ይህ የቁም ነገር መፅሔት ቅ ፅ 13 ቁጥር 187 የሽፋን ርእስ ነው
በኢትዮጵያ ሥነ ፅሐፍ ውስጥ ስማቸው ጎልቶ ከሚጠሩት ደራሲያን መካከል አንዱ የሆነው ደራሲና ጋዜጠኛ በዓሉ ግርማ ‹ኦሮማይ› በሚል ርዕስ ባሳተመው መፅሐፉ ሳቢያ መስዋዕትነትን የከፈለ ደራሲ ነው፡፡ በአፃፃፍ ቴክኒኩ፤ በአጫጭር አርፍተ ነገሮቹና በድርሰት መዋቅሩ አዲስ የአፃፃፍ ብልሃትን አምቷዋል ተብሎ የሚታመነው ደራሲ በዓሉ ግርማ የካቲት 24 ቀን 1976 ዓ.ም ከቀኑ 11 ሰዓት ላይ ከቤቱ እንደወጣ የደረሰበት ያልታወቀ ደራሲ ነው፡፡ የበዓሉ መጨረሻ ከዓመት ዓመት ሲያነጋግርና የቆየና ያውቃሉ የሚባሉ ሰዎችን ምስክርነት እንደሻተ እነሆ 30 ዓመት ሞላው፡፡ ይህኑ መሰረት በማድረግ የሙያ አጋሩ ደራሲና ጋዜጠኛ አበራ ለማ ባለፉት ሁለት ተከታታይ እትሞች ‹የማይጮሁት በዓሉን የበሉ ጅቦች › የሚል መጣጥፉን አስነብቦናል፡፡ ይህንኑ መነሻ በማድረግ የበዓሉ ግርማን ባለቤት ወ/ሮ አልማዝ አበራን የመፅሔቱ አዘጋጅ ጋዜጠኛ ታምራት ኃይሉ በመኖሪያ ቤቷ ተገኝቶ ‹ህይወት ከበዓሉ በፊትና በኋላ ምን ይመስላል?› ብሏታል፡፡ ‹መጨረሻውን የሚያውቁ ሁሉ ለህሊናቸው ሲሉ ቢናገሩ ጥሩ ነው› የምትለው ወ/ሮ አልማዝ ባዶ ቤት ሶስት ልጆቹን ትቶ እንደ ወጣ የቀረ ባለቤቷን የዓላማ ፅናት ተጋርታ ልጆቿን አስተምራ ለወግ ለማዕረግ ያበቃች ጠንካራ ሴት ናት፡፡ ‹ በዓሉ ይመጣል ብዬ በር በሩን አሁንም አያለሁ› የምትለው ወ/ሮ አልማዝ ‹በዓሉ መፅሐፉን ሲፅፍ ምን ሊመጣበት እንደሚችል ያውቅ ነበር› ትላለች፡፡
ቁም ነገር፡- ወ/ሮ አልማዝ በቅድሚያ በመፅሔታችን ላይ እንግዳ ሆነሽ ስለ ባለቤትሽ ደራሲና ጋዜጠኛ በዓሉ ግርማና ስላለፉት 30 ዓመታት ህይወት ለመነጋገር ፍቃደኛ ስለሆንሽ እጅግ አድርጌ አመሰግናለሁ?
ወ/ሮ አልማዝ፡- እኔም አመሰግናለሁ፡፡
ቁም ነገር፡- እስኪ ወደኋላ ልመልስሽና በዓሉ በመፅሐፉ ሳቢያ ከስራ ከታገደ በኋላ ለ6 ወራት ያህል ቤት ውስጥ ነበር የሚውለው፤ እንዴት ነበር ጊዜውን የሚያሳልፈው የሚለውን ንገሪኝ ?
ወ/ሮ አልማዝ፡- ምንም አይጨነቅም ነበር፤ ብዙ ጊዜውን ቤት ውስጥ ያሳልፍና ከቤት ወጥቶ ዞር ዞር ብሎ ይመጣል፤ ቤት ውስጥ በነበረበት ጊዜ ምንም አይጨነቀም መሳቅ መጫወት ነበር፡፡ የት እንደወሰዱት አላውቅም እንጅ አንዳንድ ነገሮችን ይፅፍ ነበር፡፡ 6 ወር ቤት ውስጥ ሲቀመጥ ምንም አልተቸገርንም ነበር፡፡ እኔ እንዲያውም በጣም ነው ደስ ያለኝ፡፡
ቁም ነገር፡- ለምን?
ወ/ሮ አልማዝ፡- ሥራ ላይ በነበረበት ጊዜ የት አግኝተነው እናውቅና አሁን ነው ቤት መዋል ሲጀምር በደንብ ቆም ብለን ማወራት ልጆቹንም አንዳንድ ነገር ማሳየትና ማዝናናት የጀመረው፡፡ ደሞዝ የለንም ግን የምንበላው አላጣንም ነበር፡፡ ሰው ቤታችን መጥቶ ሲመለከት ይገረመዋል፡፡ ይህ ሁሉነገር ሆኖ አንቺም አታዝኚም እሱም አያዝንም ይለናል፡፡ እግዚአብሔር ይመስገን ነበር የምላቸው፡፡ በዓልዬን አይቼው አላውቅም ነበር ቤት ውስጥ ሲቀመጥ፡፡ እረፍት ያለው ሰው አልነበረም፤ እሱ እንደውም የኔን ሁኔታ እያየ ‹‹ደስ አለሽ አይደል አልሚ ቤት ውስጥ በመዋሌ›› ይለኝ ነበር፡፡ እንደዚህም ሆኖ ቀን ቀን ቤት አየዋለ መሸትሸት ሲል ይወጣ ነበር፡፡ ተው አትውጣ ስለው እሱ ምንም የሚፈራው ነገር የለም፤ እንደሚከታተሉት ቢያውቅም አይፈራቸውም ነበር ባዶ እጁን ነበር የሚወጣው፤ ያኔ ስራ ላይ በነበረበት ጊዜ እንኳ ሽጉጥ እንኳ የሚይዝ ሰው አልነበረም፤ የኢሰፓ ደብተሩንም እኔ ጋር አስቀምጦ ነበር፡፡ የሚሄደው፡፡ ከስራ እንዳገዱት ነው ራሱ ሄዶ የመለሰላቸው፤ ‹‹ምን ምነው ትንሽ ብትቆይ? ባትቸኩል ሌላ ነገር እንዳያስቡብህ›› ስለው ባክሽ ተያቸው በቅቶኛል ይለኝ ነበር፡፡
ቁም ነገር፡- ፅሑፍ ላይ ግን እንዴት ነበር የሚፅፈው፤ ስለ በዓሉ ከሰማኋቸው ነገሮ መሀከል አንዱ በዓሉ ማስታወሻ ስይዝ አይታይም፤ ነገር ግን አንድ መፅሐፍ ፅፎ ለመጨረስ ጊዜ አይወስድበትም ነበር ይባላል?
