Quantcast
Channel: Ethiopian News | ዘ-ሐበሻ | Latest News Provider | News For All
Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Health: “ብብቴን፣ ግምባሬን፣ መዳፌንና እግሬን በጣም ያልበኛል”ጥያቄና 9 መፍትሔዎቹ

$
0
0

የከባድ ላብ ነገር
/Hyperhidrosis/

<<ከፍተኛ የሆነ የላብ ችግር አለብኝ፡፡ ብብቴ ውስጥ፣ በግንባሬ ላይ በተለይም በመዳፌ ላይ እንደ ውሃ ይቀዳል፡፡ እግሬም እንደዚሁ በጣም ያልበኛል፡፡ ከሰው መቀላቀል ትቻለሁ፡፡ እባካችሁን ከዚህ እግር ከወርች ከያዘኝ የከባድ ላብ ችግር መፍትሄ ካለ ጠቁሙኝ፡፡>> ሲል አንድ የዘ-ሃበሻ አንባቢ በስልክ ያቀረበልንን ጥያቄ መሰረት በማድረግ ጉዳዩን የዛሬ የጤና አምዳችን ጉዳይ አድርገነዋል፡፡
© Copyright 2010 CorbisCorporation
ላብ ሰውነታችን ራሱን የሚያቀዘቅበት ተፈጥሯዊ መንገድ ነው፡፡ አብዛኛው ይህ ሁኔታ ተፈጥሯዊ እና የጤንነት ምልክት ነው፡፡ አንዳንድ ሰዎች ግን ተደጋጋሚ እና የማያቋርጥ ላብ ይታይባቸዋል እና ይህ ሁኔታ በህክምና ቋንቋ ሃይፐርሃይድሮሲስ/Hyperhidrosis/ ይባላል፡፡
ሃይፐርሃይድሮሲስ/ከባድ ላብ/ በላብ ዕጢዎች የሚመረተው ላብ ሰውነት ራሱን ለማቀዝቀዝ ከሚፈልገው በላይ ነው፡፡ ይህ በሽታ በአብዛኛው መዳፍንና የእግር ስርን እና ብብትን ያጠቃል፡፡ የዕለት ተዕለት ስራን ከማወኩም በተጨማሪ ከባድ ላብ ማህበራዊ ጭንቀት እና የመሸማቀቅ ስሜት ብሎም ራስን ማግለል ሊያስከትል ይችላል፡፡

ጥሩው ነገር ግን ይህንን ችግር ለማከም የተለያዩ ዘዴዎች መኖራቸው ነው፡፡ ከባድ ላብ እጅግ ከባድ ሲሆን እስከ ቀዶ ጥገና የሚያደርስ ህክምና አለው፡፡ ምንም እንኳን መቼ የት እና ምን ያክል ያልበናል የሚለው በስፋት ቢለያይም አብዛኛው ሰው ከበድ ያለ የጉልበት ስራ ሲሰራ፣ ሞቃታማ ቦታ ሲሆን፣ ድንጋጤ ወይም ጭንቀት እና አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ሲሆን ያልበዋል፡፡ ከባድ ላብ ሃይፐርሃይድሮሲስ ያለበት ሰው የላብ ሁኔታ ግን ከላይ ከተጠቀሰው በእጅጉ ከፍ ያለ ነው፡፡
የከባድ ላብ ዋና ዋና ምልክቶች ቶሎ ቶሎ መምጣቱ የሚታይ ከሚገባው በላይ የሆነ እና ብብትን የሚያበሰብስ ሲሆን ነው፡፡ ከሚገባው በላይ የሆነ የሚያስጨንቅ የላብ መኖር በተለይም በእግር ስር፣ በብብት፣ በራስ እና በፊት ላይ የሚታይ ሲሆን፣ የቆዳ ማጣበቅ ወይም ከእጅ መዳፍና ከእግር መርገጫ ጠብ ጠብ የሚል ላብ ሲታይ ነው፡፡

