸውን ለማስከበር ወደ ሕግ እንደሚሔዱ ከተጫዋቾቹ ተወካይ አንዱ ሲራክ ለህብር ሬዲዮ ገልጿል።
የቡድኑ አባላት ላለፉት ሁለት ዓመታት በደብዳቤ፣በስልክ ለፌዴሬሽኑ የስራ አስፈጻሚና ለቦርድ አባላት ችግሩን እንዲያውቁ ማድረጋቸውን ነገር ግን ፌዴሬሽኑ አሁንም ሊሰማቸው እንዳልፈቀደ ይህም የሆነው በስራ አስፈጻሚ ውስጥ በግል በተደራጀና የራሱን ደጋፊ ባሰባሰበ ቡድን ኢትዮጵያውያንን እየከፋፈሉ መሆናቸውን የገለጸው ወጣት ሲራክ ስብሰባው ያለ ስምምነት እንደተበተነ ለህብር በሰጠው ሰፋ ያለ ማብራሪያ አመልክቷል።
ትላንት ረቡዕ ሜይ 29 በቬጋስ ኢትዮጵያ ኮሚኒቲ አዳራሽ የፌዴሬሽኑ ተወካይ አቶ ተካበ ዘውዴ ፌዴሬሽኑ በተወካይነት የሚያውቀው አመራር ላይ ያሉትን ተወካዮች መሆኑን ተጫዋቾቹ ባሉበት ባካሄዱት ስብሰባ ጠቅሰዋል። ተጫዋቾቹ መጫወት ከፈለጉ በተወካዩ በኩል የተዘጋጀውን ፎርም ሞልተው በሱ ቡድን መሪነት ለውድድሩ ሊመጡ እንደሚገባ በስብሰባው ላይ ገልጸዋል።ችግር ካለ ወደፊት ንገሩን ብለዋል። በከተማው የሚገኝን የቀድሞ የቡድኑን መስራች አቶ ዘውዱም ስላለ እኔም አለሁ የሚገጥማችሁ ችግር የለም ብለዋል።
የቬጋስ ኢትዮ ስታር ቡድን አባላት የፌዴሬሽኑ ተወካይ በተገኘበት በቀድሞው አመራሮችና በቡድኑ አባላት መካከል ያለውን ችግር እንወያይ ሲሉ የጠየቁ ሲሆን ተወካዩ<< እኔ ይህን ለማድረግ ስልጣን አልተሰጠኝም >>ሲሉ ደጋግመው የፌዴሬሽኑ ስራ አስፈጻሚ ወሰነ ያሉትን ውሳኔ ተናግረዋል።
<<እሱ ስልጣን ስትይዙ እጅ ስላወጣላችሁ ነገም እጅ ያወጣልናል በማለት ነው የእኛን ጥያቄ የማትመልሱት? ብቃት የለውም አይወክለንም!>> ያለ አንድ የቡድኑ አባል በፌዴሬሽኑ አመራር ተሰጠ የተባለውን ውሳኔ እንደማይቀበሉት ገልጿል። ተጨዋቾቹ አንቀበልም አይወክለንም ያሉትን ተወካይ ፌዴሬሽኑ በግድ ተቀበሉ ማለቱ አግባብ አይደለም ብሏል።ምፍትሔ የማትሰጡን ከሆነ ለምን መጣችሁ? ሲሉ በምሬት ጠይቀዋል።
ከቬጋስ ኢትዮ ስታር አባላት መካከል አንዱ ወጣት ብዙነህ አሁን ያለውን ችግር ለመፍታት አስታራቂ ያለውን ሀሳብ አቅርቧል። በዚህም አንድ ከቀድሞ ስራ አመራር አንድ ከተጫዋች ተወክሎ ቡድኑን ለዘንድሮ ወደ ዲሲ ይዘው ይሒዱ ብሏል።በዚህ ተጫዋቾቹ ስምምነት ያሳዩ ቢሆንም የፌዴሬሽኑ ውሳ ድጋፍ ያለው የቡድኑ ተወካይ በፌዴሬሽኑ ውሳኔ መሰረት መጫወት የሚፈልግ እሱ ያዘጋጀውን ፎርም እንዲሞላ ጠይቋል።አቶ ተካበም የመጡበት ውሳኔ ይሆው መሆኑን አስረድተው ከተጫዋቾቹ መፍትሄ ተብሎ የመጣውን የመወሰን ስልጣን እንደሌላቸው ገልጸዋል።
በፌዴሬሽኑ የተወሰኑ አመራሮች በተያዘ አቋም እየተበደሉ መሆኑን የሚገልጹት የቡድኑ አባላት መካከል አንዱ ለአቶ ተካበ የቡድኑ ተወካይ የሰጣችሁ ድምጽ እኮ የእኛ ድምጽ ነው? በማለት የተጫዎቹን መብት ረግጠው የሚወስኑትን ውሳኔ እንደማይቀበሉት ተናግረዋል።
<<ፌዴሬሽኑ ጊዜው ሳይሄድና አየር ትኬት ሳይወደድ ከዓመት በላይ ለቀረበለት አቤቱታ እንዴት ምላሽ አይሰጥም? >> ተብለው የተጠየቁት አቶ ተካበ ለዚህ እሳቸው መልስ እንደሌላቸው ተጫዋቾች ሲበደሉ እንደማይወዱ ነገር ግን የተጠየቀውን ምላሽ ለመስጠት ስልጣን አልተሰጠኝም ሲሉ ገልጸዋል።
