(ዘ-ሐበሻ) የግንቦት 7 አባል ነው ተብሎ የታሰረው አበበ ካሴ የተባለ ወጣት በቂሊንጦ ማረሚያ ቤት በሕወሓት/ኢሕአዴግ ካድሬ ወታደሮች ከፍተኛ የሆነ ግፍ እየተፈጸመበት መሆኑን ከስፍራው ለዘ-ሐበሻ መረጃ ያደረሱ ወገኖች አስታወቁ።
“ዛሬ ከወደ ቂሊንጦ የደረሰኝ መረጃ እጅግ የሚዘገንና እንቅልፍ የሚነሳ ነው” በሚል መረጃውን ያቀበለን ውስጥ አዋቂ አበበ ካሴ ግንቦት 7 ነው በሚል የታሰረ ሲሆን መቀጣጫ እናደርግሃለን፤ ምስጢር አውጣ እያሉ በሚዘገንን መልኩ የ10 ጣቶቹን ጥፍሮች እንደነቃቀሉት አስታውቋል። እንደ መረጃ ምንጩ ገለጻ ከሆነ ብልቱ ላይ የታሸገ የላስቲክ ውሃ (ሃይላንድ) በማንጠልጠል ሲያሰቃዩት የቆዩ ሲሆን በአሁኑ ወቅት ከብልቱ ፈሳሽ መውጣት መጀምሩም ተገልጿል። እንደመረጃ ምንጩ ገለጻ ከሆነ አበበ በብልቱ ላይ በደረሰበት ከፍተኛ ሕመም ህክምና እንዲደረግለት ቢጠይቅም “ሕክምና ማግኘት አይደለም ገና እንግድልሃለን” ብለው ከልክለውታል።
አበበ በአሁኑ ወቅት የእስረኛ መለያ መታወቂያውን መቀማቱን ያጋለጠው የመረጃ ምንጫችን የሚፈጸምበት ግፍ ከእለት ወደ እለት እየጨመረ መምጣቱን እና እየተፈጸመበት ያለው የጭካኔ ተግባርም በምን ዓይነት ቋንቋ መግለጽ እንሚቻል ከባድ እንደሆነ ገልጾልናል።