Quantcast
Channel: Ethiopian News | ዘ-ሐበሻ | Latest News Provider | News For All
Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

“የራያ ህዝብ የማንነት ጥያቄ እና የማዕከላዊ መንግስታት ምላሽ ከአፄ ዮሐንስ IV እስከ ኢህአዴግ”–የመጽሐፍ ግምገማ

$
0
0

የመጽሐፍ ግምገማ
ደራሲ፡- አለሙ ካሳ ረታ እና ሲሳይ መንግስቴ አዲሱ
ገምጋሚ፡- መንገሻ ረቴ እንዳለው
የግምገማ ቦታ፡- አዲስ አበባ ዩንቨርስቲ መኮንን አዳራሽ
ቀን፡- ጳጉሜን 2፣ 2005 ዓ.ም
የራያ ህዝብ የማንነት ጥያቄ እና የማዕከላዊ መንግስታት ምላሽ ከአፄ ዮሐንስ IV እስከ ኢህአዴግ
እንደ መጽሐፍ ገምጋሚ በአዎንታዊነት የታዩኝን እና መካሪ ወይም ማስተካከያ የምላቸውን ጉዳዮች ለመግለጽ እሞክራለሁ :: መጽሐፉ መልዕክት ያዘሉ ዓረፍተ ነገሮችንና ገላጭ የሆኑ ፎቶግራፎችን በሽፋኑ የያዘ ሲሆን በአጠቃላይ በስድስት ምዕራፎች የተከፈለ ነው:: የመጀመሪው ምዕራፍ ታሪካዊ ዳራው ላይ ያተኮረ ሲሆን አሁን ራያ ተብሎ በሚጠራው ቦታ ይኖሩ የነበሩ ቀደምት ህዝቦች ከቀደምት ነገስታቶች ጋር የነበራቸው ትስስርና ተጽዕኖ እንዲሁም ከአጎራባች ህዝቦች ጋር የነበራቸውን ግጭትና የአብሮነት ኩኔታ ያሳያል:: በዚህ ምዕራፍ በቀጣዮቹ ምዕራፎች የተንጸባረቁት የራስን በራስ ላስተዳድር ጥያቄያዊ መልዕክቶችም ተነስተዋል:: አምስቱ ምዕራፎች ከአፄ ዮሐንስ IV አሁን እስካለንበት ጊዜ ድረስ ኢትዮጵያን የመሩ ገዥዋች ለራያ ህዝብ የማንነት ጥያቄ የነበራቸው ምላሽ ምን እንደሚመስል ያተኮሩ ናቸው::
1. የመጽሐፉ አዎንታዊ ጎኖች
Raya Book
የመጽሐፉን ጭብጥ በመረዳት የተገነዘብኩት ጉዳይ የጸሐፊዎቹ ዓላማ የዘውግ/የብሔር ፖለቲካ – ethnocentric politics or ethno-nationalism የሚንጸባረቅበት የራያን የፖለቲካ ታሪክ መተረክ ነው :: ጽሁፉ ሲገመገም አንድ የታሪክ መጽሐፍ ሊያሟላቸው የሚገቡ የጥናት ስልቶችን በተለይም የመረጃ አጠቃቀምን ከሞላ ጎደል ይዞ ይታያል :: የመጀመሪያና የሁለተኛ ደረጃ የታሪክ መረጃዎችን በተለያዩ ቋንቋዎች ማለትም በአማርኛ፣ በትግርኛ፣ በጣሊያንኛና በእንግሊዝኛ የተጻፉ ጽሁፎችን እንዲሁም ቃለ መጠይቆችን በሰፊው በመጠቀም ልፋት የሚታይበት ፍሬ ያለው ስራ እንዳከናወኑ መረዳት ተችሏል:: አለፍ ሲልም መረጃዎቻቸውን በግርጌ ማስታወሻዎች በማስደገፍ የጽሁፉን ተዓማኒነት ለማሳየት ጥረዋል::

ከታሪክ አጻጻፍ የሚጠበቀውን የክስተቶችን ምክኒያታዊ መንስኤና ውጤት በደንብ ማብራራት የተቻለበት በመሆኑ ቁምነገር ያዘሉ መልዕክቶች በመጽሐፉ ይገኛሉ:: ለምሳሌ በአፄ ዮሐንስ IV፣ በዳግማዊ አፄ ምንሊክና በቀዳማዊ አፄ ኃይለስላሴ አልገዛም የሚል አመጽ በራያዎች ሊነሳ የቻለው ራያዎች በራሳቸው ወግና ባህል መሰረት በሚመርጧቸው መሪዎች መመራት በሚሹበት ወቅት ነገስታቶቹ ያለምንም ስልት ከሌላ አካባቢ በሚመጡ ፊውዳላዊ ገዥዎች በሀይል እንዲተዳደሩ ስለሚደረጉ መሆኑን በበርካታ የታሪክ መረጃዎች በማስደገፍ በአሳማኝ ሁኔታ ተገልጧል:: መንስኤን ከውጤት ጋር በማገናኘት በኩል ስኬቱ የላቀ መሆኑን ካሳዩበት ክፍል ለማንሳት ያክል የራያ ህዝብ ወራሪው ጣሊያንን መደገፉንና በሌላ በኩል ደግሞ ጣሊያንን መውጋቱ ታሪካዊ ክስተቱን ከማሳየት በላይ ለምን ይህ ሊሆን እንደቻለም በመረጃ አስደግፈው ለታሪክ አንባቢያን በሚያረካ መንገድ ተርከዋል::

