(ኢሳት ዜና) – ያለፉትን 9 ወራት ንብረቶቻቸውን በመሸጥ ውጭ የሚወጡበትን አጋጣሚ ሲያፈላልጉ ከርመዋል።
98 በመቶ የሚሆነውን የመከላከያ ሰራዊት ከፍተኛ የአዛዥነት ቦታዎችን ከተቆጣጠሩት የህወሃት ጄኔራሎች ባልተናነሰ በከፍተኛ የስልጣን ቦታ ላይ የነበሩት ብቸኛው የአማራ ተወላጁ ጄኔራል አበባው ታደሰ በጄ/ል ሳሞራ የኑስ ትእዛዝ ከሃላፊነታቸው ዝቅ ብልው እንዲሰሩ ከተወሰነባቸው በሁዋላ በመጨረሻ ከመከላከያ ሰራዊት መሰናበታቸውን ምንጮች ገልጸዋል።ጄ/ል አበባው ከጄ/ል ሞላ ሃ/ማርያም እና ከጄ/ል ሰአረ መኮንን ጋር በመነጋገር ጄ/ል ሳሞራ የኑስ በመከላከያ ውስጥ የሚታየውን ሙስና አልተቆጣጠሩም በሚል ሊገመግሙዋቸው ነበር የሚል ሪፖርት ቀርቦባቸው ከሃላፊነት ዝቅ እንዲሉ መደረጉን ኢሳት ከ9 ወራት በፊት ” የመተካካቱ ተውኔት በመከላከያ ሰራዊት ውስጥ” በሚል ርእስ ባቀረበው የምርመራ ዘገባ ገልጿል። በጊዜው እንደተዘገበው ጄ/ል ሳሞራ የኑስን የሚተካው ኢታማዦር ሹም ከህወሃት እጅ እንዳይወጣ ለማድረግ ተፎካካሪ ሆነው ይቀርባሉ ተብሎ የተገመቱትን ጄ/ል አበባውን ጠልፎ ለመጣል ሁለቱ ጄኔራሎች የቤት ስራውን ወስደው ሲሰሩ ቆይተዋል፡፤ ጄ/ል አበባው ግሳጼ ደርሶባቸው ከሃላፊነት እንዲለቁ ሲደርግ የህወሃቶቹ ጄ/ል ሰአረ መኮንንና ጄ/ል ሞላ ሃ/ማርያም ወደ አዲስ አበባ ተጠርተው ከፍተኛ ስልጣን ተሰጥቷቸዋል። በአንጻሩ ጄ/ል አበባው ከሃላፊነት ተቀንሰው ያለፉትን 9 ወራት ንብረቶቻቸውን በመሸጥ ውጭ የሚወጡበትን አጋጣሚ ሲያፈላልጉ ከርመዋል።
ጄ/ል አበባው በባህርዳር ከተማ የሚገኘውን አልዋቅ ሆቴልና ሌሎች ድርጅቶቻቸውን ለሼክ ሙሃመድ አላሙዲን ከሸጡ በሁዋላ ከአገር ለመውጣት ቢያስቡም መከልከላቸውንና የቁም እስረኛ መሆናቸውን ምንጮች ገልጻል።የጄ/ል አበባው የቁም እስረኛ መሆን በብአዴንና በህወሃት የመከላከያ የሰራዊት አባላት መካከል ያለውን ሽኩቻ ሊያባብሰው ይችላል የሚሉት ምንጮች፣ አንዳንድ ምልክቶች መታየታቸውን ተከትሎ በመካከለኛ ደረጃ ላይ በሚገኙ የአማራተወላጅ መኮንኖች ለይ ጥበቃ እና ክትትሉ ጨምሯል። የብአዴን አባል የሆኑ መኮንኖች በሰራዊቱ ውስጥ የሚታየውን የህወሃት ፍጹም የባላይነት በተደጋጋሚ ይቃወማሉ።