ወ/ሮ አልማዝ፡- ትክክል ነው በዓሉ ፅሑፍ የሚጀምረውም የሚጨርሰውም ጭንቅላቱ ውስጥ ነው፡፡ ብዙ ጊዜ አንድ ቦታ ተቀምጦ ይመሰጣል አትኩሮ አንድ ነገር ካየ ተመዘገበ ማለት ነው፡፡ ያን ጊዜ በዓልዬ እየፃፍክ ነው አይደል አለዋለሁ፡፡ ከዚህ ውጪ ወረቀት አያገላብጥም አንድ ጊዜ ለመፃፍ ከተቀመጠ ግን ብዙ ገፅ ፅፎ ነው የሚነሳው፡፡
ቁም ነገር፡- ብዙ ጊዜ የሚፀፈው መቼ ነው ምን ሰዓት ላይ ነው?
ወ/ሮ አልማዝ፡- ከስራ መልስ ነው፤ ያው ያለው ጊዜ ያ ብቻ ነው፡፡ መስሪያ ቤት ከባድ የሥራ ውጥረት ነው ያለበት ከስራ ከተመለሰ በኋላ ልጆች በጊዜ ራታቸውን ከበሉ በኋላ ነው ለመፃፍ ቁጭ የሚለው ልጆቹ ሲተኙ ቤቱ ፀጥ ይላል፡፡
ቁም ነገር፡- በዓሉ ምን ይወዳል?
ወ/ሮ አልማዝ፡- ፀጥታ ይፈልጋል ዝምተኛ ነው ሁል ጊዜ ዝም ነው የሚለው፤ ንፅህና ይወዳል ጥሩ ቤት መኖር ይወዳል፤ ለሰው ያዝናል፤ ሙዚቃ ያደምጣል፤ ገንዘብ አይዝም፡፡ እንደ እሱ ያለውን ገንዘብ ላገኘው ሰው ሁሉ የሚሰጥ ሰው የለም፡፡ የመፅሐፉ ሽያጭ እንኳ በአግባቡ የሚቀበል ሰው አልነበረም፡፡ አንድ ጊዜ እንደውም ምን ሆነመሰለህ? አንድ መፅሐፉን እንዲያሳትምለት ከአንድ ሰው ጋር ይዋዋላል፡፡ ሰውየው መፅሐፉን ሽጦ ለማተሚያ ቤትም መክፈል አልቻለም፡፡ በዓሉ ነበር ዋስ አድርጎ ያስመዘገበው፡፡ ታዲያ ማተሚያ ቤቱ ሰውየውን ይከስና ቤተሰቦቹን የሚያስተዳድርበት ዳቦ ቤት ነገር ነበረው፡፡ እና ያ ዳቦ ቤት ይሸጥና ገንዘቡን ይውሰድ ተባለ ሰውየው ትንሽ ህመምተኛ ነበረ፡፡ ሆዱ እያበጠ ብዙ ጊዜ ታክሟል፡፡ ከዛ በዓሉ ጋር ሰውየው ይመጣና ይኽውልህ እንዲህ ሆንኩልህ በዛ ላይ ታምሜያለሁ ይለዋል፡፡ በዛ ጊዜ በዓሉ ቤቱ ይሄዳል፡፡ ሲሄድ ሚስቱ ልጆቿን ይዛ ምሳ ሲበሉ ይደርሳል፡፡ እንዴት ነው ብሎ ሲጠይቃት በቃ ቤታችንም ሊሸጥ ነው መውደቂያ የለንም ትለዋለች፡፡ በዛ ጊዜ በቃ ሀራጁ ነገ ነው እኔ እመልሰዋለሁ ሰው ሲሰቃይ ማየት አልፈልግም፡፡ ዝም ብላችሁ ተቀመጡ ልጆችሽን አሳድጊ፡፡ ብሏት ወጣ ሀራጁንም አስቆመው ያው እሱ ዋስ ስለነ በር ለስንት ዓመት ያህል ስንት ሺህ ብር ስገፈግፍ ኖርኩ፡፡ በዓሉ እንደዚህ አይነት ሰው ነበር፡፡ የተቸገረ ሰው አይቶ ማለፍ አይችልም፡፡ ስብሃት እራሱ ተናግሮታል የቸገረ በዓሉ ካየ ቦርሳው ይቀድመዋል ብሏል፡፡ ማድረግ የፈለገውን የሚያደርገው ከራሱ ተማክሮ ነው፡፡
ቁም ነገር፡- የመጀመሪያ ልጃቸው መስከረም በዓሉ በ1991 ዓ.ም ገደማ ይመስለኛል አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በተዘጋጀ ፕሮግራም ላይ ተገኝታ አንድ የተናገረችው ነገር ነበር፡፡ አባቴ ከአድማስ ባሻገር አበራ ወርቁ ጋር ይመሳሰልብኛል፤ በመፅሐፉ ላይ አበራ በ5 ዓመት ዘጠኝ የኪራይ ቤት ቀያይሯል ይላል እኛም ያደግነው እንደዛ ነበር ብላ ነበር?