የክስተቶች ምክኒያታዊ መንስኤና ውጤት በሚገባ ከተገለጸበት የመጽሐፉ ክፍሎች ውስጥ ከሶስቱ አፄዎች ጋር የነበሩትን ግጭቶች በምሳሌነት በማንሳት በሚከተሉት አንቀጾች ማብራራት ይቻላል::

አፄ ዮሐንስ እ.አ.አ በ1879 ዓ.ም በቁጥጥራቸው አድርገው በተወካያቸውና በአካባቢው ባህላዊ መሪዎች ያስተዳድሩት በነበረው የራያ መሬትና ህዝብ አንድ ባለሟላቸውን ወደ ተወካያቸው ደጃች ገ/ኪዳን ዘሞ ሲልኩ የቆቦና የአካባቢዋ አስተዳዳሪ የነበሩት አባ ቦና ኩቢ ከአንድ ሸኝ ጋር የንጉሱን ባለሟል በሸኙበት ወቅት ባለሟሉ በመገደላቸው ምክኒያት አፄ ዮሐንስ አባ ቦና ኩቢንና ሰራዊታቸውን ለእርቅና ለደስታ ጨዋታ እንደሚፈልጓቸው በማታለል ሶስት ሺ የራያ ታጣቂ ገበሬዎችን በግፍና ተመጣጣኝ ባልሆነ መንገድ ጨፍጭፈዋል:: በዚሁ ምክኒያት ራያዎች የሚከተሉትን የግጥም ስንኝ መደርደራቸው በመጽሐፉ ተገጧል::

አትመኑት ትግሬን ቢምል ቢገዘት፣
ክርስትና አግብተው ኩቢን አረዱት፣
ያበሉታል እንጂ ያጠጡታል እንጂ
እንዴት ይገደላል ለሆነለት ልጅ::

ልብ ይበሉ አባ ቦና ኩቢ አንገቱ ከመቀላቱ በፊት ክርስቲያን እንዲሆን ያደረጉት እንዲሁም ክርስትና አባቱም ራሳቸው አፄ ዮሐንስ IV እንደነበሩ ፀሀፊዎቹ አስረድተዋል::

በዳግማዊ አፄ ምንሊክ ዘመንም ቢሆን ራያዎችን ረግጦ የመግዛቱ ሂደት በመቀጠሉ የማዕከላዊ መንግስቱ ሰራዊት በአንፃራዊነት ዘመናዊ መሳሪያ ከመያዙም ባለፈ በእጅጉ የተደራጀ በመሆኑ ራያዎች ራሳቸውን በራሳቸው ለማስተዳደር የሚሞክሩት ሙከራ ግፍ በተሞላበት ጭፍጨፋ በመጨናገፉ በንዴትና በዕልህ ብቀላ ለማካሄድ መላ እየፈለጉ ባለበት ወቅት ከንጉሱ ጋር ቅራኔ ያላቸውን የህ/ሰብ ክፍሎች በማጥናት ኢትዮጵያዊያንን ከፋፍሎ ለመግዛት ሲያጠና የነበረውና ለወረራ ሲዘጋጅ የነበረው ጣሊያን ፐሪስኮ የተባለ ጣሊናዊ ሰላይ ወደ ራያዎች ላከ፡፡ ሰላዩም በእስልምና ሀይማኖት ረገጣ ምክኒያት በነገስታቶቹ ላይ ተቃውሞ የነበረውን የወሎውን ሸህ ጣላህ ከራያዎች ጋር በማገናኘት በሚስጢር ራያዎች በርካታ መሳሪያዎች ከጣሊያን እንዲያገኙ አደረጓቸው እና በሸህ ጣላህ መሪነት አሸንጌ ላይ የመንግስትን ጦር ለመውጋት ጦርነት ተካሄዶ ራያዎች በምኒልክ ሰራዊት ተሸነፉ፡፡ ከዚሁ በመቀጠልም የምኒልክ ሰራዊት ወደ አድዋ በዘመቱበት ወቅት የራያን ህዝብ በጥላትነት በማየት በአሰቃቂ ሁኔታ ጨፈጨፉት፤ ቤቱን አቃጠሉት፤ ሴቶችንም ደፈሯቸው፡፡ የግፉ መጠን የበዛባቸው ራያዎች በምላሹ የምኒልክ ሰራዊት ከአድዋ ጦርነት ሲመለስ በየዛፉና በየቋጥኙ ሆነው እያነጣጠሩ ከባድ እልቂት አወረዱበት፡፡ የምኒልክ ሰራዊት በአድዋ ጦርነት ላይ ካለቀው በላቀ በራያ መሬት እንደላቀ እንደነ ፍራንኬቲ የመሳሰሉ ፀሐፍት ተናግረዋል፡፡