ሃይፐርሃይድሮሲስ የሚለው ስያሜ የሚሰጠውን የተቸጋሪውን የዕለት ተዕለት ስራን የሚያደናቅፍ ከፍተኛ የላብ መጠን/ከባድ ላብ ሲኖር ነው፡፡ ይህ ክስተት ያለ ምንም በቂ ምክንያት ቢያንስ በሳምንት አንድ ጊዜ ይታያል፡፡ ለእነዚህ ሰዎች ከባድ ላብ የማህበራዊ ህይወትን ያውክባቸዋል፡፡ እጃቸው ያለማቋረጥ ስለሚረጥብ ስራ መስራትም ሆነ መዝናኛ ቦታ ራሳቸውን ማዝናናት ይሳናቸዋል፡፡ በዚህም ምክንያት ከሰው ጋር ሲጨባበጡ በእጃቸው ላብ ምክንያት እና ሸሚዛቸው የላብ ቅርፅ ስለሚያሳይ አንዳንዴ ላቡ ጠረን ስለሚኖረው በዚህ በሚፈጠርባቸው መሸበር ራሳቸውን ከሰው ያገላሉ፡፡
እንደዚህ ያለ ችግር ያለበት ሰው ከተለመደው በላይ ድንት ከፍ ያለ ላብ ሲያይ፣ ላብ የዕለት ተዕለት ስራውን ሲያደናቅፍበት፣ እና የሌሊት ላብ ያለ በቂ ምክንያት ሲኖረው ሐኪም ጋር መቅረብ ይኖርበታል፡፡ የብርድ ላብ የታየበት ማንኛውም ሰው ሐኪም ዘንድ መቅረብ አለበት፡፡ በተለይም ደግሞ ሁኔታው ከጭንቅላት ቅል መቅለል እና የደረት ወይም የሆድ ህመም ስሜት ጋር አብሮ ከመጣ የልብ በሽታ፣ የጭንቀት ወይም የሌላ ከፍተኛ ህመም ምልክት ሊሆን ስለሚችል ጊዜ ሊሰጠው አይገባም፡፡
የከባድ ላብ ምንጩ ሰውነታችን ሙቀቱን ከሚቆጣጠርበት የቁጥጥር ስርዓት ይመነጫል በተለይ ደግሞ የላብ ዕጢዎች ቆዳችን ሁለት አይነት የላብ ዕጢዎች አሉት፡፡ አንደኛው ኢክራይን ዕጢ ሲባል ሌላኛው ደግሞ አፓክራይን ዕጢ ሲባል ሌላኛው ደግሞ አፓክራይን ዕጢዎች ይባላሉ፡፡ ኢክራይን ዕጢዎች በአብዛኛው ሰውነታችን ውስጥ ሲገኙ በቀጥታ አፋቸው ወደ ቆዳ ላይኛው ክፍል ይከፈታል፡፡ አፓክራይን ዕጢዎች ግን የሚገኙት በብዛት ፀጉር በሚሸፍናቸው የቆዳ ክፍሎች ላይ ነው፡፡ ለምሳሌ የራስ ቅል፣ ብብት እና ጭገር አካባቢ ነው፡፡
የሰውነታችን ሙቀት ሲጨምር አውቶኖሚክ ነርቨስ ሲስተም የተባለው የአዕምሮ ክፍል እነዚህን ዕጢዎች ላብ ወደ ቆዳ የላይኛው ክፍል እንዲለቁ ያደርጋል፡፡ ላቡም ሰውነታችንን ከቀዘቀዘ በኋላ ይተንና ቆዳችን ይደርቃል፡፡ ይህ ላብ በውስጡ በአብዛኛው ውሃ እና ጨው ይይዛል አልፎ አልፎ ደግሞ ሌሎች ኬሚካሎችም በተጨማሪ ይይዛል፡፡

ከባድ ላብ በአንድ ቦታ የተወሰነ ወይም ጠቅላላ ወይም በርካታ ሰውነታችንን የሚያካትት /generalized hyperhidrosis/ በመባል ይከፋፈላል፡፡ የመዳፍና የእግር ከባድ ላብ በአብዛኛው ቀን ቀን የሚከሰት ነው፡፡ አንዳንዴም በብብት አካባቢም ይታያል፡፡ ይህ ላብ ሌሊት በአመዛኝ አይታይም፡፡ በሁለቱም የሰውነታችን ክፍል በእኩል መልኩ ይታያል፡፡ ይህ አይነት ከባድ ላብ ወደ ሃያው የዕድሜ ክልል አካባቢ በአብዛኛው ይጀምራል፡፡ ከሌላ በሽታ ጋር ግንኙነት የሌለውና ራሱን የቻለ ችግር ነው፡፡ ትክክለኛው ምክንያት ወይም መነሻ ገና አይታወቅም፡፡ ነገር ግን በዘር የመምጣት አዝማሚያም ይኖረዋል፡፡