ወ/ሮ አልማዝ፡- ልክ ነው፤ ቤት እንቀያይራለን፤ ዘጠኝ ቤት ቀያይረናል፡፡ እቃችንን ይዘን መዞር ነው፡፡ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ እቃችን እዛው ትተን ለአዲሱ ቤት የሚሆን ሌላ ዕቃ ገዝተን ነው የምንገባው፡፡ ሰፊ ቤት ሲገኝ የመጀመሪያ ስራችን ቦታውን በሜትር መለካት ነው፡፡ ከዛ ጋር የሚሄድ ሶፋ ገዝተን እንገባለን፡፡
ቁም ነገር፡- ብዙ ጊዜ የምትከራዩት ቪላ ቤት ነው ወይስ አፓርታማ?
ወ/ሮ አልማዝ፡- ቪላ ቤት ነበር በፊት የምንኖረው፡፡ በኋላ ላይ ነው፡፡ እኔ ወደ አፓርታማ እንድንገባ ያደረግሁት::
ቁም ነገር፡- ለምን ?
ወ/ሮ አልማዝ፡- ቪላ ቤት የተከራየን ጊዜ በግቢው ሰፊ ነው፡፡ ግቢውን የሚጠብቁ ዘበኛ ነበሩ፡፡ ዘበኛው የተለያዩ ስራ የሰሩ ሰው ሲመጣ በር ቶሎ አይከፍቱም፡፡ እሱም በር ላይ ብዙ ሰዓት ይቆም ነበር፡፡ ከዛ በቃ አፓርታማ እንግባ ብዬ ራሴ ፈልጌ ነው ይህንን ቤት ያገኘሁት፡፡ እሱም አፓርታማ ነው የሚወደው ድሮስ ብዬ አልነበረም ብሎ ገባን፡፡
ቁም ነገር፡- በዓሉ ከስራ ከታገደ በኋላ ቤት ውስጥ ሲውል ችግር ሊገጥመው እንደሚችልና ከሀገር ስለመውጣት አያስብም ነበር ?
ወ/ሮ አልማዝ፡- ከሀገር ስለመውጣትም ፍፁም አያስብም ነበር፤ ችግር ሊገጥመው እንደሚችል ያውቀ ነበር፡፡ ነገር ግን ከዚህች ሀገር ንቅንቅ አልልም ነበር የሚለው፡፡ ስለ ልጆቹም ቢሆን ወደፊት ሲያድጉ እውነቱን ብቻ እንዲናገሩ አድርጊያቸው ነበር የሚለኝ፡፡ ከሀገር ስለመውጣት አያስብም ነበር፡፡
ቁም ነገር፡- ግን ኢምባሲ አካባቢ ያሉ ሰዎች ጠይቀውት ነበር የሚባለውስ ?
ወ/ሮ አልማዝ፡- ተጠይቋል፤ በሞስኮ ኤምባሲ፣ የአሜሪካ ኤምባሲ አንተን ብቻ ሳይሆን መላ ቤተሰቦችህን እናውጣችሁ ተብሏል፡፡ ግን እምቢ ነው መልሱ፡፡ ህንድ ኤምባሲም ይሄ ነገር አጉል ነው ብትወጣ ይሻልሃል ብለውት ነበር፡፡ እሱ ግን ምንእግር አለው አስቤ ያደረኩ ነገር ነው፡፡ ከሀገሬ የትም አልወጣም ነበር መልሱ፤ ወንድሜም ውጭ ሀገር ነበር ሊያወጣው ይችል ነበር፤ ግን ሀገሩን ለቆ መውጣት አልፈለገም፤ እዚሁ መስዋዕት ሆነ፡፡
ቁም ነገር፡- ብዙ ጊዜ ለአለማቸው ፅኑ የሆኑ ሰዎች እንደዚህ አይነት ጥያቄ ሲቀርብላቸው ባለመቀበል እራሳቸውን ብቻ ነው መስዋዕት የሚያደርጉት፤ ለልጆቻቸውና ለቤተሰቦቻቸው ግን የተሻለ የሚሉትን ነገር አድርገው ነው ያንን መስዋዕትነት የሚቀበሉ፤ በዓሉ ለእናንተ ለልጆቹ ላይ ስለሚደርሰው ነገር ምን ነበር ሀሳቡ?
ወ/ሮ አልማዝ፡- ልጆቹን በቃ አንቺ አሳድጊ ነበር የሚለው፤ በመፅሐፉ ሳቢያ የሚመጣውን ችግር እዚህ ሀገር ውስጥ ሆኖ መቀበል ስለሆነ የወሰነው ምንም ነገር ቢመጣ ልጆቹን እንደምንም ብለሽ አሳድጊ ነበር የሚለው፤ እኔ በሰራሁት ስራ ከሀገር ወጥቼ ልጆቼና ሚስቴ መቸገር መታሰር የለባቸውም ነው የሚለው እዚም እዚያም ተሯሩጪ ስራ መስራት እንደምችል ያውቃል በፊት ማስታወቂያ ሚኒስቴር ሰርቻለሁ፤ ቴሌቪዥ ውስጥም ሰርቻለሁ:: እኔ ባልኖር ልጆቼን ልታሳድጋቸው ተትችላለች ብሎ ይተማመንብኝ እንደነበር ነው የምረዳው፡፡ ያለምንም ጡረታ ያለምንም ገንዘብ ባዶ ቤት ነው ትቶ በወጣበት የቀረው; ግን እግዚአብሔር ይመስገን ልጆቼ እንደጓደኛ አድርጌ ነው ያሳደግኋቸው ያኔ አንተ መፅሐፍ ስትፅፍ እኔ እየዞርኩ እሸጥልሃለሁ እለው ነበር፡፡ ደግሞም አድርጌያለሁ፡፡ ያኔ ማስታወቂያ ሚኒስቴር ስሰራ በቀን 80 እና 90 ከአድማስ ባሻገር መፅሐፍን የቢሮ እያዞርኩ እሸጥ ነበር፡፡ ምሳ ሰዓት ላይ ምሳ ለመብላት እንገናኛለን ዛሬ ይኸውልህ ይህን ያህል መፅሐፍ ሸጫለሁ እለው ነበር፡፡
ቁም ነገር፡-በዓሉ የቤት ውስጥ ስራ ይሠራል ?