የማዕከላዊ መንግስት እና የራያዎች ፍጥጫ በቀዳማዊ አፄ ኃይለስላሴ ዘመንም እንደቀጠለ በመጽሐፉ የተብራራ ሲሆን ራያዎች ከሌሎች አካባቢዎች ጋር የሚያደርጉትን ዉጊያ (በተለይም ከአፋር ጋር) ለማስቆም በሚል ሰበብ እነሱ የሚፈልጉትን ራስን በራስ የማስተዳደር መብት በራስ ጉግሳ አራያ፣ በደጃች አያሌው ብሩ እና በራስ ሙሉጌታ የተመሩ የመንግስት ወታደሮች በራያ ላይ አሰቃቂ ግፍ እንደፈጸሙ ተተርኳል፡፡

ይሁንና የደረሰባቸውን ግፍ ወደ ጎን በመተው ተንቤን ላይ ከጣሊያን ጋር በተደረጉት ሁለት ዙር ጦርነቶች ራያዎች የኃይለስላሴን ሰራዊት ደግፈው በቆራጥነት መዋጋታቸውን ኮሎኔል አሌሳንድሮ ዴልቫዬ የተባሉ የቀዳማዊ አፄ ኃይለስላሴ የጦር አማካሪ መኮንን የሚከተለውን የአይን ምስክር እንደጻፉ ተተርኳል፡፡
« ….. እነዚህ ራያዎች ያለማቋረጥ ትንፋሻቸውን ዋጥ አድርገው ይዋጋሉ፡፡ ደከመኝን፣ እንቅልፍንና ራበኝን አያውቁም፤ ተወዳዳሪ የማይገኝለት ሀይል አላቸው፡፡ ጠላታቸውን ከአካባቢያቸው ለማስወገድ፣ ህይወታቸውን ለመስጠት በፍጹም አይሳሱም፤ ፈጣንና ጠንካሮች እንዲሁም ቀልጣፎች ናቸው፤ የሰው ልጅ ያልፍበታል ተብሎ በማይገመተው ቦታ ሁሉ ተሸለክልከው ያልፋሉ፡፡ »

የሚያሳዝነው ግን እንደዚህ የመሰለ ጀብድ እየፈጸሙና ህይወታቸውን እየሰጡ ራያዎች በቀዳማዊ አፄ ኃይለስላሴ የጦር መሪዎች በደል ይደርስባቸው እንደነበር ፀሀፊዎቹ በመረጃ አስደግፈው እንዲህ ሲሉ ያወሩናል፡- « እንደ ሌሎቹ የቀዳማዊ አፄ ኃይለስላሴ ወታደሮች በቂ ምግብ፣ ውሃ እና ለውጊያው አስፈላጊ የሆኑ ትጥቅና ስንቅም በበቂ ሁኔታ ከሌሎቹ ጋር እኩል [አይቀርብላቸውም ነበር]፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ በራስ ሙሉጌታ የሚመራው በቀዳማዊ አፄ ኃይለስላሴ ሰራዊት የሚከተለውን አሰቃቂ ግፍ በራያዎች መፈጸሙን ቀይ አንበሳ በሚል ርዕስ በታተመው መጽሐፍ ላይ የሰፈረውን ትረካ ጸሐፊዎቹ በሚከተለው ሁኔታ አንጸባርቀዋል፡፡

“ቆቦን በምናቋርጥበት ወቅት የጦር አለቃው ደጃዝማች መሸሻ ክብራቸው ተደፍሮ ነበር፣ ከመንደሩ ነዋሪዎች አንዱ በአደባባይ ከጓደኞቻቸው አንዱን ገድሎባቸዋል፡፡ የሰፈርንበት ቦታ ከቆቦ 3 ማይል ርቀት ላይ ወጣ ብሎ ነው የሚገኘው፡፡ መሸሻም ቁጭታቸውን ለመወጣት የነኳቸውን ሰዎች አይቀጡ ቅጣት ለመቅጣት በልባቸው ወስነዋል፡፡ በጧት ድምጽ ሳያሰሙ 5000 ሰዎችን አሰባስበው ወደ ቆቦ ጉዞ ቀጠሉ፡፡ ከተማዋንም እንዳልነበረች አድርገዋት ተመለሱ፡፡ ያጠቋቸውንና የደፈራቸውን በሙሉ በጎራዴ ቀነጠሱ፡፡ ሽማግሌዎች፣ ልጆች፣ ወንድ ሴት፣ ሳይለዩ ገድለዋል፡፡ እነኝህ ሊወድቁ የደረሱ ቤቶች በውስጣቸው ከ1200 በላይ ሬሳ ታቅፈው ቀርተዋል፡፡”