በርካታ የሰውነት ክፍልን የሚያጠቃው የከባድ ላብ ችግር አይነት በድንገት የሚጀምር ነው፡፡ በርካታ የሰውነት ክፍልን ያጠቃል፡፡ በአብዛኛው ሌላ ምክንያት አለው፡፡ ለምሳሌ የመድሃኒት የጎንዮሽ ጉዳት፣ የበሽ ምልክት፣ የማረጥ ምልክት፣ የስኳር መጠን በደም ውስጥ ዝቅ ማለት፣ የታይሮይድ በሽታ፣ የደም ካንሰር በሽታ፣ የልብ ድካም በሽታ ወይም የአንድ ወይም የሌላ ኢንፌክሽን በሽታ ምልክት ሊሆን ይችላል፡፡ በዚህ ጊዜ አስፈላጊውን መድሃኒት በመውሰድ ወይም መንስኤውን በሽታ በማከም ላቡን ያጠፋዋል፡፡

በከባድ ላብ መንስኤነት የሚመጡ በርካታ የአካልና የስነ ልቦና ችግሮች መካከል የፈንገስ ኢንፌክሽን፣ በባክቴሪያ ምክንያት የቆዳ እና የቆዳ ፀጉር አካባቢ ኢንፌክሽን በእግር ጣቶች አካባቢ የሚመጡ ኢንፌክሽኖች፣ የጎዳ ኪንታሮት /warth/ በሽታ ወይም ኪንታሮት ሲታከም ቶሎ ያለመዳን ችግር፣ በቆዳ ላይ በሙቀት የሚመጡ ሽፍታዎች መብዛት፣ እና ማህበራዊ መገለል ከላይ እንደተጠቀሰው ግለሰቡ ራሱን ማግለል የመጀመር ሁኔታ ይታያል፡፡

በከባድ ላብ ምክንያት ወደ ሐኪም ዘንድ ሲቀርቡ ሐኪሙ የተለያዩ የበሽታ ታሪኮችን ይጠይቃሉ፡፡ የአካል ምርመራም ያደርጋሉ፡፡ የደምና የሽንት ምርመራ በማዘዝ በሽታው በምን ምክንያት እንደመጣ ለማወቅ ይሞክራሉ፡፡ ከተገኘም ሐኪምዎ ቴርሞ ሬጉሌተር ቴስት ሊጠቀሙ ይችላሉ፡፡
የተለያዩ ምርመራዎች ካደረጉ በኋላ ሐኪሙ የተለያዩ የህክምና ዘዴዎችን ሊጠቀም ይችላል፡፡ ሐኪምዎ እንደ አልሙኒየም ክሎራይድ የመሰሉ የመድሃኒት ይዘት ያላቸውን ሊይዙ ይችላሉ፡፡ ይህ መድሃኒት ከቀላል እስከ መካከለኛ ደረጃ ሃይፐርናይድሮሲስን ለማከም ወይም ለመቀነስ ይችላል፡፡ ይህ መድሃኒት ከተገኘ ጥሩ ውጤት ለማግኘት ላብ በሚበዛበት አካል ላይ ሌሊት ሌሊት ማድረግ ነው፡፡ መድሃኒቱ ቆዳን የማሳበጥ፣ የማቅላት እና የማሳከክ ፀባይ ያለው ጠንካራ ኬሚካል ነው፡፡ ይህንን ለመከላከል ጠዋት በደምብ ማጠብ ያስፈልጋል፡፡ በርካታ የሰውነትን ክፍሎች የሚያጠቃልል የላብ ችግር ከሆነ ሐኪምዎ አንቲ ኮለነርጂክ መድሃኒቶችን ሊይዙ ይችላሉ፡፡ ይህም መድሃኒት የጎንዮሽ ጉዳቶች አሉት፡፡ የቆዳ ሐኪሞች ደግሞ አዩንቶፎረሲስ በሚባል ዘዴ ያክሙታል፡፡ ከዚህም ሌላ በቶሊየም ቶክሲን የተባለ መድሃኒት ጥቅም ላይ ሊውል ይችላል፡፡ ይህ ኬሚካል የተወሰኑ ጡንቻዎችን ፓራላይዝ በማድረግ የቆዳን የእርጅና ገፅታ ለማጥፋት ባደጉት ሀገሮች ጥቅም ላይ የሚውልበት ጊዜ አለ፡፡ይህም የሚደረገው ላብን በሚመለከት አዕምሮ ወደ ላብ ዕጢዎች የሚመጣውን የነርቭ ሂደት በማቋረጥ ነው፡፡ ወደዚህ ቀዶ ጥገና አሰራር ዝርዝር ሂደት ውስጥ መግባት አንባቢያን ማደናገር ነው፡፡ ይህም ዘዴ እንደየሁኔታው ባደጉ ሀገራት ጥቅም ላይ ይውላል፡፡