ወ/ሮ አልማዝ፡- ይሠራል፤ እኔ ነፍሠ ጡር ስሆን የቤት ውስጥ ስራዎችን ይሠራ ነበር፡፡ ምግብ ያበስላል ቤት ማፅዳት፣ አልጋ ማንጠፍ የልጆች ልብስ መተኮስ ይሠራል፤ ከስራ የወጣ ጊዜ እነዚህን የቤት ውስጥ ስራዎችን ይሠራ ነበር፡፡
ቁም ነገር፡- ምግብ የሚወደው ምንድን ነው?
ወ/ሮ አልማዝ፡- ምግብ የሚወደው ሩዝ ነው፤ የተወሰነ ዶሮ ወጥ ይወዳል፤ ሱፕ ስቴክ ይወዳል፤ ግን ቀን የበላውን ምግብ ማታ ቢቀርብለት አይበላም፡፡
ቁም ነገር፡- መኪና ይቀያይራል ወይስ?
ወ/ሮ አልማዝ፡- በፊት ፔጆ መኪና ነበረችን፣ ከዛ እሷን ሸጥንና ያቺን አዲስ ቮልስዋገን ገዛን፤ ለኔም ሌላ መኪና ገዝተን ነበር፤ ሁለት መኪና አንድ ቤት ምን ያደርጋል ብለን ሸጥናት፡፡
ቁም ነገር፡- በዓሉ ማስታወቂያ ሚኒስቴር ውስጥ ትልቅ ባለስልጣን ነበር፤ ቤታችሁ አንዳንድ ትልልቅ ባለስልጣናት ተጋብዘው ይመጡ ነበር? እናንተስ ተጋብዛችሁ ትሄዱ ነበር?
ወ/ሮ አልማዝ፡- ብዙም አይደለም፤ግብዣ ቦታ እሱም እንደነገሩ ነው፤ እኔም ሲጠሩኝ የደርግ ባለስልጣናት ጋር አልሄድም ነበር፤ ብቻውን ሲሄድ ሚስትህስ ሲሉት እሷ እኮ እንደዚህ አይነት ነገር አይመቻትም ነበር የሚላቸው፡፡
ቁም ነገር፡- ኦሮማይ መፅሐፍ ከወጣና በገበያ ላይ ተሰብስቦ ከተቃጠለ በኋላ ኮለኔል መንግስቱ ቤተመንግስት ድረስ አስጠርተውት እንደተናገሩት ለገነት አየለ በሰጡት ቃለ ምልልስ ላይ ተናግረዋል፤ የዛን ዕለት ምን ነበር የተነጋገሩት? ምን ነገሮሽ ነበረት በዓሉ ?
ወ/ሮ አልማዝ፡- በእርግጥ ጠርተውት አነጋግረውታል፤ ነገር ግን በመፅሐፉ ላይ ሰውየው እንደሚሉት አይደለም የተነጋገሩት፤ ውሸት ነው የሚናገሩት፡፡ የዛን ዕለት ተጠርቶ የሄደው ብቻውን አልነበረም፤ የሸዋረን የተባለው ህንድም የፊልም ሰው ነበር አብሮት፡፡ እንደገባ ሊቀመንበሩ ያሉት‹‹ ምነው በዓሉ ከዚህ በፊት በቀይ ኮከብ ጥሪ አብዩቱን እንደዛ አድርገህ ሳልከው፤ አሁን ደግሞ በዚህ መፅሐፍ መንጋጋ ውስጥ ነው ከተትከን፤ አንተ ምሁር ነህ፤ አብዩቱንስ ወታደሩንስ ለምን እንደዚህ ትላለህ? አሉት ሲጋራቸውን ይዘው ወዲያና ወዲህ ይሉ ነበር ብለውኛል… ለምን አላስየኸኝም ከመውጣቱ በፊትም ብለውት ነበር፡፡
ቁም ነገር፡- በዓሉ ምን አላቸው?
ወ/ሮ አልማዝ፡- ምንም አላለ፤ እንደዛ እየተቆጡ ሲናገሩ ዝም ብሎ ሲያዳምጥ ቆይቶ እኔ ዘመቻ ላይ ሆኜ ያየሁት ነው የፃፍኩት፤ ወልደማርያም ሀብተማርም ብዬ የተናገርኩት የጠቀስኩት ሰው የለም፤ እኔ ስለሀገሬ ነው የፃፍኩት፡፡ እዛ ውስጥ ተጠቅስናል የሚሉ ሰዎች ስራቸው የሚያውቁት ናቸው፡፡ ኢትዮጵያ የጋራ ሀገራችን ናት ብያለሁ እጅ መሰንዘርም ዋጋ የለውም፤ ከዚህ ውጭ ያልኩት ነገር የለም ሲላቸው ‹‹ይሄውነው አቋምህ? አሉት›› ‹‹አዎ ያሄው ነው›› ሲላቸው ‹‹በቃ ሂድ ውጣ›› ብሎ አስወጣው ከዛ በኋላ ስራቸውን ሰሩ፡፡ ከስራ የተሰናበተበትን ደብዳቤ እንኳ ሚኒስትሩ ሊሰጡት ሲጨነቁ ግድ የለም ፈርሙበትና መጥቼ እወስደዋለሁ ብሎ ያላቸውን ‹‹‹በዓሉ ይህ ነገር መጣ እንዴት አድርጌ ፀፊ ልስጥህ?›› ብለውት ነበር፡፡
ቁም ነገር፡- በዓሉ የመንግስት ከፍተኛ ባለስልጣን ከመሆኑ አንጻር የዚህ አይነት ውሳኔ /እርምጃ/ ላይ ይደርሳሉ የሚል ግምት ነበረሽ ?