ይህን ከነገሩን በኋላ ጸሐፊዎቹ በመቀጠልም ሰባት የራያ ሽፍቶች በመያዛቸው በራስ ሙሉጌታ የሚመራው ሰራዊት የሚከተለውን አጸያፊ ድርጊት እንደፈጸመ ከላይ የተጠቀሰው መጽሐፍ ውስጥ ሰፍሮ እንደሚገኝ በሚከተለውን አስቀምጠው እናገኛለን፡፡

«በመጀመሪያ ጆሯቸውን፣ቀጥሎ እጆቻቸውን፣ ቆየት ብሎ ምላሳቸውን፣ ቅጣት ፈጻሚዎቹ የእነዚህ ያልታደሉ ጥፋተኞች እያንዳንዷን የሰውነት አካል በፍጥነት ሲቆራርጡ ማየት በጣም ይዘገንን ነበር፡፡ ያለ እግር ያለ እጅ በደም የተለወሰ መሬት ላይ የተቀመጠ ጭንቅላት፣ወገብና ደረት ብቻ ከአይናቸው በስተቀር ምንም የሚንቀሳቀስ ክፍል የሌላቸው የተቆራረጡ ገላዎች፣አሳዛኝ ፍጡሮች፡፡ አይኖቻቸውም ቢሆኑ ከዚያ ከፊታቸው ክብ ቦታ በጦር ተቦርቡረው እንዲወጡ ተወሰነ፡፡ ዙሪያውን የከበበው ሰራዊትም የበቀል ምኞቱን ለመወጣት እየጮኸ ድርጊቱ ሲፈጠም ያደምቃል፡፡”

ከዚህ በኋላ ነው እንግዲህ ራያዎች ከጣሊያን ጋር ወግነው አረመኔውን የቀዳማዊ አፄ ኃይለስላሴን ጦር ለመውጋት ቆርጦ የተነሳው፡፡ በዚህ ምክኒያት አምባራዶም ላይ በጣሊያን ወታደሮች ሽንፈት የደረሰበት የራስ ሙሉጌታ ሰራዊት በራያ በኩል ሲሸሽ ራያዎች ብቀላ እንዳካሄዱ የሀበሻ ጀብዱ በሚል ርዕስ መጽሐፍ ላይ ፀሀፊው አዶልፍ ፓርለሳክ እውነታውን በሚከተለው ሁኔታ እንዳስቀመጠ የአለሙ ካሳ ረታ እና የሲሳይ መንግስቴ መጽሐፍ የሚያበስረን፡፡

“[ራስ ሙሉጌታ] ከፈረንሳይ አገር የወታደራዊ ትምህርቱን አቋርጦ በመጣው ልጃቸው ታጅበው የአሸንጌን ሀይቅ በፈረሳቸው ላይ ተቀምጠው በመሻገር ላይ እንዳሉ ታልመው በተተኮሱ ሁለት የራያና የአዘቦ ሽፍቶች ጥይት ተመትተው ወደቁ፡፡ ከፊት ለፊቱ ከፈረሳቸው ላይ ዘንበል እያሉ የወደቁትን አባቱን ለመርዳት ከፈረሱ ላይ ዘሎ በመውረድ አባቱን ለመደገፍ ጎንበስ ያለውንም ልጃቸውን ታልመው ተደጋግመው የተተኮሱ ጥይቶች በአባቱ ሬሳ ላይ ጣሉት::”

በዚሁ በመቀጠል ወሳኝ የነበረውን የማይጨውን ጦርነት የቀዳማዊ አፄ ኃይለስላሴ ሰራዊት ለማሸነፍ ሲቃረብ ከጣሊያን ጋር ሆነው ጉዳት በማድረስ ለጦርነቱ መሸነፍ ራያዎች ዋነኛ ምክኒያት እንደሆኑ የተተረከ ሲሆን ከዚህ በኋላ ግን የተወሰነው የራያ ጦር ከአርበኞች ጋር በሚስጢር በመገናኘት የጣሊያንን ሰራዊት ሲጨፈጭፍ እንደነበርና እንደማናኛውም ኢትዮጵያዊ አርበኛ እስከመጨረሻው እነደተዋጋ ተገልጧል፡፡ በዚህም ምክኒያት ወራሪው ጣሊያን ከአገር ከተባረረ በኋላ ሹመትና ሽልማት ያገኙ ራያዎች እንዳሉ ጸሀፊዎች የተሸላሚዎቹን ስም ሳይቀር ዘርርረው እስረድተዋል፡፡

