በዶ/ር ቁምላቸው አባተ
የእናቶችንና የልጆችን ጤንነት ማሻሻል የዓለም ሁሉ ቀዳሚ ጉዳይ ነው፡፡ ብዙ እናቶች በእርግዝና ወቅት ሊያደርስ የሚችለውን ጉዳት ብዙም ሳያስተውሉ ባህላዊም ሆነ ዘመናዊ መድሃኒት ይወስዳሉ፡፡ መድሃኒትም ይሁን እፅ በእርግዝና ወቅት በሚወሰድበት ጊዜ እንግዴ ልጁን አቋርጦ በእድገት ላይ ወዳለው ሽል ይደርሳል፡፡ ከሚያስከትላቸው ችግሮች ውስጥም፡-
- ማስወረድ
- የፅንሱ እድገት መሰናከል
- የአዕምሮ ዝግመትና
- የአካል ጉድለት ይጠቀሳሉ፡፡
አንዲት እናት በክትትል ወቅትም የወሰደቻቸውን መድሃኒቶች በሙሉ ዘርዝራ መናገር ይኖርበታል፡፡ በሀኪም ትዕዛዝና ያለ ትዕዛዝ የወሰደቻቸውን እንደ ምግብ ድጋፍ የሚውሉ ቫይታሚኖች እንዲሁም የባህል መድሃቶች ሊጠቀሱ ይችላሉ፡፡ አልፎ አልፎም ይሁም በተደጋጋሚ ሲጋራ ማጨስ፤ አልኮል መጠጣት ወይም ሌላ እፅ የመውሰድ ልማድ ካለም ክትትል ለሚያደርጉት ባለሞያ መንገር ጥቅም ይኖረዋል፡፡
መድሃኒት ወይም እፅ በመውሰድ በሽሉና እርግዝና ላይ ሊያስከትል የሚችላቸው ጉዳቶች የሚከተሉት ናቸው፡-
- የሽሉን ተገቢ እድገት መግታት
- እንግዴ ልጁ ላይ ጉዳት በማድረስ ሽሉን አደጋ ላይ መጣል
- የውርጃ መከሰት ዕድልን መጨመርና እንዲሁም ምጥ ቀድሞ እንዲመጣ ማድረግ ናቸው፡፡
የሚከተለው ጉዳት በመድሃኒቱ ወይም በሚወሰደው የእፅ አይነት፤ በአወሳሰዱ፤ በመጠኑ፤ ከሌሎች ተደራቢ መድሃኒቶች ወይም እፆች ጋር በመወሰዱ፤ በተወሰደበት የእርግዝና ወቅት የእናት የጤና ሁኔታና የአመጋገብ ልምድ ወዘተ ሊወሰን ይችላል፡፡
እንደሚወሰደው መጠንና ተደጋጋሚነት በትዕዛዝም ይሁን ያለትዛዝ የሚወሰዱ መድሃኒቶች፣ እፆች፣ ሲጋራ፣ አልኮልና የመሳሰሉት ለእርግዝና እክል ናቸው፡፡ በእርግዝና ወቅት መሰጠት የሚገባቸው መድሃኒቶች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ለሽሉ ጤናማ እድገት የእናትየው መልካም ጤና አስፈላጊነት አያጠያይቅም፡፡ እንደ አስም፣ የሚጥል ህመም፣ ስኳርና መሰል ህመም ያላቸው እናቶች ተገቢውን መድሃኒት በእርግዝና ወቅት መቀጠል ይኖርባቸዋል፡፡
አንዳንድ ጊዜ በባለሙያ የታዘዘ መድሃኒት ለሽሉ አደጋ የሚፈጥር ሊሆን ይችላል፡፡ መድሃኒቱን ማቋረጥ ግን በእናትየውና በልጁ ላይ አደጋ ሊፈጥር ይችላል፡፡ በሚቻልበት ጊዜ ተቀራራቢ ጥቅም ያለውና በእርግዝና ላይ አደጋ የማይፈጥር መድሃኒት ተተክቶ ሊታዘዝ ይችላል፡፡
በእርግዝና ወቅት የሚከሰቱ ህመሞች በመድሃኒት ሊታከሙ ይችላሉ፡፡ ከባለሙያው ትእዛዝና ፈቃድ ውጪ መድሃኒቱን መጠንና የሚወሰድበትን የጊዜ ብዛት ግን መቀየር አይገባም፡፡ ለአንዳንድ ህመሞች ተገቢውን ህክምና በተገቢው ወቅት ካልተወሰደባቸው እናትንና የሽሉን ጤና አደጋ ላይ እንደመጣል ይቆጠራል፡፡ ለሁሉም ነገር አንዲት እናት ስለመድኃኒት ያላትን ማንኛውንም ሃሣብ ባለሙያ ብታማክር መልካም ነው፡፡ እንደ አጠቃላይ ማስታወሻ ግን አንዲት ነፍሰጡር እናት እንዳትጠጣ፣ እንዳታጨስ፣ እፅ እንዳትወስድ፣ ሱስ ካለባት ደግሞ ለማቆም ይረዳት ዘንድ ባለሙያ ማማከር ከዚህ ባሻገር ደግሞ ምንም እንኳን አንዳንድ መድኃኒቶችን በቀላሉ ያለባለሙያ ትእዛዝ ማግኘት ቢቻልም በእርግዝና ላይ አደጋ አያደርስም ብሎ አለመደምደም አስፈላጊ ነው፡፡