ወ/ሮ አልማዝ፡- በዓሉ ባለስልጣን ቢሆን እኮ ፈልጎት አይደለም የሚያሰሩት ስልጣን የማይፈልግ የማይወድ ሰው መሆኑን ያውቃሉ፤ እሱ የሚፈልገው መፃፍ ብቻ ነው፤ ግን የተማረ ሰው አጣን ብለው ነው በግድ ያስገቡት፡፡ ቢሮው እንኳ ሲያመሽ ቢሮው መስኮት ስር ታንካቸውን እያስጠጉ ነበር የሚያስጠብቁት፤ እንደማይወዳቸው ያውቁ ነበር፡፡ አንድ ጊዜ እንደው ውጪ ሀገር እንግሊዝ ሀገር ንግስት ኤልሳቤት ጋር ደርሶ ሲመለስ ሊቀመንበሩ ‹‹ምን አለችህ?›› ብለውት በተናገረው ነገር ተናደው ነበር፡፡
ቁም ነገር፡- ምንድ ነው ?
ወ/ሮ አልማዝ፡- የዛን ጊዜ የንጉሳውያን ቤተሰቦች ታሰሩበት ጊዜ ስለ ነበር በኢትዮጵያ እስረኞች በዝተዋል፤ የንጉሳውያን ቤተሰቦችንም ብትለቋቸው እዚህ ዘንድ መጥተው ይኖራሉ ንግስቲቱ ማለቷን እንደመጣ ለሊቀመንበሩ ይህንኑ ነግሯቸው ተቆጥተው ነበር፤ እንዲያውም በዓሉ የንግስቲቱ ሀሳብ ደግፎ ይፍቀዱና ሰዎቹን እንግሊዝ ሀገር አድርሻቸው ልምጣ›› በማለቱ እንዴት ነው የምትደፍረን ብለውታል፡፡ በእንዲህ እንዲህ አይነት አጋጣሚዎች አቋሙን ያውቁታል፡፡
ቁም ነገር፡- በመፅሐፍ ድርሰት ሥራ ቤተሰብን መምራት ማኖር ይቻላል የሚል እምነት ነበረው?
ወ/ሮ አልማዝ፡- የለው ም፤ ለስሜት ያህል ነው የሚፅፈው እንጂ የድርሰት ገቢ ያን ያህል አይደለም፤ ገቢ ቢኖርም አሳታሚና ማተሚያ ቤት ነው የሚወስዱት፤ ደራሲ የሚያገኘው ነገር የለም ነው የሚለው፡፡
ቁም ነገር፡- ከስራ ከታገደ በኋላ በሌላ መ/ቤት ሥራ የመጀመር ሀሳቡ አልነበረውም ?
ወ/ሮ አልማዝ፡- ጀርመኖች ጋር ስራ አግኝቶ መንግስት መ/ቤት ከሚያገኘው ደሞዝ በሁለት ሶስት እጥፍ ሊቀጥሩት ሲሉ ነው የወሰዱት፤ ከዛም በኋላ ወረቀት አግኝተናል የሚሉት ይህንን የጀርመኖች ድርጅት ጋር የተፃፃፈውን ወረቀት ነው፡፡
ቁም ነገር፡- ከቤት ወጥቶ ከጠፋ በኋላ ምን አደረግሽ ?
ወ/ሮ አልማዝ፡-ምን አደርጋለሁ? ያወቃሉ የምላቸው ሰዎች ጋር ሄድኩ፡፡ ምንም ነገር የለም፤ እዚህ ቦታ ሲሉኝ ተነስቼ እሄዳለሁ፡፡ ሸሚዝ ከአንድ ቀን በላይ የማያደርገው በዓሉ እስር ቤት ነው ያለው ሲሉኝ የሸሚዝ መአት ይዤ እዞራለሁ፡፡ ሁሉም መልሳቸው አንድ ነው፡፡ ከንፈራቸውን መጠው የለም ነው የሚሉኝ፡፡ ያ ክፉ ዘጠኝ ዓመት ያለፈው በመከራ ነው፡፡ በዛ ላይ ከቤቴ ወጥቼ ወደየትም ብቻዬን መሄድ አልችም ነበር፡፡ 24 ሰዓት ይከታተሉኛል፡፡ ልጆቼን ት/ቤት ሳደርስ ይከተሉኛል፤ የሆነ ገበያ ስሄድ ይከተሉኛል ወደ በኋላ ላይ ግን ለመድኳቸውና ሰው እንደሚከተለኝ እንኳ ረሳኋቸው፤ እኔ መፃፍ ስለማልችል ነው እንጂ ያሳለፍኩ ህይወት ራሱ መፅሐፍ የሚወጣው ነው፡፡
ቁም ነገር፡- የበዓሉ ግርማ ፋውንዴሽን ያቋቋመው ማነው?
ወ/ሮ አልማዝ፡- መስከረምና ዘላለም ናቸው እዛው አሜሪካ ያቋቋሙት፡፡ መስከረም በዓሉ ሲጠፋ የ13 ዓመት ልጅ ነበረች፡፡ ግን አንዳንድ ነገሮች ታውቅ ነበር፡፡ ዘላለም ትንሽ ልጅ ይሁን እንጂ ያውቃል፡፡ እሷም እሱም ማስተርስ ድግሪያቸውን ከያዙ በኋላ ነው ፋውንዴሽኑን ያቋቋሙት፡፡ መስከረም በልጅነቷ አንባቢ ልጅ ነበረች ማስተርስ ድግሪዋን የሰራችውም በጋዜጠኝነት ነው፡፡
ቁም ነገር፡- ፋውንዴሽኑ ምን ምን ስራዎችን ይሰራል ?