መንስኤና ውጤትን በጥሩ የታሪክ መረጃ አስደግፈው ማቅረባቸውን ከጠቆምኩ በኋላ ፀሐፊዎቹ አንዳንድ የተደበቁ ጣሪካዊ ክስተቶችንም በጽሁፋቸው ማካተታቸው መጽሐፉን ይበልጥ ጠቃሚ ያደርገዋል፡፡ ራያዎች በብዙ መንገድ በዘር ሐረግ ትስስር ካላቸው የወሎና የየጁ ህዝቦች ጋር እንዴት በፍቅር ይተያዩ እነደ ነበር እርስ በእራሳቸው ሲያደርጉት የነበረውን ግጭት እንደሚፈቱትና አልፎም በመረዳዳት ያሳዩትን ትብብር ለማተት ተሞክሯል፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ የራያዎችና የልጅ እያሱ ግንኙነት የሚስብ ታሪክ ነው፡፡ ለምሳሌ “የሸዋ መሳፍንቶችና ራስ ተፈሪ መኮነን (ኋላ ላይ አጼ ኃይለስላሴ የተባሉት) ልጅ እያሱን የቤተክርስቲያን ነገር ትቶ መስጊድ ድረስ በመሄድ እየሰገደ ነው፤ የተለያዬ ሀይማኖት ከሚከተሉ ወይዛዝርት ጋር አብሮ እየወጣ ነው በማለት በእሱ ላይ አመጽ ንዲነሳሳ ሴራ አሲረው” በልጅ እያሱ ላይ መፈንቅለ መንግስት ሲያደረጉበት ራያዎች ጋር ተደብቆ በመቆየቱና የልጅ እያሱን ልጅ ማለትም አንድ ጊዜ ወርቀልዑልሰገድ እያሱ ሌላ ጊዜ ደግሞ ሸህ ሰይድ አህመድ እያሱ በመባል የሚታወቀውን ወደ አፋር አካባቢ ወስደው በመደበቃቸው ኋላ ላይ ቀዳማዊ አፄ ኃይለስላሴ የብቀላ እርምጃ በራያዎች ላይ እንደወሰዱ ጸሐፊዎቹ ሲያወሱ በሌላ በኩል ደግሞ ራያዎች የቀዳማዊ አፄ ኃይለስላሴን ስልጣን አንቀበልም ብለው የልጅ እያሱን ልጅ ለማንገስ ከመሞከር አልፈው ንጉሳችን የልጅ እያሱ ልጅ ነው ብለው ማወጃቸውን ገልጠዋል፡፡

በመጨረሻም የወያኔ እንቅስቃሴ የተጸነሰውም ሆነ ከህዝባዊ አመጽነት ወደ ትግል የተሸጋገረበት በራያ መሆኑን በማስረዳት አትተዋል፡፡ የወያኔ ህዝባዊ አመጽ በራያዎችና በዋጀራቶች ትብብር የተካሄደ ሲሆን ከዚህ ህዝባዊ አመጽ እንቅስቃሴ በፊት በራያ ህዝቦች መካከል ሲከናወን የነበረ ዘመን ጠገብ የራያ ባህላዊ ፍልሚያ መሆኑን ተርከዋል፡፡ እንደ ፀሐፊዎቹ በወያኔ አባባል ህዝባዊ አመጽ ምክኒያት የቀዳማዊ አፄ ኃይለስላሴ ሰራዊት ከብዙ ተጋድሎ በኋላ በለስ እነደ ቀናው እና የተለመደውን የብቀላ እርምጃ እንደወሰደ ተርከዋል፡፡ በጦርነቱ መጨረሻ ገደማ ከሰሜን የመጡ ትግሬዎች ህዝባዊ አመጹን እንደተቀላቀሉ እና የመሪነት ሚናውን እኛ እንውሰድ ማለታቸውንም አውስተዋል፡፡

ለማጠቃለል ያክል ጽሁፉ በርካታ ቁም ነገሮችን ያዘለ ከመሆኑም አልፎ አሁን ያለው ትውልድ ካለፈው ስህተት መማር የሚችልበትን እውነታ ፀሐፊዎቹ አለሙ ካሳ ረታና ሲሳይ መንግስቴ አዲሱ የበኩላቸውን ሚና ሲያበረክቱ የወደፊቱ የራያ ህዝብ እጣ ፈንታስ ምን መሆን አለበት ለሚለው የግል አስተያየታቸውን አስቀምጠዋል፡፡

2. አሉታዊ ጎኖች

– በተወሰኑ ምዕራፎችና ገጾች ጸሐፊዎቹ የተጠቀሙት ትረካ በምናባዊ ልብወለድ እንደሚታወቀው ሁሉን አዋቂ(Omniscient) ባህሪ ማላበሱና የግል ገጠመኞች (Personal anecdots) መስለው መቅረባቸው የታሪክ ምርምርነቱን ልፋታቸውን አደብዝዞታል፡፡ ለምሳሌ በገጽ 140 ጸሐፊዎቹ እንዲህ ይላሉ፡- «ራያዎች ግን ይህንን የትም ፍጭው ዱቄቱን አምጭው አይነት ፓሊሲ በፍጹም አይቀበሉትም ነበር ብቻ ሳይሆን አጥብቀውም ይቃወሙት ነበር፡፡ ኩሩና ታማኝ የአገር አንድነት ጠበቃ ለመሆንም የግድ አንድ ቋንቋ፣ አንድ ሐይማኖት ወይም አንድ ወጥ የሆነ ታሪክና ባህል ሊኖረን የግድ አይደለም የሚል የጸና እምነት ነበራቸው፡፡ እንዲያውም ራያዎች ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ይህች አገር የብዙ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች እንዲሁም የበርካታ ሀይማኖቶች አገር መሆኗን ጠንቅቀው የሚያውቁና በአግባቡም የተገነዘቡ ህዝቦች ነበሩ ብሎ በድፍረት መናገር ይቻላል፡፡”

