ላለፉት ሦስት ወራት በሽብርተኝነት ተጠርጥረው በእስር ላይ የቆዩት የዓረና ፓርቲ አባል ወ/ሮ አልጋነሽ ገብሩና ሌሎች ስድስት ግለሰቦች እያንዳንዳቸው በ15 ሺሕ ብር ዋስ ተለቀቁ፡፡
የመቐለ ምንጮች ለሪፖርተር እንደገለጹት ከሆነ፣ ‹‹ሕገ መንግሥቱንና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱ በኃይል ለመናድ ተንቀሳቅሰዋል›› በሚል በሽብር ተጠርጥረው በእስር እንዲቆዩ የተደረጉት ወ/ሮ አልጋነሽ ገብሩ፣ አቶ ምዑዝ ፀጋይ፣ አቶ ሐለፎም ገብረ እዝጊ፣ አቶ አያሌው ጣዕምያለው፣ ቄስ ብርሃኑ ቆባዕ እና አንድ ስማቸው ያልተጠቀሱ ግለሰብ ባለፈው ማክሰኞ ከእስር ተለቀዋል፡፡
ግለሰቦቹ እግሪ ሐሪባ የተባለ በመቐለ ዙርያ የሚገኝ አንድ ገበሬ ማኅበር ቀበሌ ነዋሪዎች ሲሆኑ፣ ‹‹መንደሩ ወደ ከተማ ይቀላቀል አይቀላቀል›› በሚል በተፈጠረ አለመግባባት የክልሉን መንግሥት በመቃወማቸው ለእስር መዳረጋቸው መዘገቡ ይታወሳል፡፡
ከተወሰኑ የእስራት ቀናት በኋላ በዋስ ለማስለቀቅ ጥረት ቢደረግም፣ ከፍርድ ቤት በሽብርተኝነት መጠርጠራቸውን የሚገልጽ ደብዳቤ የደረሳቸው ወ/ሮ አልጋነሽና ሌሎቹ ታሳሪዎች በእስር እንዲቆዩ ተደርጓል፡፡
ወ/ሮ አልጋነሽና ሌሎቹ ተጠርጣሪዎች እያንዳንዳቸው በ15 ሺሕ ብር ዋስ ቢለቀቁም፣ የአምስት ልጆች እናት የሆኑት ወ/ሮ አልጋነሽ ገብሩ ልጆቻቸው ደጋፊ አጥተው ችግር ላይ ወድቀው እንደነበር፣ ሕዝቡ ባደረገላቸው ድጋፍ ወደ ጎዳና ከመውጣት እንደታገደጋቸው ከዓረና ፓርቲ የተገኘው መረጃ ያስረዳል፡፡
Source:: Ethiopian Reporter