ወ/ሮ አልማዝ፡-የተለያዩ ስራዎችን ይሠራል ልጆቼ እየተማሩ ስለሆነ የፋውንዴሽኑ ስራ የሚያንቀሳቅሱት እንደሚፈልጉት አልሠሩበትም፡፡ ግን እስካሁን ባለው ጊዜ በበዓሉ ስም የተለያዩ ደብተሮችን እስክርቢቶዎችን አሳትመው በሀገር ውስጥ ለተለያዩ ችግረኛ ተማሪዎች አከፋፍለዋል:: ወደ ፊት ደግሞ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት እዚህ የመክፈት ሀሳብ አላቸው፤ የበዓሉ የተለያዩ ሥራዎችና ፎቶግራፎች አሰባስበው በሙዚየም መልክ የማስቀመጥና ቀጣዩ ትውልድ እንዲማርበት የማድረግ ሀሳብ መስኪ አላት፡፡
ቁም ነገር፡- የትውልድ ሀገሩ ኢሊባቡር ጎሬ በስሙ ት/ቤት ተሰይሟል አይደል ?
ወ/ሮ አልማዝ፡-የመንግስት ት/ቤት ነው በስሙ የተሰየመለት፤ ተጠይቄ በደብዳቤ አስፈቅደውኝ ነው የሰየሙትና በትውልድ ቦታው ብዙ ልጆች የሚማሩበት ት/ቤte ነው
ቁም ነገር፡- እናቱ እዛ ነበር የሚኖሩት ?
ወ/ሮ አልማዝ፡-አዎ ቅርብ ጊዜነው ያረፉት፡፡ አንድ ወቅት ላይ አዲስ አበባ አስመጥቻቸው ነበር፡፡ የኔ እናትም በጣም ተወደው ነበር እዬዬ እያለች ነው የሞተችው፤ እናቱ የባላባት ልጅ ስለሆኑ ሀብታም ነበሩ፤ አርሻና ወፍጮ ቤት ነበራቸው፡፡ የቡና መፈልፈያም ነበራቸው፤ ተወርሶባቸው ነበር ኢህአዴግ ከገባ በኋላ ነው እኔ ጠይቄ የመለሰላቸው፡፡
ቁም ነገር፡- 30 ዓመታት ረዥም ጊዜ ነው፤ ምን ከፉና ደግ ነገር ታስታውሻለሽ ከበዓሉ በኋላ ?
ወ/ሮ አልማዝ፡- ልጆቼን ጥርሴን ነክሼ አሳድጌ ለወግ ማዕረግ ማብቃት በመቻሌ እግዚአብሔር አመሠግነዋለሁ፡፡ ልጆቼ አባታቸው ከቤቱ ወጥቶ እንደቀረባቸው ሳይሳቀቁ የሚፈልጉትን ነገር እያሟላሁላቸው የሚፈልጉት ቦታ በዓሉ በነበረ ጊዜ የምንወስዳቸው ቦታ ሶደሬ ላንጋኖ እየወሰድኩ ሳይሰማቸው ነው እንዲያድጉ ያደረግሁት ሁለቱ አሁን አሜሪካ ሀገር ተምረው ተመርቀው ትዳር ይዘዋል ትንሹ ክብረ በዓሉ አብሮኝ አለ፡፡ ለዚህም እግዚአብሔርን አመሠግነዋለሁ፡፡ ያ ነገር ሆኗል ከዛ ውጪ ያለው ነገር የሚነሳ አይደለም ክፉ ጊዜ ነበር፡፡
ቁም ነገር፡- መንግስት ሲቀየር ምን ታስቢ ነበር፤ በዓሉ ታስሮም ከሆነ ቦታ ይገኛል ብለሽ ታስቢ ነበር?
ወ/ሮ አልማዝ፡- እጠብቅ ነበር፤ ተስፋ አደርግ ነበር ግን ያው የዛን ጊዜ መንግስት እንደተቀየረ በሬዲዮ አንድ ነገር ሲነገር ሰማሁ፤ አንድ በወቅቱ ሹፌር ነበርኩ ሊገረፍ ሲል አመላልሰው ነበር ያለ ሰው አውቃለሁ የሚለውን ሲናገር ስሰማ ራሴን ስቼ ወደቅሁ፡፡ ከዛ በኋላ የማውቀው ነገር የለም፡፡ በኋላ በቤታችን ዙሪያ እኔ ምንም ሳላውቅ ‹‹ከቤቱ እንደወጣ የቀረው ደራሲና ጋዜጠኛ በዓሉ ግርማ›› ብለው ፎቶውን ሁሉ አባዝተው በየህንፃው ላይ ለጥፈው ተመለከትኩ፡፡ በዓሉ የሚወዳትን ሚስቱን ትቶ፤ የሚወዳቸውን ሶስት ልጆቹን ትቶ ከቤቱ እንደወጣ ለሀቅ የወደቀ ሰው ነው›› ይላል የተለጠፈው በከተማው ላይ፡፡ ሰዎች ይህንን ከተማ ላይ የተለጠፈውን አይተው እያለቀሱ ቤቴ ድረስ መጡ እኔ ግን አሁንም ድረስ በዓሉ ይመጣል ብዬ በር በሩን ነው የማየው፤ ግን አንዳንድ ጊዜ ደግሞ በግሌ በነፍስ ካለ በእኛ ላይ እንዴት ሊጨክንና ሊጠፋ ይችላል እላለሁ ግን አሁንም ድረስ እንዲህ ነው የሚል ሰው አላገኘሁም፡፡
ቁም ነገር፡- ግን በወቅቱ ራስ ካሳ ግቢ ተንደው ከተቀበሩ ሰዎች መሀከል አንዱ በዓሉ ግርማ ነው ተብሎ አፅሙ ሲወጣ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን መታየቱን አላወቅሽም ?