ታሪክ የተደረገን ነገር በማስረጃ አስደግፎ ማቅረብ እንጂ በዘመነኛ ቃላት ራያዎች እንዲህ ያስቡ ነበር ብሎ መጻፍ ከታሪክ አጻጻፍ የወጣ አተራረክ ከማድረጉም በላይ የምርምር ውጤትነቱን ያቀጭጨዋል፡፡
– 15 ገጽ ያለው የተንዛዛ መግቢያ ከማዘጋጅትም ባለፈ የጸሐፊዎቹን እምነት የሚያንቀባርቅ ሀሳብ አስቀድሞ ማቅረቡ ከፈረሱ ጋሪው እንዲሉ ውጤትን አስቀድሞ መወሰን እና ማሳየት ስለሆነ አንባቢን አስቀድሞ ከመዝጋቱ ባለፈ መጽሐፉ የምርምር ስራ መሆኑን አስቀድሞ ጥያቄ ምልክት ውስጥ ያስገባዋል፡፡
– በመካከለኛው ዘመን አማራ ተብሎ ከሚታወቀው ህዝብ ጋር የአስተዳደርና የባህል ተቀራራቢነት እንዲሁም የቋንቋ አንድነት የነበራቸውና አሁን ራያ ተብሎ በሚጠራው ቦታ ይኖሩ የነበሩ የአንጎትና የቀዳ ህዝቦች እንዲሁም የበዕደማሪያም ሰሪዊትና የዘር ሐረጋቸውን ከጎንደር ከሚመዙት የዘወልድ ህዝቦች ከዶባዎችና ከራያ ኦሮሞዎች ጋር የነበራቸውን ውህደት በማመልከት በኩል የተነሳ ጉዳይ ስለሌለ የቅጽ ሁለት ህትመት በቀጣይ የማያካትተው ካልሆነ በስተቀር መጽሐፉ የራያን ታሪክ ጎደሎ ያደርገዋል፡፡
– በመጽሐፉ አነዳንድ ክፍሎች ከታሪክ ጽሁፍ የማይጠበቁ ጸሐፊዎቹ ጀማሪ መሆናቸውን የሚያሳዩ ይገኛሉ፡፡ ለምሳሌ በገጽ 71 እንዲህ ተብሏል፡- «በዚህ መድብል ፀሐፊዎች እምነት ይህ ከአገር ግንባታ ሂደት ውስጥ የሚካተት ስለሆነ “እውነተኛ የቅኝ ግዛት” ቦታዎች የሚለውን ሐረግና ተከትሎት የሚመጣውን ሐሳብ በፍጹም አይቀበሉትም፡፡”

የታሪክ ምርምር እውነትን ፈልፍሎ አውጥቶ በመረጃ አስደግፎ መተረክ ነው፡፡ ታሪካዊ ትንታኔም ካስፈለገ ከሀቁ ተመርኩዞ ነው የሚተነተነው፡፡ አገር ግንባታን እዚህ ላይ ምን አመጣው ? አገር ግንባታ ወይም ማፍረስ የተመራማሪ ሳይሆኑ የፖለቲከኛ ማጭበርበሪያ ቃላት ናቸው ፡፡

– ከገጽ 83 – 94 ያሉት 12 ገጾች የራያ ህዝብ በራስ ወሌ ሲተዳደር ከነበረበት ወደ ራስ ሚካኤል አስተዳደር እንዲሆን መደረጉንና ራያዎች በየጁ፣ በላስታ፣ በዋግና በትግራይ ተከፋፍለው እንዲተዳደሩ መደረጉን ለማስረዳት የተሄደበት አተራረክ ለአንባቢ አሰልቺ በሆነ መንገድ ስለቀረበ በ2 ገጽ ጨምቆ ማቅረብ የሚቻል ነው፡፡

– ለአካዳሚክ ማህበረሰብ ብቻ ቀላል የሆኑ የእንግሊዝኛ ቃላት እነደወረዱ ማስቀመጥ ከአካዳሚክ ውጭ የሆነውን አንባቢ ስለሚያደናግር ለምሳሌ በገጽ 128 ወታደራዊ ጁንታ የሚለውን ደርግ/ወታደራዊ ሸንጎ ብሎ መተካቱ ይመረጣል፡፡