ለአንዳንድ ከባድ ላብ ላላባቸው ሰዎች መፍትሄው ቀላል ነው፡፡ ከፋርማሲ በሚገዛ ላብ መከላከያ ሊቆም ይችላል፡፡ እነዚህ የላብ ማቆሚያ መድሃኒቶች የላብ መተላለፊያ መንገዶችን በመዝጋት ይህንንም በአልሙኒየም ጨው አማካኝነት ወደ ቆዳ የሚደርሰውን የላብ መጠን ይቀይሳል፡፡ ማስታወስ ያለብን ላብ መከላከያ ላብ ሲከላከል ዲኦራንት ደግሞ የላብን መጥፎጠረን ብቻ ነው የሚከላከለው፡፡

ከላብ መከላከያ በተጨማሪ የሚከተሉትን ማድረግ ላብን ለመቀነስና ከላብ ጋር ለተያያዙ የሰውነት መጥፎ ጠረን ጠቃሚ ነው፡፡
1. ቢቻል በየቀኑ መታጠብ ይህ በቆዳችን ላይ ያሉ ባክቴሪያዎችን ይቀንሳል
2. ከመታጠብ በኋላ እግርን በፎጣ በደንብ ማድረቅ፡፡ ይህም ባክቴሪያዎች እና ሌላ ጀርሞች ለመራባት የሚያመቻቸውን እርጥበት ይቀንሳል፡፡ በተጨማሪም እርጥበት የሚመጥ ፓውደር መጠቀም ይቻላል፡፡
3. ከተፈጥሮ ማቴሪያል የተሰሩ ጫማ እና ካልሲ መጠቀም ከቆዳ የተሰራ ጫማ እግራችን አየር እንዲያገኝ በማድረግ የእግር ላብን ይቀንሳል፡፡
4. ጫማ ውስጡ ቶሎ ስለማይደርቅ እያቀያየሩ /በየቀኑ/ ማድረግ ላብ በብዛት ያለበት እግርን ችግር ይቀንሳል፡፡
5. የጥጥና የሱፍ ካልሲ በመጠቀም እግርን እርጥበት ስለሚመጥ በተለይ ደግሞ ሯጭ ሰው እርጥበት መጣጭ ስፔሺያል ካልሲ እንዲጠቀም ይመከራል፡፡
6. ካልሲን በየቀኑ መቀየር ቢቻል በቀን ሁለቴ በመቀየር ካልሲ በተደረገ ቁጥር ታጥቦ እና በደንብ እግርን እንዲደርቅ በማድረግ ተጨማሪ መፍትሄ ይሆናል፡፡
7. እግርን ማናፈስ ከተቻለ በባዶ እግር መሄድ ካልሆነም ቶሎ ቶሎ እግርን እያወጡ ማናፈስ (ቢቻል በቀን ለ30 ደቂቃ እግርን ከጫማ አውጥቶ ማናፈስ ቢቻል)
8. በአጠቃላይ የተፈጥሮ ክር ልብሶች መልበስ /የጥጥ የሱፍ እና የሀገር ልብሶች ሰውነት በቂ አየር እንዲያገኝ ያደርጋሉ/
9. አንድ ዮጋ፣ ሜዲቴሽን ወዘተ… የመሳሰሉ ዘዴዎችን በመጠቀም ጭንቀትን በማስወገድ የላብ መከሰትን መቀነስ ይቻላል፡፡
ስለዚህ ጠያቂያችን ከላይ የተጠቀሱትን በማድረግና መፍትሄ ካልሆኑ ወደ ሐኪም ዘንድ በመሄድ መፍትሄ መሻት ይመከራል፡፡


Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>