ወ/ሮ አልማዝ፡- እኔ አላየሁም፡፡ ምን ያህል አስተማማኝ ነው በምን ተረጋገጠ ሲወጣ ለብሶት የነበረው ልብስ ምን ነበር ብሎ ያረጋገጠ አለ በበኩሌ አልሰማሁም፡፡
ቁም ነገር፡-መንግስት እንደተቀየረ የኢህአዴግ ባለስልጣናቱን አግኝተሸ የበዓሉን ግድያ ያውቃሉ ከሚባሉት ሰዎች ጠያቃችሁ እባካችሁ አሳውቁኝ አላልሻቸውም ?
ወ/ሮ አልማዝ፡- ብያለሁ፤ ወዲያው እኮ ነው ባለስልጣናቱ ከታሰሩ በኋላ ለተቋቋመው ልዩ አቃቤ ህግ ክስ ሲመስረት ቃሌን ሰጥቻለሁ፤ ለፍ/ቤቱ የሰጠሁት ቃል ለታሪክ ተመዝግቦ ይገኛል፡፡ መላ የኢትዮጵያ ህዝብ ሁሉ ስለ በዓሉ መጨረሻ የሚያውቁት እንደነግሩኝ ጠይቀያቸዋለሁ፤ ግን አቃቤ ህጉ፤ ‹‹በዓሉ ግርማ ላይ ለፍርድ የተገደለ ነው›› ብለው ደብዳቤ ፅፈው ሰጥተውናል፡፡ ምን ያደርጋል በዓሉ ግርማ ለህዝብ ብሎ ለሀቅ ብሎ የተሰዋ ደራሲ ነው፡፡ ግን አንዳንድ ሰዎች ያልሆነ ነገር ሲናገሩ ሲፅፉ አያለሁ፡፡ ለምሳሌ በዓሉ ግርማ ገዳም ውስጥ ነው ያለው ብለው በሬዲዮ ሁሉ ቅርብ ጊዜ ሲናገሩ ነበር፡፡ እዚህ ታይቷል፤ እዚያ ነው ያለው የሚሉና የሚፅፉ መፅሔቶች አሉ የበዓሉን ማንነት ተረድተው ሀቅ ቢያወጡ ነበር የምፈልገው፡፡ የቤተሰቡ ሀዘን ከመጨመር ውጪ ዋጋ የላቸውም፡፡ ስለ በዓሉ የተፃፉ ማናቸውም ነገሮች አያመልጡኝም፤ ግን እውነቱን የሚናገር የለም፡፡ የወደቀበትን የሚናገር የለም፡፡
ቁም ነገር፡- ኦርማይ መፅሐፉ እንደወጣ ነበር የታገደውና ከገበያ ላይ የተሰበሰበው ሰው እጅ ገብቶ ነበር ለማለት ይቻላል?
ወ/ሮ አልማዝ፡-የገዙ ሰዎች እያከራዩ ያስነብቡ ነበር፤ ሽያጭም 600 ብር ደርሶ ነበር፡፡
ቁም ነገር፡- መታገዱን ያወቃችሁት እንዴት ነበር ?
ወ/ሮ አልማዝ፡-እኔ መርካቶ ለቅሶ ለመድረስ ስሄድ ሰዎች የበዓሉ ግርማ መፅሐፍ ከገበያ ላይ እየተሰበሰበ ነው ሲሉ ሰማሁ፡፡ ደንግጪ ቦርሳዬን ከነ ገንዘቡ የት ቦታ እንደጣልኩት አላውቅም፤ ስበር ቤት ስደርስ ‹‹ዳዲ መጥቶ ነበር፤ መፅሐፉ ከገበያ ላይ እየተሰበሰበ ስለሆነ አታስቢ›› ብሎሻል አሉኝ ልጆቼ፤ እሱ ለካ ቀድሞ አወቋል፡፡
ቁም ነገር፡- በወጣ በስንተኛው ቀን መሆኑ ነው?
ወ/ሮ አልማዝ፡-የተሰጠው ለ10 ቀናት ብቻ ነው፡፡ ልክ በ10ኛው ቀን ነው የሰበሰቡትና ያቃጠሉት
ቁም ነገር፡- ቤት ውስጥ መፅሐፉን አምጥቶት ነበር?
ወ/ሮ አልማዝ፡- ያው ሁሌም እንደሚያደርገው ለሰዎች በስጦታ መልክ የሚሰጠውን የተወሰኑ መፅሐፍት አምጥቶ ነበር፤ ልክ ያንን የሰማሁ ዕለት አንዷን መፅሐፍ ወስጄ ደብቄያት አሁንም ድረስ አለ፡፡
ቁም ነገር፡- በታተመው እና በቀድሞው መፅሐፍ መሀከል ልዩነት አለ የሚሉ ወገኖች አሉ፤ የተቀነስ ነገር አለ እንዴ?
ወ/ሮ አልማዝ፡- ራሱ ነው የታተመው፤ ያው ኢህአዲግ እንደገባ የወቅቱ የማስታወቂያው ሚኒስትር አቶ በረከት ነው ራሱ ጠርቶኝ ልክ እንደወረደ መፅሐፉ ይታተምለት ብሎ ትዕዛዝ የሰጠልኝ፡፡ ያው ድጋሚ ሲታተም ለመታሰቢያ ይሁን ብዬ የሆነ ነገር ማስታወሻ ፃፍኩለት፤ አብሮታተመ፡፡
ቁም ነገር፡- ቤቱን ልቀቂ ተብለሽ ነበር ?