– በገጽ 148 የራያ ህዝብ ከጣሊያኖች ጋር ጥብብር ያደረገባቸውን ወቅቶች ባንዳ እንደማያሰኝ ለማስረዳት ፀሐፊዎቹ ያደረጉት ሙግት የሚከተለውን ይመስላል፡- « … እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ሀገር እየመሩ የሚገኙ ፖለቲካኞች ሳይቀር የጠባብነት አሊያም የባንዳነት ስሜት እያንጸባረቁ ባለበት ሁኔታ ያውም አብዛኛው የራያ አካባቢ ህዝብ እንደሌሎቹ ኢትዮጵያውያን አርበኞች ሁሉ ማድረግ ያለበትን ነገር ሁሉ አድርጎ በማለፉና ጥቂት የሚባሉ የራያ ተወላጆች ከጣሊያን ጋር ወግነው ቢገኙ ምኑ ነው የሚያስገርመው? ከሌላው ኢትዮጵያዊ ባንዳስ በምን ስለሚለይ ነው ይኸን ያህል ተጋኖ እንዲቀርብ የሚደረገው? እያለ ይቀጥልና በግርጌ ማስታወሻ ደግሞ “የግንቦት 7 ሊቀመንበር የሆኑት ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ ቀደም ሲል ከወራሪው የኤርትራ መንግስት መሪዎች በቅርቡ ደግሞ ከግብጽ ፖለቲከኛች የገንዘብና የመሳሪያ ድጋፍ እንዲደረግላቸው መጠየቃቸው በመገናኛ ብዙሃን ሰዎች ሲገለጽ የሰነበተ ጉዳይ ነው” …. አሁንም በመቀጠል ኦብነግ፣ ኦነግ እየተባለ በተመሳሳይ ተጠቅሰዋል፡፡

ይህ አንድ ገጽ የማይሞላ ክፍል የመጽሐፉን በርካት ኩምነገሮች ወደታች እዘጭ አድርጎ የጣለበት የኢህአድግ የፖለቲካ ጠመቃ/political brainwashing/ የፈጠረው ክፉ ተጽዕኖ ነው፡፡

በመጀመሪያ ነገር ራያዎች ለምን ጣሊያንን ሊተባበሩ እንደቻሉ በጥሩ መረጃ በማስደገፍ በምክኒያታዊነት የተረዳንበት የጽሑፍ ክፍል አለ፡፡ ሲቀጥል ግለሰብ ወይም በቁጥር ብዙ ያልሆኑ የተወሰኑ ግለሰቦች ከጥቅም ጋር በተያያዘ ከጠላት ጋር የሚያደርጉት ትብብር ነው አንጂ ባንዳ የሚያስብለው እንደ ህዝብ የሚዋጋ ከሆነ የሚዋጋበትን ምክኒያት መግለጽ እንጂ ህዝቡን በሞላ ባንዳ ልትለው አትችልም፡፡ ይህም ሆኖ ህዝቡን ባንዳ ብሎ የሚጠራ ካለ ጣሊያን በወረረ ወቅት በተመሳሳይ ሁኔታ ከጣሊያን ጋር ወግነው የነበሩ ሌሎች የኢትዮጵያ ህዝቦችን በትይዩ በመጥቀስ የኢትዮጵያ ገዥዎች ቱርፋት እንጂ ጣሊያንን የወገኑት ያልተማሩት ህዝቦች የባንዳነት አባዜ አለመሆኑን ለማስረዳት በተቻለ ነበር፡፡ የኢህአዴግ የፖለቲካ ፕሮፓጋንዳ መንዣ የሆኑ ሚዲያዎችን ዋቢ አድርጎ ግንቦት 7፣ ኦነግና ኦብነግን ከራያ ታሪክ ጋር አገናኝቶ ማቅረብ ግን ፈጽሞ የማይገናኝና የታሪክ ምርምርነቱን ክብደት የሚያቀለው ነው፡፡ ድርጅቶቹ ለነጻነት፣ ለፍትህና ለዴሞክራሲ ብለን ነው የምንታገለው ስለሚሉ ስለነሱ መጻፍ ካስፈለገ ከራያ ታሪክ ጋር ሳያዘበራርቁ ለብቻው መጻፍ ይቻል ይሆናል፡፡ ስለሆነም በራያ ህዝብ ስም የመጽሐፉን ገጽ 148 በቀጣይ እትም ላለማካተት ቃል ቢገባ መልካም ነው፡፡

– በገጽ 186 እና 187 “የሰሜን ትግራይ ሰዎች የወያኔን አመጽ የተቀላቀሉት የቀረችባቸውን የስልጣን ፍርፋሪ ለማስመለስ ሲሆን ራያዎች ግን መሰረታዊ የሆነውን መብታቸዉን ለማስከበር ነበር” የሚለው ለአንዱ ህዝብ ወገንታዊነትን ስለሚያሳይ የተመራማሪነትን ብቃት ስለሚያጎድፍ በተገቢ ቃላት አስተካክሎ ማቅረብ ያስፈልጋል፡፡