በተጫዋቾቹ ገለጻ ፌዴሬሽኑ ለሁለት በተከፈለበት ወቅት የቬጋሱ ኢትዮ ስታር ቡድን ተወካይ እና የቡድኑ አባላት ከነባሩ አመራር አባላት ጋር የቆዩ ሲሆን ከዓመት በፊት የቡድኑ ተወካይ ለረጅም ጊዜ በስልጣን መቆየትን ተከትሎ ተጫዋቾች ወኪላችንን በዲሞክራሲያዊ መንገድ መርጠናል ያሉ ሲሆን ፌዴሬሽኑ ከማውቀው ተወካይ ውጭ ያለውን አመራር አልቀበልም በማለቱ ተጫዋቾች በማይወክለን ሰው ወደ ዳላስ አንሔድም በማለት የቀሩ ሲሆን ፌዴሬሽኑ ከውድድሩ በሁዋላ ችግራችሁን እፈታለሁ ቢልም ዛሬም ለችግሩ መፍትሄ ለምን እንዳልሰጠ በስብሰባው ላይ የተጠየቁት አቶ ተካበ ይህን እኔ አላውቅም ሲሉ ተናግረዋል።
ጉዳዩ በይቅር ባይነት እንዲፈታ በቡድኑ መካከል የተፈጠረውን ችግር ማንሳት እንደማይፈልጉ የገለጹት አቶ ተካበ ዘውዴ የሳቸው ስልጣን ያዩትንና የሰሙትን ለፌዴሬሽኑ ማቅረብ መሆኑን ገልጸዋል።
<<ይሔ ችግር ፌዴሬሽኑን ለማጥፋት የደረሰበት ደረጃ ላይ ነው።ቦርዱ መፍትሔ እንዲሰጥበት እጠይቃለሁ >> ሲሉ ለህብር ሬዲዮ ከስብሰባው በሁዋላ በሰጡት ቃለ መጠይቅ ለቦርዱ ጥሪ ያቀረቡት አቶ ተካበ ዘውዴ በስብሰባው ወቅት ተጫዋቾች የራሳቸውን ተወካይ የመምረጥ መብት እንዳላቸው እንደሚያምኑ ሲገልጹ ይሄ ለቬጋስ ኢትዮ ስታር ፋሲለደስ ክለብ ለምን አልሰራም ተብለው ሲጠየቁ ይሄን ለመመለስ ስልጣን የለኝም ብለዋል።
የፌዴሬሽኑ ተወካይ በቬጋስ ኢትዮጵያ ኮምኒቲ የመሰብሰቢያ አዳራሽ የተጠራው የረቡዕ ስብሰባ ያለ ውጤት የተበተነ ሲሆን ተወካዩ አቶ ተካበ ከስብሰባው በፊት አስቀድመው የቡድኑን አባላት ልምምድ በሚያደርጉበት ሜዳ ላይ ያስተዋሉ ሲሆን በስብሰባው ወቅት ተጫዋቾቹ ተወካዮቹ ተጫዋች አለን ካሉ የታሉ እስቲ ያሳዩዋችሁ ሲሉ ሞግተዋል። አቶ ተካበን ለፌዴሬሽኑ በአግባቡ ያዩትን በትክክል እንዲናገሩ አሳስበዋል።
ከቡድኑ ነባር አባላት አንዱ ሲራክ የፌዴሬሽኑ ጥቂት አመራሮች ኢትዮጵያውያንን በሚያቀራርበው ፌዴሬሽን ስልጣን ላይ ተቀምጠው ለግለሰቦች ወግነው ፍትህ የሚያጣምሙበትን አሰራር እውነተኛ የሆኑ የቦርዱ አመራሮችና የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት መፍትሄ ይሰጡበታል ብለው ለሁለት ዓመት ከፌዴሬሽኑ ጋር በመጻጻፍ መቆየታቸውን ገልጾ አሁን ግን እንደትላንቱ ጊዜያችንን አናቃጥልም የሕግ አማካሪ ይዘን የፈጸሙብንን በደል እንጠይቃለን ሲል ይህንኑ ውሳኔ ከፌዴሬሽኑ ተወክለው ለመጡት አቶ ተካበ ጭምር እንደሚነግር ለህብር ሬዲዮ ደግሞ አረጋግጧል።
የፌዴሬሽኑ የሕዝብ ግንኙነት ሀላፊ አቶ ዮሀንስ ብርሃኑ ባለፈው ዓመት ለህብር ሬዲዮ በሰጡት ቃል የቬጋሱን የኢትዮ ስታር ፋሲለደስ ቡድንና ተመሳሳይ ችግር ያለባቸውን ሌሎች ክለቦች ችግር ፌዴሬሽኑ ከዳላሱ ውድድር በሁዋላ በሚያደርገው የቦርድ ስብሰባ ይፈታዋል ሲሉ ማረጋገጫ ሰጥተው ነበር።
ህብር ሬዲዮ የፌዴሬሽኑ ተወካይ በቬጋስ ተገኝተው ያደረጉትን ስብሰባ ሙሉ ገጽታ የሚያሳይ ድምጽና የቪዲዮ ቅጂ የሚከተለው ነው፦