ወ/ሮ አልማዝ፡-እነሱማ በላዬ ላይ ሁሉ ሊያሽጉ መጥተው ነበር፡፡ በር ላይ ጠብቄ ዞርበሉ አልኳቸው፤ በማግስቱ የኪቤአድ ዋና ስራ አስኪያጅ ጋር ሄጄ ባለቤቴ ከቤት እንደወጣ አልተመለሰም፡፡ ሶስት ልጆቼን ይዤ የት ልወድቅ ነው? ስለው ባለቤትሽ ማነው አለኝ፤ አላውቅም አልኩት፡፡ ወታደር ነው? አለ አይደለም፡፡ ማነው? ሲለኝ አልናገርም አልኩት፡፡ እሺ ለጊዜው ሰው እያነጋገርኩ ነው ከቢሮ ውጪ ጠብቂኝ አለኝ፤ ከቢሮ ስወጣ ፀሐፊው አየችኝ፤ አወቀችኝ ከዛ ገብታ ነገረችው መሰለኝ እንግዶችን ከሸኙ በኋላ ‹‹የበዓሉ ግርማ ባለቤት መሆንሽን ለምን አልነገርሽኝም›› አለኝ፤ ለምን እነግርሃለሁ አልኩት የአንቺ ጉዳይ በጣም ከባድ ነው፡፡ ለማናቸውም ምን ልርዳሽ ብሎ 100 ብር ከኪሱ አውጥቶ ሊሰጠኝ እጁን ዘረጋ፡፡ እኔ ልመና አልመጣሁም፤ ምፅዋትህን ቤተክርስትያን ሄደህ ስጥ አልኩትና ‹‹ባሌ ወንድ ነው እኔም የወንድ ልጅ ነኝ እስኪ ማነው መጥቶ የሚያሰወጣኝ አያለሁ›› ብየው ወጣሁ ከዛ በኋላ አልመጡም፤ ክትትሉ ግን እንዳለ ነበር፡፡
ቁም ነገር፡- በመጨረሻ ያ ክፉ ጊዜ ከነልጆቸሽ ስታሳልፊ አይዞሽ ሲሉ የነበሩ አንቺንም በዓሉንም ሳያውቁ ግን የሚቆረቆሩ በብዕራቸውም የሚጠይቁ ሰዎች ይኖራሉና የምታመሰግኚያቸው ሰዎች አሉ ?
ወ/ሮ አልማዝ፡-በጣም ብዙ ሰዎች አሉ፤ ያን ጊዜ እኮ መንገድ ላይ ሁሉ ሰዎች ይሸሹኝ ነበር፤ ፊታቸውን ሁሉ የሚያዞሩ ነበር ስንት ነገር አብረን ያሳለፍን ሁሉ ለእግዚአብሔር ሰላምታ ይፈሩ ነበር፤ የሆነ ሆኖ ያ ጊዜ አለፈ፡፡ በመጀመሪያ የኢትዮጵያ መፅሐፍት ድርጅት ባለቤት አቶ ተስፋዬ ዳባ ብዙ መፅሐፉን ያተሙለት ባለውለታችን ነው፤ አቶ አማረ ማሞ፣ ደራሲ አበራ ለማ፣አመሰግናቸዋለሁ፤ ዶ/ር ሙለጌታ በዛብህ የቅርብ ጓደኛው ነው ይጠይቀኛል፤ የልጆች ት/ቤት ያግዘኝ ነበር፤ አቶ ጌታቸው ብናልፈው ሳይፈራ የሚጠይቀኝ ሰው ነው፡፡ አቶ እስቂያስ አገኘው ቤተሰብ ነው፡፡ ከኔ ያልተለየ ሰው ነው፡፡ እግዚአብሔር ውለታቸውን ይክፈላቸው፤ ብድራቸውን ይመልስላቸው ነው የምለው፤ ፕሮፊሰር መስፍን ወልደ ማርያም ቤተሰብ ነበር፤ አሁን አሁን ሲታሰር ሁሌ ሄጄ እጠይቀው ነበር፤ ከበዓሉ ጋርም ይግባቡ ነበር የወንድሜም ጓደኛ ነው
ቁም ነገር፡- በወቅቱ ከነበሩ መንግስት ባለስልጣናት መሀከል አንዳንዶቹ በአሁኑ ወቅት ከሎኔል መንግስቱን ጨምሮ መፅሐፍ እየፃፉ ነው፤ ስለ በዓሉ ግርማ መጨረሻ የሚያውቁትን ነገር እንዲናገሩ ምን መልእክት ታስተላልፊያለሽ ?
ወ/ሮ አልማዝ፡- እኔ የምላቸው ነገር የለም፤ የሚያውቁትን ግን ለኢትዮጵያ ህዝብ ቢናገሩ እውነቱን ቢያወጡ ጥሩ ነው ለህሊናቸው ቢሆን ሀቁን ቢያወጡ ደስ ይለኛል፡፡
ቁም ነገር፡- ደርግ ግን ይወድቃል ብለሽ ታስቢ ነበር ?
ወ/ሮ አልማዝ፡-ለምን አይወድቅም? ጃንሆይም ወርደዋል፤ ደግሞ የእነሱ ግፍ ይበልጣል፣ ግፉ ራሱ ይጥላቸዋል ብዬ ነበር የማስበው፡፡
ቁም ነገር፡- በዓሉ ከቤት ከወጣ በኋላ መኪናው ቃሊት አካባቢ ቆማ ነበር ተብሏል እንዴት አገኘሻት ?
ወ/ሮ አልማዝ፡- ያው በየዕለቱ ወዲያ ወዲህ እያልኩ በየ እስር ቤቱ ሁሉ እጠይቅ ነበር፤ በ10 ኛው ቀን ቃሊቲ መንገድ ዳር ቆማለች ብለው ነገሩኝ፤ ሄጄ ጠይቄ ልወስድ ብዬ አስፈቀድኩ፤ መኪና ተመድቦ አጅበውኝ መኪናዋን ከቆመችበት አመጣናትና ጊቢ ውስጥ አቋምኳት፡፡ ጠዋት ጠዋት ባየኋት ቁጥር መበሳጨት ስላልፈለግሁ ሸጥኳት፡፡
ቁም ነገር፡- አመሠግናለሁ፤