– በምዕራፍ ስድስት «የኢህአዴግ ስልጣን መያዝና የራያ ህዝብ የማንነት ጥያቄ» በሚለው ክፍል የግል አስተያየት በዝቶበት ይታያል፡፡ ይህ ከሚሆን የተለያዩ ወገኖችን በህወሐት ትግል የተሳተፉ የራያ ልጆችንና ትግሬዎችን ጭምር በሰፊው ቃለ-መጠይቅ አድርጎ ማብራራት ቢቻል ጥሩ ነበር፡፡ በርካታ የራያ ሰዎች ልጆቻቸውን ኃየሎም እያሉ እስከመጥራትና በጥግሉም እስከመሳተፍ ለድርጅቱ ፍቅራቸውን ያሳዩበትን እና በሌላ በኩል ደግሞ ድርጅቱ መልኩን ቀይሮ ተግባራዊ ሂደቱ ሌላ የሆነበትን ክስተት በማስረጃ አስደግፎ ማቅረብ ላይ ውስንነት ይታይበታል የሚል እይታ አለኝ፡፡

– በመጨረሻም ራያ እንደነ ስልጤ የራሱ አስተዳደር ሊያገኝ ይገባዋል የሚል አስተያቶች መንጸባረቃቸው ሁለት አይነት ችግሮችን እንዳዘለ ይታየኛል፡፡ በመጀመሪያ እንደ ምርምር ስራ እውነትን አስቀምጦ ማለፍ ብቻ ተመራጭ ስለነበር በሌላ ፖለቲካዊ ነክ ጽሁፎች ማንሳት ሲቻል ታሪክንም፣ ፖለቲካንም ጥያቄንም አንድ ላይ ማቅረቡ ስራዉን የምርምር ጽሁፍ ነው ለማለት አስቸጋሪ ያደርጋል፡፡ ሁለተኛውና ወሳኙ ግን የራያ ህዝብ አሁን ያለበት ችግር በአንድ ቡድን ፍጹም የላይነት ተጨንፍሮ የተያዘው አስተዳደር ተቀይሮ ፍትሃዊ አስተዳደር ሲይዝ ከአጠቃላዩ የኢትዮጵያ ህዝብ ችግር ጋር የሚፈታ እንጂ እየተደረገ እንደምንመለከተው ተላላኪ ለመፍጠር ተብሎ በዚሁ ጠባብ ቡድን « ራስህን በራስህ አስተዳድር » ተብሎ ምላሽ እንዲሰጥ ማሰብ ያው የኢህአዴግ የፖለቲካ ጠመቃ ተጽእኖ የፈጠረው ጥያቅ ከመሆን ለራያ ህዝብ የሚፈይደው ጥቅም የለም የሚል አስተያየት አለኝ፡፡

ማሳሰቢያ፡- መጽሐፉን ከደረሱት አነዱ፣ ሲሳይ መንግስቴ አዲሱ፣ ከልጅነት እድሜው ጀምሮ ከብአዴን ጋር ሆኖ ደርግን ለመጣል የተዋጋና ኃላ ላይም በአማራ ክልል በቢሮ ሃላፊነት ደረጃ ስርዓቱን ሲያገለግል ቆይቶ የፍትህ፣ የዴሞክራሲና የነፃነት ጥያቄዎችን በተለያዩ መድረኮች በማቅረቡ ምክኒያት በተለይም የህወሐት አመራሮች ብአዴንን እንደ ፈለጉ ማሽከርከራቸው ተገቢ እንዳልሆነ በግልጽ መናገሩ ተጽእኖ እንዲደርስበት ስላደረገው በራሱ ፈቃድ ስልጣኑን ትቶ በአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ መምህር ሆኖ መስራትን መርጦ እየሰራ ይገኛል፡፡ የሚያሳዝነው ይህን መጽሐፍ አሳትሞ እንዳወጣ አቻው ባልሆኑ ሆድ አድር ካድሬዎች በእጂ አዙር ከድርጅቱ እንዲባረር ከመደረጉም በላይ በህወሐት ካድሬዎች ማስፈራሪያ እና ዛቻ በተለያዩ ወቅቶች እየደረሰበት ይገኛል፡፡

ሕወሐቶች መረዳት ያለባቸው ጉዳይ ሲሳይ ከአካዳሚክ አንጻር ምንም ይሁን ምን ዓየነት ጽሁፍ ቢጽፍ ጽሁፉን የመውደድ ወይም የመተቸት የሁሉም ኢትዮጵያዊ መብት ሆኖ በሲሳይ መንግስቴ ላይ በሚቃጣ ማናቸውም ዓይነት እርምጃ ግን የራያ ህዝብ ከሲሳይ መንግስቴ በስከጀርባ መሆኑን መዘንጋት የለባቸውም፡፡ ባጭሩ ሢሳይ ጋር መጣላት ከራያ ህዝብ ጋር መጣላት ነው፡፡


Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>